የ“እንቂት” የጋብቻ ልማዳዊ መሀላ

21

በጉራጌ ብሔረሰብ የ “እንቂት” “የጋብቻ ልማዳዊ መሀላ” መሰረት ለጋብቻ የተጫጩ ጥንዶች በመጨረሻው የስምምነት ቀጠሮ ዕለት መተጫጨቱ የሚጸና ቢሆንም ለጋብቻው ከመተጫጨት በተጨማሪ የቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓት ይኖረዋል። ይህም በስልጤ “ችግ” ሲባል በተቀሩት ቤተ ጉራጌዎች “ቸግ” በመባል ይታወቃል። በአማርኛው በተለምዶ “የቀለበት ሥነ ሥርዓት” እንደሚባለው ማለት ነው።

ደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ “ቃል ኪዳን የማይቀር፣ የማይታበል፣ እንደ መሀላ ያለ የውል ቃል ነው” በማለት ያሰፈሩ ሲሆን “ቀለበት ከብር ፣ከወርቅና ከነሐስ የተሰራ የጣት የአንገት ክብ ጌጥ በሚል መልኩ ይተረጉሙታል።

የሁለት ቃሎች ትርጉም መሠረት በማድረግ የጉራጌ ብሔረሰብ የ “ችግ” ወይም የ “ቸግ” ሥነ ሥርዓትም ቃል ኪዳን የሚይዘው ትርጉም የያዘ መሆኑን የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ እና በዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት አቶ መንግሥቱ ኃይለማርያም ይናገራሉ።

ይህ “የችግ” “ቸግ” ሥርዓት አፈጻጸሙ የሚመራው ቀደም ሲል በተሰየመው የቃልኪዳን ዳኛ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መንግስቱ በብሔረሰቡ አጠራር የ“ችግ” “ቸግ” ወይም የቃል ኪዳን ስርዓት በምግብ እና በመጠጥ ግብዣም ይደገፋል። በስልጤ ትንሽ ይለያል፤ የሙሽራው ጓደኞች በቦታው ተገኝተው ከመጨፈር በስተቀር ምንም ዓይነት ግብዣ አይኖረውም።

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በመስቃን ቤተ ጉራጌ የቃል ኪዳኑን ሥርዓት አፈጻጸም ለመጀመር በዕለተ ቀጠሮው የጥሎሽ ግማሽ ወይም አንድ ሶስተኛው ከወንድ ወገን ካልቀረበ ሥርዓተ አፈጻጸሙ አይካሄድም። እንዲሁም በሶዶ ሙሉ ጥሎሽና ለልጅቷ ልብስ እና ጌጥ በዚሁ ዕለት ተሟልተው ካልቀረቡ ሥርዓቱ አይጀመርም።

በሶዶ ቤተ ጉራጌ ያለው አቀባበል ለየት የሚለው በቃል ኪዳን ቀጠሮ ዕለት የወንዱ የ (ሙሽራው) ወገኖች መጥተው የልጅቷ ቤተሰብ ቤት ሲደርሱ የልጅቷ ቤተሰቦች በቸልተኝነት ወይም በኩራት ከተቀመጡበት ቦታ ምንም ንቅንቅ ሳይሉ እንግዶችን ቁጭ በሉ በማለት ይቀበሏቸዋል።

መቀመጫ ፈልገው የሚቀመጡት እንግዶቹ ናቸው። ይህም ልጅቷን በልመና ያገኟት መሆናቸውን ለማስገንዘብ ነው። ከተወሰነ ቆይታ እና ጭውውት በኋላ የወንዱ ወገን ያመጣውን ለሙሽሪት የሚሆነውን አልባሳት ከልጅቱ ወገን ለተመረጡ ሽማግሌዎች አንድ በአንድ ቆጥረው ያስረክባሉ። ተረካቢው ደግሞ እያንዳንዱን ለእድምተኛው እያሳየ ይረከባል።

