ስልጣን በአራት ኪሎ

18


አራት ኪሎ አካባቢ በእግሬ ስንቀሳቀስ የስልጣን ነገር ሽው ይልብኛል፤ ለምንድ ነው? አራት ኪሎ ግር ግር የማይጠፋበት፣ ከባለስልጣን እስከ ተራው ሰው የሚተራመስበት ስፍራ በመሆኑ ነው እንዳትሉ። እኔን ሲመስለኝ ግን አራት ኪሎ ከፊትም ጀምሮ ለመንግሥት መቀመጫነት የተመረጠችው ለብዙ ነገር ቅርብ በመሆኗ ነው። በሌላ በኩልም አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመግባት ነፍጥና ድምፅ ወሳኝ መሆኑን ያሳየች ቦታም እንደሆነች የገቡትን ማየት በቂ ይመስለኛል። ይህንን አውቆ ያከበራት የለም እንጂ … ያው ቀን እስኪወጣላት እየጠበቀችም አልነበር። የሚገርመኝ አራት ኪሎን ደርሶ የማይመኛት ሰው የለም፤ የሚያገኟት ጥቂቶች ሆኑ እንጂ።

አራት ኪሎ ለመምጣት ዓመታት የዘለቀ ጦርነት መካሄዱን ሳስብ ቦታው ምን ቢኖረው ነው ብዬ እኔም ለመግባት ጉጉቴ ጨምሯል (መቼም ለስልጣን ቋምጠሀል አትሉኝም)። ግን ግን ስልጣን የሚጠላ አለ እንዴ! መቼም እጠላለሁ የሚል ሰው ቢኖር ከስልጣን የወረዱ ብቻ ቢሆኑ ነው። ለምን ቢባሉ በስልጣን ዘመናቸው አራት ኪሎን ተጠቅመዋታልና ይመስለኛል ምላሹ። አራት ኪሎ ባለስልጣናት የሚመሩባት ብቻም ሳይሆን የሚቀበሩባትም ስፍራ ናት። የማይታይባትም ነገር የለም፤ ሰው እንዳሻው ዘሎባት ሲያበቃ ሰፊ ቦታ ይዞ የሚቀበርባት ሲፈልግ ደግሞ አጥሮ የሚቀመጥባት ምድርም ከሆነች ሰነባብታለች…።

አራት ኪሎ ተማሪው፣ መምህሩ፣ ደራሲው፣ መጽሐፍ አዟሪው፣ ጋዜጣ ሻጩን ከነ አታሚው፣… አቅፋ ይዛለች። እነዚህን ብቻ ሳይሆን የምሁራን መፍለቂያ ተብለው የተከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎችም ከትመውባታል ( ዩኒቨርሲቲዎቹ በአሁኑ ወቅት የምሁራን ሳይሆን የሥራ እጥ መፍለቂያ ሆኑ እንጂ)። ሥራ የሌለው ሰው ሥራ ለማግኘት ከሚያምነው አምላክ ቀጥሎ የሚሳለመው ስፍራ አራት ኪሎም አይደል። ከአራት ኪሎ በኋላ ነው እንግዲህ የስልጣን አምላክ የሆነውን እንቶኔን ወደ መለመኑ የሚገባው… (እንቶኔ የአራት ኪሎ መንግሥት የሚለውን ተክቶ የገባ ነው)።

አራት ኪሎን የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የእምነት መናኸሪያ ወይም አምብርት ያደረጋት ሰው ግን ምስጋና ይገባቸዋል (በየተራ እየመጡ የመንግሥታቸው መቀመጫ ያደረጓት ሰዎች ባያባክኗት) ። ገዥዎች ጨካኝ፣ ሩህሩህ፣ ሰጪ እና ነሺ ናቸው። ሲፈልጉ በየሰበብ አስባቡ ያበላሉ፣ ያጠጣሉ… ሳይፈልጉ ደግሞ ሰበብ ፈጥረው ያስራሉ፤ ይገርፋሉ… ። እኔን የሚገርመኝ ግን የአራት ኪሎን ቤተ መንግሥት የረገጠ ሰው ሁሉ እንዴት ተመሳሳይ ይሆናል? ማብላት፣ ማጠጣት፣ መሰብሰብ፣ መግረፍ …(ግርፋቷን ግን የቀመሰ ሰው ብቻ ነው የሚያውቀው)::

ሰሞኑን ቤተመንግሥት መጎብኘት ተጀምሯል ተብሎ ህዝቡ እየጎረፈ ነው፤ ፓርኩን ምን እንደሚመስል ከተመለከተ በኋላም የሰራውን መንግሥት ሳይሆን በር የከፈተለትን ሰው እየተደፋ አመስግኗል። እናንተዬ እኛ እኮ ጥሩ አመስጋኞች ነን…በልተን ተመስገን…ተርበን ተመስገን…ተገርፈን ተመስገን… ከዚያ ደግሞ ‹‹ይህቺንስ ማን አየብኝ›› ብለን ጥቅልል ብለን እንተኛለን። ኧረ አራት ኪሎ እንግባ ጎበዝ (ኧረ ተው ተው¡)።

ምነው እንለመን አላችሁ …ብቻዬን ሁለት መቶ ብር ከፍዬ የማልገባ መሰላችሁ እንዴ። እንደ ድሮው ቢሆን አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመግባት ነፍጥ አንግቶ ተዋግቶና ብዙ ነፍሶችን መስዋዕት አድርጎ ወይም የምርጫ ኮሮጆ እንደምንም መገልበጥ ያስፈልግ ነበር። አሁን ግን ቤተ መንግሥት ለመግባት ሁለት መቶ ብር ብቻ በቂ ነው። አንድ ሺ ብር የከፈለ ደግሞ ለአንድ ቀን አገር ይመራል አሉ! አሉ ነው ደግሞ እውነት መስሏችሁ «ገብተን እንምራ» እንዳትሉ!!

መቼም አራት ኪሎ ታሪክ አያጣትም አንዳንድ ከድሮ ጀምሮ ህዝብ የመምራት አቅም አለን ያሉ አቅም ያነሳቸው አዛውንቶች ሰብሰብ ብለን ሱባኤ ልንገባ ነው ብለዋል። ‹‹የት?›› ብትሉ አራት ኪሎ አደባባይ…ከነፍጥና ከኮሮጆ ግልበጣ ውጪ በረሃብ ቤተ መንግሥት ይገባል ብለው አስበው ይሆን? ወይስ ቤተ መንግሥት ለመግባት የሚከፈለውን አንድ ሺ ብር ለማግኘት የቀን ወጪ ቅነሳ ነው ምግብ የሚያቆሙት? እንግዲህ ጊዜ ያሳየናል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012

መርድ ክፍሉ