“የቡና እንጠጣ” ወሬዎች

8

እርስ በእርስ መዋደዳችን የሚገለጸው በብዙ መንገድ ነው። በመረዳዳት፣ መልካም ተግባር በመፈጸም፣ በመተሳሰባችን፣ በጥሩ ሰላምታ አሰጣጣችን ጭምር ነው። ጥሩ የሚባል ሰላምታ ከአንገት ጎንበስ ብሎ (ዝቅ ብሎ ከወገብ)፣ በአክብሮት ደግሞ ሞቅ አድርጎ በፈገግታ ፤ ብቻ የሰላምታ አይነቱ ብዙ ነው። ሀይ! ብሎ እጁን ከፍ አድርጎ የሚያልፈው፣ የአይኑን ቅንድብ፤ የግንባሩን ሸንተረር ከፍ ዝቅ አድርጎ ሰላምታ ሰጠሁ የሚለው፣ ሰላምታ ይሉት አይሉት የማይታወቅ ድምጽ አሰምቶ የሚሄደው ብቻ ሰላምታ ከተባሉ ያው ሰላም ተባብሏል ለማለት ያክል የሚባሉ አሉ። ከእንደዚህ አይነት ብባልስ ባልባልስ ከሚያስብሉ ሰላምታዎች ግን የቀረ ይሻላል። ምክንያቱም ሰላምታ ማለት በራሱ ሰላምን መፈለግ አይደል? ሰላም የምንለውን ሰው ስለ ሰላሙ ፣ ጤንነቱ፣ አዋዋሉ፣ አመሻሹ፣ አስተዳደሩ አስበን፣ ተጨንቀን፣ ለመጠየቅ ይመስለኛል። እንዲያ ያለው ሰላምታ ታዲያ ለምን በቅሬታ የታጀበ ይሆናል?።

ኧረ እንዲያውም ሰላምታ የእግዜር ምሳ እና እራቱ ነው ይባል የለ። አያቴ እንዲህ እያለች ነው ያስተማረችኝ። አሁን አሁንስ ካላችሁ መቼም ሰላምታ ድሮ ቀረ አይባልም። ምክንያቱም የቀረውን ማንነታችንን ፣ ባህል ወጋችንን እንመልስ ብለን እየሰራን ይመስለኛልና። ሁሉም ነገር የሚያምረው በራስ ባህልና ወግ ነው። እርቁ ፣ሰርጉ፣ ለቅሶው፣ ይቅርታና ሽምግልናው ሰሚም ተሰሚም ያለው እንደየባህሉ ነው። ይሄን ማለት ግን ዘመንኛው አይንካን ለማለት አይደለም። ማን እንደባህላችን ብዬ እንጂ። እውነት እኮ ነው ብዙ ቂም በቀሎች የሚሽሩት በዘመናዊ የዳኝነት ስርዓት አይደለም። በባህሉ መሰረት ነው። ያጠፋ ይቀጣል፤ የተበደለ ይካሳል፤ በዳይ ይክሳል። ያኔ ቂም ይቆማል። በቀል ይሽራል። እንዳው የጠፋውም ጠፍቶ፤ የወደመውም ወድሞ ያ ማህበረሰብ አብሮ ይበላል። አብሮ ይጠጣል። ከዛም አልፎ ይጋባል፤ ይዋለዳል። በክርስትና ልጅ ፣ በጡት እናት በመሳሰሉት ብቻ ላይፈታ ይጋመዳል። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን መልካም ነገር አለ።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው የሰላምታን ነገር ሳስታውስ ትዝ ያለኝን ላንሳ። የአሁኑን አላውቅም እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜ የሀይማኖት አባት፣ አረጋውያን፣ የጎሳ መሪዎች፣ በእድሜ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችን ዝቅ ብሎ ከጉልበት በታች በመሳም ማክበር ነበር። አሁን አሁን ግን ቀርቶም ይሆን እንጃ ብዙም አላጋጠመኝም? እንጃ ብቻ ሰላምታ የሚያሳየው መካበበርንና መዋደድን ነው እንጂ የበታችነትን አይደለም። ጉልበታቸውን የተሳሙም አንድም ሳሚውን ቀና አድርገው አይገባም ይላሉ። አክለው ደግሞ ምርቃታቸውን ያጠግቡታል። በብዙ ቦታዎች ላይ ምርቃት ትልቅ ቦታ አለው፤ ይደርስልናል ተብሎም ይታሰባል። ስለዚህ ምርቃት በሚኖርበት ቦታ የመራቂውን ጉልበት ቀድሞ ለመሳም ብዙ ሰዎች በተለይ ወጣቶች የሚጠባበቁት በመራቂው በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ነው። ልክ ምርቃቱ ሲያበቃ ጉልበት ላይ ተጣብቀው ለመሳም። ይሄ ባህል በተለይ በጉራጌ ብሄረሰብ ዘንድ የተለመደ ነው። አሁንም እንዳለ አለ። የአንድ ነገር መነሻም ሆነ መድረሻው በምረቃት ይሆናል። በልተው፣ ጠጥተው ምርቃት ሰጥተውም ሆነ ተቀብለው ያንን ፕሮግራም የሚያጠናቅቁት በምረቃ ነው። ኬ…ር..ኬር…ኬር ይሁን ብለው።

