ዕውነቱ እማን ዘንድ ነው?

25

መንግስት በከተማዋ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል። ከዚህ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ቢሆንም የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው ቤቶችም ይህ ነው የማይባል ጥቅምን ሳያበረክቱ እንዳላለፉ ዕሙን ነው። ሆኖም ግን ቤቶቹ ሕጋዊ ተዋዋይ ሆነው ከኮርፖሬሽኑ ወይንም በቀድሞ መጠሪያው ኪ.ቤ.አ.ድ. በውል ከተከራዩ በኋላ ወደ ግል የማዞር ዝንባሌ ተቋሙን እየፈተነው መሆኑ ይነሳል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቦሌ ክፍለ ከተማ ግለሰቦች የኮርፖሬሽኑ ይዞታ የሆነን ቦታ የግል የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ እያወጡበት ነው በሚል ለተቋማችን ጥቆማ ደርሷል። እኛም ይዞታው የመንግስት ከነበረ እንዴት ወደ ግል ዞረ? የግል ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድስ ስለምን ተሠራለት? በሚል ኮርፖሬሽኑን፣ ቅሬታ የቀረበባቸውን ግለሰብ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት አነጋግረን እንዲሁም ሰነዶችን አገላብጠን ያጠናቀርነውን ዘገባ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

ኮርፖሬሽኑ

ኮርፖሬሽኑ ከግለሰቦች ጋር የሚያደርገውን ክርክር በተመለከተ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ሦስት ጽሕፈት ቤትን አነጋግረናል። ቤቶቹን አስመልክቶ በጽሕፈት ቤቱ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊዋ በቢሯቸው በአካል ተገኝተን ማህደሮቹን እየተመለከቱ ምላሽ እንደሚሰጡን ገልፀውልን በቀጠሯችን ዕለት ብንገኝም ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት የቤቶች ደህንነት ተቆጣጣሪ አቶ አብረው ጫኔ ምላሽ እንዲሰጡን መርተውልናል። በተባለው መሠረት የኃላፊዋን ትዕዛዝ ተቀብለው በቤቶቹ ላይ ምላሻቸውን ቢሰጡንም ከጽሕፈት ቤቱ ከወጣን በኋላ ስልክ በመደወል ኃላፊዋ ‹‹ሥራ አስኪያጁ ሳያውቁ መረጃ መውጣቱ ተገቢ ባለመሆኑና በእንጀራዬ ላይ የመጣ ጉዳይ በመሆኑ መረጃው እንዳይወጣ ብላኛለች። ስለዚህ በእኔም እንጀራ ላይ መምጣቱ ስለማይቀር መረጃውን እንዳይለቀቅ›› ሲሉ ጠይቀውናል። እኛም የጽሕፈት ቤቱን ሥራ አስኪያጅ እንዲያገናኙን ብንጠይቅም ሊሳካ ባለመቻሉ ፈቃደኛ ሆነው የሰጡንን መረጃ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።

ልዩ መጠሪያው ደረጃ መዳቢ ጀርባ ወይም እግዚሐርአብ ቤተክርስትያን አካባቢ በሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ቤቶች ላይ ክርክር እንደገጠማቸው አቶ አብረው ይናገራሉ። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የመንግስት ቤቶች የሆኑት የቤት ቁጥር 413/6 እንዲሁም የቤት ቁጥር 413/7 ላይ ቤቶቹ እንዳሉ ሆነው ቦታውን በመቁረጥ ወደ ግል የማዞር እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነም ነው የሚገልጹት። ችግሩን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ሥራ ሲሠራ የቆየ በመሆኑ ጉዳዩ ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ አልፎ እስከ ኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ደርሷል። በአሁኑ ወቅትም በይዞታው ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ እንዳለ ይታወቃል በማለት የመንግስት ይዞታ የሆነውን ቦታ ወደ ግል ይዞታ ለመቀየር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ከዚህ ቀደም 413/7 በቤቱ ላይ ካርታ አውጥተውበት ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ትግል እንዲከሽፍ መደረጉን በማስታወስ 413/7 ግን እንቅስቃሴው እንዳለ ይገልፃሉ። ግለሰቦቹ ዋነኛ መከራከሪያቸው ኮርፖሬሽኑ ቤት እንጂ ቦታ የለውም የሚል ሲሆን፤ ይዞታውን በሰነድ አልባ እንደያዙት የሚያስረዳ መሆኑን አቶ አብረው ይናገራሉ። ኮርፖሬሽኑ ቤት እንጂ ቦታ አያስተዳድርም የሚል መከራከሪያ የሚያነሱት ግለሰቦቹ ክርክር ቢያደርጉም ኮርፖሬሽኑ ደግሞ ቤቱን የሚያስተዳድርበትና ቤቱ ያረፈበት ቦታ የራሱ እንደሆነ ያምናል ይላሉ።

ክርክሩ በእነዚህ ሁለት ሀሳቦች ላይ ያጠነጠነ ነው የሚሉት ተቆጣጣሪው፤ ኮርፖሬሽኑ ቤቱ ያረፈበትና በይዞታው አካባቢ የሚገኝ ቦታ የመንግስትና የሕዝብ በመሆኑ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበትም ዕምነት ይዞ እየተከራከረ እንደሆነ ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት ይህን እኩይ ድርጊት ለመከላከል ቅርንጫፉ ትግሉን አጠናክሮ እንደቀጠለ የሚናገሩት አቶ አብረው፤ ጉዳዩን እልባት ለመስጠት የቤቶቹን ማህደር ለኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት መላኩን ያብራራሉ። በዚህም የሕግ ባለሙያዎች እየተከታተሉትና አጠናክረው ለመጻፍ እየሠሩ መሆናቸውንም ነው የሚጠቁሙት።

ሌላው ወገንስ ምን ይላል?

ወይዘሮ ዛይድ ገብረህይወት፤ ቤታቸው ሰነድ አልባ በመሆኑ የቤት ቁጥር እንደሌለው በማስረዳት የክርክሩን ጅማሮ ያስረዳሉ። ከኮርፖሬሽኑ ጋር ክርክር የተጀመረበትን ሁኔታ ሲያስታውሱም፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሰነድ አልባ ይዞታ በመያዛቸው ነው። ክርክር ያስነሳውን ይዞታውን ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ለረጅም ዓመታት ሲጠቀሙበት እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ዛይድ፤ በተለምዶ ጨረቃ ቤት እንደሚባለው ቦታውን አጥረው ሲኖሩ እንደነበር ነው የሚገልጹት።

2007 ዓ.ም መንግስት በዚህ መልኩ ሰነድ አልባ ይዞታ የያዙ ዜጎች እንዲስተናገዱና ሕጋዊ እንዲሆኑ በገለጸው መሠረት ወደ ወረዳው በማቅናት መብት እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ። እንደማንኛውም ዜጋ የሰነድ አልባ አገልግሎት እንዲያገኙም ሥማቸው ይለጠፋል። ይሁን እንጂ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀና አጥጋቢ መነሻ በሌላቸው አካላት ተመሳሳይ ጉዳይ ያላቸው ነዋሪዎች ሲስተናገዱ እርሳቸው ግን ለእንግልት መዳረጋቸውን ይገልፃሉ። ይህም ‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁምን?›› የሚል ጥያቄን ዘወትር እንደሚጭርባቸው ይናገራሉ።

በወቅቱ አገልግሎቱን ሊያገኙ ያልቻሉት በግለሰቦች ጥላቻና የግል ስሜት እንጂ አገልግሎቱን የማግኘት መብት ሳይኖራቸው ቀርቶ እንዳልነበር ሁኔታውን ያብራራሉ። በዚህ መልኩ አንዳንድ በመንግስት የሥራ ኃላፊነት በተሰጣቸውና ከምክንያታዊነት ይልቅ ግላዊ ስሜታቸውን በሚያስቀድሙ ግለሰቦች በሚያደርሱት ጥቆማ በእርሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ተገልጋዮች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚፈጠርም ነው የሚጠቁሙት።

የወረዳው አስተዳደር በወቅቱ ጥቆማውን ማጣራት እንደሚገባው ምላሽ እንደሰጣቸው ወይዘሮ ዛይድ ይናገራሉ። በዚህም ከወረዳው የተውጣጡ ነዋሪዎችና የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት በተሳተፉበት የማጥራት ሥራ ተከናውኖ ቤቱን በቅርብ ስለሚያውቁት አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው ይወሰንላቸዋል። ይሁን እንጂ የወረዳው አስተዳደር ይህን ተቀብሎ አገልግሎት እንዲያገኙ ከመሥራት ይልቅ ጥቆማ ከሕብረተሰቡ እንዳገኘ በመጥቀስ ይዞታውን አስመልክቶ መሬቱ እየተወረረ እንደሆነ ገልፆ ለፌዴራል የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ደብዳቤ ይጽፋል። ኮርፖሬሽኑም ባለሙያ በመላክ ያጣራ ሲሆን፤ በምላሹም ‹‹መሬቱ የእኛ አይደለም›› በሚል እንዳልተወረረ ይገልጻል።

ወረዳው ከኮርፖሬሽኑ ምላሽ በኋላ አገልግሎት እንዳያገኙ የሚከለክልበት ምክንያት ባለመኖሩ ወደ ክፍለ ከተማ አገልግሎት ለማግኘት ማቅናታቸውን ያስታውሳሉ። ሆኖም ግን ተቋጨ ሲሉት እንደ አዲስ ብቅ የሚለው ጥቆማ ዳግም ይነሳና አገልግሎቱን ሳያገኙ ይቀራሉ። ቤታቸው ተለክቶ አገልግሎት ለማግኘት በሒደት ላይ ሳሉ ጥቆማውን ያደረሱት የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ ኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ሦስት ጽሕፈት ቤት ያመራሉ። ጽሕፈት ቤቱም የኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ይዞታውን አስመልክቶ እንዳልተወረረ የገለፀው ተሳስቶ እንደሆነና ቦታው የኮርፖሬሽኑ በመሆኑ አገልግሎት እንዳያገኙ ወደ ክፍለ ከተማው ደብዳቤ እንደፃፈ ይናገራሉ።

ምንም እንኳ ኮርፖሬሽኑ የመንግስት አካል ቢሆንም በሕግ ፊት ግን እኩል እንደሆኑ የሚገልጹት ወይዘሮ ዛይድ፤ ይህን ያልተገነዘቡ አካላት ግን ሁኔታውን ከመሠረቱ አጣርተው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ አገልግሎት ሊሰጧቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ነው የሚናገሩት። ክፍለ ከተማው ዳግም ኮሚቴ አዋቅሮ ጉዳዩን በአካል ወርዶ ይፈትሻል። በዚህም ክርክር የተነሳበት ይዞታ የእርሳቸው እንደሆነ መንግስት ያወጣቸው መመሪያዎች ሁሉ እንደሚደግፋቸውና መስተናገድ እንደሚገባቸው ያረጋግጣል። ሆኖም ግን የክፍለ ከተማው የበላይ አመራሮች ይዞታው ክርክር የሚደረግበት ከመንግስት አካል ጋር በመሆኑ ምላሽ ለመስጠት እንደማይችሉ በመግለጽ፤ ወደ ከተማ አስተዳደሩ እንዲሄዱ ይነግሯቸዋል።

ወይዘሮ ዛይድ የሰነድ አልባ ይዞታቸው ከኪራይ ቤቶች ጎን በመሆኑ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደማይገባ ባለመገንዘብ የተፈጠረባቸው እንግልት ቅስማቸውን ቢሰብረውም ፍትሕን ለማግኘት ግን የሚመለከታቸው አካላትን በር ማንኳኳት እንዳላቆሙ ይገልፃሉ። በዚህም የክፍለ ከተማውን ምላሽ በመያዝ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እንዳቀኑ ይናገራሉ። ቢሮውም ለኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ ይጽፋል። በደብዳው በ20 ቀናት ውስጥ ኮርፖሬሽኑ ይዞታው እንደሆነ ሊያረጋግጥለት የሚችል መረጃ እንዲያቀርብ የሚጠይቅ ነበር። ይሁን እንጂ በተጠቀሰው ቀናት ውስጥ ምላሹን ሊያቀርብ ያልቻለው ተቋሙ፤ በይዞታው ላይ ባለቤትነቱን ሊያረጋግጥለት የሚችል ማስረጃ የሚያቀርብበት ተጨማሪ 20 ቀናት ይሰጡታል።

