ለሰላም ፋና ወጊ የተሰጠ ሀገራዊ ክብር

36

ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ለመላ ኢትዮጵያውያን ታላቅ የድል ብስራት የተሰማበት እለት ነው። ምክንያቱም ደግሞ የዓለማችን ሃያላን አገራት መሪዎች ጭምር የሚመኙትና ለሰላም እውነተኛ ክብርና እውቅናን የሚሰጠው የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በማቅናቱ ነው። የዚህ ሽልማት አሸናፊ ደግሞ ስለሰላም አብዝተው እየሰሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው።

ዶክተር አብይ አህመድ ለዚህ ክብር ከበቁባቸው በርካታ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ለ20 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮ-ኤርትራ ሞት አልባ ጦርነት እንዲያበቃ በማድረግ ሰላም ማስፈናቸው ሲሆን ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማምጣት ያደረጉት ጥረትና ያስገኟቸው ስኬቶችም ተጠቃሽ ገድሎቻቸው ናቸው።

 በአገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ለእስር ተዳርገው የቆዩ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ፣ የተለያዩ የፀረ ዴሞክራሲ ህጎች እንዲሻሻሉ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ያከናወኗቸው ተግባራትም ለሰላም ዘብነታቸው ማሳያዎች ናቸው።

በአገር ቤት ያለው የፖለቲካ ምህዳር ዝግ በመሆኑ ነፍጥ አንግበው ሲዋጉ የቆዩና በስደት ሆነው መንግሥትን በተለያየ አግባብ ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎችም ወደአገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወደ አገራቸው የተመለሱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እንደሆነ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ለሴቶች የሰጡት ክብርና እውቅናም የድላቸው ሌላኛው ገጽታ ነው። በአገሪቱ የስልጣን ታሪክ ውስጥ 50 ከመቶ የካቢኔ አባላት ሴቶች የሆኑት በእኚሁ የሰላም ተምሳሌት መሪ ነው። እነዚህን ጉዳዮች መነሻ በማድረግ ነው ዓለምአቀፉ የኖቤል ሸላሚ ተቋም የዘንድሮውን የሰላም የኖቤል ሽልማት ያበረከተላቸው። ይህ ሽልማት ደግሞ ለአገሪቱ ጭምር ትልቅ ክብርና እውቅናን የሚያሰጥ ነው።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት ትላንት በሚሊኒየም አዳራሽ “ሰላም መቶ በመቶ ያሸልማል” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ተካሂዷል። በዚህ የእውቅና ስነስርዓት ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ክብርት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፤ ይህች በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የኋላቀርነት፣ የርስ በርስ ግጭትና የረሃብ ምሳሌ ሆና የቆየች ሃገር በአዲስ ገጽ መፃፍ ጀምራለች ብለዋል።

ወይዘሮ ሙፈሪያት፣ አረንጓዴ ልማት፣ ማስታረቅ፣ የሴቶች እኩልነት፣ ሰላም የሃገራችን መገለጫዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፋና ወጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‹‹ሰላም ማለት የጦርነት እጦት ብቻ አይደለም›› ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ የህዝቦች መከባበር፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን በሰላም ማከናወን መቻል፣ ልጆች በሰላም ትምህርት ቤት ውለው የሚመለሱበትና እናቶች በሰላም ውለው የሚገቡበት፣ ትምህርት ቤቶች የሰላም ማዕከላት የሚሆኑበት፣ ፍትህ የሰፈነበትና በሰላም ወጥቶ መግባትን የሚመለከት መሆን አለበት ብለዋል። ሰላምን ማረጋገጥ ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር ሥራ ብቻ ባለመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ለሰላም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ልናበረክት ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወይዘሮ ሙፈሪያት እንዳሉት፤ ሃገር መለወ ጫም ሆነ መተኪያ የላትም፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ሃገራችን ላይ ተረባርበን ከሰራን መስቀለኛውን መንገድ መሻገር እንችላለን። ኢትዮጵያ መሪዎቿ ወደሰነቁላት ማማ ከፍ እንድትል ከጥላቻና ከፅንፈኝነት ርቀን በመተባበር ልንሰራ ይገባል።

