”ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ‘

7

ርዕሱ የተውሶ ነው። ያውም ለመጽሐፍ የተሰጠ ርዕስ። የዚህ ግሩም ግለ ታሪክ መጽሐፍ ባለቤት ሥዩም ወልዴ ራምሴ ይባላሉ። ባለታሪኩ ስዩም በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ አንቱታና ክብር ከተጎናጸፉት ጥቂት የሀገራችን ጠቢባን መካከል አንዱ ነበሩ። በሰዓሊነታቸው ብቻ ሳይሆን በሥነ ጥበባት በሳል ሃያሲነታቸውም ይታወቃሉ። በህልፈተ ሕይወት ከተለዩን ዓመታት ያስቆጠሩት እኒህ ሁለገብ ጠቢብ “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት ግለ ታሪክ መጽሐፍ የብዕራቸውን ብርታት ያሳዩበት፣ በመልዕክቱና በይዘቱም እጅግ ማራኪና ተነባቢ ለመሆን የቻለ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉን ጥንቅቅ አድርገው ለህትመት ዝግጁ ያደረጉት በ1985 ዓ.ም ከህልፈታቸው ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ነበር።

በቤተሰቦቻቸው እጅ ለዓመታት በክብር ተቀምጦ የነበረው ይህ የመጽሐፍ ረቂቅ የህትመት ብርሃን እንዲያይ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም የተዟዟሪ ፈንድ በመመደብ አሳትሞ ለንባብ በማብቃቱ የሙያ ግዴታውን ስለተወጣ አንጋፋው ማኅበር በእጅጉ ሊመሰገን ይገባዋል።

በሀገሬ ከታተሙ በርካታ የግለ ታሪክ መጻሕፍት መካከል በቀዳሚነት ከምጠቅሳቸው ጥቂት ማራኪ መጻሕፍት መካከል አንዱ ይህ መጽሐፍ እንደሆነ የምመሰክረው በእውነትና ስለ እውነት ነው። አንባቢያን መጽሐፉን ካነበቡ በኋላ የምስክርነቴን እውነታ እንደሚያረጋግጡ ተስፋ አደርጋለሁ።

የእኚህን ታላቅ ሰው የመጽሐፍ ርዕስ የተዋስኩት ስለ መጽሐፉ ሙያዊ ሂስ ለመስጠት ሳይሆን የርዕሱ ይዘት በሃሳቤ የፀነስኩትን የሀገሬን ወቅታዊ እውነታ በሚገባ ይገልጽልኛል ብዬ ስላመንኩ ነው። ልቀጥል።

ርዕሱ አያዎ (አይ እና አዎ) ዓይነት ይዘት ያለው ነው። የኩርፊያ ደመና ስሜትን ጋርዶ እያለ እንዴት ፈገግታ ይኖራል? የሚል ተከራካሪ ሃሳቡን ለሙግት ከማቅረቡ በፊት የጥላሁን ገሠሠን አንድ የዜማ ግጥም አንዲያስታውስ እመክራለሁ፡

”መሳቁን ይስቃል፤ ጥርሴ መች አረፈ፣

ልቤ ነው በጣሙን እጅግ ያኮረፈ።‘

ለካስ ጥርስ እየሳቀ ልብ በሀዘን ሊመታ ይችላል። በኩርፊያ ውስጥ ተዘፍቆም ቢሆን ጥርስን ፈገግ እያደረጉ ያረረ አንጀትን በአርቲፊሻል ፈገግታ መሸንገል ይቻላል። ስለዚህም ነው አያዎ የሚሉት የዘይቤ ዓይነት ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን ቅርብ ነው የሚባለው።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ልብ ብለን ብናስተውል በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍ በርካታ በኩርፊያ የተሸፈኑ ፈገግታዎችን የምናስተውልባቸው አጋጣሚዎች እጅግ በርካታዎች ናቸው። ሀገራዊ የፖለቲካ እውነታዎቻችን ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ መልኩ የተለበጡት ኩርፊያ በሸፈናቸው የማስመሰያ ፈገግታዎች እንደሆነ መታዘብ ከጀመርን ሰነባብተናል።

