ለነገ ከፍታ ዛሬ እንስራ!

19

 አገራችን አንዴ የከፍታ ሌላ ጊዜ ደግሞ የውድቀት ታሪኮችን አስተናግዳለች። ከዚህ አንጻር የከፍታ ታሪኮቻችንን ስንመለከት ቀደምት የታሪክ ቅርሶቻችን እና የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆኑ የድል ታሪኮቻችን ጎልተው ይወጣሉ። እነዚህ ታሪኮቻችን ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች ያመላክታሉ።

በአንጻሩ የኢትዮጵያን ገጽታ ያበላሹና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ አንገታችንን ያስደፉ ታሪኮችም አሉን። እነዚህ ታሪኮቻችን ደግሞ በዋናነት ከድህነት ጋር የተያያዙ ናቸው። በተለይ በአንድ ወቅት የምእራባውያን የመዝገበ ቃላት የድርቅ ተምሳሌት እስከመሆን የደረስንበት ጊዜ ሊሆን የማይገባና ለኢትዮጵያ ህዝብ የማይመጥን ታሪካችን ነው። ለዚህ ውድቀት መንስኤ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የእርስ በርስ ግጭት እና የመሪዎቻችን ድክመት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ። የነዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የግለኝነትና የራስ ወዳድነት መንሰራፋትና የጥላቻ ፖለቲካ መስፋፋት ናቸው።

“ሰዎች የጥላቻና የሌሎች መጥፎ ምግባሮችን እውነተኛ ውጤት ቢያውቁ፣ የሚያስከትሉትን የመንፈስ ድቀትና ዝቅጠት ቢረዱ ያለምንም ጥርጥር ከእኩይ ድርጊታቸው ይቆጠቡ ነበር” ሲል እውቁ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጠስ ተናግሮ ነበር። የዘመናችን የስነልቦና ባለሙያዎችም ይህንን እውነታ ይጋራሉ። ጥላቻ በቅድሚያ የሚጎዳው ራሱን በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያለውን ሰው እንደሆነም በተለያዩ ጥናቶች ማረጋገጥ ተችሏል።

ሰው የራሱ አእምሮ ውጤት ነው። እያንዳንዱ ሰው የሚለካው በአእምሮው ልክ ነው። በተፈጥሮው የተሰጠውን የማሰብና የማገናዘብ ፀጋ በአግባቡ ተጠቅሞ አእምሮውን የሚያሰራ ሰው የተሻለ ስብእናና ማንነትን ያዳብራል። ይህ ደግሞ የተሻለ ህይወት እንዲኖረው ያደርገዋል። በአንጻሩ አእምሮአችንን ላልተገባ ድርጊትና ጥላቻ ስንጠቀም በቅድሚያ ራሳችንን እንጎዳለን፤ ከዚያም አልፎ ሌሎችን ብሎም አገርን እናፈርሳለን።

ሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብን ካላዳበረ “ሰው” የሚለውን ባህርይ ሊያሟላ አይችልም። ከሰውነት ይልቅ ለእንስሳነትም ቅርብ ይሆናል። እንስሳት ደግሞ ከነገ ይልቅ ዛሬን ብቻ የሚኖሩ ናቸው።

በአገራችንም አልፎ አልፎ እያየን ያለነው የዚህ ፀጋ መጓደል ነው። ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ ስሜታዊነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት ሁኔታ በስፋትይስተዋላል። ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ በጅምላ የመነዳት ሁኔታ ይስተዋላል። ከእውቀት ይልቅ ስሜት ሲገዛን እንታያለን። በዚህም የተነሳ በተለያዩ የግለኝነት አስተሳሰቦች ተጠምደን ሰዎችን ለጉዳት ስንዳክር እንታያለን።

ለምሳሌ በቅርቡ የሆነውን እንኳ ብንመለከት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በዓለም ትልቁን የሰላም ሽልማት ከዓለም የዴሞክራሲ ተምሳሌት ከሆኑ አገራት መሪዎች ጭምር በመላቅ ተሸልመዋል።

ይህ እንደ አገር የጋራ ኩራታችን ነው። ይህ ሽልማት ግን ለአንዳንዶች ራስ ምታት ሆኗል። አገር በበጎ ስትነሳ የሚያምን ከሆነ የአገር ጥላቻ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። አገርን የምንጠላ ከሆነ ደግሞ ለውድቀቷ እንጂ ለልማቷ አንሰራም። ይህ ደግሞ የጥላቻ ጥግ ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከምትታወቅባቸው መገለጫዎቿ ውስጥ አንዱ ሰንደቅ ዓላማዋ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቷ ሰንደቅ አላማ ደግሞ ይታወቃል። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሆኖ በመሃሉ ላይ ኮከብ ያለበት ነው። ይህ የማያስማማን ቢሆን እንኳን ለመለወጥ የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ የግድ ነው። እስከዚያ ግን የጋራ መገለጫችን ነው። ይህ ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱን ህልውና የሚያሳይ ነው። በዚህ የጋራ አጀንዳ መያዝ ካቃተን አገር አለን ለማለት ከባድ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ ያደለን በርካታ ሃብቶች አለን። በቀላሉ ሊለማ የሚችል ምድርና የተፈጥሮ ፀጋ፣ ለዘመናት በጠንካራ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የተገነባ ህዝብ፣ ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች ወዘተ ያለን ህዝቦች ነን። እነዚህ የማንነት መቅረጫ እሴቶቻችን ደግሞ ለነገው ትውልድ የተሻለች አገር ለመገንባት ትልቅ ሃብቶች ናቸው።

ይሁን እንጂ እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ ለመጠቀም ከመጣር ይልቅ በማንነት ውስጥ ተሸሽገን በአቋራጭ ለመክበር ሩጫ ውስጥ ስንገባ እንውላለን። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው ሁኔታ የቀደመውን ጠንካራ አንድነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻል እና የመልካምነት እሴቶች በመሸርሸር አገርን ወደሚያፈርሱ የግጭትና የመለያየት አዳዲስ ባህሎች እየገባን በመሆኑ ከዚህ ለመላቀቅ ራሳችንን ቆም ብለን እንይ። አሳፋሪ ታሪኮቻችንን ለመመለስ ከመጣር ይልቅ የከፍታ ዘመናችንን እያሰብን ለሌላ ከፍታም እንትጋ።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012