የገዳ ሥርዓትን ለዓለም ያስተዋወቁ ምሁር

15

የሚታወቁት የኦሮሞ የገዳ ባህላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለዓለም በማስተዋወቃቸው ነው። የምሥራቅ አፍሪካን ባህላዊ ኩነቶች እና የህብረተሰቡን ጥንታዊ አኗኗር አብጠርጥረው እንደሚረዱ በርካቶች ይመሰክ ሩላቸዋል። ውልደታቸው በአገረ ኤርትራ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ተምረዋል። ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ቦረና ኦሮሞዎች ጋርም ያላቸው ቁርኝት የተጠናከረ ነው። ከኦሮሞዎች ጋር ግንኙታቸው የጀመረው ከአራተኛ ትውልድ ዘር ሃረጋቸው ቄስ ዘርአጽዮን ሙሴ ጀምሮ እንደነበር ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስን ወደኦሮምኛ የተረጎሙትን ኦነሲሞስ ነሲፕን ቅድመ አያታቸው ኤርትራ ውስጥ አስተም ረዋቸዋል። ይህ ግንኙነት እርሳቸውንም የገዳ ሥረዓት ላይ ጥናት እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗቸዋል። ቁጭ ብለው ሲያዳምጧቸው የሚገለጡ መጽሐፍ መሆናቸውን እርሳቸው ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት የታደሙ ምሁራን ይመሰክራሉ። እኛም ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰን ለዛሬ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን አድርገን መርጠናቸዋል። ከረጅሙ የህይወት ተሞክሯቸው ልምድ እንድትቀስሙ ጋብዘናል።

ልጅነት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ የተወለዱት በእ.ኤ.አ በ1931 (1924 ዓ.ም) ኤርትራ አሥመራ ከተማ ነው። የእናታቸው ስም ተመርፃ ዮሴፍ፤ አባታቸው ለገሰ አርአያ ይባላሉ። ከወላጆቻቸው በተጨማሪ በልጅነታቸው እንደ አባት ሆነው ያሳደጓቸው አጎታቸው ሲሆኑ፤ ግራዝማች በርኤይ ቢኪት ይባላሉ። ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር አስመሮም፤ አራት ወንድሞች እና አንድ እህት አላቸው። በአሥመራ ጥንታዊው ገዛኸኒሻ መንደር ነው ያደጉት። ልጅነታቸውን ያሳለፉት እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ በመንደራቸው ቦርቀውና ከጓደኞቻቸው ጋር ተጫውተው ነው።

በአካባቢያቸው የሚገኘው ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በወቅቱ ኤርትራን የተቆጣጠረው ጣሊያን «ማንኛውም ጥቁር እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ ነው መማር ያለበት» የሚል መመሪያ ስለነበረው እስከ አራተኛ ክፍል ተምረዋል። ነገር ግን አራተኛ ክፍልን ሲጨርሱ እንግሊዞች ኤርትራን በመያዛቸው እስከ ስድስተኛ ክፍል የመማር ዕድል አገኙ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሥመራ እንዳጠናቀቁ ያላሰቡት ክስተት አጋጠማቸው። አጎታቸው ግራዝማች በርኤይ «የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አንድነት ማህበር» የሚል የትግል ማህበር ውስጥ ገብተው ስለነበር በእንግሊዞች አማካኝነት ለእስር ተዳረጉ። በኋላም ከእስር ሲፈቱ ከነቤተሰባቸው ኤርትራ ውስጥ መቆየት እንደማይችሉ ስለተነገራቸው አጎታቸው መላ ቤሰባቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

ፕሮፌሰር አስመሮም ከመላው ቤተሰባቸው ጋር በኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ያረፉት ደሴ ከተማ ነበር። አጎታቸውም ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ትውውቃቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተቀበሏቸው እርሳቸው ናቸው። ምን መሥራት ተፈልጋለህ? ሲባሉም ገበሬ መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረው አምባሰል ላይ ቡና እንዲያመርቱ ሰፊ ቦታ ተሰጣቸው። የቡናው እርሻም ውጤታማ ሆኖላቸው ነበር። በተጨማሪ ደሴ ላይ ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን የሚል ቡና ቤት ከፍተው መሥራት ጀመሩ።

