ጥበብ ሌላ! ዝና ሌላ!

26

‹‹ፌስቡክ›› የተባለው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ አንድ ሙዚቃ ላይ ጣለኝ፡፡ የመገናኛ ዘዴው የአንዲት እንስት ፎቶ ጨምሮ ‹‹ፍላጎት›› የሚል የአማርኛ ጽሑፍ ያለው አገናኝ (Link) ሰጠኝ፡፡ የሰጠኝን አገናኝ (Link) ስከፍት ወደ ‹‹ዩ ትዩብ›› መራኝና ረጋ ያለ፣ የዘመኑን ዓይነት አለባበስ ያልሆነ ዘፈንና ዘፋኝ አገኘሁ፡፡ ዘፋኟን ለማወቅ ብሞክርም ላውቃት አልቻልኩም፡፡ ‹‹ይሄ የኔ ችግር ይሆናል እንጂ የዚህ ዘፈን ባለቤትማ ታዋቂ መሆኗ አይቀርም›› ብዬ ሌሎች ሰዎችን መጠየቅ ጀምርኩ፡፡ የጠበቅኩትን ያህል የሚያውቃት ሰው አላገኘሁም፡፡ ቃለ መጠየቅ ያደረገችባቸው የመገናኛ ብዙኃን ካሉ ብዬ በይነ መረብ ላይ በስሟ መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ምንም ላገኝ አልቻልኩም፡፡

ወዲያውም ሌላ ነገር አሰብኩ፡፡ ለካ ዘመኑ እንዲህ ዓይነት ዘፈን የሚፈለግበት አይደለም፡፡ ጭን እና ጡት የተገላለጠበት፤ ጉራማይሌ ቋንቋ የተቀላቀለበት እንጂ የዚህ ዓይነት በሙሉ ልብስ የተለበሰ ዘፈን ትኩረት አያገኝም በሚል ገመትኩ፡፡ ባህል ነክ በሆኑ ውይይቶች ሁሉም ‹‹በውጭ ባህል ተወረርን›› ከሚል ጉንጭ አልፋ ወቀሳ በስተቀር ለእንዲህ ዓይነት ሰዎች ምንም ሲያደርሱ አይስተዋሉም፡፡

የመገናኛ ብዙኃንም ቢሆን እነዚያኑ የውጭ ፋሽን ተከታዮችን ካሉበት አፈላልገው ያቀርባሉ እንጂ ጀማሪ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ማቅረብ ለመገናኛ ብዙኃን ሽፋን የሚበቃ አይመስላቸውም፡፡ በዚያ ላይ ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እስከ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ስለተወጠሩ የኪነ ጥበብ ነገር ትኩረት የተነፈገ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለዚች ዘፋኝም ለማወቅ ባስስ ላገኝ አልቻልኩምና ራሷን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ በአንድ የኪነ ጥበብ ሰው ጠቋሚነት ስልኳን አገኘሁና ደወልኩላት፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አጠገብ ተገናኘንና አወራን፡፡ ድምፃዊት ሰላማዊት አብተው እና የሙዚቃ ሕይወቷ የሚከተለው ነው፡፡

አስተዳደግ እና ሙዚቃ
ተወልዳ ያደገችው በድሬዳዋ ከተማ ነው፡፡ ሰላማዊት ከልጅነቷ የቤተ ክርስቲያን ዘማሪ ነበረች፡፡ በዓለማዊው ትምህርት ደግሞ በሆቴል ማኔጅመንት ተመርቃለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት የነበረው የሙዚቃ ፍቅር ግን የተመረቀችበትን የትምህርት ክፍል ብዙም እንድትሄድበት አላደረጋትም፡፡ ቢሆንም ግን ትንሽ ጊዜ ሠርታበታለች፡፡

ሰላማዊት ያደገችው ከአያቷ ጋር ነው፡፡ ታዲያ ይሄ በብዙ ዘፋኞች ዘንድ ‹‹አንቺ አዝማሪ!›› የሚለው የቤተሰብ ስድብ ሲያልፍም አልነካት፤ ኧረ እንዲያውም አያቷ የውጭ ሙዚቃዎችን ይሰሙ ነበር፡፡ ከአገር ውስጥም እነ ክቡር ዶክተር ዓሊ ቢራንና ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠን ይወዱ ነበር፡፡ ይሄ የአያቷ የሙዚቃ ፍቅር ታዲያ ሰላማዊትንም ወደ ሙዚቃው የመገፋፋት ዕድል ነበረው፡፡ በዚያ ላይ ድሬዳዋ ውስጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ነፃ አስተሳሰብ ያለው መሆኑ ደግሞ ሙዚቃን የሚያበረታታ እንጂ የሚነቅፍባት አልነበረም፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ ‹‹በሚኒሚዲያ›› ትዘፍን ነበር፡፡

