ኢትዮጵያ ጠንካራና የተሟላ ፌዴራሊዝምን ትሻለች!

23

 ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአገር ህልውና ጠንቅ ነው የሚሉ ወገኖች ‘ብሔረሰብና ቋንቋ ተኮር የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ዜጎች በጠባብ ብሔረሰባዊና ክልላዊ ማንነት ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል፡፡ የክልሉ ብሔረሰቦች ሌሎችን ዜጎችን በጥላቻ እንዲመለከቱ፤ ከዚህም አልፎ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር እንዳይንቀሳቀሱ ገድቧል፡፡

በፖለቲካ ምሁራን ውስጥ በተለይ በወጣቱ መካከል አስፈሪ ጽንፈኝነት እንዲታይ መንገድ የከፈተ ነው” ይላሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚቆሙ ወገኖች ደግሞ፤ “አሁን በሥራ ላይ ያለው ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓት በሕዝቦች መካከል አላስፈላጊ ፉክክር፤ ጥላቻና ቂም ፈጥሯል በሚል ብቻ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት አያስፈልግም ወይም ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ጠንቅ ነው” ማለት እንደማይገባ ያመለክታሉ፡፡

ፌዴራላዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አማራጭ ነው የሚሉት አካላት መነሻቸው፤ደርግን በመቃወም ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድራለን ብለው፤ ነፍጥ አንግበው፤ ጫካ ገብተው ጦርነት የገጠሙ የብሔር ተቆርቆሪ ነን ባይ ፓርቲዎችንና ግንባሮችን በማስታወስ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በወቅቱ የብሄርን ጥያቄ የመታገያ መፈክር አድርገው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ኃይሎች መነሻቸው “ነፃነት አልተሰጠንም፤ ተጨፍልቀናል፤ ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር ስልጣን ይሰጠን” የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ የእነዚህን ፓርቲዎችና ግንባሮች ጥያቄ ለመመለስ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት እውን ማድረግ የግድ በመሆኑ ሥርዓቱ ተዘርግቷል፡፡

ብሄራዊ ጥያቄን ለመመለስና ለዘመናት የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ሲባል የፌዴራሊዝም ስርዓት ህገ መንግሥታዊ ሆኖ እውን ሆኗል፡፡ አተገባበሩ ላይ ግን በተጨባጭ ክፍተት ነበረበት፡፡ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ያለው መስመር በጣም የሳሳ በመሆኑ የገዥው ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሠራር፤ አደረጃጀቶች እና አካሄዶች ወደመንግሥት ሥርዓት በመግባታቸው ክልሎች መሆን በአለበት ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አልቻሉም ነበር፡፡

ብሔር ብሔረሰብ የሚለው የፖለቲካ ጽንሰ-ሐሳብ ለአንድ ዜጋ የዘር ሐረጉ ከየትም ይሁን ከየት የአካባቢውን ቋንቋና ባሕሉን ካወቀ በክልሉ በሁሉም ጉዳዮች የመሳተፍ ዕድል የሚፈቅድ ቢሆንም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የዘር እና የብሔር ሐረግ እየተመዘዘ ጥቃት መሰንዘር እየተስተዋለ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ፌዴራሊዝም አስፈላጊ አለመሆኑ በተለያየ መልኩ እየተነገረ ነው፡፡ ነገር ግን ከፍተቱን በማስተካከልና በማረም ይበልጥ እንዲጎለበት ማድረግ እንጂ “አስፈላጊ አይደለም” ማለት ስህተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ፌዴራሊዝም ዴሞክራሲን ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲን ለመተግበር ፈቃደኝነቱ ከመንግሥት ወገን ብቻ ሳይሆን በህዝብ ውስጥም መታየት አለበት፡፡ አሁን ለተፈጠረው ችግር ምንም እንኳ ከአወቃቀሩ ጀምሮ ያለፈው ጣልቃ ገብነት፤ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩትም ጉዳዩን በፌዴራል አወቃቀር ላይ በመለጠፍ ስርዓቱ አያስፈልግም ብሎ መደምደሙ አያዋጣም፡፡ ስለሆነም በተለይ በአመለካከት ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት እና የዜጎችን ዴሞካራሲያዊ ባህል በማዳበር የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ይበልጥ አጎልብቶ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡

የፌዴራሊዝም ስርዓት አስፈላጊነቱ አያጠያያቂ ባይሆን፤ ባለፉት ጊዜያት ክፍተቶች ተስተውለዋል፡፡ ይህን “በምን መልኩ እናስተካክለው?” በሚለው ላይ መወያየት ያስፈልጋል እንጂ፤ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች የተነሳውን የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት በአንድ ጀንበር አሽቀንጥሮ መጣል አይቻልም፡፡ አይገባምም።

መፍትሔው የፌዴራል መንግሥቱ እና የክልል መንግሥታት ስልጣንና ተግባር በህግ ተቀምጦ በዚያ መሰረት እንዲሠራ ሁኔታውን ማመቻቸት ነው፡፡ ይህ ማለት ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ ከጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው፤ በተሰጣቸው ስልጣን ላይ ተመስርተው ሙሉ መብታቸውን መጠቀም ሲችሉ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ካለምንም መድሎ መብቱ ሙሉ በሙሉ ተረጋግጦ ራሱን በራሱ ስለማስተዳደሩ ሲያምን ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ በስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ተገቢ ነው፡፡

ህብረተሰቡ ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር የብሔር ማንነቱንና ኢትዮጵያዊነቱ መሳ ለመሳ መከበር አለባቸው፡፡ በክልል መብቱ ተከብሮ፤ በአገር ደረጃ በመረጠው መሪ ተወክሎ፤ የአገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆኑ ከተረጋገጠ በፌዴራላዊ ሥርዓት መተዳደሩን አጥብቆ ያስቀጥለዋል እንጂ በተለየ የጥላቻ ዓይን አይመለከተውም፡፡

ነገር ግን “የፌዴራላዊ ሥርዓት ከፋፋይ ነው በሚል ጥላቻ ብቻ” ስርዓቱን ለመቀየር ጥረት ከተደረገ ቀድሞ የነበረው የ“ተጨፍልቀናል” አስተሳሰብ አንሰራርቶ እንደገና ለዳግም ግጭት ሊዳርግ ስለሚችል የዚህ ሃሳብ ባለቤቶች ቆም ብለው ማየት የግድ ይላቸዋል፡፡

በመሆኑም፤ ህገመንግሥቱን ጨምሮ መሻሻል ያለባቸውን ህጎች በማየት፤ ህዝቡን በማሳተፍ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ አሁን ያሉ ከወሰን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በጥንቃቄ በማየት መፍትሔ በማበጀት፤ ዴሞክራሲን በትክክል በማስፈን በብዙሃን ተቀባይነት ያለውን ፌዴራሊዝም መገንባት ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ስርዓቱ የይስሙላ የስልጣን ክፍፍል ሳይሆን ጠንካራና የተሟላ ፌዴራሊዝም ሆኖ ህዝቡ “ራሴን በራሴ እያስተዳደርኩ ነው” የሚል ስሜት እስኪፈጠርበት የዘለቀ ሊሆን ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2012