ፕሮፌሰር አስመሮም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደሴ ከተማ ብዙም አልቆዩም ነበር። ለተጨማሪ ትምህርት አዲስ አበባ መጥተው አቃቂ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገቡ። ወዲያው ተፈሪ መኮንን አዳሪ ትምህርት ቤት በመከፈቱ አዲስ አበባ መኖር ጀመሩ። አልፎ አልፎ ቤተሰቦቻቸውን ለማየት ደሴ ይሄዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ስለሚያሳልፉም ትኩረታቸው ውጤታማ መሆን ላይ ነበር። ያሰቡት ተሳክቶላቸው የወቅቱን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥተው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተቀላቀሉ። በወቅቱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ጨምሮ ከነ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረጉ ሰዎች ጋር ተምረው ተመረቁ።

ቀድሞ እንደሚደረገው ወደ ውጭ ተልኬ እማራለሁ ብለው ሲጠብቁ ያልገመቱት ነገር ገጠማቸው። አገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲ በመከፈቱ ሁሉም ተማሪ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚማር ተነገራቸው። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያዎቹ የተፈሪ መኮንን ተመራቂዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲያጠናቅቁ አገር ውስጥ የተገነባ ዩኒቨርሲቲ ባለመኖሩ ውጭ አገር መሄድ አለብን ብለው ለንጉሡ ጥያቄ ያነሳሉ። ይህንን ተከትሎ ተማሪው አመጽ እንዳያነሳ በሚል ለይስሙላ ውጭ ተላኩ እንዲባል ብቻ አብዛኛው ተማሪ ወደአፍሪካ እና እስያ መላኩን ያስታውሳሉ። ለአብነት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፑና ወደተባለ የሕንድ ዩኒቨርሲቲ ሲላኩ እርሳቸው ደግሞ ወደ ዩጋንዳው ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት መላካቸውን አይረሱትም።

ከዩጋንዳ እስከ አሜሪካ
በዩጋንዳ ታዋቂ በሆነው ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት ፕሮፌሰር አስመሮም፤ በዩኒቨርሲቲው ያለው የቅኝ ገዥዎች የትምህርት አሰጣጥ አልተመቻቸውም። ጥቁሮች አመጽ እንዳያነሱ በሚል ከታሪክ እና ከሕግ ጉዳዮች ጋር የተያዙ ትምህርቶችን እንዲማሩ አይፈቀድም ነበር። በተጨማሪም ፖለቲካል ሳይንስ እና ለአመጽ ይዳርጋሉ የሚል እምነት ያላቸውን ኮርሶች እየቆረጡ ያወጡ ነበር። ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው እንግዳችንም ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው ጉዳዩን በመቃወም ተማሪዎቹን ያስተባብሩ ነበር። ይህ ተቃውሞ እየተስፋፋ በመሄዱ አንድ ቀን የለየለት አመጽ ተነሳ።


ፕሮፌሰር አስመሮም ከህክምና ትምህርታቸው በተጓዳኝ «ኢስት አፍሪካን ስታንዳርድ» ለተባለው ጋዜጣ «ማካሬሬ አት ስታንሲል» በሚል ርዕስ የተማሪዎች አመጽ ዩኒቨርሲቲው ሥራ እንዳቆመ የሚያትት ዘገባ ጽፈው ነበር። ጋዜጣው ደግሞ በፊት ገፁ ይዞት ወጣ። በዚህ የተናደዱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትም ዩኒቨርሲቲው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ አድርገው አመጽ ያስነሱትን ተማሪዎች አባረሩ። ፕሮፌሰር አስመሮምም ከሁለት ዓመት የህክምና ትምህርት ቆይታ በኋላ ተባረው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመማር ማስተማር ትምህርት ክፍል ገቡ። በወቅቱ ግን አንድ አሜሪካዊ ጥናት ሊያዘጋጅ አዲስ አበባ ነበርና እርሳቸውም ከጓደኞቻቸው ጋር ጥናቱን አገዙት። ጥናቱ ሲጠናቀቅ አሜሪካዊው ረዳቶቹን እየጠራ «የት መማር ትፈልጋላችሁ?» እያለ ጠይቋቸው ነበርና ፕሮፌሰር አስመሮም ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሄደው መማር እንሚፈልጉ መናገራቸውን ያስታውሳሉ። ከዚያም ዕድላቸው ቀንቶ በአሜሪካዊው የድጋፍ እገዛ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲያጠናቅቁ የኢትዮጵያ መንግሥት እርሳቸውን እና የተወሰኑ ተማሪዎችን ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ ላካቸው።

