ልበ ብርሃናማዋ የፈጠራ ባለቤት

40

ተመራማሪዎችና ጠበብቶች ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ጠዋት ማታ ደፋ ቀና ይላሉ። ቀደመው በመተንበይና መፍትሔ ይሆናል የሚሉትን ሃሳብ በማመንጨት ጭምር ለችግሮች ዓይነተኛ መፍትሔ ጀባ ይላሉ። ቁጥራቸው የሌላውን ዓለም ያህል አይሁን እንጂ ችግር ፈቺ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ የዛሬዋ እንግዳችን ምንም እንኳ በሥራዋ አንቱታ ለማግኘት ብዙ የሚቀራት ቢሆንም ከራሷ ችግር ተነስታ ለብዙዎች መፍትሔ በማበጀትና የብርሃን ጭላንጭል በማሳየት ረገድ በአብነት ልትጠቀስ የምትችል ናት፡፡

ወጣት ሜሮን ተስፋዬ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በዚያው በአክሱም ከተማ መጋቢት 18 አንደኛ ደረጃና አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን፣በልዩ ፍላጎት ትምህርት ዘርፍ ዓደዋ ከተማ ከሚገኘው ዓደዋ ኮሌጅ በዲፕሎማ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ወጣቷ ያካል ጉዳት ቢኖርባትም ያካል ጉዳቷ ሳይበግራት ለሌሎች ብርሃን ለመሆን ትታትራለች፡፡

«አንድ ቀን ዓደዋ ከተማ በአንድ ሆቴል በመዝናናት ላይ እያለሁ፤ አንድ ዓይነስውር የሆነ ሰው ጎራ ይላል። ምግብና የሚጠጣ ለማዘዝ ፈልጎ አስተናጋጇን የምግብና የመጠጥ ዝርዝር ደብተሩን ታነቢልኝ ይላታል፡፡ አስተናጋጇም አስቸኳይ ትዕዛዝ አለብኝ ብላው ሌላ አስተናጋጅ እንዲያግዘው ነግራው ትሄዳለች፡፡ የሚረዳው ባለማግኘቱ የሚፈልገውን ምግብ ሳይመርጥና ዋጋውንም ሳያውቅ ለመጠቀም ተገደደ፡፡ በወቅቱ የተጠቀመው ምግብ ዋጋ በኪሱ ከያዘው ገንዘብ በላይ ስለነበር ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኩን አስይዞ ነበር ከምግብ ቤቱ የወጣው፡፡ የተፈጠረው ነገር ልቤን በጣም ነካው» የምትለው ወጣት ሜሮን በግለሰቡ ላይ የተፈጠረው አጋጣሚ ለፈጠራ ሥራ እንዳነሳሳት ትገልጻለች፡፡

ዓይነስውራን ያለማንም ዕርዳታ የምግብና የመጠጥ ዝርዝር ደብተሩን በመጠቀም የሚፈልጉትን እንዲጠቀሙ ምን ማድረግ እንዳለበት ጊዜ ወስዳ አስባ የምግብና የመጠጥ ዝርዝር በብሬል በማዘጋጀት የመጀመሪያዋ የሆነውን የፈጠራ ሥራዋን አበረከተች፡፡ የፈጠራ ሥራዋ ሆቴል ቤቶች የሚያቀርቡት የምግብና መጠጥ ዝርዝር ከነዋጋው የሚገልጽ በመሆኑ ዓይነስውራኑ የሌላ ሰው ዕርዳታ ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ ለመጠቀም ያስችላቸዋል፡፡ ካላስፈላጊ ወጪም ያድናቸዋል፡፡

በብሬል የተጻፈ የምግብና የመጠጥ ዝርዝር ደብተሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ሠርታ ተግባር ላይ እንዲውል ያደረገችውም አክሱም ከተማ በሚገኘው ኮንሶላር ኢንተርናሽናል ሆቴል መሆኑን ገልጻለች። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተመሳሳይ ሳሬም ሆቴልና አፋራነሲሰ ሆቴል እንዲሁም የምሥራች ማየት የተሳናቸው ማዕከል እንዲጠቀሙበት ማድረጓን ተናግራለች፡፡ በብሬል የተጻፈ የምግብና የመጠጥ ዝርዝር ደብተሩን ለካፒታልና ሀርመኒ ሆቴሎች በማዘጋጀት ላይ መሆኗንም ገልጻለች፡፡ ፈጠራው የሆቴል ቤቶችን አገልግሎት እንደሚያቃልላቸውም አመል ክታለች፡፡

የወጣቷ ፈጠራ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ስትከታተል ዓይነስውራን ተማሪዎች የተለያዩ ሥራዎችን በኮምፒውተር ለመሥራትና ለመጠቀም ሲቸገሩ ታያለች፡፡እርሷ እንዳለችው ተማሪዎቹ ብዙ ጊዜ በጆሮ ማዳመጫ ነው የሚጠቀሙት፡፡ አዘወትረው መጠቀማቸው ለጆሮ የጤና ችግር እንደሚ ያጋልጣቸው ታውቃለች።

