የኮርፖሬሽኑ ተምሳሌታዊ የስፖርት ፖሊሲ ትግበራ

6

በ1990 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የስፖርት ፖሊሲ ሕዝቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ ስፖርት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባው ይደነግጋል። ህብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሠራበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሚሆንበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት ያስቀምጣል። ከመንግሥት ተቋማት እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል በየደረጃው ኅብረተሰቡ ለሚሳተፍባቸው መድረኮች ትኩረት በማድረግ ልሂቃን (ኤሊቶች) የሚፈጠሩበት ዕድል እንዳለም ፖሊስው ያመለክታል። በሌላ በኩል አምራች ዜጋ ለመፍጠር፣ የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚዳብርበት፣ ከዚያም ሲያልፍ ዜጎች ጤንነታቸውን ለመጠበቅና ለመዝናናት እንዲሁም አካላቸውን ለማጎልበትና አዕምሯዋቸውን ለማበልጸግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኖበታል።

የስፖርት ፖሊሲውን መሰረት በማድረግ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማስፋት ረገድ እየተሄደበት ያለው መንገድ አጥጋቢ አለመሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል። በመንግስትም ሆነ በህብረተሰቡ በኩል እንደሚነሳው «ሕዝቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ የስፖርት እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት»በሚል በፖሊሲ ደረጃ ቢቀመጥም ወደ ተግባር ከመለወጥ አንጻር ከፍተኛ ክፍተት መኖሩ ይታመናል። በተለይ በመንግስትና በግል ተቋማት ህብረተሰቡ በሚሰራበት ቦታ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ እድል በመፍጠር ረገድ የፍላጎትም ሆነ የግንዛቤ ክፍተቶች እንዳሉ በስፖርቱ አዋቂዎች በኩል ይነገራል።

በተቋማት የስፖርቱን ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን በመረዳት ስፖርታዊ ክንውኖችን የማዘጋጀት ባህሉ በእጅጉ አናሳ መሆኑም አብሮ ይነሳል። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኩል የስፖርቱን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመረዳት የስፖርት ፌስቲቫል የማዘጋጀት ልምድ ባለቤት የሆኑ ተቋማት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከእነዚህ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። የቤተሰብ ስፖርት ፌስቲቫሉ ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ ከመስከረም 26 ጀምሮ ለአስር ቀናት ያክል «የኋላውን እያደስን የወደፊቱን ለመገንባት እንተጋለን »በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል። የኮርፖሬሽኑ የቤተሰብ ስፖርት ፌስቲቫል በ2002 ዓ.ም እንደተጀመረ መረጃዎች ያመላከታሉ ። ኮርፖሬሽኑ በሚያከናውነው የስፖርት ፌስቲቫል፤ አገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲውን ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር በሰራተኞች መካከል መቀራረብን እንደሚፈጥር ታምኖበታል። የስፖርት ፌስቲቫሉ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን በማፍራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማሳያ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የቤተሰብ ስፖርት ፌስቲቫል አስተባባሪ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥንፉ ሙጬ፤ የስፖርት ፌስቲቫሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን የስፖርት ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ። ህዝቡ በሚኖርበትና በሚሰራበት አካባቢ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማጉላት እንደሚችል መሰረት ባደረገ መልኩ ተቋሙ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ። እንደ አቶ ጥንፍ ገለጻ፣ ስፖርት በተለይ ደግሞ በሰራተኞች መካከል እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን ለማፍራት እንዲቻል፣ የሰራተኞችን አንድነት ለማጠናከር ፋይዳው ግዙፍ መሆኑን ያብራራሉ። በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ የቤተሰብ ስፖርት ፌስቲቫሉን እነዚህን ውጤቶች መሰረት በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደጀመረ ይናገራሉ። «ፌስቲቫሉ በየሁለት ዓመቱ ቢደረግ የበለጠ ዝግጅት ተደርጎ በጠንካራና ባማረ ሁኔታ ማከናወን ይቻላል »በሚል አስተዳደሩ ወስኖ በየሁለት ዓመቱ ሊካሄድ እንደቻለም ያስታውሳሉ።

የኮርፖሬሽኑ የቤተሰብ ስፖርት በዚህ መልኩ በመቋቋም ባለፉት አስር ዓመታትን መጓዝ ችሏል። በስፖርት ክንውኑ ተቋሙ ውጤታማ መሆን ችሏል? ስንል ጥያቄ ሰንዝረናል። አቶ ጥንፍ ባለፉት አስር ዓመታት በነበረው ስፖርታዊ ክንዋኔ ተቋሙ ውጤታማ መሆኑን ይገልጻሉ። በመጀመሪያ ደረጃ አመራሩና ሰራተኛው መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲፈጥሩ አድርጓል። እያደረገም ይገኛል። በአካልም፣ በአዕምሮም የበለፀገ ሰራተኛና አመራር እንዲኖር አስችሏል። ጤናማ ሰራተኛ በመፍጠር ረገድ ውጤት ማምጣት ተችሏል። መታወቅ ያለበት ያለ ጤናማ ሰራተኛ የኮንስትራክሽን ስራ የሚታሰብ እንዳልሆነም ያብራራሉ።

