አገራቱ የህዳሴ ግድብ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኝነታቸውን አረጋገጡ

35

አዲስ አበባ:- የህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላልና ኦፕሬሽን በተመለከተ በዋሽንግተን ዲ.ሲ የተወያዩት የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኝነታቸውን አረጋገጡ።

በአሜሪካን መንግስት ጋባዥነት በዋሽንግተን ዲ.ሲ ከትናንት በስቲያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ኦፕሬሽንን በተመለከተ በተካሄደው ውይይት ላይ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የልዑክ ቡድናቸውን ይዘው ተካፍለዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የሦስቱ አገራት ሚኒስትሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አድርገው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል:: በመግለጫቸው በግድቡ የውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ የሁሉንም ፍላጎት የሚያረካ ስምምነት ላይ ለመድረስ በትብብር እና በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ምክክሩ የአሜሪካን የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን መንቺን እና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተደረገ ሲሆን፤ ሦስቱም አገሮች እ.ኤ.አ በ2015 በካርቱም የተፈራረሙትን የመርሆዎች ስምምነት /Declarations of principles/ ተፈፃሚ ለማድረግ ተስማምተዋል። በዚህም እ.ኤ.አ እስከ ጥር 15/2020 ድረስ በውሃ ሚኒስትሮቹ አማካኝነት አራት የቴክኒክ ውይይቶችን በማድረግ ውጤት ላይ እንደርሳለን ብለዋል።

የመጀመሪያው የቴክኒክ ውይይት እ.ኤ.አ ህዳር 15/2019 በአዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል። በእነኚህ ውይይቶች ላይ የአሜሪካ መንግስት እና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት ይገኛሉ።

በተጨማሪም እ.ኤ.አ እስከ ጥር 15/2020 ድረስ ሚኒስትሮቹ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚጥሩ የገለጹ ሲሆን፤ የስምምነቱን አፈፃፀም ለመገምገምና ለመደገፍ ሁለት ስብሰባዎችን በዋሽንግተን ለማከናወን ከወዲሁ ቀጠሮ ይዘዋል።

በሌላ በኩል፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን የተካሄደው ውይይት ውጤታማ እንደሆነ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም የሶስቱ አገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች ውይይት እንዲያደርጉ መግባባት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ጠቁመዋል።

ከውይይቱ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያን ልዑክ ቡድን ይዘው ወደስፍራው ያቀኑት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሱዳንና ከግብጽ አቻዎቻቸው ጋር በመሆን በዋይት ሀውስ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተወያይተዋል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2012

ሶሎሞን በየነ