ኮርፖሬሽኑ መረጃ ሊያቀርብ ባለመቻሉ ቢሮው የራሱን ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመላክ ያረጋገጠ ሲሆን፤ በዚህም ዳግም አገልግሎት እንዲያገኙ ወደ ክፍለ ከተማው ጉዳያቸው መላኩን ወይዘሮ ዛይድ ይገልፃሉ። በ2008 ዓ.ም ዳግም መስተናገድ ሲጀምሩ አገልግሎቱ ይቁም ብሎ ኮርፖሬሽኑ ይጠይቃል። ቢሮውም ለክፍለ ከተማው በሕጉ መሠረት መስተናገድ እንደሚችሉ ጠቅሶ፤ ይህን የሚያስተጓጉል አካል ተጠያቂ እንደሚሆንም አስረግጦ ይጽፋል። ደብዳቤው ተቋሙ ክርክር ያነሳበት ይዞታ በጂአይኤስ ማስረጃዎችም ከቤቶቹ ጋር የተለያየ እንደሆነና አገልግሎት እንዳያገኙ የሚያደርግ በቂ ምክንያት እንደሌለው የሚያብራራ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ ሊፈታ ያልቻለው ጉዳይ ሲንጓተት ቆይቶ በ2011 ዓ.ም ኮርፖሬሽኑ በ30 ቀናት ውስጥ ቤቱን ለቅቀው እንዲወጡ ደብዳቤ እንደፃፈላቸው ይናገራሉ።

መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም ቤቱን ለቅቀው ካልወጡም በፀጥታ ኃይሎች ተገድደው እንደሚወጡ ኮርፖሬሽኑ እንደገለጸላቸው የሚያስታውሱት ወይዘሮ ዛይድ፤ እየደረሰባቸው ያለው እንግልት ግፍ እንደሆነ ሊያስረዱ ቢሞክሩም ሰሚ ጆሮ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም የመጨረሻ አማራጭ አድርገው የወሰዱት ጉዳዩን ወደ ሕግ መውሰድና የተቋሙ ትዕዛዝ ላይ እግድ ማውጣት ነበር። ፍርድ ቤቱም ኮርፖሬሽኑ በ”ይገባኛል” የሚጠይቀው ይዞታ ላይ መብት እንደሌለው ይወስናል። በዚህም ከቤቱ ሊያስወጧቸው እንደማይችሉ ውሳኔ ያሳርፋል።

በፍርድ ቤት ውሳኔ አግኝቶ አገልግሎት ማግኘት ሲጀምሩም ከማዕከል ጥቆማ ደርሷል በሚል እንዲቆም ይደረጋል። ወይዘሮ ዛይድ ሒደቶቹን የሚያስረዱ ማስረጃዎቻቸውን በመያዝ ወደ ከተማ አስተዳደሩ በመሄድ ጥቆማውና ማስረጃዎችን በመመርመር አገልግሎት እንዲሰጣቸው ለክፍለ ከተማው ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ እየተሠራላቸው እንደሆነና በደረሰባቸው እንግልት ሥነልቦናቸው እንደተጎዳም ነው የሚገልጹት።

ሰነዶች

ይዞታውን አስመልክቶ በክፍለ ከተማው ከሚገኘው ማህደር ውስጥ ወይዘሮ ዛይድ ካርታ እንዲሰራላቸው የጠየቁበት ማመልከቻ፣ በሰነድ አልባ እንዲስተናገዱ አስተዳደሩ ባወጣው ሥም ዝርዝር ውስጥ የእርሳቸው አንዱ መሆኑን የሚያሳይ ሰነድ፣ ይዞታው ከሚያዚያ 1997 ዓ.ም በፊት እንደተገነባና ወይዘሮ ዛይድ ያስተዳድሩት እንደነበር፤ ከየትኛውም ወገን የይገባኛል ክርክር ነፃ ስለመሆናቸው የወረዳው ኮሚቴ የሰጠው የውሳኔ ሃሳብ ሰነድና የቤዝ ማፕ ቁጥር ቦሌ 06/61/D-02 የሴሪ ቁጥሩ ደግሞ 0145603 የሆነ አጠቃላይ ስፋቱ 224 ሜትር ካሬ ስፋት ያለው የከሸፈ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተመልክተናል።

በክፍለ ከተማው የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሰነድ አልባ ይዞታ ሬጉላራይዜሽን ፕሮጀክት ዴስክ በቀን 18/07/2005 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር ቦ/ክ/ከ/ሲ/አ/2535/2005 በቀድሞ አጠራር በመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ለቅርንጫፍ ሦስት የሥራ ሒደት ወጪ አድርጎ የላከው ደብዳቤ በማህደሩ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል አንዱ ነው። ደብዳቤው፤ ኤጀንሲው በይዞታው ላይ ሕገወጥ ቤት ግለሰቦች ሠርተው ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን በደብዳቤ እንዳሳወቀ ያብራራል። በዚህም ቦታው ድረስ በመገኘት ጽሕፈት ቤቱ እንዳረጋገጠው በኤጀንሲው ከሚተዳደሩት የቤት ቁጥር 413/06 እና 413/07 የተሰራላቸው ካርታ እንደሚያሳየው እና በክፍለ ከተማው የሚገኘው የጂ.አይ.ኤስ መረጃ ቅሬታ የቀረበበት ቦታ ከኤጀንሲው ይዞታ ጋር ምንም ዓይነት የድንበር ግንኙነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ማሳወቁን ያሳያል።

በ26/05/2008 ዓ.ም ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት የተላከ የውሳኔ ሐሳብ ማስታወሻ ከሰነዶቹ መካከል ይገኛል። በማስታወሻው ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው፤ እነ ወይዘሮ ዛይድ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ቤት ንብረት አፍርተው እየኖሩበት ያለውን ቤታቸውን መንግስት በፈቀደው የሰነድ አልባ ይዞታዎች ለመስተናገድ በወረዳ በተቋቋመው የሰነድ አልባ ይዞታዎች አጣሪ ኮሚቴና በወረዳው ካቢኔ ተረጋግጦ ለክፍለ ከተማው ለካርታ ማውጣት ከተላከ በኋላ ኤጀንሲው ቦታው የእርሱ እንደሆነ ጥያቄ በማሳቱ በይዞታቸው ላይ ካርታ የማግኘት መብታቸውን እንደተከለከሉ ለዋና ሥራ አስፈፃሚ ቅሬታቸውን በ25/12/2007 ዓ.ም ማቅረባቸውን ያስረዳል። ቅሬታቸውን ተከትሎም በተደረገው ማጥራት ማስረጃዎችን ተመልክቶ የደረሰባቸውን ግኝቶችና የውሳኔ ሐሳቦች በሰነዱ ይታያሉ።

በማስታወሻው፤ በተለያዩ ዓመታት የገቢ ግብር

 የተከፈለባቸው ደረሰኞች፣ መብራትና ስልክ የገባባቸው ማስረጃዎች እንደቀረቡና እንደታዩ ሰፍሯል። የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር የኮንስትራክሽና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ይዞታ የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ሰነድ አልባ ይዞታ ሬጉላራይዜሽን ፕሮጀክት ዴስክ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ይዞታውን አስመልክቶ የጻፏቸው ደብዳቤ ማስረጃዎችም እንደተፈተሹ ነጥብ በነጥብ ተቀምጠው ይነበባሉ። በዚህም የመንግሥት መሬት ተቋማቱ በሰጡት ማስረጃ መሠረትና ኤጀንሲው በጂአይኤስ ላይ በሚያመለክተው የቦታ ስፋት መሠረት ካርታ ተሰርቶለት የራሱን ይዞታ በካርታው አግባብ እያስተዳደረ ቢሆንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ የያዙት ይዞታ ወደ ግለሰቦች እንዳይዞር መግለጹን ያትታል። ቅሬታ አቅራቢዎቹም ቦታው ከኤጀንሲው ይዞታ ውጪ ነው በማለት ለማስረጃነት የሚሆኑ ሰነዶች ማቅረባቸውን፣ የወረዳው ሰነድ አልባ ኮሚቴ አጣርቶ የላከበት ማስረጃ የቀረበ በመሆኑ በመመሪያው መሠረት በመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የይዞታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ የሰነድ አልባ ይዞታ ሬጉላራይዜሽን ፕሮጀክት ዴስክ እና የከተማ ፕላን ጽሕፈት ቤት በጋራ በመሆን ኤጀንሲው ያለውን ቦታ በትክክል በመመልከት ለቅሬታ አቅራቢዎቹ የማያዳግም መልስ እንዲሰጣቸው የውሳኔ ሐሳብ መቅረቡን ያሳያል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በ13/11/08 ዓ.ም በቁጥር አአ/መልማቢሮ/07/47/77/08 ወጪ አድርጎ ለኤጀንሲው የላከው ደብዳቤ ሌላው ከማህደሩ ከሰነዶች መካከል ያገኘነው ደብዳቤ ነው። ሰነዱ እንደሚያመላክተው፤ ኤጀንሲው አገልግሎት እንዳይሰጣቸው በመጻፉ ክፍለ ከተማው መስተንግዶ እንደከለከላቸው አቤቱታቸውን አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ኤጀንሲው በአየር ካርታው ላይ ለሚታየው ይዞታ ካርታ የወሰደ ሲሆን፤ የአመልካቾቹ ይዞታ የመንግስት ቤቶች ከሚገኙበት ፓርሴል ወይም ግቢ ውጪ ተገንብተው በ1997 መስመር ካርታ ላይ እንደሚታዩ ቢሮው ገልጧል። ከኤጀንሲው ይዞታ ውጪ በተገነቡት ቤቶች ላይ ደግሞ ለቤቱ ባለቤት የመብት ፈጠራ ስለማይከለከል ኤጀንሲው የእርሱ እንደሆነ ጥያቄ የሚያነሳ ከሆነ ይህንን የሚደግፍ ሰነዶች ከማብራያ ጋር እንዲልክ፤ ይዞታው የኤጀንሲው ካልሆነም እንዲያሳውቀው ቢሮው ኤጀንሲውን በደብዳቤ መጠየቁ በሰነዱ ይታያል።

የከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዳግም ለኤጀንሲው በ13/12/08 በቁጥር አአ/መልማቢ/07/4778/08 ወጪ አድርጎ የላከውን ደብዳቤም ተመልክተናል። ከዚህ ቀደም ይዞታው የኤጀንሲው ስለመሆኑና አለመሆኑ አጣርቶ እንዲልክ ቢሮው ቢጠይቅም ኤጀንሲው ግን ለአንድ ወር ምላሽ እንዳልሰጠ ያብራራል። በጂአይኤስ ላይ ማረጋገጥ እንደተቻለው አመልካቾች የይዞታ ካርታ የጠየቁባቸው ቤቶች የኤጀንሲው ቤት ከሆኑት የቤት ቁጥር 413/6 እንዲሁም 413/7 ውጪ ሆኖ በ1997 መስመር ካርታ ላይ የሚታይ ግንባታ እንዳለው ቢሮው ለኤጀንሲው በጻፈው ደብዳቤ መላኩን ያስረዳል። በመሆኑም ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በይዞታው ላይ ባለቤትነቱን የሚያረጋግጡ ሰነዶች ተጠይቆ ለአንድ ወር ሳይሰጥ የቆየ ቢሆንም ይህ ደብዳቤ በደረሳቸው 20 የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቁን ደብዳቤው ያሳያል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ምላሽ የማይላክ ከሆነ ግን ለተገልጋዮቹ አገልግሎት ከተሰጣቸው በኋላ በመንግስት ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ ኤጀንሲው ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን ገልፆ ልኳል።

