ኢትዮጵያዊያን ለ2 ዓመታት የምርጥ አትሌቶች ሽልማት አልታጩም

12

የጽናት ምልክቱና በ10ሺ ሜትር ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ኢትዮጵያን ወክሎ የዓለም ምርጡ አትሌት ሲሰኝ የመጀመሪያው ነው። በአቴንሱ የዓለም ቻምፒዮና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በፈረንሳይ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 3ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ አገሩን ባስጠራ ማግስት፣ የጎልደን ሊጉ አሸናፊም በሆነበት ዓመት እአአ 1998 የዓመቱ የዓለም ምርጥ አትሌት በሚል ለመሸለም በቃ። በኃይሌ እግር የተተካው ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ ይህንን ክብር በማግኘት ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ለመሰኘት ቻለ። የ5ሺ፣ 10ሺ እና የአገር አቋራጭ ንጉሱ በተከታታይ እአአ በ2004 እና 2005 በወንዶች የዓለም ምርጥ አትሌት በመሆንም ታሪካዊ አትሌትነቱን አስመስክሯል።

በወንዶች በኩል ከቀነኒሳ ቀጥሎ ይህንን ክብር ያገኘ ኢትዮጵያዊ አትሌት ባይኖርም በሴቶች በኩል ግን እስከ ቅርብ ዓመታት ለማሸነፍ የቻሉ አትሌቶች ታይተዋል። አትሌት መሰረት ደፋር እአአ በ2007 ይህንን ሽልማት ያሳካች አትሌት ናት። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ባይቆጠርም እአአ በ2015 ገንዘቤ ዲባባ ሁለተኛውን ክብር እንዲሁም በረጅም ርቀት የዓለም እና የኦሊምፒክ ቻምፒዮናዋ አልማዝ አያና በ2016 የዓመቱ ምርጥ አትሌት በመባል ለመሸለም በቅተዋል።

በዓለም ላይ በተለይ በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሚባሉ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያናት። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዕውቅና በተሰጣቸው ውድድሮች ላይ በግላቸው ከሚሳተፉት አትሌቶች ባሻገር በዳይመንድ ሊግ፣ ዓለም ቻምፒዮና አንዲሁም በኦሊምፒክ መድረክም ሜዳሊያ ያጠለቁ የዝነኛ አትሌቶች ምድርም ናት፤ ኢትዮጵያ። አሸንፎ ሜዳሊያውን ማጥለቅ ብቻም ሳይሆን ሰዓት በማሻሻልና የዓለም ክብረወሰንን በመስበር ጭምር በርካታ ስኬታማ አትሌቶችን ለዓለም አበርክታለች።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም ምርጥ አትሌቶች ሽልማት ማሸነፍ ባይችሉ እንኳን ከመጀመሪያዎቹ አስር እጩዎች በሁለቱም ፆታ መካተታቸው ብርቅ አልነበረም። ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ ግን በተከታታይ ከአስሩ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሙያዎች እንዲሁም ከሁሉም አህጉራት በተወጣጡ ተወካዮች በሁለቱም ጾታ በዓመቱ ጥሩ ብቃት ያሳዩ 20 አትሌቶች ቀርበዋል። ዕጩዎቹም በዳይመንድ ሊግ፣ በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና፣ በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም ማህበሩ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ በሩጫ፣ ዝላይ እና ውርወራ የተሻለ ብቃት ያሳዩ ሲሆኑ ከነዚህ መካከል ለተከታታይ ሁለት ዓመታት አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት ሳይካተት መቅረቱ አስገራሚ ሆኗል።

ዘንድሮ እጩ ሆነው ከቀረቡት አትሌቶች መካከል አሜሪካ በርካታ አትሌቶችን በማስመረጥ ቀዳሚዋ አገር ሆናለች። በዓመቱ ከተካፈለባቸው አምስት የ800 ሜትር ውድድሮች አራቱን ያሸነፈው ዶናቫን ብራዜር በእጩነት ከቀረቡት መካከል ይገኛል። አሜሪካዊው አትሌት በቻምፒዮናው ላይ በ800 ሜትር 1:42.34 የዓለም ክብረወሰን የሆነ ሰዓት ከማስመዝገቡም ባሻገር የዳይመንድ ሊጉ አሸናፊ ነው። በዓመቱ በ100 ሜትር ውድድር ተዕእኖ ፈጣሪ የነበረውና የዶሃ ርቀቱን 9 ሰከንድ ከ76 ማይክሮ የገባው ክርስቲያን ኮለመንም ሌላኛው እጩ ነው። የከፍታ ዝላይ አሸናፊው ሳም ኬንድሪክስ፣ የ200 ሜትር ሯጩ ናህ ላይለስ እንዲሁም የርዝመት ዘላዩ ክርስቲያን ቴይለር በእጩነት የቀረቡ አሜሪካዊያን አትሌቶች ናቸው።

ባለፈው ሳምንት ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት ታሪክ ያጻፈው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌም በእጩነቱ ተካቷል። አትሌቱ ዕውቅና የሌለውን የስፖርት ትጥቅ አምራቹን ኩባንያ ናይኪ ፕሮጀክት የሆነውን ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የማጠናቀቅ ህልም ከማሳካቱም ባለፈ በለንደን ማራቶን 2:02:37 በመግባት የራሱን ፈጣን ሰዓት በማሻሻል የዓለም ክብረወሰኑን አለማስነጠቁ የሚታወቅ ነው። የአገሩ ልጅ የሆነው ቲሞዚ ቺሩዪት ሌላኛው እጩ ሲሆን፤ በ1ሺ500ሜትር የዳይመንድ ሊግ እንዲሁም የዓለም ቻምፒዮን ነው።

በአውሩስ በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮን የሆነው ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊም ከእጩዎቹ ተካቷል። አትሌቱ በ10ሺ ሜትር ቀዳሚ የሆነውን 26:48.36 ሰዓት ሲያስመዘግብ በ500ሜትር የዳይመንድ ሊጉ ቻምፒዮን ነው። የ400ሜትር አትሌቱ ባህሬናዊ ስቲቭ ጋርድነር፣ በዲስከስ ውርወራ የዓለም ቻምፒዮኑ ስዊድናዊ ዳንኤል ስታል እንዲሁም ኖርዌያዊው ካርስቴን ዋርሆልም በምርጫው የተካተቱ ሌሎች እጩዎች ናቸው።

ለምርጫው የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ባለሙያዎች 50 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ የሚሰጡ ሲሆን 25 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ሌላው ህዝብ በድረገጾች ድምጹን የሚሰጥ ይሆናል። እጩዎቹን አሸናፊ ለማድረግም በየትኛውም የህዝብ መገናኛ እንዲሁም የማህበራዊ ገጾች ማስተዋወቅ የሚረዳቸው ሲሆን፤ ከወር በኋላ የመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች ይታወቃሉ። አሸናፊው እትሌትም በሞናኮ በሚኖረው ስነስርዓት ላይ ይፋ እንደሚደረግ ይታወቃል።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጥቅምት 5/2012

ብርሃን ፈይሳ