ከርክክቡ ሥነ ሥርዓት በመቀጠል የእጩ ሙሽሪት እናት ያልተነጠረ ቅቤ ከቄጠማ ጋር በሳህን ይዛ በመምጣት ለወንድ ልጅ (ለእጩ ሙሽራው አባት) ትሰጠዋለች። አባትየውም ቅቤውን በቄጤማው እየነካካ መርቆ ወደ ሌሎች ሽማግሌዎች ለምርቃት እንድታስተላልፍ ለእናቲቱ መልሶ ይሰጣታል።

በምርቃቱ መጨረሻ የተመረቀበትን ቄጠማ እና ያልተነጠረውን ቅቤ ለሙሽራው አባት መልሳ ትሰጠዋለች። እንዲህ … እንዲህ … እያለ የጥሎሽ ስርዓት ይካሄዳል። በተቀሩት ቤተ ጉራጌዎች ጥሎሽና አልባሳት ከቃልኪዳን ማሰሪያው በፊት ወይም በኋላ አሊያም በእለቱ ሊሆን እንደሚችል አቶ መንግሥቱ ይናገራሉ።

ጥሎሹ በወንድ ሙሽራው ቤተሰብ አቅም ላይ ተመስርቶ ሊፈጥንም ሊዘገይም እንደሚችል የሚናገሩት አቶ መንግስቱ የሙሽሪቱን የጥሎሽ ልብስ እያቆራረጡ አንድም ሁለትም ጊዜ አድርገው ሊሰጡ ይችላሉ። ይህም ከሰርጉ ጊዜ ማጠርና መርዘም ጋር የተያያዘ ነው።

እንደ አቶ መንግሥቱ ገለጻ በቃል ኪዳን ማሰሪያው ላይም በጉራጌ ባህል መሰረት ከወንዱ ወገን ከተሰየሙ ሽማግሌዎች አንደኛው የልጁንና የቤተሰቡን ባህሪይ እንዲሁም ማህበራዊ አኗኗር በቃልኪዳን ዳኛው ጥያቄ መሰረት ያብራራል። የልጅቷ አባትም በመቀጠል ለልጄ ለአይኗ ለጥርሷና ለመላ አካሏ ተጠያቂና አጠቃላይ ችግር በሚገጥማት ወቅት በቅርብ ሆኖ የሚከታተላት ዋስ ይሰጠኝ ይላል። የወንድ አባትም “እገሌን ሰጥቻለው” ይላል። የወንድ አባትም በተራው “ልጅቷ የጉራጌን ደንብ እና ስርዓት ጠብቃ ትዳሯን አክብራ እንድትኖር መካሪና ተጠያቂ የሚሆን ዋስ ይሰጠኝ” በማለት የልጅቱን አባት ይጠይቃል። የሙሽሪትም አባት “እግሌን ስጥቻለው” ይላል። ሁለቱም ተጠሪዎች ተራ በተራ በመነሳት በየበኩላቸው የየቤተሰቡ ማለትም የሙሽራውንና የሙሽሪትን መልካም ባህሪይ በመግለጽ በቃል ኪዳን ዳኛው አማካይነት ተጠሪነታቸውን ያረጋግጣሉ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የልጅቱ አባት “ልጄ እገሊት እገሌ ለተባለው ለአቶ እገሌ ልጅ ለጋብቻ ሰጥቻለሁ” ሲል የቃል ኪዳን ዳኛውም ሶስት ጊዜ “ሰጥተሃል” በማለት ሲጠይቀው አባትየውም ሶስት ጊዜ “ሰጥቻለሁ ቃል ቃል በማለት ያረጋግጣል።

እንዲህ ዓይነቱ የቃል ኪዳን ሥነሥርዓት ከዚህ ቀደም በመስቃን ቤተ ጉራጌ የሴቷ አባት ልጁን መስጠቱን ሲያረጋግጥ የወንድ ልጅ አባት ማረጋገጫ እና ማሰሪያ እንዲሆነው የሽማግሌዎችን ጆሮ እየዞረ በመቆንጠጥ እና የወንድ ወገን መሪ ደግሞ ትከሻ በመሳም የቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓት አፈጻጸሙ ይከወን እንደነበር አቶ መንግስቱ ኃይለማርያም ይናገራሉ።