በ19/05/08 ቢሮው ለክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ሌላው ሰነድ ሲሆን በዚህም ቢሮው በተደጋጋሚ ለኤጀንሲው በደብዳቤ ይዞታውን አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ከኤጀንሲው ግን ምንም ዓይነት ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን አስፍሯል። በመሆኑም የወረዳው አስተዳደር በቀጣና ኮሚቴ አባላቶች የአመልካቾች ይዞታ ጉዳይ አጣርቶ የላከ በመሆኑ መረጃው ስህተት ከሆነ ይህን የፈጠረ አካል በመመሪያ ቁጥር 18/2006 አንቀጽ 21 ተጠያቂ እንዲደረግ ካልሆነ ግን ተጠያቂነት በሌለው መንገድ ሥራዎችን በመምራት ባለጉዳይን ማጉላላት ተገቢነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን በመግለጽ ለጽሕፈት ቤቱ እንዳሳወቀ በደብዳቤው ይነበባል።

በ20/01/2009 ዓ.ም በቁጥር አአ/መልማቢ/07/0267/09 ቢሮው ዳግም ለጽሕፈት ቤቱ የነበሩትን ሒደቶች አብራርቶ ጽፎ ልኳል። ኤጀንሲው ማስረጃ የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም ከዚህ በላይ መጠበቅ የማያስፈልግ በመሆኑ ግለሰቦቹ የግዴታ ውል ገብተው አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበት ገልጧል።

በክፍለ ከተማው በይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ፕሮጀክት ዴስክ በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ሰ/አ/085/2011 በቀን 2/2/2011 ዓ.ም ለወረዳ ስድስት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የወይዘሮ ዛይድ ማህደር እንዲላክለት የጠየቀበት ደብዳቤን መመልከት ችለናል። በዚህም አገልግሎት ለመስጠት ማህደራቸውን ማግኘት መቸገሩን በመግለጽ፤ የማህደራቸው ግልባጭ እንዲላክለት መጠየቁ በደብዳቤው ሰፍሮ ይነበባል። በተያያዘ ዴስኩ፤ ዳግም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ሰ/አ/173/2011 በ7/12/2011 ዓ.ም ለወረዳ አስተዳደሩ በጻፈው ደብዳቤ የወይዘሮ ዛይድ ማህደር እንዲላክ በጠየቀው መሠረት ወረዳው የላከ ቢሆንም ተሞልቶ ያልተላከ መረጃ በመኖሩ ይህ ተሟልቶ እንዲላክ መጠየቁን ያሳያል። በዚህም መነሻ ለክፍለ ከተማው መሬት ይዞታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የሰነድ ማጣራት፣ የሽንሻኖ ማስተካከልና ካርታ ዝግጅት የሥራ ሒደት የወረዳው አስተዳደር በ6/12/2011 ዓ.ም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ/064/11 መረጃውን የላከበት ደብዳቤን ከሰነዶች ውስጥ አግኝተናል።

ፍርድ

ሚያዚያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 266663 የወጣው የመዝገብ ግልባጭ፤ ከሳሽ ወይዘሮ ዛይድ እንደሆኑና ተከሳሽ ደግሞ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንደነበር ያሳያል። ሆኖም ግን ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ በችሎቱ እንዳልቀረቡ መዝገቡ ያስነብባል። ችሎቱም መዝገቡን መርምሮ ፍርዱን አሳርፏል። በዚህም ከሳሽ ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ አጠራር ወረዳ 17 ቀበሌ 21 በአሁኑ ወረዳ 06 የቤት ቁጥር አዲስ የሆነ ቤትና ይዞታ በ1989 ዓ.ም ከአቶ ኢኒ ገደፋ በመግዛት ተጨማሪ ቤቶችን በመስራት ዙሪያውን በማጠር ከ22 ዓመት በላይ ሲጠቀሙ እንደነበር ማቅረባቸውን ያትታል። በወረዳ 06 የሰነድ አልባ ይዞታዎች አጣሪ ኮሚቴና የወረዳ 06 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተጣርቶና ተረጋግጦ ካርታ እንዲሰራላቸው ለክፍለ ከተማው ሰነድ አልባ ይዞታዎች ዴስክ ተላልፎ የሚገኝ መሆኑን ያስረዳል። ተከሳሽ በጻፈው ደብዳቤ ከሳሽ የማያውቋቸው ግለስብ ለወይዘሮ አበባ ተስፋዬ ከቤት ቁጥር 413/06 ማለትም የኮርፖሬሽኑ ቤት ይዞታ ቆርሰው በማስተላለፍ በተናጠል ወይንም በጋራ ካርታ እንዲያወጡ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ያለ ቢሆንም፤ ከሳሽ ይዞታውን ያገኙት በግዥ ከመሆኑም በላይ አቶ ዘሩባቤል ዮሐንስ ከተከራዩበት ቤት ቁጥር 413/06 ዋናው ቤት ሁለት ክፍል የይዞታ ስፋት 154 ነጥብ 83 በቅጽ ዐዐ8 የካዳስተር ኮድ 3-17-21-75-016-413/6 እና ብሎክ 75 ፐርስል 16 የሆነው በቁጥር ቦሌ 11/6/5/19/16081/00 የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ለተከሳሽ ማረጋገጫ ካርታ መስጠቱን መዝገብ ግልባጩ ያብራራል።

በተሰጠው ማረጋገጫ፤ ከሳሽ የሚኖሩበት ቤት ተከሳሽ ከሚያከራየው ቤትና ይዞታ ጋር ልዩነት እንዳለው እንደሚያሳይና እንደተረጋገጠ ይህንንም የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር የኮንስትራክሽና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ሰነድ አልባ ይዞታ ሬጉላራይዜሽን ፕሮጀክት ዴስክ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮና ተከሳሽ እራሱ በጻፉት ደብዳቤ ማረጋገጣቸውን ያብራራል። ከሳሽ ይዞታውን ያገኙት አቶ ዘሩባቤል ዮሐንስ ቤቱን ከመከራየታቸው 17 ዓመት በፊት መሆኑን፤ ከሳሽ የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ካርታ ሊሰራላቸው ባለመቻሉ ለክፍለ ከተማው የሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ጽሕፈት ቤት አቅርበው በዋና ሥራ አስፈፃሚ በኩል ትዕዛዝ እንደተሰጠውም መዝገብ ግልባጩ ያስረዳል።