ሰዎች ይህችን ዓለም ተሰናብተው ሲሄዱ ብዙ ጊዜ በመጥፎም በጥሩም ስማቸው ይነሳል። ከአልቃሾቻቸው የሚሰማ አባባልም አለ። እንዴት አይነት ጥሩ ሰላምተኛዬ ነበረች። ለቅሶውም የእኔ ሰላምተኛ… የእኔ ሰላምተኛ … የሚል ይሆናል። ይሄ ማለት ሰዎች ከሚደረግላችው ነገር ማለቴ በአይነት ከሚሰጠው ነገር በላይ ከፍትፍቱ ፊቱ የሚባሉበት ይበልጣል። ሌላው ነገር ትርፍ ነው የሰው ልጅ በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ የሚያስፈልገው ፈገግ ያለ ፊት፤ ጥሩ ንግግር ፤ መልካም መስተንግዶ ነው። ይሄ ሲሟላ ታዲያ ሌላው ተከታይ ጉዳይ ይሆናል።

መቼም ሰዎች ሲገናኙ መጀመሪያ የሚባባሉት እስኪ ቡና እንጣጣ ነው። ቡና ባህላችን፣ መታወቂያችን፣ መሰባሰቢያችንና የጨዋታ አጀንዳ ማመንጫ መድረካችን ነው። በቡና ላይ የሚነሱ የጨዋታ ዓይነቶች እንደተገናኙት ሰዎች ይወሰናል። ስለቤት ሰራተኛ፣ ስለ ልጅ፣ ስለ ትዳር የሚያወሩት በዚህ ረድፍ ላይ ጨዋታቸውን ያጠነጥናሉ። ስለ ሴትና ስለ ወንድ ጓደኛ ኧረ ከዛም አለፍ ብሎ የሀገራችንን ፖለቲካ የምናነሳ የምንጥልበት ነጻ መድረክም ነው። አቤት …አቤት … በዚህ መድረክ ላይ መገኘት ብዙ ብዙ የተባሉ ያልተባሉም ይነሳሉ ይወድቃሉ። የአዋቂዎች ጎራ ከሆነ ደግሞ እውቀትም ይሰበሰባል የእውቀት ማዕድ ይሆናል።

እውነት አንዳንድ ንግግር የውስጥን ይነካል፤ የውስጥን የሚነካ ንግግር ደግሞ መቼም ቢሆን ከውስጥ አይወጣም። በየምክንያቱ ይሄንኑ ሀሳብ ምሳሌ ማድረግ ይኖራል። ብዙ የሚጠቀሱ ንግግሮችን ከፖለቲካ ልሂቃን፣ ከሀይማኖት አባቶች ኧረ አልተማሩም ከሚባሉም ይደመጣል። ተናግረው የማይጠገቡ ሰዎችን እናውቃለን። ቢያወሩ ቢያወሩ አይሰለቹም፤ ከአፋቸው ሁሉ የሚወጣው ለጥቅስ የሚበቃ አይነት ነው። አሁን አሁን ደግሞ ለፌስቡከ የሚበቃ የዓመቱ ምርጥ አይነት አባባሎች የሚባሉም ዓይነት አሉ። እንዳው ነገርን ነገር ያነሳዋል ብዬ አነሳሁት ወሬው የቡና ቁርስ ነው።

በቡና ጠጡ መድረክ ያደመጥኩት ነው። ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ የሚባሉ ሰዎች ናቸው ጀርባቸውን ሰጥተውኝ ይጨዋወታሉ። አንዱ ሀገሩን ፣ መሪውን፣ኑሮንና ዘመኑን ያማርራል፣ በቃ… ያማርራል …ያማርራል። ይሄን የታዘቡት ሌላው በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰው ታዲያ ከማድመጥ ወደ ሀሳብ መስጠት ተቀላቀሉና “ልጄ “ አሉ። እኔም የትልቅን ሰው ምክር፣ ተግሳጽ ፣ሀሳብ መስማት ድሮም እወዳለሁ ጆሮዬን ሰጥቼ ማድመጡን ቀጠልኩ። አቀማመጣችን ጀርባ ሰጥቶም ቢሆን ጆሯችንን ማን ከልክሎን ።

አሁን ይሄንን ሁሉ እያነሳህ የምታፈርጠውን ወሬ ከየት አገኘህ? ጠየቁ። እሱም መልስ ሰጠ። “ ከማህበራዊ ድረ ገጽ ፣ ከአንዳንድ መገናኛ ብዙሀን፣ ከሰዎች ወሬ፣ አውቃለሁ ከሚሉ ፖለቲከኞች፣ ተንታኝ ነኝ ከሚል…” የእሱ ባይሰማኝም ከዚህ ግን አያልፍም። ይሄ የኔ ግምት ነው። ምክንያቱም እሱ ውሳኔ ሰጪ ቦታ ላይ አይደለማ። እሱ ባለስልጣን ወይም ደግሞ እዛ አካባቢ አይደለማ። ስለዚህ ከተለያየ ቦታ የሰማውን፣ በአይኑም ያየውን፣ እሱም እየኖረበት ያለውን ደምሮ መሆኑ ሀቅ ነው። እና ይሄ የምትለውን ችግር እንዲወገድ አንተ ምን ሰራህ? ነው ቀጣዩ ጥያቄ “ ማን አድርሶን” ጠየቁ “ማን ከልክሎህ?” መልስ ግን አልነበረም። አሁን አሁን የምንሰማቸው የምናያቸው ነገሮች ከበሬ ወለደ የዘለሉ አይደሉም። ማስረጃና መረጃ የላቸውም። ብቻ ሰው ተረጋግቶ ኑሮውን እንዳይኖርና ህይወቱን እንዳይመራ ወከባ መፍጠር አስጨናቂ ወሬ መንዛት…ልማድ ሆኗል። ማለቴ የወሬ ጀግና በዝቷል። የቡና እንጠጣ ወሬዎች ህዝብን እያሳሳቱ መሆናቸውን ግን እኛም ቡና እየጠጣን የቡና ላይ ቁርስ አናድርገው። ምክንያቱም እውነታ አይደለምና!

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012

አልማዝ አያሌው