ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶች

22

እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!

እርስዎ ወደ ትዳር ዓለም ያልተቀላቀሉ “ላጤ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አልያም አግብተው ከውሃ አጣጭዎ ጋር በሞቀ ትዳር ውስጥ ያሉ ዕድለኛ መሆንዎ አይቀርም፡፡ ትዳርዎ ከዕለት ዕለት በመቀዛቀዙ “ከእንግዲህስ ይብቃኝ” ብለው ለመፋታት ወስነው ግን እንዴት እንደሚያደርጉ ግራ ተጋብተውም ይሆናል። ወይንም ደግሞ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያለ ወዳጅ ዘመድ ሊኖርዎት ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ስለፍቺና ስለጋብቻ መፍረስ ጉዳዮች ያልዎት ግንዛቤ እንዲጎለብት በማሰብ ይህንን ጽሁፍ አሰናድተናል፡፡

በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ መሰረት ቤተሰብ አንድም በስጋ ዝምድና ማለትም አያት፣ አባትና እናት እንዲሁም ልጆች እየተባለ በተወላጅነት ይመሰረታል፡፡ በሌላ በኩል በጋብቻ ይመሰረታል ቤተሰብ። በጉዲፈቻም እንዲሁ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ታዲያ ቤተሰብ የሚመሰረትበት ዓይነተኛ መሳሪያ ጋብቻ ነው፡፡ ባልና ሚስት በትዳር ሲተሳሰሩ ሚስት የባሏ ወላጆችም ልጅ ወይም ምራት (Daughter in law) ትሆናለች፤ ባልም እንዲሁ የሚስቱ ወላጆች ልጅ ወይም አማች (Son in law) ይሆናል፡፡ በዚህ መነሻ ባልና ሚስት በሚጋቡበት ወቅት ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር በማጋባት የጋብቻ ዝምድና ስለሚፈጥሩ ሰፊ ማህበራዊ ትስስር ያለበት ግንኙነትን ይፈጥራሉ ማለት ነው፡፡

ጋብቻ በሶስት ዓይነት መልኩ ከተከናወነ የጸና እና በሕግም ፊት ዋጋ ያለው ይሆናል፡፡ ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት ይፈጸማል። ይህም በአሁኑ ወቅት እንደ ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ያሉትን ወሳኝ ኩነቶች በሚመዘግብ መስሪያ ቤት ውስጥ በባለሙያው ፊት ምስክሮች ባሉበት የሚፈጸም ጋብቻ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ ተጋቢዎቹ በሐይማኖታቸው ወይም ከሁለቱ በአንዳቸው ሐይማኖት መሰረት የሚጸና ጋብቻ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ስርዓት በመፈጸም የሐይማኖታዊ ስርዓት ጋብቻ ይፈጽማሉ፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናትና አንድ ሴትና አንድ ወንድ በሚኖሩበት አካባቢ ባህል መሰረት በሕግ የሚጸና ጋብቻ መመስረትም ይችላሉ። እነዚህ ሶስቱም የጋብቻ አፈጻጸም ስርዓቶች በኢትዮጵያ ሕግ እኩል የሆነ እውቅናና ጥበቃ የተደረገላቸው ናቸው፡፡

በየትኛውም ዓይነት መንገድ የተመሰረተ ጋብቻ እስከ ህይወት ፍጻሜ ድረስ ጸንቶ እንደሚቆይና ባልና ሚስትን ከሞት በስተቀር ሌላ የሚለያቸው እንደማይኖር ይታሰባል፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ጋብቻ እድሜው አጥሮ ባልና ሚስቱም አይንህን ላፈር፣ አይንሽን ላፈር መባባላቸው አይቀርም። በዚህ መነሻም የባልና ሚስት የእህል ውሃ ገመድ ይበጠሳል፤ ባልና ሚስት መሆናቸውም ቀርቶ እንደ ሌላ ባዕድ (ሶስተኛ ወገን) ይተያያሉ፡፡ ጋብቻ ሲፈርስ የራሱ ውጤቶች ስላሉት ሲፈርስም ሆነ መፍረሱን ተከትሎ የሚከናወኑት ነገሮች በአግባቡ እንዲፈጸሙ ህግ የራሱን መፍትሄዎች አስቀምጧል፡፡

ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶች

ጠቅለል ባለ አነጋገር ጋብቻ በሁለት መልኩ ነው የሚፈርሰው ህግ በሚያስቀምጣቸው ምክንያቶች እና በባልና ሚስቱ ምክንያት፡፡ ከተጋቢዎቹ የአንዱ መሞት ወይም በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ መሰጠቱ ጋብቻ የሚፈርስበት አንዱ ምክንያት ነው፡፡

ባል ወይም ሚስት በህይወት ከሌለ/ች አብሮ መኖር የሚባለው ጉዳይ በመሰረቱ ስለማይኖር ጋብቻ በህግ ይፈርሳል ማለት ነው። በሌላ በኩል ባል ወይም ሚስት ጠፍቶ/ታ ወሬው/ዋ ለሁለት ዓመታት ያልተሰማ እንደሆነ ማንኛውም ሰው ቢሆን የመጥፋት ውሳኔ በፍርድ ቤት እንዲሰጥበት ያስደርጋል፡፡ በዚሁ መነሻ ፍርድ ቤቱ የመጥፋት ውሳኔውን በሰጠበት ቀን ጋብቻው እንደሚፈርስ ስለ ሰዎች የተመለከተው የፍትሐብሔር ሕጋችን ይደንግጋል፡፡ የመጥፋት ውሳኔ የተሰጠበት ተጋቢ ተመልሶ ቢመጣ እንኳን ቀደም ሲል የነበረውና በመጥፋቱ ምክንያት የፈረሰው ጋብቻ ተመልሶ በመምጣቱ ምክንያት ዳግም ነፍስ አይዘራም፡፡

ለጋብቻ መፍረስ ሕጉ ራሱ ከሚያስቀምጣቸው ከሞትና ከመጥፋት ምክንያቶች በተጨማሪ ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ከተጣሰም ለጋብቻ መፍረስ ምክንያት ይሆናል። ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነጻና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሳይሰጡ ወደ ትዳር ውስጥ ገብተው ከሆነ፤ 18 ዓመት ሳይሞላቸው የተጋቡ ከሆነ፤ ተጋቢዎቹ ወላጆችና ተወላጆች አልያም እህትና ወንድም ወይም አክስት አጎት ከሆኑ ጋብቻውን ህጉ ራሱ ፈራሽ ነው ይለዋል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በርካታ መዛግብት ላይ ከተሰጡ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የተጋቢዎች ተለያይቶ ለረዥም ጊዜ መኖር ወይም በዚህ ረዥም ጊዜ ውስጥ ሌላ ትዳር መስርቶ መገኘት የቀደመውን ጋብቻ ፈራሽ ያደርገዋል፡፡ ጋብቻው በሞት፣ በመጥፋት ወይም በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ ፈርሷል ባይባልም ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የመተጋገዝ፣ የመደጋገፍና የመከባበር እንዲሁም አብሮ የመኖር ግዴታን የሚጥል ሆኖ ሳለ ባልና ሚስቱ በተለያየ ምክንያት ተለያይተው ለረዥም ጊዜ መኖራቸው ጋብቻውን እንደሚያፈርሰው ነው የሰበር ችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠበት፡፡

ከእነዚህ የህግ ምክንያቶች ሌላ ራሳቸው ተጋቢዎቹ በሚወስዱት ርምጃ ጋብቻ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ይኸውም ፍቺ መፈጸም ነው፡፡ አንድም ባልና ሚስት ጋብቻቸውን ለማፍረስ ሊስማሙ ይችላሉ፤ አልያም በተናጠል ጋብቻቸውን በፍቺ ማፍረስ ይችላሉ፡፡ ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑ ይህንኑ ለፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔያቸው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ እንዲሁም ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ካመለከቱ ጋብቻ ይፈርሳል፡፡ ጋብቻ ባልና ሚስት በራሳቸው የሚፈጽሙት ጥብቅ የሆነ ሕጋዊ ድርጊት በመሆኑ ፍቺንም ቢሆን በራሳቸው እንጂ በውክልና ሊፈጽሙ አይገባም፡፡

