ሥራና ህይወታቸውን አንድ ያደረጉ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ

127

ዕውቁ ደራሲ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ የተወለዱት ከ 110 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት ሰባት ቀን 1902 ዓ.ም ነበር።

በፍቅር እስከመቃብር 19ኛ ዕትም የጀርባ ሽፋን ላይ የተጻፈው የደራሲው አጭር የሕይወት ታሪክ እንደሚያትተው ሀዲስ አለማየሁ ሰለሞን በ1902 ዓ.ም ጎጃም ደብረማርቆስ አውራጃ እንዶዳም ኪዳነምሕረት ነው የተወለዱት። አያታቸው የዜማ መምህር ስለነበሩ እዚያው በተወለዱበት አገር በስድስት ዓመታቸው ፊደል መቁጠር ጀምረው አስራ አምስት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ የዜማ ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ደብረኤሊያስ ደብረወርቅና ዲማ በሚባሉ አድባራት እየተዘዋወሩ የቅኔ ትምህርት ተምረው አጠናቀዋል።

በ1918 ዓ.ም አዲስ አበባ መጥተው መጀመሪያ በስዊድን ሚሲዮን ቀጥሎም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ መጀመሪያ በተማሩበት በስዊድን፤ ሚሲዮን ቀጥሎም በጎጃም ዳንግላና ደብረማርቆስ በአስተማሪነት አገልግለዋል። በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ማስተማሩን ትተው በዘመኑ የጎጃም እንደራሴ ከነበሩት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴ ስር በመሆን ትግራይ ሽሬ ግንባር ዘምተዋል። ሀዲስ ጣሊያንን ለመውጋት ጠመንጃ ከመንግስት ሳይጠብቁ ራሳቸው ገዝተው ነው የዘመቱት። ስለሁኔታው ሲገልጹ “ደብረ ማርቆስ አስተማሪ ሳለሁ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረች። እኔም ማስተማሬን ትቼ፣ ጠመንጃ ገዝቼ ዘመትኩ።” ይላሉ።

በ1929 ዓ.ም በታህሳስ መጨረሻ ላይ ጌራ ላይ ከተደረገው ትልቅ ጦርነት በኋላ ጅማንና ከፋን በሚያዋስነው ጎጀብ ወንዝ ላይ ተከበው ተይዘው ወደ ጣሊያን አገር ተግዘዋል። በ1936 ዓ.ም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣሊያንን ድል አድርገው በያዙት በእንግሊዝና በካናዳ ወታደሮች እስኪፈቱ ድረስ ፖንዛና ሊፓሪ በሚባሉ ደሴቶች በኋላም በላይቤሪያ ውስጥ ሎንግቦኮ በሚባል ተራራማ ገጠር ከሰባት ዓመት በላይ ታስረዋል።

በ1936 ዓ.ም ከጣሊያን ተመልሰው በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ፣ ተቀማጭነታቸው እንግሊዝ አገር ሆኖ የእንግሊዝና የሆላንድ አምባሳደር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ አምባሳደር፣ ከዚያም መልስ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የሕግ መወሰኛ እና የብሔራዊ ሸንጎ አባል እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት አገልግለዋል።

ሀዲስ አለማየሁ በድርሰት ዓለም የመጀመሪያ የፈጠራ ድርሰታቸው ያበሻና የወደኋላ ጋብቻ የተሰኘ ተውኔት ሲሆን፤ በወቅቱ የተመልካችን ልብ የሳበ ነበር። ሀዲስ ከግዞት ከተመለሱ በኋላ የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም፣ ተረት ተረት፣ ፍቅር እስከ መቃብር፣ ወንጀለኛው ዳኛ፣ የልምዣትና ትዝታ የተባሉ ድርሰቶቻቸውን አሳትመዋል።

በ 1974 አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ፍቅር እስከመቃብርን በኢትዮጵያ ራዲዮ ግሩም አርጎ ከተረከው በኋላ ኢትዮጵያውያን መጽሐፉን እጅግ አድርገው ወደዱት። በዚህ ጊዜ ሀዲስ አለማየሁ መጽሐፉን እኔ ጻፍኩት እንጂ ህይወት የዘራህበት አንተ ነህ ብለው ፊርማቸው ያረፈበትን ቅጂ እንደሰጡት ይነገራል።

እሱባለው አማረ “ያልተነገሩ የሀዲስ ዓለማየሁ ታሪኮች” በሚል ርእስ ደራሲውን የተመለከቱ አንዳንድ አስደናቂ ጉዳዮችን ጽፈዋል። ሀዲስ ዓለማየሁ ዘመናዊ ትምህርት የመማር ፍላጎት አልነበራቸውም። ስዊዲን ሚስዮን ትምህርት ቤት የገቡት ከብዙ ማባበልና ልመና በኋላ ነው። ትምህርቱን ላለመማር ያቀርቡት የነበረው ምክንያትም “የፈረንጅ ትምህርት ሃይማኖት ያስለውጣል” የሚል ነበር።

