40 ሺህ ሕጻናት ከሕገወጥ ስደት ተርፈዋል

22

አዲስ አበባ፡- ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች 40 ሺህ ሕጻናትን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ለማስወጣት ሲሞክሩ መያዛቸውን በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሕገወጥ ዝውውር ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲያ ሰኢድ አስታወቁ።

ተጠባባቂ ኃላፊዋ ትናንት በኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዳስታወቁት ከታህሳስ 2008 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ብቻ 40 ሺህ ሕጻናት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከሀገር ለማስወጣት ሲሞከር በድንበር ቁጥጥር የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

መልክና ይዘቱን እንደሁኔታዎች እየቀያየረ የሚከናወነው ሕገወጥ ስደት ሁኔታ መጨመር እንጂ መቀነስ እንደማይስተዋልበት ያነሱት ወይዘሮ ፈቲያ በዚህም በኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብና ትግራይ ክልሎች ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ቀያቸውን ለቀው ከሚጎርፉባቸው አካባቢዎች ቀዳሚዎቹ መሆናቸ ውን ጠቁመዋል።

በየአካባቢው ለዜጎች የሚፈጠረው የሥራ እድል እዚህ ግባ የሚባል ካለመሆኑ የተነሳ አምራቹ ወጣት ኃይል በየጊዜው ሀገር ጥሎ መኮብለሉ ሳያንስ አሁን አሁን ለጋ ሕጻናት ጭምር በአስደንጋጭ ሁኔታ የስደቱ አካል እየሆኑ መምጣታቸው ለችግሩ ሁሉም አካል ትኩረት እየሰጠው እንዳልሆነ አመላካች በመሆኑ እንደ ሀገር ምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥቶ ሊመክር እንደሚገባ ወይዘሮ ፈትያ አመልክተዋል።

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት በሚያሳልፉ አስራ አራት ሕገወጥ የመተላለፊያ መስመሮች በየጊዜው እድሜ፣ጾታና ፈታኝ ሁኔታዎች ሳይበግሯቸው በርካታ ዜጎች ለሕገ ወጥ ስደት እንደሚዳረጉ ታውቋል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012

ሙሐመድ ሁሴን