በአሜሪካም የትምህርት ወጪያቸው ተሸፍኖ የመማር ማስተማር ትምህርታቸውን ጀመሩ። ከዓመት ትምህርት በኋላ ግን ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ለሁለተኛ ዲግሪ የወሰዱት ትምህርት እንደሚበቃ ገልፆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያዝ መልዕክት አስተላለፈ። ፕሮፌሰር አስመሮምና ጓደኞቻቸው ግን የዩኒቨርሲቲውን ሃሳብ አልደገፉምና የየራሳቸውን አማራጭ በመውሰድ እዛው ቆይተው ለመማር ወሰኑ።

ፕሮፌሰር አስመሮም እየተማሩ ለመሥራት ፈታኝ በሆነው ሰሜን አሜሪካ ግማሽ ቀን እየሠሩ ግማሹን ቀን ደግሞ እየተማሩ ለማሳለፍ ተገደዱ። ከቤተሰባቸው ጋር እያሉ የተለማመዱት የእንጨት ሥራ ሙያን ይተዳደሩበት ጀመር። በወቅቱም አንድ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች አቅራቢ ዘንድ ሥራ ተቀጥረው በርካታ ጨርቆችን በአንድ ጊዜ የሚቆርጥ ማሽን ላይ ሠርተዋል። ተሯሩጠው በሚያገኙት ገንዘብ አማካኝነት የትምህርት ወጪያቸውን ይሸፍኑ ነበር።

እንዲህ እንዲህ እያሉ ብርታትን ተላብሰው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀቁ። የሴሜቲክ ቋንቋ ትምህርት ለመቀጠል ቢያስቡም መምህር ባለመኖሩ የተነሳ ፊታቸውን ወደ አንትሮፖሎጂ አዞሩና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጀመሩ። የኑሮ እንግልቱ፤ ቀን ቀን ሥራው እና ውጣ ውረዱ ተዳምረው የትምህርት ጊዜያቸውን አራዘመባቸው። በዚህ ምክንያት የዶክትሬት ትምህርታቸውን ለመጨረስ አስር ዓመት እንደወሰደባቸው ያስታውሳሉ።

የገዳ ሥርዓትን ፍለጋ
ፕሮፌሰር አስመሮም የዶክትሬት ትምህርታቸው ሊጠናቀቅ ሲሉ አንድ ጥናት ማዘጋጀት ነበረባቸው። ኤርትራ ለመሄድ የተለያዩ መረጃዎችን ለአንድ ዓመት ያክል ማሰባሰብ ላይ ተጠመዱ። ኤርትራ ሄደውም የ300 ዓመት ያለውን ባህላዊ ሥርዓት ለማጥናት እንደፈለጉ ሲጠየቁ በወቅቱ ኤርትራ በውጥረት ውስጥ ነበረችና ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥናታቸውን ማካሄድ እንደሚችሉ ተነገራቸው። ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ መረጃዎችን ሲሰበስቡ ቆይተው በአሜሪካ ቤተ መጽሐፍት ያገኟቸውን የኦሮሞ ታሪክ መነሻ በማድረግ ጽሑፎችን ማዘጋጀት ጀመሩ።