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቆንስል ሆነው ለሁለት ዓመታት ባገለገሉበት ወቅት ከባለቤታቸው ወይዘሮ ክበበፀሐይ በላይ ጋር ተዋውቀው ለጋብቻ በቅተዋል። በጊዜው ወይዘሮ ክበበፀሐይ ከአያታቸው ጋር ኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። ከ15 ዓመት የትዳር ሕይወት በኋላ ባለቤታቸው በጸና ታመው በአሜሪካ፣ ኒውዮርክ በህክምና ሲረዱ ቆይተው አረፉ። ሀዲስ ዓለማየሁ ከዚህ በኋላ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ ሌላ ሚስት አላገቡም።

ከባለቤታቸው ሞት በኋላ አዲስ አበባ ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገኘውን መኖሪያ ቤታቸውን የሕጻናት ማሳደጊያ እንዲሆን አድርገዋል። መኖሪያ ቤታቸው “ክበበፀሐይ የሕጻናት ማሳደጊያ” በሚል መጠሪያ ተሠይሞ በርካታ ህጻናት አድገውበታል፤ እስካሁንም ድረስ አያሌ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ሕጻናት እያደጉበት ነው። ለአብነትም ከ15 ቀናት በፊት በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የትምህርት ዕድል ተመቻችቶላቸው ወደናይጄሪያ እንዲያቀኑ ከተደረጉ አምስት ወላጆቻቸውን ያጡ የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ሁለቱ የተመረጡት ከክበበፀሐይ የህጻናት ማሳደጊያ ነው።

ሀዲስ ከአንድም ሁለት ጊዜ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር የተካረረ ጸብ ውስጥ ገብተው ያውቃሉ። የትምህርት ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅት በተደረገ የአፍሪካ የትምህርት ሚኒስትሮች ጉባኤው መሃይምነትን በሃያ ዓመት ውስጥ ከአፍሪካ ምድር ለማስወጣት በተያዘው ዕቅድ ተስማምተው በወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴር የነበረው በጀት አነስተኛ ስለነበር ለጃንሆይ የበጀት ጥያቄ አቀረቡ። የተሰጣቸው መልስ ግን እንዲያውም “የገንዘብ እጥረት በመኖሩ ከትምህርት ሚኒስቴር በጀት እሩቡ ይቆረጥ” የሚል ሆነ፤ ሀዲስም ተቆጥተው ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።

የእነ መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በተደረገበት ወቅት የሀዲስ ጓደኞች በሙከራው ተጠርጥረው ታስረው ነበር። ሀዲስ ጓደኞቻቸው ያልጥፋታቸው እንደታሰሩ የሚገልጽ 13 ገፅ ልዩ ማስታወሻ ጽፈው ለጃንሆይ ሰጧቸው። ጃንሆይ ልዩ ማስታወሻውን ሲያነብቡ ‹‹ከንቱ ውዳሴ›› የሚል ሀረግ ስላገኙበት ተቆጥተው

ሀዲስን ቤተ-መንግሥት አስጠርተዋቸው “ሰደብከን!” ብለዋቸው ጽሑፉን አርመው እንዲያመጡ አዘዙ። ሀዲስ “ምንም የማርመው የለኝም” ብለው ከቤተ-መንግሥቱ ወጡ።

ደርግ ሀዲስን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ጥያቄ ያቀረበላቸው ቢሆንም አልተቀበሉም። ምክንያቱን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ “ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁን ተባልኩ። ለውጥ ለውጥ ይባላል ለውጡ ምን ልታመጡ ነው? ስላቸው ዝርዝሩን በኋላ እናመጣለን አሉኝ። እኔ ላምጣና ቁጭ ብለን እንስማማበት ስላቸው አይሆንም አሉ። እንግዲያውስ እኔም አይሆንም አልኩ።”

ሀዲስ ኢትዮጵያ ወደፊት ይገጥማታል ያሉትን ፈተና አሻግረው በመመልከት በ 1985 ዓ.ም መጋቢት 19 ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቀረቡትን ንግግር በወቅቱ ይታተም የነበረው ኢትዮጵያዊነት መፅሄት እንዲህ አስነብቦ ነበር። “…አሁን በይፋ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮች ስመለከትና እንዲሁም በይፋ በየመድረኩ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮችን ስሰማ በኔ አስተያየት የኢትዮጵያ ህልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ቆሞ የሚገኝ ይመስለኛል። ይህን የምልበት ምክንያት ዛሬ ራሳቸውን በልዩ ልዩ የነፃነት ግንባር የሰየሙ ቡድኖች ‘የህዝቦች የራስን እድል – እስከነፃነት በራሳቸው የመወሰን መብት’ ለተባለው ድንጋጌ የተሳሳተ ትርጉዋሜ ሰጥተው የራሳቸው ነፃ መንግስት እንዲኖራቸው … ያሰቡት ሀሳብ ፍፃሜ የሚያገኝ ከሆነ ይህ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የማይጣጣም ሆኖ ስለሚታየኝ ነው።