ካርታውን ሰርቶ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ቅሬታ አቅርበው ተከሳሽን ይዞታው የራሱ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ዕድል ቢሰጠውም ባለማቅረቡ ካርታው ተሰርቶ እንዲሰጣቸው ግልጽ ትዕዛዝ ቢሰጥም ተከሳሽ ወይንም ኮርፖሬሽኑ በቁጥር ቀ3/17/21/413/06/776/10 በነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ቤቱን እንዲያስረክቡ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሁከት የፈጠረባቸውመሆኑን በዚህም ኮርፖሬሽኑ የፈጠረው የሁከት ተግባር ተወግዶ ከሳሽ በክሱ ምክንያት ያወጡት ወጪእንዲተካላቸው መጠየቃቸውን መዝገብ ግልባጩ ያስነብባል። ከክሱ ጋር የሰነድና የሠው ማስረጃ ማቅረባቸውንም አስፍሯል።ተከሳሽ ታህሳስ 08 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ከሳሽ ቤቱንና ይዞታው በሽያጭ ውል እንደገዙት ያቀረቡት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1720/1፣ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1723/1 እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 21448 አስገዳጅነት ባለው ትርጉም መሠረት ቤቱን በተመለከተ የሽያጭ ውል በሕግ ፊት የፀና የሚሆነው በጽሑፍ ብቻ ሲደርግ ሳይሆን፤ የተደረገው የፅሁፍ ውል ሥልጣን በተሰጠው አዋዋይ ክፍል በፍርድ ቤት የተደረገ ሲሆን፤ ከሳሽ በሽያጭ ውሉ መሠረት ለሦስት መቶ ሜትር ካሬ በላይ ለሆነው ይዞታ ስድስት ሺህ ብር ተከፍሏል ያሉት በአዲስ አበባ የቤት ዋጋ የማያሳምን መሆኑን ከሳሽ ምንም ዓይነት የባለቤትነት መብት ከሌላቸው ከአቶ ኢሳ ገደፋ ላይ በሽያጭ ያገኙት ይዞታ መሆኑን የሚገልጹት ተከሳሽ በሚያስተዳድረው የመንግስትና ሕዝብ በሆነ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታለማግኘት ባቀረቡት ጥያቄ ካርታ የሚሰጠው አካል ሕገወጥ አካሄዳቸውን በመረዳት ሊሰጣቸው የነበረውን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያገደ መሆኑን በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ሰነድ አልባ ይዞታ ሬጉላራይዜሽን ኘሮጀክት ዴስክ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ እና ተከሳሽ ይዞታው የከሳሽ ስለመሆኑ ተረጋግጧል ሲል ያትታል።

ከላይ የተገለጹት የመንግሥት አካላት የተፃፈ ደብዳቤዎች በምንም መልኩ ባለቤትነትን የማያሳዩና በስህተት ተገቢውን ማጣራት ሳይደረግባቸው የተጻፉ መሆኑናቸው ስለተረጋገጠ ለከሳሽ ሊሰጥ የነበረው ማረጋገጫ ካርታ እንዲቆም የተደረገ ሲሆን፤ የሚመለከተው አካል ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ለተከሳሽ ይዞታዎቹን በሙሉ ያጠቃለለ ካርታ ሰርተው ለመስጠት በዝግጅት ላይ በመሆኑ ተከሳሽ ለአቶ ዘሩባቤል በሰጠው ማስጠንቀቂያ ከሳሽ የሁከት ተግባር እንደተፈጠረባቸው ክስ ለማቅረብ መብት የሌላቸው በመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግና ኮርፖሬሽኑ በክሱ ምክንያት ላወጣው ወጪና ኪሳራ በቁርጥ እንዲከፈለው ጠይቆ ከመልስ ጋር የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክስ በሰማበት ወቅት ከሳሽ ቤቱን የያዙት ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ አቶ ዮሐንስ ከተከሳሽ ቤቱን የተከራዩት 1999 ዓ.ም ላይ በመሆኑ በ1989 ዓ.ም ግብር መብራት ደረሰኝ ያለው ሰነድ አልባ መሆኑን በወረዳው ኮሚቴ የተረጋገጠ መሆኑን ተከሳሽ እየጠየቀ ያለው በተከሳሽ ዘንድ የማይገኝ ባዶ ቦታ የግል ይዞታ ስለመሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን በመመሪያ መሠረት ለተከሳሽ ካርታ የተሰጠ መሆኑን በመግለጽ በጽሁፍ ባቀረቡት ላይበማጠናከር ተከራክረዋል።

ተከሳሽም በከሳሽ ባቀረበው መከራከሪያ ላይ በሰጠው መልስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ በ413/06 ላይ መሆኑን ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ምክንያት የሆነው ከሳሽ ወደ ይዞታው በመግባት ካርታ ለማውጣት በእንቅስቃሴ ላይ በመሆኑ 413/06 ይዞታ ላይ ካርታ ተጠቃሎ ያልተሰጠው በመሆኑ፣ እንዲስተካከል ጠይቆ በሒደት ላይ መሆኑን፣ ከሳሽ ሰነድ አልባያሉት ቤት በተከሳሽ ያልተሰራ መሆኑን ገልፆ በጽሑፍ ያቀረበውን መከራከሪያ በማጠናከር መከራከራቸውን መዝገብ ግልባጩ ያብራራል። ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ የተፈጠረ ሁከት አለ ወይ የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መመርመሩንም ያሳያል።