ብዙ ፖለቲከኞቻችንና ምሁራን በሚዲያዎች ፊት ሲቀርቡ የሚያሳዩን ፈገግታ ብዙውን ጊዜ በኩርፊያ የደበዘዘ እንደሆነ በቅርብም በርቀትም እያስተዋልን ነው። በአንዱ ጉዳይ ላይ ብቻ ተመስርቼ እንዴታውን ላብራራው። የፖለቲካ ካፖርት የደረቡ በርካታ ቡድኖች በአርቴፊሻል ፈገግታ ተቀራርበው ለመዋሃድ ከወሰኑ በኋላ ጥቂት ምዕራፍ እንኳን ቃላቸውን ጠብቀው ሳይጓዙ በኩርፊያ ተጠላልፈው መፋታታቸውን እንዘርዝር ብንል “የዜና መዋዕል ጸሐፊነትን” ብርታት ሳይፈታተን የሚቀር አይመስለኝም። “የማይዘልቅ ማኅበር በጠጅ ይጀመራል” እንዲሉ ተጋብተው አንድ የማር ጨረቃ ምሽት (Honey Moon) አብረው ሳያሳልፉና የፊርማቸውና የማኅተማቸው ቀለም ሳይደርቅ የተፋቱ ብዙ የፖለቲካ ቡድኖችን አስተውለናል።

በአሁኑ ወቅት “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” እየተስተዋለ ያለው እንደ እንጉዳይ በፈሉት በተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ ዙርያ በተሰባሰቡ ቤተኛ ፓርቲዎች ዘንድም እንደሆነ የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ ሰንብቷል። በግሌ በኩርፊያ በዳመነው የኢህአዴግ ድርጅቶች ፊት ላይ የሚነበበው “የለበጣ ፈገግታ” እንደተጠበቀ ሆኖ ስያሜያቸው ውስጥ የተሰነቀረው “ግንባር” የሚለው ቃል ትርጉሙ ራሱ እስከዛሬ ግር እንዳለኝ አለ። ዛሬም ቢሆን የፍቺው ትርጉም እንዲህ ነው የሚል ተንታኝና አስተንታኝ አላጋጠመኝም። ወደፊትም ይግባኝ አይግባኝ እርግጠኛ አይደለሁም።

በሀገሬ ቋንቋ የተዘጋጁ ጎምቱ መዛግብተ ቃላትም ቢሆኑ “የግንባርን ፍቺ” በመስጠቱ ረገድ በእማኝነት አልረዱኝም። እርግጥ ነው ባህሩ ዘርጋው ግዛው ባዘጋጁት መዝገበ ቃላት ውስጥ የጊዜው ፖለቲካ የሚደግፈውን ብጤ ፍቺ ለመስጠት ሙከራ ቢያደርጉም በግሌ ግን ድንጋጌው አልጣመኝም። “Frons” ከሚለው የላቲን ሥርዎ ቃል የተገኘው የእንግሊዘኛው “Front”ም ሆነ የቃላቱ ውልዶች ኢህአዴግ ከተጠቀመበት “የግምባር” ዐውድ ጋር ሙጥኝ ብሎ የሚገጥም አልመስለኝም። “የጦር ሜዳ ግንባር፣ ግንባር ፈጠሩ ወዘተ.” የሚሉት መሰል ሀገራዊ ሀረጋትም ቢሆኑ በእማሬያዊ ወይንም በፍካሬያዊ ትርጉማቸው ኢህአዴግ የተጠቀመበትን ሃሳብ ስለመደገፋቸው እርግጠኛ አይደለሁም። እንደታሰበው እንረዳ ቢባል እንኳ “ግንባር” የሚለው የቋንቋችን ፅንሰ ሃሳብ ተፈልቅቆ ቢጠና ከአዎንታዊ ዐውዱ ይልቅ አሉታዊ ፍቺው እንደሚያመዝን መገመት አይከብድም።

እማሬና ፍካሬ የሚሉት ሁለት ቃላት ከግዕዝ የተገኙ ሲሆን፤ እማሬ የሚወክለው ጥሬ ትርጉም ወይንም የመዝገበ ቃላትን ትርጉም ሲሆን ፍካሬያዊ ይዘት ያላቸው ቃላት ደግሞ ከጥሬ ትርጉሙ በስተጀርባ ያሉትንና በይሁንታ የፀደቁትን ሰፊና ጥልቅ ሃሳቦችን የሚወክሉ ናቸው። ጎጆ ስንል ሣር ቤትን (እማሬያዊ ትርጉም) ብቻ ሳይሆን ትዳርንም (ፍካሬያዊ ትርጉም) ጭምር ነው።

