ለሚ ብርሃኑ የቶሮንቶ ማራቶን ክብረወሰን ለመስበር ተዘጋጅቷል

16

የቶሮንቶ ማራቶን ዛሬ ሲካሄድ ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሚ ብርሃኑ የቦታውን ክብረወሰን ለማሻሻል ይሮጣል፡፡ በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች ሁሉ ፈጣን ሰዓት ያለው የሃያ አምስት ዓመቱ ለሚ በኬንያዊው አትሌት ፊልሞን ሮኖ የተያዘውን የውድድሩን ክብረወሰን የሆነ 2፡06፡52 ሰዓት ለማሻሻል መዘጋጀቱን አይ ደብል ኤፍ በድህረ ገፁ አስነብቧል፡፡ በውድድሩ የክብረወሰኑ ባለቤት ሮኖ እንዲሁም ያለፈው ዓመት አሸናፊ ቤንሶን ኪፕሩቶ የሚሳተፍ ሲሆን ቀዳሚ ሆኖ የሚያጠናቅቀው አትሌት ሰላሳ ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል፡፡ ሁለቱ ኬንያውያንና ኢትዮጵያው አትሌት ከሰላሳ ሺ ዶላሩ በተጨማሪ ከተሳካላቸው የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል አርባ ሺ ዶላር ጉርሻ ለማግኘት ይፋለማሉ፡፡ ለሚ በዛሬው የቶሮንቶ ማራቶን ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበራ ኩማ ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥመው ይጠበቃል፤ አበራ በማራቶን 2፡05፡50 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ጠንካራ አትሌት ነው፡፡

የአሸናፊነት ግምት የተሰጠው ለሚ ብርሃኑ የ2016 የቦስተን ማራቶን ቻምፒዮን ሲሆን በዚያው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በሪዮ ኦሊምፒክ በመሳተፍ አስራ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡ ፡ ለሚ ብርሃኑ ከነዚህ ውድድሮች በፊት 2015 ላይ በዱባይ ማራቶን 2፡ 05፡28 በማስመዝገብ በዚያ የውድድር ዓመት በርቀቱ አራተኛውን ፈጣን ሰዓት መያዙ በማራቶን ጠንካራ ከሆኑ አትሌቶች ተርታ ስሙን ማሰለፍ አስችሎታል፡፡ ለሚ በ2017 የዱባይ ማራቶን ክብሩን ለማስጠበቅ በሮጠበት ውድድር ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም ያስመዘገበው 2፡04፡33 ሰዓት ዛሬ በቶሮንቶ ማራቶን የአሸናፊነት ግምቱ ወደ እሱ እንዲያደላ አድርጓል፡፡

‹‹ውድድሩን ማሸነፍ እፈልጋለሁ፣ የቦትውን ክብረወሰን ማሻሻልም አንዱ ግቤ ነው›› ያለው ለሚ የውድድሩ አሯሯጮች የርቀቱን አጋማሽ 1፡03 በሆነ ሰዓት መጓዝ ከቻሉ ክብረወሰኑ መሻሻል እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ የቶሮንቶን ማራቶን ሁልጊዜም በቴሌቪዥን እንደሚከታተል የተናገረው ለሚ ከዚህ ቀደም በውድድሩ የተሳተፉ አትሌቶች የቶሮንቶ ማራቶንና የአካባቢው የአየር ፀባይ ጥሩ መሆኑን እንደነገሩት ያስታውሳል፡፡