ሌላኛው ይላሉ አቶ መንግስቱ በሶዶ ቤተ ጉራጌ የሙሽራው አባት ለልጃቸው ሚስት የምትሆነው ልጃገረድ ቤተሰቦቿ የሰጡት እንደሆነ ማረጋገጫ ይሆነው ዘንድ የልጅቷ አባትና የቃል ኪዳን ዳኛውን ጆሮ ተራ በተራ በሁለቱም እጆቹ በመያዝ “ሰጠኸኛል” “ሰምተሃል” እያለ በሚያረጋግጥበት ሁኔታ ነበር ።

የጉራጌ ብሔረሰብ የእስልምና እምነት ተከታዮች ይህንን የቃል ኪዳን ትስስር የሚፈጽሙት በ “ኒካ” ደምብ መሰረት ነው። አፈጻጸሙም የእስልምና ደንብ እና አስተምሮ በሚያዘው መሰረት ነው። ሙሽሮች “ኒካ” በሚያስሩበት ጊዜ የወንድ ሙሽራ አባት የልጁን ስምምነት ጠይቆ በማረጋገጥ ልጅን ወክሎ “ኒካ” ያስራል። ሴቷ ግን አባቷ ቤት ውስጥ በመሆን ስርዓት የሚፈጽሙ ቃዲዎችና አዛውንቶች በተገኙበት መስማማቷን በአባቷ አማካይነት ትገልጻለች። በስምምነቱ መሰረት የሁለቱም ሙሽሮቹ አባቶች “ኒካ”ውን በሽሪአ ሕግ መሰረት ይፈጽማሉ። በሽሪአ ሕግ መሰረት አባቶቻቸው መፈጸም ካልቻሉ በሁለቱም የጋራ ስምምነት በቃዲዎች እንዲፈጸም ይደረጋል። ቃዲዎችም “የእገሌን ልጅ ከእገሌ ልጅ ጋር አጋብተናል። ” በማለት በሸሪአ ሕግ መሰረት “ኒካ”ውን ያስራሉ።

በማንኛውም ሁኔታ የቃል ኪዳን ትስስሩ ከተፈጸመ በኋላ እጮኛሞቹ ቅርርብ እና ትውውቅ ባይኖራቸው እንኳን “እሷ የእሱ ፤እሱም የእሷ በመሆናቸው በሽማግሌዎች ስለጸና ምንም እንኳ ሰርጋቸው ባይደርስም ማንም የትኛው ወገን ቃል ኪዳኑን ማፈረስ አይችልም። እንዲያውም በቤተ ጉራጌ ባህል መሰረት የሴት ልጅ ቤተሰብ በቀጣይ ቀጠሮ ልጄን ለእገሌ እሰጣለሁ ብሎ በልቦናው ከወሰነ በኋላ ሀሳቡን አይለውጥም። ምክንያቱም በልቦናው ቃል በመግባቱ ልጅቱ ላይ “እንቂት” ስለሚኖር ህይወቷ ይሰናከላል የሚል እምነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለሚኖር ነው ።

በእያንዳንዱ ዞኖች እንዲሁም ክልሎች እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ በባህላዊ ዕውቀት የደረጀ ድንቅ የመቻቻል፣የሰላም እና የፍቅር እሴቶች አሉት፤የመጣብንንና የሚመጣብንን ሰይጣናዊ የጥፋት ውሃ ለመከላከል ለመግታት የሚረዱ። ስለዚህም ልክ እንደ ቤተ ጉራጌ የሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ድንቅ ባህላዊ ዕውቀት ከአገር አልፎ ለዓለም ምሳሌ እንዲሆን ማበልጸግ እና ለአገራዊ መግባባት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ የፍቅር የመቻቻል አገርና ምድርነቷ ይቀጥላል። ሰላም!!

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012

አብርሃም ተወልደ