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1149/1 ድንጋጌ ላይ እንደተመለከተው በሕግ ጥበቃ በሚደረግለትና በእጁ አድርጎ በዕውነት በሚያዝበት ይዞታው ላይ ሁከት የተነሳበት ሠው የተነሳው ሁከት በፍርድ ኃይል እንዲወገድለት ለመጠየቅ የሚችል ሲሆን፤ ይዞታውን በሕግ አግባብ ያገኘው መሆኑን በማረጋገጥ ክስ ማቅረብ ያለበት ስለመሆኑም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1140 እና 1146 ይደነግጋሉ ሲል መዝገቡ ያስረዳል። ከሳሽ  በክሳቸው ላይ እንደገለጹት በተከሳሽ ሁከት እንደተፈጠረባቸው ለክሱ ምክንያት የሆናቸው ሰነድ አልባ የሆነውንና በቤት ቁጥር አዲስ የሚታወቀውን ቤት የቤት ቁጥር 413/06 የሆነ የመንግሥት ቤት ነው በሚል እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው መሆኑን በመግለጽ ሲሆን፤ ይህንን ደብዳቤ ፍርድ ቤቱ እንደተመለከተው ተከሳሽ በነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ለአቶ ዘሩባቤል ዮሐንስ እና ወይዘሮ ዛይድ ገብረህይወት በማለት በሰጠው ደብዳቤ ተከሳሽ በሚያስተዳድረው ይዞታ ላይ ካርታ የሌለው መሆኑን እንደ ክፍተት በመጠቀም የቤት ቁጥር 413/06 የሆነውን ያዞታ በመቁረስ ለወይዘሮ አበባ ተስፋዬ በማስተላለፍ በሥማቸው ካርታ እንዲወጣ በማድረግ ጥረትያደረጉ መሆኑንና ያለአግባብ ይዞታውን በሕገወጥ መንገድ የያዙና በቦታው ላይ ቤት እንዲሰራ ያመቻቹ በመሆኑ የኮርፖሬሽኑ ይዞታ ሲወሰድም በመመሪያ መሠረት ያላሳወቁት በመሆኑ ለውል ግንኙነቱ መቋረጥ ምክንያት በመሆኑ የያዙት ቤትና አለአግባብ የተላለፈውን ይዞታ ጭምር እንዲያስረክቡ፤ በራሳቸው የማያስረክቡ ከሆነ ደግሞ ተቋሙ በራሱ የሚረክብ መሆኑን እንደገለፀላቸው ያብራራል።

መዝገብ ግልባጩ፤ በቀድሞ ወረዳ 17 ቀበሌ 21 የቤት ቁጥር 413/06 የሆነውን የመንግሥት ቤት ተከሳሽ ለከሳሽና ለህጻን ዘሩባቤል ዮሐንስ በመጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም አከራይቶት የነበረ ሲሆን፤ ይህንን ቤት ቀደም ሲል የከሳሽ ባለቤት አቶ ዮሐንስ ተከራይተውት የነበረ መሆኑን የግራ ቀኙ ክርክር የሚያስረዳ ነው ይላል። ክርክሩ እየተደረገ ባለበት ወቅትም ቤቱ በአቶ ዘሩባቤል ዮሐንስ ሥም ብቻ የቤት ኪራይ ውል እየተደረገበት መሆኑን ተከሳሽ ለፍርድ ቤቱ አስርድተዋል። ከሳሽ ክስ ያቀረቡበትን ቤት ከአቶ አኒ ደገፋ መስከረም 2 ቀን 1989 ዓ.ም የገዙ መሆኑን የሚገልጽ የሰነድ ማስረጃ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከሳሽ ያቀረቡት የሰነድ ማስረጃ እንደሚያስረዳውም ተከሳሽ በቤት ቁጥር 413/06 ላይ በካርታ ቁጥር ቦሌ 11/651/16ዐ81/00 የሆነ የይዞታ ማረጋገጫ የተሰጠ ነው ሲል ያስረዳል።

ተከሳሽ ደንብ ቁጥር 398/2009 አንቀጽ ዘጠኝ እንዲሁም በአ/ቁ 555/ 2000 አንቀጽ ስድስት ቁጥር ሦስት ብሎም በመመሪያ ቁጥር 02/2010 ድንጋጌዎች መሠረት ውል ሳይኖራቸው የመንግሥት ቤት የያዙትን የማስለቀቅ በመንግሥት ቤቶችና ይዞታዎች ላይ የሚከናወኑ ሕገወጥ ግንባታዎችን የማስፈረስ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ በዚህ በካርታ ተመልክቶ በተሰጠው ይዞታ ላይ ያለን በሕገወጥ መንገድ የተያዘን ቤት ለማስለቀቅና የተሰራ ሕገወጥ ግንባታን ለማፍረስ በሕግ ሥልጣን እንዳለውም ያትታል። በጉዳዩ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት ለተከሳሸ በካርታ ቁጥር ቦሌ 11/651/19/16081/00 ከተሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ውጪ ያለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮን ጨምሮ የቦሌ ክፍለ ከተማ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በተለያየቀን የፃፏቸው በከሳሽ የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያስረዱም መዝገብ ግልባጩ አስፍሯል።

ከሳሽ ለክርከሩ መነሻ በሆነው ቤት ላይ የንግድ ሥራ ሲሠሩ የነበረ መሆኑን ያቀረቡት የገቢ ግብር ደረሰኝ የሚያሳይ ሲሆን፤ በቤቱም በሥማቸው መብራት እንዳስገቡ ያስረዳል። በዚህም ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት ተከሳሽ በካርታ ተመልክቶ በተሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ውስጥ የማይገኝ ሲሆን፤ ይህ ቤትም በቤት ቁጥር 413/06 ይዞታነት የማይታወቅነው። ተከሳሽ የቤት ቁጥር 413/06 በተመለከተ ተከራይ የሆኑት አቶ ዘሩባቤልን በተመለከተ የውል ጥሰት ከፈፀመ የመጠየቅ መብት ያለው ሲሆን፤ ይህንን ክርክር የቀረበበትን በከሳሽ እጅ ያለውን ቤት በተመለከተ ግን ባለቤት ነኝ የሚል ከሆነ ክስ አቅርቦ መብቱን የሚጠይቅ ከሚሆን በስተቀር ቤቱ በይዞታው ላይ የተሠራ ነው በሚል መከራከሪያ ብቻ ከሳሽን ከቤቱ ለማስለቀቅ የሰጠው ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር የሆነ ከሳሽ ይዘውት ባለው ይዞታ ላይ እንዳይገለገሉ የሚያደርግ ተግባር መሆኑን ገለጾ ድርጊቱን ተችቶታል። ይህም ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ጣልቃ ገብነት በመሆኑ ከሳሽን ከቤት ለማስለቀቅ እያደረገ ያለውን እንዲያቆም ፍርድ እንደተሰጠ ሰነዱ አስፍሯል።