በተለይ ጣሊያናዊው ቼሩሌ የተባለው ፀሐፊ ያዘጋጀው የቱለማ ኦሮሞዎችን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ በጥቂቱም ቢሆን ስለገዳ ሥርዓት ግንዛቤ ሰጥቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተማሪነት ጊዜያቸው የጥምቀት በዓል ጃንሜዳ ሄደው ያዩት የኦሮሞዎች ጭፈራ እና የፈረስ ጉግስ ውድድር ዛሬም ደረስ ከትውስታቸው አልጠፋም። በይበልጥ ደግሞ ይሰሙት የነበረው የቅድመ አያታቸውና የኦሮምኛ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚው ኦነሲሞስ ግንኙነት ታሪክ ጥናታቸውን ወደ ኦሮሚያ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል። በዚህም በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ላይ የሚያተኩር ጥናት ለማድረግ ወስነው አዲስ አበባ መጡ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት አንትሮፖሎጂን እያስተማሩ የገዳ ሥርዓት የትኛው አካባቢ ላይ በደንብ ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን መመርመራቸውን ቀጠሉ። ጅማ፣ አርሲ፣ ሸዋ፣ ጉጂና ቦረና አካባቢዎችን እየተዘዋወሩ ባህሉን ተመለከቱ። በመጨረሻ ግን የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ተጠብቆ ያለው ቦረና ውስጥ መሆኑን በመረዳታቸው ቦታው ላይ ሆነው ጥናት ለማድረግ ወሰኑ። ለጥናቱ እንዲረዳቸው ነገሌ ቦረና ላይ ቤት ተከራዩ። ታሪ ጃርሶ የተባለ ጎበዝ ረዳት ይዘው ሥራቸውን ማካሄድ ጀመሩ። አንድ ቀን ግን በነገሌ ገበያ የኦሮሞ አባገዳ እና አዱላ ሃዮ የተባሉ አመራሮች መምጣታቸውን ረዳታቸው ነገራቸው። ፕሮፌሰር አስመሮምም አባገዳዎቹን ቤታቸው ጋብዘው ዶሮ ወጥ አሰርተው ጠጅ ጋበዟቸው።

ቦረናዎች የዶሮ ሥጋ እንደማይበሉ የማያውቁት ጋባዥ በአባ ገዳዎቹ ቀልድ እየተሰነዘረባቸው ዛሬም ድረስ አልዘነጉትም። እርሳቸው ግን አጥብቀው ስለገዳ ሥርዓት ከዋና ባለቤቶቹ ይጠይቃሉ። በኋላ አባገዳው ሁሉንም የገዳ ሥርዓት ማወቅ ከፈለጉ ኦላ አርቦሬ የተባለው የቦረና መንደርን ማየት እንደሚችሉ ገለፁላቸው። እንዲሄዱም ጋበዟቸው። ግብዣውን በደስታ የተቀበሉት ፕሮፌሰር አስመሮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከራዩትን ላንድሮቨር ተሽከርካሪ ይዘው ጉዞ ወደ ተባሉት ቦታ አደረጉ።

አባገዳው በሰጧቸው ሁለት ረዳቶች አማካኝነት መንገድ እየተመነጠረ አንድ ቀን ሙሉ በፈጀ ጉዞ መንደሯ ደረሱ። ከምንጩ የሚቀዳውን የገዳ ሥርዓትን ለማጥናት ድንኳን ተክለው መኖር ጀመሩ። እያንዳንዱን የገዳ ስብሰባ እና የህዝቡን አኗኗርም እያጠኑ ሁለት ዓመት ቆዩ። በእርግጥ አልፎ አልፎ ወደ አዲስ አበባ ቢመላለሱም ልባቸው ግን ድንኳኗ በተተከለችበት መንደር ውስጥ ሆና የገዳ ሥርዓትን ውስጠ ምሥጢሩን እየፈተሸች ነበር። እስከ ኬንያ ድረስ በመዝለቅ የቦረና ኦሮሞዎችን ሥርዓት መርምረዋል። ጥናት ሲያከናውኑም እንደ አንድ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባል የሚጠበቅባቸውን የገዳ ሥርዓት ክንውኖች ይፈጽሙ እንደነበር ይናገራሉ።

የመጽሐፍ አበርክቶዎች
ጥናታቸውን አገባደው ተመልሰው ወደ አሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። «ገዳ- የአፍሪካ ማህበረሰብ ለማጥናት በሦስት የጥናት እይታዎች ወይም በእንግሊዝኛው «Gada: three approaches to the study of African society» የሚል ባለ 340 ገጽ የተሰናዳ መጽሐፍ አሳተሙ። በጊዜው የገዳ ሥርዓት በዓለም ዘንድ እንዲታወቅ ያደረገ መጽሐፍ በመሆኑ በርካቶች አድናቆታቸውን ችረዋቸዋል። የገዳ ሥርዓት ከእንግሊዞች፣ ከፈረንሳዮችና አሜሪካኖች የምርምር ዕይታ አንፃር በመገምገማቸው በብዛት መጽሐፉን ያነቡ የነበሩ የአንትሮፖሎጂ ፍላጎት ያላቸው አጥኚዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

