የህወሃት መግለጫና የኔ ትዝብት!

17

ትህነግ ለሰባት ቀናት አካሄድሁት ያለውን የማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ አጠናቆ ጥቅምት 4 ፣ 2012 ዓ ም ባወጣው መግለጫ እንደተለመደው ዛሬም ፦

1ኛ . የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ከፍታውና ልዕልናው አውርዶ ከራሱ ጋር አንድ ሊያደርገው ሞክሯል። በሰው ልጅ ታሪክ ሕዝብና ገዥ መደብ መቼም አንድ ሆኖ አያውቅም። ናዚም ሆነ ፋሽዝም ከጀርመንም ከጣሊያን ሕዝቦች ጋር አንድ ሆነው አያውቁም። በስማቸው ቢፈልጥ ቢቆርጥ ቢዘርፍም ሕዝቦችን አይወክልም። ህወሃትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ሆነው አያውቁም። የትግራይ ሕዝብ ከህወሃት በፊት ለእሺህ ዓመታት ኢትዮጵያን ዋልታና ማገር ሆኖ ያቆመ ፣ የጠበቀ ከፓርቲ ፣ ከአይዶሎጂ በላይ ሉዓላዊ ሆኖ የኖረ ዛሬም ሆነ ነገ ህወሃት ኖረም አልኖረ ከኢትዮጵያውያን እህትና ወንድሞቹ ጋር በአንድነት በክብር የሚኖር የተከበረ ሕዝብ ነው።

2ኛ . የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንቅረው የተፉት ፤ ከትክሻቸው ያሽቀነጠሩት ግፈኛውን አምባገነኑን የትህነግ ገዥ ቡድን መሆኑን ራሱ ህወሃት ልቡ እያወቀ የትግራይ ሕዝብ ህልውና ለአደጋ ለጥቃት እንደተጋለጠ ፤ እንደተገፋ አድርጎ የሚነዛውን ፕሮፓጋንዳ በዚሁ መግለጫውም እንደ በቀቀን ደግሞታል። ሆኖም የትግራይ ሕዝብ በዚህ ባዶ ፕሮፓጋንዳ የሚታለልም ሆነ የሚሞኝ አይደለም።

3ኛ . ስህተት በሆነ ስሜታዊና ኢተጠየቃዊ ትንተና አንድን ሕዝብ እና ሃይማኖት በማኒፌስቶው በጠላትነት ፈርጆ ግፍ ሲቀፈቅፍ የኖረ ድርጅት ዛሬ ስለአማራ ሕዝብ ትንፍሽ የማለት የቅስም ልዕልና የሌለው ቢሆንም ለስውር ደባው ያመቸው ዘንድ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት ከንቱ ሙከራ አድርጓል። ላለፉት 27 ዓመታት አጋር ፓርቲ በሚል በሀገራቸው ሁለተኛ ዜጋ ፣ ባይተዋር በማድረግ የበይ ተመልካች አድርጓቸው ኑሮ ዛሬ ደግሞ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት በዚህ መግለጫው ተውኗል። ሆኖም ውህደቱን ከማንም በፊት ቀድመው በመደገፍ አበክረው እዛው በፀበልህ ብለውታል።

4ኛ . በግንባር እስከ መቼ ! ? ግንባር ታክቲካዊ፣ ጊዜአዊ የጋራ አላማን ለማሳካት ማለትም ፖለቲካዊ ሕብረትን እውን ለማድረግ የሚቀየስ ጊዜአዊ ስልት እንደሆነ ቢታወቅም ህወሃት ግን ስልጣን ላይ የሚያቆየው ብቸኛ ስትራቴጂ ስለነበር በዓለማችን የፖለቲካ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ከ30 ዓመታት በላይ የሙጥኝ ብሎት መኖሩ ሳያንስ ይህን ግትር አቋሙን ወደ መቃብር ይዞት ለመውረድ መወሰኑን በዚሁ ወለፈንዲ መግለጫው አረጋግጦልናል።

5ኛ . ውህደቱን ለምን አምርሮ ጠላው …!? እስከ ለውጡ ዋዜማ ድረስ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በህወሃት ፈላጭ ቆራጭነት እና በሞግዚት የሚመሩ ከመሆናቸው ባሻገር 5 ሚሊዮን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው ህወሃት ከእሱ ከ5 እስከ 8 እጥፍ ሕዝብ ከሚወክሉ አባል ድርጅቶች ጋር በግንባሩ እኩል የውክልና ድምፅ ነበረው። ከዚህ በላይ ህወሃት በግንባሩ ውስጥ ፍፁም የበላይነት እንደነበረው ፀሐይ የሞቀው ጥሬ ሀቅ ነው። ከሀገሪቱ ግማሽና ከዚያ በላይ የሚሆነውን መልክዓ ምድር የሚወክሉ አምስት ክልሎችን ገዥ ፓርቲዎች በአምሳሉ ጠፍጥፎ ከመስራቱ ባሻገር በእሱ ቀጥታ የዕዝ ሰንሰለት ወይም ጥርነፋ ስር በማድረግ ለጥ ቀጥ አድርጎ መግዛቱ ሳያንስ ለእሱ ፍፁማዊ አምባገነንነት እንዲመቸው በአጋርነት ስም 2ኛ ዜጋ አድርጓቸው ኖሯል። እነዚህ አጋር ፓርቲዎች በሀገሪቱም ሆነ በሞግዚትነት በሚያስተዳድሮአቸው ክልሎች መፃኢ እድል የመምከርና የመውሰን መብት አልነበራቸውም። ውህደቱ እውን ሲሆን ህወሃት የበላይነቱን፣ ያልተገባና ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነቱን ስለሚያሳጣው አበክሮ የማጠልሸት ዘመቻውን ተያይዞታል። ይሁንና በከንቱ ይፍጨረጨራል እንጂ ውህደቱንም ሆነ የለውጡን ሒደት ለቅፅበት እንኳ ሊያዘገየው አይችልም። አንድ ጊዜ የኢህአዴግ መስመር ተጣሰ ሌላ ጊዜ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል አደረጃጀት ሲያሻው ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል እያለ ውዥንብር የሚነዛው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተግባር ያጣውን ያልተገባ የበላይነትና ተጠቃሚነት በአሰራርና በአደረጃጀት ለመቋጨት የሚደረገውን ጥረት ለማጨናገፍ ነው።