በወሽመጥ የገባው ይህ “ነገረ ግንባር” ብዙ እንደሚያከራክርና እንደሚያወያይ ይገባኛል። ሊያስቆጣ እንደሚችልም እገምታለሁ። ግዴለም እንደተባለው ቃሉ “ስብስብን” ይወክላል ቢባል እንኳን ቡድኖች በጊዜያዊነት ውሳኔ ግንባር ፈጥረው የሚሰባሰቡት አንድን አካል በአሉታዊ መልኩ ለመገዳደር፣ አለያም በአንድነት አብሮ ለአንድ ወቅታዊና ወዲያውነት ላለው ዓላማ“ጡንቻን ለማፈርጠም” ወደሚል ከፀጉር የቀጠነ ትርጉም ይመራናል። ካልሆነ በስተቀር በስመ ግንባር ተሰባስቤ ለረጂም ዘመናት ሀገር ልምራ፣ ወይንም ሕዝብ ላስተዳድር ብሎ ግንባር መፍጠር እጅግም የተለመደ አይደለም። ስምን መልዓክ ያወጣል እንዲሉ በኢህአዴግ ግንባር ሥር የተጠለሉት ቡድኖች ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል ሥልጣናቸውን አደላድለው ምን ሲሰሩ እንደከረሙ ለመግለጽ አዋጅ ነጋሪ አያስፈልግም። በአጭሩ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” ነበር ቢባል ያስኬዳል።

ከላይ ያቀረብኩት ምልከታ ፉርሽ ይሁን ቢባል እንኳ ራሳቸው ባፀደቁት ስያሜና ሕዝቡም ስያሜውን ተቀብሎ እውቅና የሰጣቸው አራቱ የኢህአዴግ ክልላዊ የፖለቲካ ግምባርተኞች ሆድና ጀርባ በመሆን እየተሸነጋገሉ እንደኖሩና እንደሚኖሩ እኛ ተመሪ ዜጎች ያልገባን ከመሰላቸው ተሳስተዋል። አጋር እየተባሉ የቅጽል ስም እንጂ የተግባር ድርሻቸው ለተመናመነው ለአምስቱ ክልሎችም የጡንቸኛው ግንባር አካሄድ በኩርፊያ የተሸፈነ ፈገግታ እንዲኖራቸው እንዳስገደዳቸው ዛሬ ዛሬ በድፍረት መናገር ጀምረዋል። ጊዜው “ከተከድኖ ይብሰል” ወደ “ተገልጦ ይታይ” ደረጃ በመሸጋገሩም ደስተኞች መሆናቸውን ደጋግመው ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ኩርፊያቸውን በፕሮቶኮል ዓይነ ርግብ ሸፍነው በአርቴፊሻል ፈገግታ ሲሸነጋገሉ የኖሩት አራቱ ድርጅቶች ዛሬ ላይ ዓይነ ርግባቸውን በትንሹ ገለጥ ማድረግ ሲጀምሩ ግንባራቸው ላይ የተጋደመው ያለመተማመን ማዲያት አፍጥጦ እንደወጣ እየታዘብን ነው።

ግንባራቸው ላይ ማዲያት እየወጣ ውበታቸውን የሚፈታተነው የሀገሬ ቆነጃጅት “ገበናቸውን” በሜክአፕ ፓውደሮችና ቅባቶች ለመሸፋፈን እንደሚሞክሩት ሁሉ ገዢው ግምባር ፓርቲም ፖለቲካዊ ማዲያቱን በሜክ አፕ በተሸፈነ ፈገግታ ልሸፍነው ቢል ሊሆንለት ስላልቻለ አተካራው እየገነፈለ መምጣቱን እየሰማንም እያየንም ነው።

መቼም በማናቸውም የሕይወታችን እንቅስቃሴ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ኩርፊያ ያልሸፈነው ፈገግታ ለማግኘት እጅግ አዳጋች የሆነ ይመስለኛል። ሕዝብ ለሕዝብ የጎሪጥ እየተያየ መፍትሔውን ከመፈለግ ይልቅ “ችግሩን የፈጠሩት ጥቂት ቡድኖች ወይንም ግለሰቦች እንጂ ሕዝብ ለሕዝብ ችግር የለበትም” የሚለው አባባልና የፖለቲካ ዲስኩር በግሌ በእጅጉ ያሳስበኛል። ጥቂት ቡድኖችም ሆኑ በርካታ ቡድኖች የሚፈጥሩት የችግር ብልጭታና ብልጭታው የሚፈጥረው ነፀብራቅ ዞሮ ዞሮ መተማመን እንዳይኖር የሚያጥበረብረው ብዙውን ሕዝብ ነው።

ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ በተከበሩት የፓርላማ አባላቱ ስብሰባ ወቅትም አዘውትሮ ሲንፀባረቅ በመከረኛው የቴሌቪዥን መስኮታችን ሳናስተውል አልቀረንም። አንዳንዱ የኩርፊያ ፈገግታ በወንበረተኞቹ ስብሰባ ላይ ግድቡን ጥሶ ሁሉ ሊወጣ ሲዳዳው ፍንጮች ጠቁመውናል። በመሰረቱ በግለሰብ፣ በቤተሰብም ይሁን በቡድኖች መካከል የሃሳብና የአቋም ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው። በሰብዓዊ የዲሞክራሲ መብት ላይ ፖለቲካዊ ዲሞክራሲ ሲታከልበት ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ እንዳዜመው “ጥርሳችን እየሳቀ ቆሽታችን ቢደብን” ግድ ስለሆነ እውነታውን ልንክድ አንችልም።