ሰላማዊት ከሴት ዘፋኞች ይልቅ የወንድ ዘፋኞችን ዘፈን ነበር የምትዘፍነው፤ ምክንያቱም በልጅነቷ ድምጿም ወፍራም ነበር፡፡ የነ ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠን፣ ምኒልክ ወስናቸውን፣ ቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈን እየዘፈነች ነው ያደገች፡፡ ከውጭ ዘፋኞችም የቦብማርሌን ዘፈን ትዘፍን ነበር፡፡
እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ እዚያው ድሬዳዋ የተማረችው ሰላማዊት በ1998 ዓ.ም ቤተሰቦቿ ጋ አዲስ አበባ መጣች፡፡ አዲስ አበባም ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች፡፡

ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርቷን እስከጨረሰችበት ድረስ የሙዚቃ ፍቅሩ አብሯት አለ፡፡ የምታነባቸውን ነገሮች ሁሉ በዜማ ነበር የምታጠናው፤ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉም ትዘፍናለች፡፡
ሙዚቃ ተጀመረ
በሆቴል ማኔጅመንት የተመረቀችው ሰላማዊት በዚሁ ሙያዋ እየሠራች ነው፡፡ ከልጅነት ጀምሮ አብሯት የነበረው የሙዚቃ ፍቅር ግን አሁንም አለ፡፡ ነገሩን ስመር ሲለው እንዲህ ሆነ፡፡ በ2008 ዓ.ም አንድ ዕለት እንደተለመደው ለጸሎት ወደ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ትሄዳለች፡፡ እዚያም ከዜማና ግጥም ደራሲው ብርሃኑ ታደሰ ጋር ትገናኛለች፡፡ ብርሃኑም ጊታር ነበረው፤ የሙዚቃ ግጥምና ዜማ እንደሚሠራም አወሩ፡፡ እርሷ ደግሞ ዘፈን እንደምትችል በጨዋታ ላይ ጨዋታ ተጨመረ፡፡ ብርሃኑም ያዘጋጀው ዜማና ግጥም ስለነበረው በሆነች ወረቀት የተጻፈች ግጥም ሰጣትና ዘፈነቻት፡፡ እውነትም ዘፋኝ እንደሆነችና ወደ ሙዚቃው መግባት እንዳለባት ነገራት፡፡ ዳሩ ግን ይሄን ሁሉ ተባብለው ለአንድ ዓመት ያህል ተጠፋፉ፡፡

እንዲያው ተቀብረህ አትቅር ያለው ድምፅ ከአንድ ዓመት በኋላ ተገናኙ፡፡ የተገናኙትም ‹‹ከዚህ በኋላ ሙሉ ጊዜዬን ለሙዚቃ ነው መስጠት ያለብኝ›› ብላ በመወሰኗ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሥራዋ ሙዚቃው ላይ ብቻ ሆነ፡፡ በየጊዜው ልምምድ ታደርጋለች፡፡ ከምትሠራቸው ዜማዎችም አንዱን ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ ‹‹ፍላጎት›› የተሰኘው ነጠላ ዜማ በ‹‹አድማስ ቲዩብ›› አማካኝነት ለአድማጭ ተመልካች ደረሰ፡፡ አንድ ስለድሬዳዋ አንድ ደግሞ ለሰኔ 16ቱ የዶክተር ዓብይ የድጋፍ ሰልፍ የተዘፈኑ ለቲዩብ ያልተሸጡ ሁለት ዜማዎችም አሏት፡፡