“የህዝቦች የራሳቸውን እድል እስከ ነፃነት… የሚለው ድንጋጌ በነፃነት ግንባሮች የተሰጠው ትርጉዋሜ የተሳሳተ ከመሆኑም ሌላ እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ነገዶችና በነገዶችም ውስጥም ብዙ ጎሳዎችና ንኡስ ጎሳዎች በሚኖሩባት አገር በቃል የሚነገረውን ያክል በግብር መተርጎሙ ቀላል ሳይሆን ሊወጡት የማይቻል ገደል ነው። በተጎራባች አገሮች መካከል ያለው የወሰን የወንዝ ክፍፍል የጎሳዎችና የንኡስ ጎሳዎች አስተዳደር የሚያስነሱት ዘልአለማዊ ሁከትና ጦርነት ለሀገርና ለልማት ሊውል የሚገባውን ሀብትና ጉልበት እየበላ ሁልጊዜ አደህይቶና ሰላምን አሳጥቶ የሚኖር በመሆኑ የሚሸሹት እንጂ እንኩዋንስ ሊይዙት የሚቀርቡት አይደለም። …

ይህ ንኡስ አንቀፅ ተፈፃሚነቱ ለሽግግር መንግስቱ እድሜ ብቻ እስከሆነ ድረስ የሚፈጥረው ችግር ቢኖር ጎልቶ ላይታይ ይችል ይሆናል። አሁን ወደሚረቀቀው ቀዋሚ ህገመንግስት የሚተላለፍ ከሆነ ግን በየነገዳቸው ህዝብ ላይ ስልጣን መያዝ ለሚፈልጉ ሁሉ በር ከፋች ሁኖ መጨረሻው ለማይታይ ሁከትና ጦርነት መንስዔ ሊሆን ስለሚችል ህገመንግስቱን ለማርቀቅ ሀላፊነት የተጣለባቸው ክፍሎች አጥብቀው ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል። ተመሳሳይ ህገመንግስት በነበሩዋቸው አገሮች በሶቭየት ህብረትና በነይጎዝላቢያ ዛሬ የደረሰውም ትምህርት ሊሆነን ይገባል”

ሀዲስ በህይወት ዘመናቸውና ካለፉ በኋላ የተለያዩ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝተዋል። በ1960 ዓ.ም በሥነ ጽሑፍ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ በመሆን ከታላላቅ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ መሆን ችለዋል።

ለኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ነሐሴ 27 ቀን 1991 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያሰራው ከነኀስ የተቀረፀ ኃውልት በ2009 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ቆሞላቸዋል። በዕለቱ የሀዲስ ዓለማየሁን ያልታተሙ ግጥሞች የያዘ በዶክተር ታዬ አሰፋ ተዘጋጅቶ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሀዲስ ዓለማየሁ ጥናት ተቋም የታተመ መጽሀፍም ይፋ ተደርጓ። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርም በ2002 ዓ.ም ለክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ያዘጋጀው የፖስታ ቴምብር በኢትዮጵያ የፖስታ ድርጅት ታትሞ ተሠራጭቷል። ሀዲስ በህዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ብርሀነ መስቀል ደጀኔ በ2000 ዓ.ም ብራና ማተሚያ ቤት ካላንደር ላይ ስለእርሳቸው ባቀረቡት ፅሁፍ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በፍቅር እስከመቃብር ቅኝት ፅሁፉ ላይ ያሰፈረውን ጽሑፍ እንዲህ አስነብበዋል…

“ሀዲስ ዓለማየሁ የፍቅር እስከ መቃብር መፅሃፍ ታሪክ እውነተኛው ገፀ-ባሕሪ ይመስሉኛል። ምክንያቱም በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ትዳር መሰረቱ። ከወ/ሮ ክበበ ፀሐይ ጋር። ግን ብዙም ሳይቆዩ ወ/ሮ ክበበፀሐይ ይህችን አለም በሞት ተለዩ። ሀዲስም ከዚያ በኋላ ትዳር ሣይመሰርቱ ቀሩ። ዘመናቸውን በብቸኝነት አሣለፉ። ይህን ጉዳይ የዛሬ 14 አመት ጠየኳቸው። ለምን ሌላ ትዳር ሣይመሰርቱ ከ50 አመታት በላይ ቆዩ? ልጅም እንኳን አልወለዱም? አልኳቸው። የጣት ቀለበታቸውን አሣዩኝ። ይሔን ቀለበት ያሰረችልኝ ክበበፀሐይ ናት። እኔም አስሬላታለሁ። እሷ የኔን ሣታወልቀው ነው ያረፈችው። እኔም የእሷን አላወልቀውም። ማንም አያወልቀውም። እሷ ነች ያሰረችልኝ አሉኝ። ታዲያ ፍቅር እስከ መቃብር ለሚባለው ታሪክ ከሀዲስ ሕይወት ሌላ ምን አለ? ለትዳራቸው እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኝ የሆኑ ክስተት ናቸው።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጥቅምት 5/2012

የትናየት ፈሩ