ሀገርና ሕዝብ ለመምራት ግን ኩርፊያ በሸፈነው አርቲፊሻል ፈገግታ ብዙ ርቀት ማዝገሙ በግሌ ቀን ለመግፋት ታስቦ ካልሆነ በስተቀር አዋጭ አይመስለኝም።“ለአኩራፊ ልጅ ቁርሱ ራቱ ይሆናል” አባባል በሀገርና በሕዝብ ኩርፊያ ላይ አይሰራም። ኩርፊያ በሸፈነው ፈገግታ እየተደለሉና እየደለሉ መኖርም ጥቂት ያራምድ ካልሆነ በስተቀር ብዙ ርቀት ሊያስኬድ አይችልም።

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በብዙ የአሜሪካ ዜጎች የለበጣ ፈገግታ የተቄለባቸውን ቀናት ሲያስብ ራሱን ይታዘባል። ብዙ አሜሪካኖች ከአንድ እንግዳ ሰው ጋር ድንገት ሲተያዩ ጥርሳቸውን ለሰከንድ በሚቆይ ፈገግታ ብልጭ የማድረግ አርቴፊሻል ልማድ አላቸው። ጸሐፊውን መሰል የዋህ የባዕድ ምድር ባለሀገሮች ፈገግታቸው እውነተኛ የፍቅር ወይንም የአክብሮት መገለጫ እየመሰለው ሰላሳ ሁለት ጥርሶቹን ገለጥ ማድረግ ሲጀምር “በቴያትረኞቹ” አሜሪካዊያን ራሱም ሆነ በርካታ ዜጎች ግርምትና ድንግርግር ስሜት ሲፈጥርባቸው በተደጋጋሚ አስተውሏል።

የሀገሬ ፖለቲከኞችና መሪዎችም ኩርፊያ ከሸፈነው ፈገግታ ነፃ ወጥተው ነፃ ቢያወጡን ጸሎቴም ምኞቴም ነው። ያለበለዚያ ጥቂት ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች እየተባለ ብዙው የሕዝብ ክፍል ቂመኛ እንዳይሆን ሊታሰብበት ይገባል የሚል ጠንካራ የግል አቋም አለኝ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሰላም ሎሬት በሚል ማዕረግ ለሽልማት ያበቃቸው አንዱ የስኬታቸው አንኳር ተግባር በድንገት በሀገረ ኤርትራ ተገኝተው (አስቀድሞ የተሠራው የዲፕሎማሲ ቅድመ ዝግጅት እንዳለ ሆኖ) የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ባስደነቀ ሁኔታ ሰላም ማውረዳቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሆይ! ሽልማቱ ስለሚገባዎት ደስታችን ከእንኳን ደስ ያልዎት ቃላትም ያለፈ ነው። ደስ ብሎናል!

ልክ እንደርሳቸው ሁሉ ኩርፊያ በሸፈነው ፈገግታ ተጀቡነው እህህ እያሉ በሚተክዙ ክልሎች ዘንድ አንዳንድ መሪዎቻችን ደፈር ብለው በድንገት ባኮረፈው ሕዝብ መሃል እየተገኙ የሰላም መልዕክተኛ እንዲሆኑ ሀገሬ አጥብቃ የምትፈልግበት ጊዜና ወቅት ነው።

በግል እምነቴ የብዙ ሀገራዊ ችግሮቻችን መንስዔ ኩርፊያ በሸፈነው ፈገግታ የታጀሉ መሪዎች፣ አስታራቂ ሽማግሌዎች፣ ቡድኖች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ሚዲያዎች ወዘተ… ፊታቸው እንደጠቆረ ችግሮቻችንን ለመፍታት በሚያደርጉት ሙከራ ሀገራዊ መፍትሔ ማግኘት ያለመቻላችን እንደሆነ እረዳለሁ።

ለሀገራዊ ሰላም፣ ለሕዝቦች ክብር፣ ለብልጽግናና ለዕድገት ሌት ተቀን እንሥራ ብለን በምንማማልበት መድረክ ላይ የተለበጥንበት የለበጣ ፈገግታ በእውነተኛ የቅንነት መንፈስ ካልወዛ በስተቀር ነገራችን ሁሉ የእምቧይካብ እንዳይሆን ልንሰጋ ይገባል። “ፈገግታችን ወገግታችን ይሁን” መልዕክቴ ነው። ሰላም ይሁን!

ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጥቅምት 5/2012

  (በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)