የስፖርት ፌስቲቫሉ ሠራተኛውም ሆነ አመራሩን የበለጠ የሚያቀራርብ፣ ሠራተኛው ትርፍ ጊዜውን አዕምሮውንና አካላዊ ብቃቱን የሚያዳብርበት፣ ለተቋሙ ያለውን ወገናዊነት የሚያሳይበት፣ በሌሎች ፕሮጀክቶች ከሚገኙ ሠራተኞች ጋር ለመቀራረብና ለመተዋወቅ መንገድ እየከፈተ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። እንደ አቶ ጥንፍ ማብራሪያ፤ የዘንድሮ መድረክ ከእስከ ዛሬው ለየት የሚያደርገው የተሳታፊነቱን ኮታ ለአመራሩ አንድ ሶስተኛውን በመስጠት ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ሳይቀር ተሳታፊ ማድረጉ ነው። ስፖርት ፌስቲቫሉ ለአመራሩና ለሰራተኛው እኩል እድል ከመስጠት ባሻገር፤ በሁለቱ አካላት መካከል መቀራረብ እንዲፈጠርና የበለጠ ቀረቤታን መፍጠር እንዲያስችል ነው። ይህን በተግባርም ለመመልከት ተችሏል። የዘንድሮው ውድድር ሴቶችን የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጓል። በመድረኩ ያለፉት ዓመታት ጉዞ ሴቶች ቡድን አልነበራቸውም፤ ዘንድሮ ሁለት ቡድኖች ተቋቁመው በመረብ ኳስና በጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

«የዘንድሮው ፌስቲቫል ልዩ ገጽታው የለውጥ አስተሳሰቦችን ለማስረጽ ጥረት መደረጉ ነው። በውድድሩ ያሉትን ቡድኖች ስያሜን በዚህ ሁኔታ እንዲቃኙ የተደረገ ሲሆን ስያሜዎቹም አሸናፊ፣ ብቁ፣ ታዋቂ፣ ድንቅ፣ ባለራዕይ እና ተስፋ በሚል እንዲሰየሙ ተደርጓል›› ያሉት አስተባባሪው ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል ዘርፎች በቡድን ተደራጅተው እርስ በዕርስ የሚያደርጉት ውድድር እንደነበር ተናግረዋል። አደረጃጀቱ እንደ ኮርፖሬሽን ውህደት ባለማምጣቱ አዲስ አደረጃጀት በመፍጠር ወድድሩ እየተካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩ የበለጠ መቀራረብና ተቋማዊ ስሜት መፍጠር እንደተቻለ በውድድሩ የአምስትና ስድስት ቀናት ቆይታ ወቅት ለመታዘብ ተችሏል። የስፖርት ፌስቲቫሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቋማዊ ፋይዳውን እያሳደገ መምጣቱን የ5ኛው የቤተሰብ ስፖርት ውድድር እያሳየም ይገኛል። አቶ ጥንፍ ኮርፖሬሽኑ ግዙፍና በርካታ ፕሮጀክቶች ያቀፈ እንደመሆኑ በስፖርት ፌስቲቫሉ ሁሉም ፕሮጀክቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ በመስራት የስፖርቱን ግዙፍ ፋይዳ በተቋሙ ምሉእ እንዲሆን ለማድረግ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስቀምጠዋል።

በ5ኛው የኮርፖሬሽኑ የቤተሰብ ስፖርት ሲሳተፍ ያገኘናቸው በኮርፖሬሽኑ የፋሲሊቲ ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዜናው ደነቀው በበኩላቸው፤ የስፖርት ክንውኑን እንደ ኮርፖሬሽኑ ሁሉ ሌሎች ተቋማት ተግባራዊ ማድረግ ቢችሉ ያለውን ፋይዳ ይናገራሉ። «በእኛ ተቋም ያለውን ተሞክሮ በሌሎች የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ከስፖርቱ የሚገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም ኢሊት ስፖርተኞች የሚፈሩበትን አጋጣሚ በማስፋት ረገድ የራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል። የአገራችንን ስፖርት በማሳደግ ረገድም የመንግስት ተቋማት ድርሻቸውን እንዲወጡ አጋጣሚውን መፍጠር ይቻላል» ሲል ያብራራል።

በኮርፖሬሽኑ የቤተሰብ ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ከአሰልጣኝነት እስከ ዳኝነት የተሻገረ ተሳትፎን ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲያደርጉ እንደነበረ የገለፁልን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሰራተኛ የሆኑት አቶ አለማየሁ ገብሬ፤ የኮርፖሬሽኑ ተሞክሮን ሌሎች ተቋማት መውሰድ ቢችሉ ያለውን ነጥብ በማሳት ተመሳሳይ ሃሳብ ይጋራሉ። የቤተሰብ ስፖርቱን ከመጠንሰስ እና ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አካያ በተቋሙ የነበሩና ያሉ አመራሮች ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸውም ይናገራሉ። የኮርፖሬሽኑ አመራሮች የስፖርት ፌስቲቫሉ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ከማደርግ አኳያ ያሳዩት ቁርጠኝነት በተለይ ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ትልቅ ስራን መስራታቸውን ያስረዳሉ።

አቶ አለማየሁ ዋና ስራ አስፈፃሚው ስፖርታዊ ክንውኑ ቀጣይነት ኖሮት በጠንካራ መስመር እንዲጓዝ ከመስራት ባሻገር፤ በውድድሩ ተጫዋች በመሆን የስፖርቱ ተሳታፊ መሆናቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ይገለጻሉ። ስፖርቱ ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያም አመራሩ ያሳየው ቁርጠኝነት በሌሎች ተቋማት እንደ አርዓያ ሊወስዱት ይገባል ባይናቸው። ኮርፖሬሽኑም በየሁለት ዓመቱ ይህ የስፖርት ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባው ያስቀምጣሉ።

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የቤተሰብ ስፖርት ፌስቲቫል ተሞክሮ በሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት መውሰድ ቢቻል ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንደ አገር ማትረፍ እንደሚቻል መመስከር ይቻላል። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በህብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጠው ፖሊሲ ከመቅረጽ ባሻገር ተግባራዊ እንዲሆን እንደ ኮርፖሬሽኑ ሌሎች ተቋማት መስራት አለባቸው።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጥቅምት 5/2012

ዳንኤል ዘነበ