መዝገብ ግልባጩ እንደሚያስነብበው፤ ችሎቱ ፍርዱን መሠረት አድርጎ ውሳኔ ያሳረፈ ሲሆን፤ በዚህም ከሳሽ በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞው አጠራር ወረዳ 17 ቀበሌ 21 በአሁኑ ደግሞ ወረዳ 06 ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሚገኘው የቤት ቁጥር አዲስ የሆነውን ቤት በተመለከተ በቤቱ ላይ መብት አለኝ የሚል ከሆነ የመፋለም ክስ አቅርቦ መብቱን ለመጠየቅ ከሚችል በስተቀር ይህንን ከሳሽ በእጃቸው አድርገው የሚገለገሉበትን ቤት በራሱ ከሕግ አግባብ ውጪ ለማስወጣት የሰጠው ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር በመሆኑ ይህንን ተግባሩን ለያቆም ይገባል ሲል መወሰኑን ያትታል።

ክፍለ ከተማው

በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የመስክ ልኬትና የሽንሻኖ ካርታ ዝግጅት ባለሙያ አቶ ዳዊት ገብረማርያም፤ ማህደሩን በመመልከት ይዞታው ላይ ካርታ ሊሠራ የቻለበትን ምክንያት አስረድተውናል። በዚህም ወይዘሮ ዛይድ ገብረህይወት ማሕደር ወደ እርሳቸው ተመርቶ እንደነበር ነው የሚናገሩት። ብሎክ 61 ፓርሴል D-02 የሚል መለያ ያለው ይዞታው በመመሪያ ቁጥር 18/2006 መሠረት በ1997 ዓ.ም የመስመር ካርታ ላይ የሚታየውን ይኸን ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሠሩ ይገልፃሉ። ይኸም የሕግ ባለሙያው ችግር ስላለው ይሠራ ብለው በገለጹላቸው መሠረት ሙያዊ ሥራ እንደሠሩ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ካርታው ተዘጋጅቶ ችግር አለበት በሚል በደረሰ ጥቆማ ወጪ እንዳይሆን ተደርጓል። ከይዞታው አጠገብ የኮርፖሬሽኑ ሁለት ቤቶች እንደሚገኙም የጂአይኤስ (ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም) ማስረጃዎች በመመልከት ገልፀውልናል።

አቶ ዳዊት፤ ጉዳዩ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ከመጣ ባለጉዳዮቹ መጉላላት እንደሌለባቸው ይናገራሉ። ተገልጋዩ አገልግሎት ማግኘት ስላለባቸው የእነ ወይዘሮ ዛይድን ጥያቄ የሕግ ባለሙያውን በማማከር ማሕደሩ ምንም ችግር የለውም የሚል ምላሽ እንዳገኙ ያስታውሳሉ። በዚህም መስመር ካርታውን ጠብቀውና በአካል ወርደው አጣርተው በልኬቱ መሠረት የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ መሥራታቸውን ይናገራሉ። የእርሳቸው የሥራ ድርሻም በመስመር ካርታ ላይ የሚታየውን ይዞታ በአካል መሬት ላይ በመውረድ ማመሳከርና ጥያቄውን ማስተናገድ በዚህም ካርታ መሥራት ሲሆን፤ ጉዳዩን ማጣራት ያለበት የሕግ ባለሙያ እንደሆነ ያብራራሉ።

እኛም የአቶ ዳዊትን ምላሽ በመቀበል በክፍለ ከተማው የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የሰነድ አልባ የሕግ ባለሙያ አቶ ግደይ ነጋሽ በጉዳዩ ላይ አነጋግረናቸዋል። አቶ ግደይ ይዞታውን ማህደር በመመልከት ያስረዱን ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ይዞታው ካርታ እየተሠራለት እንደሆነም ገልፀውልናል። ክፍለ ከተማው የግለሰብ ይሁን የመንግስት ይዞታ እንደሆነ ዕውቅና ባይኖረውም ወረዳው አጣርቶ የላከው መረጃ ግን ይዞታው የግለሰብ እንደሆነ ያሳያል። የወረዳው ኮሚቴዎች ባጣሩት መሠረት ክፍለ ከተማ ተልኮ አጣርቶ ካርታ እየተሠራ ነው።

በይዞታው ላይ ክርክር ተነስቶ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ግደይ፤ በአሁኑ ወቅት ክርክሩ በፍርድ ቤት እልባት ያገኘ በመሆኑ ባለጉዳዮቹ ወይንም እነ ወይዘሮ ዛይድ አገልግሎት እንዳያገኙ የሚከለክላቸው ምንም ሕጋዊ መሠረት እንደሌለም ይገልፃሉ። በይዞታው ማህደር ላይ የሚገኙ ማስረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ካርታዎቹ ከሽፈዋልና ሕጋዊ ከሆኑ ለምን ይህ ተደረገ? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ግደይ፤ ካርታውን የሠራው ባለሙያ ምናልባት በሥራው ላይ ይዞታውን ከልኩ አሳንሶ አልያም ጨምሮ ከሆነ ለማስተካከል የሚያደርገው ክፍተት እንጂ ወይዘሮ ዛይድ አገልግሎት እንዳያገኙ የሚከለክል ማስረጃ ከማህደራቸው ውስጥ አለመገኘቱን ይገልፃሉ። ካርታ ሲመክን የራሱ ሒደት ስላለው የፍርድ ቤት እግድ ሳይመጣ በጥቆማ ካርታ እንዲከሽፍ እንደማይደረግ በመግለጽም፤ የባለሙያ ስህተት ሊሆን ይችላል ሲሉ ምላሻውን ሰጥተውናል።

በሰነድ አልባ መመሪያ መሠረት ቦታውን የያዘ ግለሰብ ካለ የወረዳ ኮሚቴ አጣርቶ ሲያመጣ ሰነድ አልባ በተመለከተ የሚሠራው ክፍል ደግሞ ባለሙያ በመላክ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ወርዶ ይመለከታል። በዚህ መልኩ ተረጋግጦ ካርታ ሊሰራለት የሚገባ ይዞታ እንደሆነ ዕምነት ከተያዘ ለካርታ ሥራ ያስተላልፋል። ካርታ ሥራም የሊዝ ክፍያው እንደተጠበቀ ሆኖ አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት ወይዘሮ ዛይድ አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ያመለክታሉ።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጥቅምት 5/2012

ፍዮሪ ተወልደ