መጽሐፉ የተወሰኑ መረጃዎች ታክለውበት ዳግም ለማሳተም ዛሬም እየታተሩ ይገኛሉ። ከአንድ ወር በኋላም መጽሐፉ ኢትዮጵያ ደርሶ በአማርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለአንባቢያን እንደሚደረስ ተስፋ አላቸው። የጀመሩት የኦሮሞ ጥናት ግን በአንድ የመጽሐፍ ሥራ ብቻ ሊያስቆማቸው አልቻለም። ከመጀመሪያው መጽሐፋቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የኦሮሞ ባህል እምነትና የገዳ ሥርዓት አዋቂ የሆኑትን ቦርቦር ቡሌን ለአንድ ወር ያህል ቃለመጠይቅ አድርገውላቸዋል። ከዚያም ቃለመጠይቁን ከእራሳቸው ጥናት እና እውቀት ጋር አስተባብረው «ኦሮሞ ዴሞክራሲ አገር በቀል የአፍሪካውያን ፖለቲካል ሥርዓት /OROMO DEMOCRACY: An Indigenous African Political System» የሚል የእንግሊዘኛ መጽሐፍ አሳተሙ።

አሁንም በዚህ ያልተገደቡት ፕሮፌሰር አስመሮም፤ በየወቅቱ በሚዘጋጁ የአንትሮፖሎጂ የምርምር መጽሄቶች ላይ ስለኢትዮጵያ እና ኬንያ ኦሮሞዎች በርካታ ጽሁፎችን ለአንባቢ አደረሱ። አሁንም ድረስ እጃቸው ላይ ህትመትን የሚጠበቁ ጽሁፎችም አሏቸው። ኬኒያ ውስጥ የሚገኙት የጋብራ እና የቦረና ኦሮሞዎች ላይ ያተኮረው «A pastoral Eco System» የተሰኘ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ያተኮረ የዕፅዋት ምርምር ጥናታዊ መጽሐፍ ለማሳተም ዝግጅት ላይ ናቸው።

የገዳ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ ቃላትንም የያዘ ባለ15 ገጽ መዝገበ ቃላት አዘጋጅተዋል። በቀጣይ ጊዜያት ስለ ኦሮሞ፣ ኩሽ ሕዝቦች እና ሱዳን ውስጥ የሚገኙትን ሜሮይ ዝምድና ለማጥነት ፍላጎት አላቸው። በተለይ በገዳዎች ዘንድ የሚደረገው «በከልቻ» የተሰኘው የግንባር ምልክት ሜሮይና ኩሽ ሕዝቦች ጋር መኖሩ እንዲሁም ሌሎች ዝምድናዎች ጥናታቸውን እንዲገፉበት እያነሳሳቸው መሆኑን ይገልፃሉ። በምሥራቅ አፍሪካ ሕዝብ እና ባህል የሚያተኩሩ የጥናት መጽሐፍትን እንደሚያሳትሙም አጫውተውናል።

«የኦሮሞን ታሪክ እና ገዳ ሥርዓት በማጥናቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ» የሚሉት ፕሮፌሰር አስመሮም፤ የኤርትራን ባህል ባጠና ለመመረቂያ የሚሆን ጽሁፍ ብቻ አዘጋጅቼ አቆም ነበር። ይሁንና የኦሮሞ ታሪክ ዕድሜ ልክ የሚጠና የማያልቅ ማዕድን ነው። በመሆኑም ስለ ኦሮሞዎች ነገም ዛሬም እጽፋለሁ ሲሉ ፍቅራቸውን ይገልፃሉ። አሁንም በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እየተዘዋወሩ የጥናታቸውን ውጤት ለማካፈል አቅደዋል።

ሦስቱ ትዳሮች
ፕሮፌሰር አስመሮም 1952 ዓ.ም መጀመሪያ አዲስ አበባ ለገዳ ሥርዓት ጥናት ላይ ሳሉ ከአንዲት አሜሪካዊት ጋር ይተዋወቃሉ። እንስቷ የጥቁር እና ፊሊፒንስ ዝርያ ቅልቅል ስትሆን ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነበር። በቁንጅናዋ ደግሞ ብዙዎች ተማርከውባታል። የመሳፍንት ልጆች ሳይቀሩ ልጅቷን ለፍቅር ቀርበዋት ነበር። የገዳ አጥኚው ግን ትውውቃቸውን በጊዜ አጠናክረው የግላቸው አደረጓት። ለበጎ ፍቃድ ሥራ ወደ ተመደበችበት ጅማ ከተማ ይዘዋት ሄደው ከመሳፍንት ልጆች እና አይናቸውን ከጣሉባት ሰዎች ገለል አደረጓት።