በስኬታማው ኢትዮጵያዊ የማራቶን አሰልጣኝ ገመዱ ደደፎ ስር የዲማዶና አትሌቲክስ ፕሮሞሽን አካል ሆኖ የሚሰለጥነው ለሚ የቶሮንቶን ማራቶን ክብረወሰን ለማሻሻል እንደሚችል እምነት ተጥሎበታል፡፡ ለዚህም በአሰልጣኝ ገመዱ ስር ሲሰለጥኑ የነበሩ በርካታ አትሌቶች ከዚህ ቀደም በቶሮንቶ ማራቶንና የወርቅ ደረጃ በተሰጣቸው ሌሎች የማራቶን ውድድሮች አስደናቂ ብቃት ማሳየታቸውና ማሸነፋቸው ምክኒያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ከነዚህ መካከል በዚሁ በቶሮንቶ ማራቶን 2015ና 2016 ያሸነፈችው ሹሬ ደምሴ እንዲሁም የ2013 ቻምፒዮኑ ደሪሳ ጪምሳ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለሚ በአትሌቲክስ ሕይወቱ በትልቅ ደረጃ የሚጠቅሳቸው ውድድሮቹ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበባቸው አይደሉም፡፡ ይልቁንም የ2016 የቦስተን ማራቶን ድሉና የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎው በእሱ ዘንድ ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ ‹‹በ2016 የቦስተን ማራቶን ምርጥ አቋም ላይ ስለነበርኩኝ ውድድሩን በቀላሉ ነበር ያሸነፍኩት፣ ምርጥ ውድድሬም የቦስተን ማራቶን ነው›› በማለትም ለሚ ይናገራል፡፡ ለሚ የሪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያው እንደመሆኑ መጠን ውጤት ማስመዝገብ ባይችልም ተሳታፊ በመሆኑ ብቻ ኩራት እንደሚሰማው ይናገራል፡፡ በኦሊምፒክ ፉክክሩ ወቅት እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበት ስለነበረም ሜዳሊያ ውስጥ መግባት እንዳልቻለ ያስታውሳል፡፡ ይህ ግን ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡ እንዲያውም ወደፊት አገሩን ወክሎ በታላላቅ መድረኮች ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንዳነሳሳው ያስረዳል፡፡

በርካታ ብርቅየ አትሌቶች በተገኙባት አሰላ የተወለደው ለሚ ቀነኒሳ በቀለና ኃይሌ ገብረስላሴን የመሳሰሉ የዓለማችን ኮከብ አትሌቶች በኦሊምፒክ ሮጠው ሲያሸንፉ በቴሌቪዥን መስኮት እየተመለከተ ነው ያደገው፡፡ እነዚህን ኮከቦች አርአያ አድርጎም ነው ወደ አትሌቲክስ ሕይወት የገባው፡፡

‹‹ሩጫን የጀመርኩት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፣ በትምህርት ቤት ውድድሮች ያስመዘገብኳቸው ውጤቶቼን ስመለከት በአትሌቲክስ ሕይወት መግፋት እንዳለብኝ ወሰንኩ›› የሚለው ለሚ እኤአ 2013 ላይ ከትውልድ መንደሩ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በአሰልጣኝ ገመዱ ስር መስራት እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡ ብዙም ሳይቆይ የመጀመሪያ ውድድሩን 2014 ካምፓላ ማራቶን መሮጥ ችሏል፡፡ የመጀመሪያ ድሉን በተመሳሳይ ዓመት በዙሪች ማራቶን ላይ 2፡10፡40 በሆነ ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን እድሜው ገና አስራ ዘጠኝ ስለነበር የበርካቶች አይን ውስጥ መግባት አስችሎታል፡፡

በአሰልጣኙ ገመዱ ስር ከሚሰለጥኑ በርካታ አትሌቶች ጋር በጋራ መስራቱም ብቃቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻሽል ቁልፍ ሚና እንደነበረው ለሚ ይናገራል፡፡ ከልምምድ አጋሮቹ ጋር ጥሩ ጓደኝነት እንደነበረው የሚናገረው ለሚ ባለፈው ዓመት የልምምድ አጋሩ ከሆነችው አትሌት መሰለች ፀጋዬ ጋር ትዳር መስርቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሩጫው ዓለም ባገኛቸው ሽልማቶችም አዲስ አበባ ላይ የራሱን ቤት ሰርቷል፡፡ ወደ ፊትም ወደ ንግዱ ዓለም የመግባት ፍላጎት እንዳለው ይናገራል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012

ቦጋለ አበበ