ቀደም ባሉት ዘመናት በተለይም የሐይማኖት ሕግጋት የሰዎች ዋነኛ መመሪያዎች በነበሩባቸው ወቅቶች ፍቺ የተከለከለ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ የኋላ ኋላ ግን በተለይም ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በርካታ አገራት ፍቺን የህጎቻቸው አካል አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያም በ1952ቱ የፍትሐብሔር ሕግ ከባድ ሁኔታዎች (እንደ ዝሙትና የባል ወይም የሚስት እብደት) ሲያጋጥሙ ጋብቻ በፍቺ እንደሚፈርስ ተደንግጓል፡፡ በጊዜ ሂደትም በ1992 በወጣው የተሻሻለው የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ የመፋታት ነጻነት ያለገደብ ተፈቅዷል፡፡ የቤተሰብ ሕጉ በታወጀበት ዋዜማ ላይ በተደረጉ ክርክሮችም ጋብቻን ባልና ሚስት ያለምንም ከባድ ምክንያት ስለተስማሙ ብቻ በፍቺ እንዲያፈርሱት ሙሉ ነጻነት መስጠቱ ቤተሰብን በቀላሉ የሚበትንና የጋብቻ ፍሬ የሆኑ ሕጻናትን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በመጥቀስ ፍቺ ከባድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ብቻ እንዲፈቀድ የሚሞግቱ ጠንካራ ሀሳቦች ተነስተው እንደነበር የተለያዩ ጽሁፎች መዝግበዋል፡፡ ይሁንና የመፋታት ነጸነት ያለገደብ ሊሰጥ ይገባል የሚለው እሳቤ ገዥ ሆኖ ሕጉም በዚሁ አግባብ ሊጸድቅ ችሏል፡፡

በዚሁ መሰረት ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት የወሰኑ እንደሆነ የፍቺ ስምምነታቸውንና ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤት (ከንብረት ክፍፍል አልያም ከልጆች አያያዝ ወዘተ በተገናኘ) በጽሁፍ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍቺው እንዲጸድቅላቸው መጠየቅ እንደሚችሉ ህጉ ደንግጓል፡፡ ባልና ሚስቱ ታዲያ ለፍርድ ቤቱ በሚያቀርቡት የፍቺ ማመልከቻ ላይ ለመፋታት የወሰኑበትን ምክንያት እንዲገልጹ አይገደዱም፡፡

« አብሮ መኖሩን ለእኛ ካላለልን፤

እስኪ እንሞክረው ደግሞ ተለያይተን” እንዳለው ዘፋኙ ለማፋታት መወሰናቸውንና ፍቺያቸውም በቀጣይነት የሚኖረውን ውጤት በመግለጽ ብቻ ለፍርድ ቤት ያመለክታሉ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር ተጋብተው ስድስት ወር ያልሞላቸው ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት እንደማይፈቀድላቸው ነው፡፡

ተጋቢዎች የፈቺ ሙሉ ነጻነት አላቸው ቢባልም ለመፋታት ስለተስማሙ ብቻ ጋብቻቸው አይፈርስም፡፡ መንግስትም ጋብቻንም ሆነ ጋብቻው የመሰረተውን ቤተሰብን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህ ነው ህጉ “ፍርድ ቤት የመፋታት ጥያቄ ሲቀርብለት ባልና ሚስትን በተናጠል ወይም በአንድ ላይ በማስቀረብ ስለፍቺ ጥያቄያቸው ያነጋግራቸዋል፤ የመፋታት ሃሳባቸውንም እንዲለውጡ ይጠይቃቸዋል” የሚለው፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን ፍርድ ቤቱ ባልና ሚስት የመፋታት ሃሳባቸውን እንዲለውጡ ጠይቋቸው እነርሱ ፈቃደኛ ባለመሆን ሀሳባቸውን የማይለውጡ መሆኑንና ፍቺያቸውን እንዲያጸድቅላቸው በመጠየቅ ቢጸኑ እንኳን እስከ ሶሰት ወር የሚዘልቅ የማሰላሰያ ጊዜ ሰጥቶ ሊያሰናብታቸው እንደሚችልም በህጉ ተመልክቷል፡፡ በማሰላሰያ ጊዜ ውስጥ ታዲያ ባልና ሚስቱ ሰክነው፣ አስበውና ተነጋግረውበት ሃሳባቸውን ለውጠው ጋብቻቸውን ለማዳን የፈለጉ እንደሆነ የመንግስት ጋብቻን የመጠበቅ ኃላፊነቱ በፍሬ ተቋጨ ማለት ነው፡፡

ይሁንና የማሰላሰያ ጊዜ ቢሰጣቸውም ባልና ሚስቱ በመፋታት ሀሳባቸው ከጸኑ የተሰጣቸው የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወር ውስጥ ጉዳያቸውን እንደገና በማንቀሳቀስ የፍቺ ስምምነታቸውን እንዲያጸድቅላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላሉ፡፡ አዲስ የፍቺ ስምምነትም ለፍርድ ቤት ከማቅረብ የሚከለክላቸው የለም፡፡

ፍርድ ቤቱም የፍቺ ስምምነቱ የባልና ሚስቱ ትክክለኛ ፍላጎት መሆኑን እና ፈቃዳቸውን በነጻነት የሰጡ መሆናቸውን እንዲሁም ስምምነቱ ከሕግና ከሞራል ጋር የማይቃረን መሆኑን በማረጋገጥ ያጸድቀዋል። በተመሳሳይም ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ (ከንብረት ክፍፍል አልያም ከልጆች አያያዝ ወዘተ በተገናኘ) ባልና ሚስቱ ያደረጉትን ስምምነትም ፍርድ ቤቱ ከፍቺ ስምምነታቸው ጋር አብሮ ያጸድቀዋል። ይሁንና ይኸው ስለፍቺው ውጤት ያደረጉት ስምምነት የልጆቻቸውን ደህንነትና ጥቅም በበቂ ሁኔታ የማያስጠብቅ ወይም የአንደኛውን ተጋቢ ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ካገኘው ፍርድ ቤቱ የፍቺውን ስምምነት ብቻ በማጽደቅ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ጉድለቶቹ እንዲስተካከሉ ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡

በባልና ሚስት የጋራ ስምምነት ከሚቀርብ የፍቺ ጥያቄ በተጨማሪ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት በመሆን ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ካመለከቱ ጋብቻ ይፈርሳል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ታዲያ ፍቺ ለመጠየቅ ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ ለመግለጽ ይችላሉ፤ ነገር ግን እንዲገልጹ አይገደዱም፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ ተጋብተው ስድስት ወር ያልሞላቸው ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት የተከለከሉ ቢሆንም ቅሉ፤ በተናጠል የፍቺ ማመልከቻ በማቅረብ ጋብቻ እንዲፈርስ ከመጠየቅ የሚያግዳቸው ህግ ግን አለመኖሩ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት ፍርድ ቤት ገና ከመጀመሪያው የፍቺ አቤቱታው እንደቀረበለት ወዲያውኑ ባልና ሚስቱ ስለሚተዳደሩበትና ስለሚኖሩበት ሁኔታ፤ ስለልጆቻቸው አጠባበቅ፤ ስለሚኖሩበት ስፍራና ስለአኗኗራቸው እንዲሁም ስለንብረታቸው አስተዳደር ተገቢ መስሎ የታየውን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ይህንን ውሳኔ ሲሰጥ ታዲያ ከተጋቢዎቹ የአንዳቸው ከጋራ መኖሪያቸው መውጣት የግድ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ለቆ ቢወጣ የባሰ ጉዳት የሚደርስበት ወገን የትኛው መሆኑን እንዲሁም የልጆቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ አመቺ የሆነውን ሁኔታ ሁሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡

ፍርድ ቤት በስምምነት የፍቺ ጥያቄ ሲቀርብለት እንደሚያደርገው ሁሉ ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር የፍቺ ጥያቄ የሚቀርብበትንና አለመግባባቱን በስምምነት ለመፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ ያግባባቸዋል፡፡ ይህንን ሞክሮ ውጤት ያላገኘ እንደሆነ ወይም የነገሩን አዝማሚያ ሲያየው ውጤት የማያመጣ መስሎ ከታየው ባልና ሚስቱ ከፍርድ ቤት ውጭ ራሳቸው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች አማካይነት ጉዳያቸውን በዕርቅ እንዲጨርሱ ሊጠይቃቸው ይችላል፡፡ በዕርቅ ለመጨረስ ካልተስማሙ ደግሞ ከሶስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ በመስጠት ሊያሰናብታቸው ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ጥረት ሁሉ አድርጎ ጥረቱ ውጤት ያላስገኘለት እንደሆነ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ሪፖርት ከደረሰው ወይም ለተጋቢዎቹ የሰጣቸው የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

የተናጠል የፍቺ ጥያቄ በጋራ ስምምነት ከሚደረግ የፍቺ ጥያቄ የሚለየው ባልና ሚስት ጋብቻቸውን በፍቺ ለማፍረስ የተስማሙ ከሆነ ለፍርድ ቤት የሚያቀርቡት የጽሁፍ የፍቺ ስምምነታቸውን ብቻ ሳይሆን ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤትም በተመለከተ የተስማሙበትንም ጽሁፍ አያይዘው ያቀርባሉ። የፍቺ ጥያቄ በተናጠል በሚቀርብበት ወቅት ግን ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ፍቺ ጠያቂው ወገን እንዲያቀርብ አይገደድም። ምክንያቱም በስምምነት የተደረገ የፍቺ ጥያቄ ባለመሆኑ እንኳንስ በውጤቱ በመሰረቱ እንኳን በፍቺው ላይ ስምምነት ሳይኖር በተናጠል የተወሰደ ርምጃ በመሆኑ “ጋብቻው ሊፈርስብኝ አይገባም” የሚል ክርክር ከሌላው ተጋቢ መቅረቡ አይቀሬ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት የፍቺ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ፍቺው ስለሚያስከትለው ውጤት እንዲስማሙ ባልና ሚስቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ ከተስማሙ ፍርድ ቤት አቅርበው ይሁንታውን ያሰጣሉ፡፡ ለመስማማት ካልፈለጉ ወይም ለመስማማት ሞክረው ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉ እንደሆነ ደግሞ ፍርድ ቤቱ በራሱ ወይም በሽማግሌዎች ወይም ራሱ በሚሾማቸው ባለሙያዎች አማካይነት ወይም አመቺ መስሎ በታየው ዘዴ የፍቺውን ውጤት ይወስናል፡፡

በተናጠል ከሚቀርብ የፍቺ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሌላው በህጋችን የተመለከተው ጉዳይ ካሳን የተመለከተው ነው፡፡ ከባልና ከሚስት አንዱ ለፍቺው ምክንያት የሆነውን በደል (ጥፋት) ፈጽሞ የተገኘ እንደሆነና ፍርድ ቤቱም ለፍትህ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በሌላው ተጋቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በዳዩ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፍል ሊወስንበት እንደሚችል ህጉ አስቀምጧል፡፡

እርግጥ ነው በሕጋችን የፍቺ ጥያቄ አቅራቢው በሌላኛው ተጋቢ የተፈጸመ በደል (ጥፋት) ስለመኖሩ እንዲገልጽ አይገደድም፡፡ የካሳ ጉዳይ የሚነሳ ከሆነ ግን ጥፋት ስለመኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ “በጋብቻው መፍረስ ምክንያት የተከሰተውን ጉዳት ነው ወይንስ የፍቺ ጥያቄ እንዲቀርብ ያስገደደው በደል ያስከተለውን ጉዳት ነው ህጉ ካሳ ለማስከፈል በምክንያትነት የወሰደው?” የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ “ካሳ ሲባልስ የሞራል ጉዳት ካሳ ነው ወይስ የማቴሪያል ጉዳት ካሳ? ሁለቱንም ሊሆን ይችላልን?” የሚለውም ሌላው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን እንደሚገልጹት ፍርድ ቤቶች በአብዛኛው በጋብቻው መፍረስ ምክንያት ለተከሰተው ጉዳት ሳይሆን ካሳ የሚያስከፍሉት የፍቺ ጥያቄ እንዲቀርብ ያስገደደው በደል ያስከተለውን ጉዳት ነው ካሳ የሚያስከፍሉት። የካሳውን ዓይነት በተመለከተም የሞራልም የማቴሪያልም ጉዳት ካሳን እንደሚያጠቃልል ነው ብዙዎች የሚስማሙት፡፡

በደህና እንሰንብት!

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጥቅምት 5/2012

(ከገብረክርስቶስ)