 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ስለሰላም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሥራ ነው ብለዋል። በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ በሱዳን ያከናወኑት ተግባር ለአፍሪካ ሰላም አፍሪካዊ መፍትሄ እንዳለ ያሳየ መሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር አሁን በዓለም ላይ በርካታ የሰላም እጦት ችግሮች በሚታዩበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህንን ሽልማት ማግኘታቸው ለአገር ትልቅ ክብር፣ ለህዝቦቿ ታላቅ ደስታ ነው።

 ‹‹እንዲህ አይነት ክብር በቀላሉ አይገኝም›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ችግር ሲፈጠር ጎራ ይዞ ከመፋለም ይልቅ የመፍትሄ አካል መሆንን ይጠይቃል ብለዋል። ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት ሁሌም መፍትሄ አለ፤ የዶክተር አብይ ሽልማትም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የአገራችን ሰላም ላይ ተስፋ መጣሉን ያመላክታል ብለዋል።

በቀጠናችን በርካታ ሰላም ማስከበር ሃይል ተሰማርቶ ይገኛል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ነገር ግን ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አለመቻሉን ጠቅሰዋል። በአንፃሩ ግን ለዚህ ሰላም ማስከበር ሥራ የሚወጣው ወጪ ለልማት ቢውል የአካባቢውን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ሊፈታ በቻለ ነበር፤ ዛሬ በእጃችን የገባው የሰላም የኖቤል ሽልማት ለሚቀጥለው ሰላምና የልማት ጉዞ እንደመስፈንጠሪያ ሊያገለግለን ይገባልም ብለዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁለት ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አንዱ በአገራችን ትልቁና በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ ሽልማት ነው። ይህ ሽልማትም ከዚህ በኋላ በሰላም ዙሪያ ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በየዓመቱ እንደሚሰጥ የሰላም ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ የሰላም ቤተሰቦች ሽልማት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ከሽልማቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ክብርና ምስጋና ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይድረስ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀጠል በተለይ ለህፃናትና ታዳጊዎች ባስተላለፉት መልዕክት የእሳቸውን ልጅነት የህይወት ተሞክሮ አጋርተዋል።

“እኔ በልጅነቴ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ መደብ ላይ ተኝቼ ነው የተማርኩት፣ ነገር ግን አሁን ያለው ትውልድ ከኔ የተሻለ፤ እድል አለው፤ በመሆኑም ከኔ የተሻለ፤ ቦታ እንደምትደርሱ እያሰባችሁ ተግታችሁ ልትሰሩ ይገባል ብለዋል። ሰላም ለኢትዮጵያ እና ሰላም ለአፍሪካ፣ እንዲሆን እያንዳንዳችን ሰላም ይኑረን፣ ለማሸነፍ መዋደድና ዝቅ ማለት ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከስኬታቸው በስተጀርባ ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል በተለይ አቶ ለማ መገርሳ ላደረጉላቸው አስተዋፅኦ ሁሉ በማመስገን ከሰላም ቤተሰቦች የተበረከተላቸውን ሽልማት አብርክተውላቸዋል።

በእለቱ “አብይ እንደ ሰው” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ዶክመንተሪ ፊልም የቀረበ ሲሆን፤ በፊልሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴያቸውም ሆነ በኑሯቸው ውስጥ ለሰላምና ለፍቅር ያላቸው ከፍ ያለ ቦታ ተንጸባርቋል። ከዚህም ባሻገር በስራቸው ላይ ያላቸው ትጋትና ለሰው ልጆች ብልፅግና የሚያደርጓቸው ጥረቶች እንዲሁም ሩህሩህና አስተዋይ መሪ ስለመሆናቸው በአጭሩ ተዳሷል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012

ወንድወሰን ሽመልስ