የኋላ ኋላ ሥራዋን ጨርሳ አሜሪካ ትሄዳለች። ፕሮፌሰር አስመሮም ርቀት ሳይገድባቸው ፍቅራቸውን ለመቀጠል መልዕክት መላላኩን አጠናከሩት። በመጨረሻም ከአሜሪካ መጥታ እንዲጋቡ ጥያቄ ሲያቀርቡላት ፍቃደኛ ሆና ኢትዮጵያ መጣች። የመጀመሪያው ጋብቻ ያማረ ቢሆንም የዘለቀው ግን ለ12 ዓመታት ነው። ምክንያቱም አሜሪካዊቷ ወደ አገሯ ሄዳ ለመቆየት በመፈለጓ እየተራራቁ መጡ፤ መገናኘቱ ሲቀንስም በዚያው ተለያዩ።

ሌላኛው ትዳር የተገኘው ደግሞ ከአድናቆት በኋላ ነው። የገዳ ታሪክ የያዘውን መጽሐፋቸውን ያነበቡት ሣራ አማኑኤል ከተባሉ ኢትዮጵያዊት የእንግሊዝ አገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ነበር የተዋወቁት። ፕሮፌሰር አስመሮም በወቅቱ የአዲስ አበባን ህዝብ ቁጥርና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማጥናት ከጓደኞቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ከትመዋል። እንስቷም አዲስ አበባ የሚገኘውን የመጽሐፉን አዘጋጅ እንዲያስተዋውቋቸው ይጠይቃሉ። በዚህም ከወጣቷ ሣራ ጋር ተዋውቀው አንዳንድ ጉዳዮችን ስለመጽሐፉ ማውራት ጀመሩ።

ከትውውቁ በኋላ ፍቅራቸው በመፅናቱ በየጊዜው መገናኘታቸውን ቀጠሉ። ጊዜው ደርግ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የተቃረበበት በመሆኑ ነገሩ ያላማራቸው ፕሮፌሰር አስመሮም የፍቅር አጋራቸውን ሣራን ወደ አሜሪካ አስቀድመው ላኳቸው። ደርግ ሙሉ ለሙሉ ሥልጣኑን ከአፄ ኃይለሥላሴ ሲረከብ ደግሞ እርሳቸውም አሜሪካ ሄደው ከሣራ ጋር ትዳር መስርተው መኖር ጀመሩ። በወቅቱ ግን በኬንያ አድርገው የቦረናን ታሪክ እያጠኑ ወደ አሜሪካ ይመላለሱ ነበር።

ኤርትራ በጊዜው ነፃ ለመውጣት ትግል ላይ ነበረች። እናም አንድ ቀን ያገኟቸው ኤርትራውያን በዘዴ ትግሉን እንዲቀላቀሉ አስበው በሱዳን አድርገው ኤርትራን እና ተዋጊዎቿን እንዲጎበኙ ያደርጋሉ። ተዋጊዎቹን ጎብኝተው የተመለሱት ፕሮፌሰር አስመሮም ከዚህ በኋላ ሙሉ ትኩረታቸውን ወደትግሉ አዞሩ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ሣራ አማኑኤል ደግሞ አባታቸው አማኑኤል አብርሃም በንጉሡ ዘመን አምባሳደርነት የተሾሙ እና እርሳቸውም ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ቅርበት ያላቸው ሰው በመሆናቸው የንጉሣዊ ሥርዓት በጽኑ ስለሚደግፉ የባለቤታቸውን የትግል ስልት አልወደዱትም። በዚህ ምክንያትም የኤርትራን ትግል ከሚደግፉት ፕሮፌሰር አስመሮም ጋር ተጣሉ፤ ትዳሩም በዚያው ፈረሰ።

በመጨረሻ ግን ፕሮፌሰሩ በተወለዱባት አሥመራ ከተማ መኖር ሲጀምሩ ብቸኝነታቸውን የተረዱት ቤተሰቦቻቸው ከአንዲት ሴት ጋር አስተዋወቋቸው። በ1988 ዓ.ም ቤታቸው መጥታ ከተዋወቀቻቸው ቆንጆ ሴት ጋር ትዳር መሰረቱ። እስከ አሁን ድረስ በዚህ ትዳር ውስጥ ናቸው። የመጨረሻው ትዳር ሁለት ሴት ልጆችን ሰጥቷቸዋል። ልጆቻቸው ኤልሳቤት እና ሣራ ይባላሉ። የ87 ዓመቱ አዛውንት ፕሮፌሰር አስመሮም አሁን ላይ በፍጥነት መራመድ እና ባሻቸው ጊዜ መንቀሳቀስ ባይችሉም ገና ብዙ ጥናቶችን እንደሚሠሩ ይናገራሉ። ያገኙትን መረጃም በመሰብሰብ ሰንደው ይይዛሉ። ምክንያቱም አንድ ቀን ለጥናቴ ይጠቅመኛል የሚል ዕምነት ስላላቸው ነው።

የህይወት ስኬቶች
ፕሮፌሰር አስመሮም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በአሜሪካ «ስወርት ሞር ኮሌጅ» የአንትሮፖሎጂ የዕውቀት አባት ሆነው አገልግለዋል። ኖርዝ ዌስተርን ቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ ደግሞ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግን አግኝተዋል። ሆላንድ አገር በሚገኘው ኢንስቲትዩት ኦፍ አፍሪካን ስተዲስ በርካታ ተማሪዎችን አፍርተዋል። ሙሉ ፕሮፌሰርነትን ያገኙት ደግሞ ቀድሞ ያስተምሩበት በነበረው ስዋርት ሞር ኮሌጅ ተመልሰው በገቡበት ወቅት ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ስለኢትዮጵያ ባደረጉት ጥናትና ምርምር ዘንድሮ የክብር ዶክትሬት አበርክቶላቸዋል። አሁን ፕሮፌሰር አስመሮም በግላቸው ጥናቶችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በበርካታ መድረኮች ላይ ስለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባህላዊ ሥርዓቶች እንዲሁም በአጠቃላይ ስለ ምሥራቅ አፈሪካ ባህል ትንተና በመስጠት ይታወቃሉ። በርካታ ቋንቋዎችንም ይናገራሉ። ኤርትራ እያሉ ቫዮሊን በሚማሩበት ወቅት ጣሊያንኛን በሚገባ አውቀዋል። ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ደግሞ ፈረንሳይኛንና እንግሊዘኛን ተምረዋል።
አማርኛ እና ትግረኛውን ደግሞ ከኤርትራ ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ድረስ በማህበረሰቡ ውስጥ ሆነው በመማራቸው መናገርም ሆነ መፃፍ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጀርመንኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎችንም ይግባቡባቸዋል።

መልዕክት
ፕሮፌሰር አስመሮም «ማንኛውም ማህበረሰብ የእራሱ የሆነ ማንነትን ሊይዝ ይገባዋል» የሚል ዕምነት አላቸው። እንደ እርሳቸው አባባል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተውሶ ከመጣ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው። የእንግሊዞች ሕግ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከእራሳቸው ባህል የተቀዳ ነው። የፈረንሳዮቹም በተመሳሳይ፤ እያንዳንዱ የአውሮፓ አገር የህዝቡን ማንነት እና ባህል የያዘ አወቃቀር አለው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን የሚንድ አካል ሲመጣ ህዝቡ የእኔነት ስሜት ስላለው መንግሥት ቢኖርም ባይኖርም ይጠብቀዋል።

የኢትዮጵያ የፓርላማ ሥርዓቱ ከእንግሊዝ የተዋሰ፤ የሕግ ሥርዓቱ ደግሞ ከፈረንሳይ ሲቪል ኮድ የተቀዳ ነው። ይህ በመሆኑ በዜጎች ዘንድ ሥርዓቱ ላይ የእኔነት ስሜት ሊኖር አይችልም። ለዚህ ደግሞ በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት፣ በአማራ የዕርስት እና የተለያዩ ባህሎች በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች አሉና የሚበጀው ይህንን ማበልፀግ እንደሆነ ይመክራሉ። ኢትዮጵያም የሁሉንም ብሔሮች ባህል ባማከለ ሁኔታ የራሷን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማነፅ አለባት ይላሉ።

አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011

ጌትነት ተስፋማርያም