ዓይነስውራን ኮምፒውተርን ተጠቅመው በራሳቸው ለመጻፍ ለማንበብና ለማድመጥ ድረ ገጽ ለመጠቀም የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚቸገሩም ትገልጻለች። የተማሪዎቹ ሁኔታ ሁሌም ያሳስባት ስለነበር መፍትሔ ለመፈለግ ጊዜ አልወሰደባትም፡፡ ከመጀመሪያው የፈጠራ ልምዷ በመነሳት በብሬል የተለወጠ የኮምፒውተር ኪቦርድ ወይም የፊደል ሰሌዳ በመሥራት የተማሪዎቹን ችግር በመፍታት የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡

እንደ ወጣቷ ገለጻ፤ ይህ ፈጠራ የኮምፒውተር ኪቦርድ በብሬል የተለወጠ ሆኖ በኪቦርዱ ላይ ያሉት ፊደላቶች፣ ቁጥሮች፣ ምልክቶች እንዲሁም መግለጫዎች በብሬል ተቀርጸው ለዓይነስውራን የተዘጋጀው የነበረባቸውን ችግር ይቀርፍላቸዋል፡፡

ፈጠራው በቀላሉ ኮምፒወተር እንዲጠቀሙ የሚረዳቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ምን እንደጻፉ በድምፅ መስማትም እንደሚያስችላቸው፣ ኢንተርኔትና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም፣የተለያዩ የዓለም እና ለትምህርታቸው የሚያስፈለጋቸውን መረጃዎች ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ታስረዳለች፡፡ ይህ ደግሞ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ትገልጻለች፡፡

«በተለይም የኮምፒተር ኪቦርዱን ወደ ብሬል ቀይሬ አካል ጉዳተኞች በቀላሉ እንዲጠቀሙት ማድረጌ አስደስቶኛል። ምክንያቱም አሁን ላይ ሁሉም ነገር የሚሠራው በኮምፒዩተር ነው። እንዲሁም ሁሉም ነገር ዲጅታል እየሆነ ነው። በመሆኑም ይህንን የፈጠራ ሥራ በማበርከቴ እነዚህ አካል ጉዳተኞች በቀላሉ ኮምፒውተርን በመጠቀም በቴክኖሎጂው ከዓለም ጋር እኩል እንዲራመዱ ያስችላቸዋል» በማለት ትገልጻለች፡፡
ሌሎች ችግር ፈች የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት በሂደት ላይ መሆኗን የምትናገረው ወጣቷ በዋናነትም የሂሳብ ማስሊያ መሳሪያ (calculator) ወደ ብሬል በመቀየር ዓይነስውራንን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዷን ትጠቅሳለች፡፡ ፈተራው ዓይነስውራን በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ እንዲማሩ ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል የሚል እምነት አላት፡፡

ወጣት ሜሮን እስከዛሬ ባበረከተችው የፈጠራ ሥራ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳተኞች ክበብ ሽልማት እንዳበረከተላት ገልጻልናለች፡፡ ለፈጠራ ሥራዋ ውጤታማነትም በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆና አብረዋት ይማሩ የነበሩና መምህራኖች በሃሳብና በተለያዩ ድጋፎች ከጎኗ እንደነበሩ አስታውሳለች፡፡

ይሁንና ሥራዎቿ በተጨባጭ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድርግ ረገድ ከመንግሥት በቂ ድጋፍ እንዳልተደረገላት ትናገራለች፡፡ «መንግሥትም ወጣቶች የፈጠራ ሥራቸው ከፍ እንዲል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል። ነገርግን የተሠሩ የፈጠራ ሠራዎች እስከመጨረሻው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እየተከታተሉ ወደተግባር እንዲገቡ በማደረግ ረገድ ክፍተቶች አሉ» ትላለች።

«በተለይም በብሬል የተጻፈ የምግብና መጠጥ ዝርዝር ደብተሩን ለሁሉም ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ፤ በብሬል የተጻፉ ጽሑፎችን ለማተም መሳሪያ በሀገራችን የለም በሚባል ደረጃ እጥረት በመኖሩ፤ የፈጠራ ሥራዬን ተደራሽ ለማድረግ ተቸግሬለሁ» በማለት የፈጠራ ሥራዎቿ ለመንግሥት ተደራሽ እንዲሆኑ የመንግሥትን ድጋፍ እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡

እንደወጣቷ ማብራሪያ፤ ሀገሪቱን ለማሳደግም ሆነ ለማጥፋት ዋነኛውን ድረሻ የሚወሰደው ወጣቱ ኃይል ነው። ወጣቱ እራሱን ከአልባሌ ቦታ በማራቅ ሁሌም ጠንክሮ በመሥራትና በመማር የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል፡፡ በተለይም ካሰቡበት ለመድረስ ቀን ከሌሊት መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚያጋጥማቸውንም ችግሮች በፅናት መወጣት አለባቸው፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011

ሰሎሞን በየነ