6ኛ . ህወሃት እንደ ቀደሙት መግለጫዎች ይሄኛውም በነጭ ውሸት fake news ፣ በተዛባ መረጃን dis information ፣ በአሳሳች መረጃ misinformation የታጨቀ ነው። ስለ ውህደቱ፣ ከማይገባው ስልጣኑ ስለመገለሉ በእሱ እና በትግራይ ሕዝብ ያለውን ልዩነት ፣ ወዘተ . በፈጠራ ትንታኔ ሆን ብሎ በማዛባት ብዥታ ፣ መደናገር ለመፍጠር ሞክሯል። ሆኖም አበው እመው ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀል እንዳሉት የእሱ ውሸትም እያደር እየተጋለጠ እየተገለበ ነው።

7ኛ . የማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በሰው ልጆች ታሪክ እንደ ህወሃት ቡድን ከነባራዊ ሁኔታ የተነጠለ እና በራሱ የቅዠት ዓለም ባለበት የሚረግጥ ቁሞ ቀር ድርጅት እንደሌለ ያረጋግጣል። ለዚህ ትልቁ ማሳያ ላለፉት 27 ዓመታት የከሸፈው ፣ የጨነገፈው አይዶሎጂ ዛሬም እንዲቀጥል ሽንጡን ገትሮ እየተከራከረ መሆኑ ነው። በእርግጥ አብዮታዊ መስመሩ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ስም የበላይነቱን አስጠብቆለት የኖረ አስማቱ ፣ ድግምቱ ነው። ዛሬ ጊዜው ተቀይሯል። ሀገርን በመተት አፍዝዞ አደንዝዞ መምራት ረክሷል ። ችግሩ ድግምቱን መተቱን እንደገና እንዳያሳድሰው ባለዛሮቹ ሌኒንም ስታሊንም ላይመለሱ ተሸኝተዋል።

እንደ መውጫ

ዛሬም በ2012 ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል ከሚል የእነ ጆሴፍ ጎብልስ ያረጀ ያፈጀ አባዜ ያልተፋታው ህወሃት እሱ ከማይገባው የስልጣን መንበር ዝቅ ስላለ የትግራይ ህዝብ ህልውና ፣ ደህንነትና ዋስትና ላይ አደጋ እንደተደቀነበት ከማራገብ አልፎ አፋኝ አገዛዙን ለመመለስ የሚያደርገውን መፈራገጥ የትግራይን ሕዝብ ህልውና የመመከት ትግል አድርጎ ጭምብል ለማጥለቅ ያልተሳካ ሙከራ አድርጓል። ከፍ ብዬ ለማብራራት እንደሞከርሁት የገዥ መደብና ሕዝብ የተለያዩ ቢሆኑም በዚህም ሆነ በቀደሙት መግለጫዎች የትግራይ ሕዝብንና ህወሃት አንድ አድርጎ ለማሳየት ብዙ ማስኗል። እንኳን ቤተሰባዊውና አውራጃዊው ህወሃት እኛ አሜሪካውያን በሚል ሕገ መንግሥት ቡራኬ በሀሳብ ልዕልና የተመሰረቱት ሪፐብሊካንም ሆነ ዴሞክራትና ሕዝብ አንድ ተደርገው ተወስደው አያውቅም ።

ይህ ቡድን የትግራይን ሕዝብ በፍርሀት፣ በሽብርና በአፈሙዝ አግቶ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ እየተጠቀመ ለውጡንም ሆነ ውህደቱን ለመቀልበስ ሀገርን ወደለየለት ቀውስ ለመዝፈቅ ከየትኛው የሀገራችን ታሪካዊ ጠላት ጋር ከመሰለፍ ጀምሮ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ የለውጥ ኃይሉም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገንዝቦ በንቃት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የተከበረው የትግራይ ሕዝብ እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ የነፃነትና የተስፋ አየር እንዲተነፍስ የበለጠ ተቀናጅቶ መስራት ይጠበቅበታል። የትግራይን ሕዝብ ያላሳተፈ ለውጥም ሆነ ውህደት ምሉዕ ሊሆን ስለማይችል አበክሮ መስራት ይጠይቃል። ዛሬ በሀገራችን የባ’ተው ለውጥም ሆነ የኢህአዴግ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ሂደት ለትግራይ ሕዝብ የስጋት ምንጭ ሳይሆን በረከትና ሲሳይ ይዞ የሚመጣ ነፃነቱን መብቱን ሳይሸራርፍ የሚያረጋግጥለት ዋስትና ከእህት ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር ቃል ኪዳኑን የሚያድስበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን በማያሻመ መንገድ ማረጋገጥ ይገባል። አይደለም የህወሃት ቡድን ምንም ኃይል የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ልዕልና ማውረድ አይችልም። የትግራይ ሕዝብ ይሄን ልዕልናውን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ደግሞ ከጎኑ ሆኖ የማገዝ ጉዳይ የመላው ኢትዮጵያዊ እና የለውጥ ኃይሉ ኃላፊነት ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012

በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )