የአገር አድባሩ ፀጋዬ

26

‹‹ … አዬ! ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?

ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?

እስከመቼ ድረስ፣ እንዲህ መቀነትሽን ታጠብቂባት?

ልቦናሽን ታዞሪባት?

ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?

አላንቺ እኮ ማንም የላት… ››

‹‹ … አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣

በፋሽስታዊ ነቀርሳ፣

ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ።

ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣

እንደኮረብታ ተጭኗት፣

ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን

ቁልቁል ጠምዝዟት፣

ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት፣

ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት።

እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ

የኃይልሽ ውጋገን፣

አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣

በርታ በይኝ እመብርሃን፣

ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣

እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን …››

(‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››

1961 .ም፣ አዲስ አበባ)

***

ከዚህ ሌላ ትእዝብት ውረሽ፥ ሳይነጋ እንዳስመሸሽብኝ

ጊዜና ትውልድ ይፍረደን፥ ሳልነቃ እንዳስረፈድሽብኝ።

ያም ሆኖ ለራስሽ እንጂ ለኔ ከቶም አታልቅሺ፣

አንቺ ነሽ እንባ እምትሺ፤

የእምነትሽ መተሣሰሪያ፤ ውልሽ ለተላቀቀብሽ ላንቺ ነው እንባ እሚያስፈልግሽ።

አዎን፥ ይኽን እወቁልኝ፥ ምስክር ሁኑኝ ሰማዕታት

ለሷ ነው እንባ የሚያስፈልጋት

(‹‹የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ››

1957 .ም፣ ደሴ)

***

ዛሬ የእነዚህ ስንኞች ደራሲ የሆኑትን አንጋፋውን ገጣሚና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅንን በጥቂቱም ቢሆን እንዘክራቸዋለን።

ጊዜው 1928 ዓ.ም … ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት በስድስተኛው ወር ፀጋዬ ከአምቦ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝና ቦዳ ተብላ በምትታወቅ አካባቢ ተወለደ። ቦዳ ተራራ ግርጌ የሚገኘው የፀጋዬ ቤተሰቦች ቤት ሲቃጠል እናቱና እህቱ ከፋሺስት ወታደሮችና ከባንዳዎች ጋር ተታኩሰው በአርበኞች እርዳታ ነፍሳቸውን ካዳኑ በኋላ እናቱ ሕፃኑ ፀጋዬን ይዘው ወደ አያት፣ ቅድመ አያቶቻቸው ቀዬ ተሰደዱ። አባቱ ገብረመድኅን ሮባ በወቅቱ ገና ከማይጨው ዘመቻ አልተመለሱም ነበር።

በ‹‹ለዛ›› መጽሔት የ1985 ዓ.ም ዕትም ላይ የወጣው ጽሑፍ ስለፀጋዬ ቤተሰቦች እንዲህ ሲል ያትታል። ሃሳቡ የራሳቸው የሎሬት ጸጋዬ ነው።

‹‹ … እናቴ ወይዘሮ ፈለቀች ዳኜ ኃይሉ በአስራ ሶስት ዓመቷ ነው አባቴን ገብረ መድኅን ሮባ ቀዌሳን ያገባችው። የጠራ ምድር አማራ ነች። በልጅ እያሱ ጊዜ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ጦር ንጉሥ ሚካኤልን ለማገድ ሲሔድ አባቴ በጦሩ ውስጥ ነበሩ። ‹የሃምሳ አለቃ› ይባል ነበር በዚያን ጊዜ ሹመት። ታዲያ በወቅቱ አንኮበር ሲቃጠል ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ለየትልልቁ ሰው ይከፋፈሉና የእናቴ ቤተሰቦች ለአባቴ ይሰጣሉ። ከዚያ ፊታውራሪ ኢብሳ ሴት አያቴን ‹ልጅሽን ለወንድሜ ስጪ› ይሉና እናቴ አባቴን ታገባለች። የሁለት ባሕሎች ውጤት- አካል ሆኜ ነው ያደግሁት። ድልድይ ሆንኩኝ። አፍ የፈታሁት በኦሮምኛ፣ እርባታ የጀመርኩት ደግሞ የግዕዝ ግሥ በመግሰስ ነበር። በጠላት ወረራ ጊዜ ካህናቱ የእናቴ ወንድሞች ከጠራ ስለሚመጡ ማምሻዬ ከእነርሱ ጋር ነበር …››

የቄስ ትምህርት ቤት ገባ። መምህሩ የዲማው ባለቅኔ አለቃ ማዕምር ዮሐንስ ጭምር እስከሚገረሙ ድረስ ቅኔን ተጠበበበት። የጸጋዬ ጉብዝና መምህሩ አለቃ ማዕምር ዮሐንስ ልጃቸውን መዝሙር ማዕምርን ‹‹ምነው እንደ ፀጋዬ በሆንክልኝ ነበር›› እንዲሉት አስገደዳቸው። ለቅኔ አስተማሪዎቹ ብርቅዬ ልጅ ለመሆን በቃ።

ሎሬት ጸጋዬ ስለዚሁ ጉዳይ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹ … በኦሮምኛና በግዕዝ ግሥ እርባታ ምላሴን ስለፈታሁ ወደ አማርኛ ስመጣ ምንም ችግር አልገጠመኝም። ለዚህም ይመስለኛል ለቅኔ አስተማሪዎቼ ብርቅዬ ልጅ ለመሆን የበቃሁት። መምህሮቼና ጓደኞቼ በጣም ይገረሙና ይደነቁ ነበር›› በማለት ተናግረዋል።

ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላም የአስተማሪዎቹ ፍቅርና አድናቆት አልተለየውም። አምቦ ማዕረገ ሕይወት ትምህርት ቤት እየተማረ በነበረበት ወቅት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሚስት ጸጋዬ በወላጆች ቀን በዓላት በእንግሊዝኛም ግጥም እንዲፅፍ ያበረታቱት ነበር። ባለቤታቸው ንግግር በሚያደርጉባቸው አጋጣዎች ሁሉ ‹‹ፀጋዬ ይተርጉምልህ›› ይሏቸው ነበር። የትምህርት ቤቱ መምህራን ለታዳጊው ጸጋዬ ያላቸው ፍቅርና ግምት ይህን ያህል ነበር።

ገና በ13 ዓመቱ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ የመጀመሪያ ሥራው የሆነውንና ‹‹የዳኒሲዩስ ዳኝነት›› የተባለውን የተውኔት ሥራውን በአምቦ ትምህርት ቤት አዳራሽ አቅርቦ ተወዳጅነት አተረፈ። ሥራውን ከተመለከቱለት ሰዎች መካከል ደግሞ ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ አንዱ ነበሩ።

ወደ አዲስ አበባ ሄዶ ጀኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሯል። በእርግጥ የፀጋዬ ትምህርት በአለቃ ማዕምር የቅኔ ትምህርት ቤት፣ በአምቦው ማዕረገ ሕይወትና በጀኔራል ዊንጌት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በ1949 ዓ.ም ከአዲስ አበባ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) ተመርቋል። ከዚያም የውጭ አገር የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ፣ ቺካጎ በመሄድ ኢሊኖይስ ውስጥ ከሚገኘው የብላክስቶን የሕግ ትምህርት ቤት (Blackstone School of Law) በዲግሪ (LLB) ተመርቋል።

ከዚያም ወደ አውሮፓ ተሻግሮ በሮም፣ በለንደንና በፓሪስ ከተሞች ስለ ትያትር ጥበብ ተምሯል። ከባህር ማዶ እንደተመለሰም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር ቤትን ማደራጀትና ማጠናከር ላይ አተኩሮ መስራት ጀመረ። ከዚህ ጎን ለጎንም በሴኔጋል በተካሄደ የኪነ ጥበብና ባሕል መድረክ ላይ እንዲካፈል ተጋብዞ ወደ ዳካር አመራ። በዚያም ባቀረበው የጥናትና ምርምር ሥራው በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እየተዘዋወረ በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብ ላይ ያተኮሩ ገለፃዎችን እንዲያደርግ አስቻለው። በአልጀርስ በተከናወነው የፓን አፍሪካ የባሕል ፌስቲቫልም ተሳትፏል።

በ29 ዓመቱ በ1959 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የስነ ጽሑፍ ሽልማት አሸናፊ ሆነ። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ አገልግለዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍልን በማደራጀት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የያዙት ሎሬት ጸጋዬ ናቸው። የኢትዮጵያ የሰላም፣ የወንድማማችነትና የወዳጅነት ማዕከል ዋና ጸሐፊም ሆነው ሰርተዋል። ‹‹ኦዳ ኦክ ኦራክል (Oda Oak Oracle) የተባለውና በእንግሊዝኛ የተፃፈው ሥራቸው በአፍሪካና በአሜሪካ የነበራቸውን ዝና ከፍ አድርጎላቸዋል። 52 የግጥምና የቅኔ ሥራዎቻቸው የተካተቱበት ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የተሰኘው መድብል እጅግ ተወዳጅና በብዙዎች ዘንድ ከሚታወሱላቸው ሥራዎቻቸው መካከል አንዱና ዋነኛው ነው።

ከሥራዎቻቸው መካከልም፡-

1. የዳኒሲዩስ ዳኝነት (ተውኔት)

2. እሳት ወይ አበባ (ግጥምና ቅኔ)

3. በልግ (ተውኔት)

4. የደም አዝመራ (ተውኔት)

5. እኔም እኮ ሰው ነኝ (ተውኔት)

6. የከርሞ ሰው (ተውኔት)

7. የእሾህ አክሊል (ተውኔት)

8. ክራር ሲከር (ተውኔት)

9. አስቀያሚ ልጃገረድ (ተውኔት)

10. እኝ ብዬ መጣሁ (ተውኔት)

11. ቴዎድሮስ (ተውኔት)

12. ምኒልክ (ተውኔት)

13. ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት (ተውኔት)

14. ዘርዓይ ድረስ በሮም አደባባይ (ተውኔት)

15. ጆሮ ገድፍ (ተውኔት)

16. ሀሁ በስድስት ወር (ተውኔት)

17. እናትዓለም ጠኑ (ተውኔት)

18. መልዕክተ ወዛደር (ተውኔት)

19. አቡጊዳ ቀይሶ (ተውኔት)

20. ጋሞ (ተውኔት)

21. ሀሁ ወይም ፐፑ (ተውኔት)

22. ቲራቲረኞች (ተውኔት)

23. ኮሾ ሲጋራ (ተውኔት)

24. የእማማ ዘጠኝ መልክ (ተውኔት)

25. ዐፅም በየገጹ (ተውኔት)

26. ትንሣኤ ሰንደቅ ዓላማ (ተውኔት)

27. የመቅደላ ስንብት (ተውኔት)

28. ጥላሁን ግዛው (ተውኔት)

29. ዐፅምና ፈለጉ (ተውኔት)

30. ጩሌ (ተውኔት) የሚሉዋቸው ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ሀምሌት››፣ ‹‹ኦቴሎ›› እና ‹‹ማክቤዝ›› የሚባሉትን የእንግሊዛዊ ደራሲ ዊልያም ሼክስፒር ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎች የትርጉም ሥራዎችንም ሰርተዋል። በሥራዎቻቸውም የሎሬትነት ማዕረግ አግኝተዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የትያትር ታሪክ ውስጥ እንደ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በሳንሱር ምክንያት የተሰቃየ ደራሲ የለም ይባላል። ሳንሱር የሎሬት ጸጋዬን ሥራዎች እየተከታተለ ማነቅ የጀመረው ገና ከጠዋቱ ከ1950ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከሠላሳ ዓመታት በላይ የሳንሱር ጽልመታዊ መጋረጃ ሥራዎቻቸውን ሲጋርድባቸው ከመቆየቱም በላይ፤ የሳንሱር ጦስ ወደ ግል ሕይወታቸው ተሸጋግሮ ኑሮን አክብዶባቸው ነበር። ሎሬት ጸጋዬ በሳንሱር ሳቢያ በጥበብ ሥራዎቻቸው ላይ የደረሰውን ግፍ በአንድ ወቅት እንዲህ ገልፀውት ነበር።

‹‹ከጻፍኳቸው 41 ቴአትሮች ውስጥ (ከተረጎ ምኳ ቸውና በእንግሊዝኛም ከጻፍኳቸው ጭምር)፣ አሥራ ሁለቱን ሳንሱር ሙሉ በሙሉ አግዶብኛል። ሃያ አንዱን ቆራርጦብኛል። ሶስቱን ግማሽ ለግማሽ ጎራርዶብኛል። አራቱ ግን ገና ለመድረክ (አልቀረቡም ) ከሶስቱ የሥነ ግጥም መጻሕፍቶቼ ውስጥ (ሁለቱ ገና አልታተሙም)፣ በሰላሳ ሰባት ነጠላ ዝርዝር ግጥሞቼ ምክንያት፣ የሳንሱር ቢሮ፣ የጸጥታው ክፍል ቢሮና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቴ ቢሮ ከፍተኛ ሹማምንት ገስጸውኛል። ቀጥተውኛል፤ዝተውብኛል። በአንዲት ‹‹ጆሮ ገድፍ›› በምትባል ትንሽ ቴአትሬ ምክንያት የጃንሆይ መንግሥት ጸጥታ ቢሮ ለሃያ አራት ሰዓታት በቁጥጥር ሥር አውሎኛል›› ብለው ነበር።

የሎሬት ጸጋዬ ትያትሮችን በሳንሱር መቆራረጣቸው ወይም መከልከላቸው አልበቃ ያላቸው ሹማምንት ‹‹ጆሮ ገድፍ›› እና ‹‹አቡጊዳ ቀይሶ›› በተሰኙት ድርሰቶቻቸው እንዲታሰሩ ወስነውባቸው ነበር። በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ከነበረው የሳንሱር መዓት ተርፈው ለመድረክ ከበቁት የባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ የተውኔት ሥራዎች መካከል ‹‹የደም አዝመራ››፣ ‹‹የእሾህ አክሊል›› እንዲሁም በዘውድ መንግሥት ፍጻሜ ዋዜማ ላይ የቀረበው ‹‹ሀሁ በስድስት ወር›› እና በድኅረ ደርግ የታየው ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ይጠቀሳሉ። ሎሬት ጸጋዬ በእንግሊዝኛ የተጻፉ ስምንት ያህል ትያትሮች ያሏቸው ሲሆን፤ በውጭ አገር የቀረቡ የጥናት ሥራዎች በመሆናቸው ከሳንሱር ምርመራ እርግማን ለመትረፍ ችለዋል።

በተለይ በደርግ ዘመን ሎሬት ጸጋዬ ከሥራ መታገድ እስከ እሥር ድረስ የዘለቀ አደጋ በሕይወታቸው ላይ ሊደርስባቸው የቻለው የሳንሱር ክፍል ለጸጥታው መስሪያ ቤት ስለትያትሮቹ ባቀረበው ሪፖርት የተነሳ ነበር። በዚህ የተነሳም ሎሬት ጸጋዬ ትያትር ከሚያዘጋጁበት መድረክ ላይ በድንገት ተጠልፈው ተወስደው ወደ ወሕኒ እንዲወረወሩ ተደርጓል። የሴኔጋል ፕሬዚዳንት የነበሩት ፀሐፊው ወዳጃቸው ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) እንዲሁም ፔን ኢንተርናሽናል (Pen International) ሎሬት ጸጋዬ ከእሥር እንዲፈቱ ለደርጉ በተደጋጋሚ ባቀረቡት ብርቱ ተማጽኖ የተነሳ ከእሥር ቤት ለመውጣት ቻሉ። ከእሥር ከተፈቱ በኋላ የነበሩት ስድስት ዓመታት ግን ሎሬት ጸጋዬ ከሥራና ከደመወዝ ታግደው የቆዩባቸው የግዞት ዘመናት ነበሩ።

በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ሠላም ወይም አጥፍቶ መጥፋት የሚል መልዕክት ያዘለውን ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› የተሠኘ የትያትር ሥራቸውን በአማተር ተዋንያን አማካይነት ለሕዝብ አሳይተው ነበር። ይሁን እንጂ ይኸው ትያትር በሀዋሳ ከተማ ለሕዝብ በቀረበበት ጊዜ ታጣቂዎች ባነሱት ብጥብጥ የተነሳ የትያትሩ ተዋንያን ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። ይህም አዲሱ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ሎሬት ጸጋዬ በጥበባዊ ሥራቸው ላይ የገጠማቸው የመጀመሪያው ችግር ሆኖ ተመዝግቧል።

ምንም እንኳ አዲሱ መንግሥት ማናቸውንም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት የሚገድብ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ን ያነሳና መዋቅሩንም ያፈራረሰ ቢሆንም፣ የሎሬት ጸጋዬ ሥራዎች ግን በትያትር ቤቶች የመታየት ፈቃድ እየተነፈጋቸው ለመድረክ ሳይበቁ ቀርተዋል። በተለያየ ጊዜ ፈቃድ ከተነፈጋቸው የተውኔት ሥራዎቻቸው መካከል ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹ቴዎድሮስ››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ›› እና ‹‹ቴራቲረኞች›› የተሠኙት ሥራዎች ይጠቀሳሉ። ሎሬት ጸጋዬም በጣም ያሳዘናቸውን ይህንን ሥውር የክልከላ ድርጊት ‹‹መንግሥታዊ ድፍን ዝምታ ወይም የመልስ አልባ ዝምታ ሳንሱር›› ነው በማለት ስም አውጥተውለት ነበር።

ባለ ቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ስለጥበብ ባደረጓቸው ቃለ መጠይቆችና ውይይቶች፣ ስለ ሳንሱር ሳያነሱ ያለፉበት ጊዜ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሎሬት ጸጋዬ ስለ ሳንሱር ሲያወሱም፣ ሳንሱር የጨቋኝ መንግሥታትን ሠይፍ ወክሎ እንደሚቆም፣ ፍልሚያውም በዚህ የጨለማ የሠይፍ ኃይልና በብርሃናማው ብዕር መካከል መሆኑን፣ የጥበብን ጥንተ ታሪክ እየጠቀሱ ያስረዱ ነበር። ሎሬት ጸጋዬ ከጨለማው ኃይል ጋር እየተፋለሙ ያሳለፏቸውን ዓመታት አስመልክተው እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹በብዕር ሕይወቴ ውስጥ በየዘመኑ መንግሥቶች የሥነ ልቡና ተጽዕኖዎች፣ መንገላታቶች፣ የደመወዝ መቁረጫዎች፣ የዝውውር መቀጫዎች፣ ዛቻዎች፣ ዘለፋዎች፣ እሥሮች ወዘተ (በግድ የለመድኳቸው ቢሆኑም) ደርሰውብኛል።

ሌሎች የዓለም ደራሲያን በተለይ የብዕር ታላላቆቹ በሕይወታቸው የከፈሉትን ጽዋ ስመለከተው ግን እጽናናለሁ። የኛ ‹‹ዙሩ በዛ›› እንጂ በሥልጣን ሠይፍና በጥበብ መካከል ያለ ትግል ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚኖር አሳዛኝ እውነታ ይመስለኛል›› ብለው ነበር። የሎሬት ጸጋዬ ብርቱ የፈጠራ ኃይል ግን ለዚህ የጽልመት አሠራር ሳይንበረከክ በርካታ ተውኔቶችን ማፍራት ችሏል። ሳንሱር ሎሬት ጸጋዬ ቱባ ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን በመድረክ እንዳያቀርቡ እያፈነ ቢያስቀርባቸውም፤ ተስፋ አስቆርጦ ብዕራቸውን እንዲጥሉ ስላላደረጋቸው የአፈናው ዓላማ ተሳክቶለታል ለማለት አይቻልም።

በሥራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የስነ ጽሑፍ ሽልማት፣ የኢትዮጵያ የወርቅ ቀይ ኮከብ ሽልማት፣ የሃሳብ ነፃነት ሽልማት፣ የዓለም ገጣሚያን ሎሬቶች ኮንግረስ የክብር ሎሬትነት ሽልማት፣ የሜርኩሪ (Gold Mercury Ad Personam) ሽልማት፣ የፉልበራይት ከፍተኛ ፌሎውሺፕ (Fulbright Senior Scholar Resident Fellowship) ሽልማት፣ የኖርዌይ ደራሲያን ኅብረትና የኖርዌይ የባሕል ሚኒስቴር የሃሳብ ነፃነት ሽልማት፣ የማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (SEED) ሽልማት እና ሌሎች በርካታ ክብሮች ይጠቀሳሉ።

የሎሬቱ 67ኛ ዓመት ልደት ሲከበር ዋሽንግተን ዲ.ሲ ውስጥ የሎሬቱን የሕይወት ጉዞና ሥራዎቻቸውን የሚዘክር ትልቅ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። ሎሬት ፀጋዬ የብዙ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ማኅበራትና ድርጅቶች አባልም ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም አምቦ ዩኒቨርሲቲ በሎሬት ጸጋዬ ስም የተሰየመ የባህል ጥናት እና ምርምር ማዕከል ሰሞኑን አስመርቋል።

ሎሬት ፀጋዬ ከጥበባዊ እውቀታቸው ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያራምዱ የሚችሉ ሃሳቦችንም በተደጋጋሚ ሰንዝረው እንደነበር ይነገርላቸዋል። ‹‹ነገን የተሻለ ለማድረግ ካለፈው ታሪክ መማር ይበጃል፤ጥላቻ የተስፋ ጠላት በመሆኑ የተሻለ ነገን በጥላቻ ላይ መገንባት አይቻልም›› ብለው ነበር።

ከሕግ ባለቤታቸው ወይዘሮ ላቀች ቢተው ጋር ስድስት ልጆችን አፍርተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ የሆነባቸው የጤንነታቸው ሁኔታ አብዝተው ከሚወዷት አገራቸው ለይቶ ወደ አሜሪካ ሰደዳቸው። የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም አሜሪካ፣ ኒው ዮርክ ውስጥ አረፉ። አስከሬናቸው ተናግረው ወደማይሰለቹላት፤አወድሰው ወደማይጠግቧት አገራቸው መጥቶ ስርዓተ ቀብራቸው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012

 አንተነህ ቸሬ