የአገር ባህልን መጠበቅ
ሰላማዊት በቲዩብ የተሸጠና የታየ አንድ ሙዚቃ ነው ያላት፡፡ በዚህ ሙዚቃ ብቻ ሙሉ በሙሉ የአገር ባህል ጠባቂ ናት ማለት አያስችልም፡፡ የሆነው ሆኖ ግን በህዝብ ዘንድ ቶሎ ተቀባይነትን ለማግኘት በአንድ ሙዚቃም ቢሆን እንደ ብዙዎቹ የዘመኑ ዘፈኖች የተደበላለቀና የተራቆተ ማድረግ ትችል ነበር፡፡ በብዙ ወጣቶች ዘንድ ይወደዳል ተብሎ የሚታሰበውም እዚያም እዚያም የሚረግጥና የሴት ልጅ ገላ ተገላልጦ የሚታይበት ዘፈን ነው፡፡ ሰላማዊት ለጊዜው ይህን አላደረገችም፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጽ ዘፈን አልዘፍንም›› የምትለው ሰላማዊት አገራዊ ይዘት የሌለው በጣም ብዙ ዘፈን ስላለ ለየት ያለ መሆን እንዳለበት ታምናለች፡፡ ‹‹ፍላጎት›› የተሰኘው ዘፈኗ ላይም የሚታየው ረጋ ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ፈልጋው ያደረገችው ነው፡፡
የዘፈን ሽያጭ
የሰላማዊት ዘፈን ለአድማስ ቲዩብ ተሰጥቷል፡፡ እሷ እንደምትለው ሽያጭ ማለት ይከብዳል፤ ምክንያቱም እስከአሁን ምንም ገንዘብ አልተከፈላትም፡፡ የግጥምና ዜማ ደራሲዋ ብርሃኑ ታደሰም ምንም ነገር አልተከፈለውም፡፡ የልጅቷን ብቃት ስላወቀ መቸም ቢሆን አገኘዋለሁ በሚል ነው፡፡ ሙዚቃዋን የገዛት (ገንዘብ ባይረካከቡም) አድማስ ቲዩብ ደግሞ ከአራት ወር በኋላ ሊከፍላት ውል አላቸው፡፡ ውላቸው አሁን አራት ወር ስላልሞላው አልከፈለም ለማለትም ‹‹ይከብደኛል›› ትላለች፡፡ የሆነው ሆኖ ግን አንድ ነገር ግራ ይገባታል፡፡ ‹‹ለአማተር ዘፋኞች እጅ በእጅ አይከፍል ይሆን?›› እያለች ትጠይቃለች፡፡ ክፍያው ለምን ከአራት ወር በኋላ እንደተባለ ለእሷም ግልጽ አልሆነላትም።
ደግነቱ ሌላ ተስፋ ደግሞ አጋጥሟታል፤ ኤሊያስ ጥላሁን የተባለ አሜሪካ የሚኖር አንድ ሰው ዘፈኗን ሰምቶ ‹‹የራስሽ ትዩብ ነው የምከፍትልሽ›› ብሏታል፡፡ አሁን ከሰውየው ጋር እየተነጋገሩ ነው፡፡

የአልበም ዝግጅት
ሰላማዊት ሙሉ አልበም ሠርታ ጨርሳለች፡፡ ዳሩ ግን በገንዘብ እጦት አልበሙ አልታተመም፡፡ ለአቀናባሪ የመቶ ሺህ ብር ውል አላት፡፡ ይህ መቶ ሺህ ብር ከተከፈለ ነው መታተም የሚችለው፡፡ የማሳተሚያ ደግሞ ሌላኛው ወጪ ነው፤ የቪዲዮም እንደዚሁ፤ እነዚህን ወጪዎች መሸፈን ባለመቻሏ አልበሙ ተጠናቆ ተቀምጧል፡፡

የሰላማዊት አልበም አሳታሚ አጥቶ የተቀመጠው አማተር ስለሆነች ነው፡፡ ታዋቂ ብትሆን ኖሮ ምናልባትም የሚያግዛት አታጣም ነበር፤ ገንዘብም አታጣም ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዘፈኗ የዘመኑ ፋሽን ናቸው የሚባሉት ዓይነት ቢሆን ምናልባትም ደጋፊ ያገኝ ነበር፡፡ እሷ ደግሞ ‹‹ተቀምጦ ይቅር እንጂ ሰውነቴን አጋልጨ አልዘፍንም!›› ብላለች፡፡ ይሄ ትክክለኛ የጥበብ ባህሪ ነው፡፡ መንጋው የሚፈልገውን ሳይሆን ጥበብ የሚፈልገውን ወይም ስሜት ያዘዘውን ብቻ መሥራት፡፡

በነገራችን ላይ ‹‹የአገራችንን ወግና ባህል ያበላሹ ናቸው›› የሚባሉት ዘፋኞች ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛሉ (ከሙዚቃ ሽያጭ ይሁን ከምን ባይታወቅም)፤ አብዛኞቹም ከአገር ውስጥ ይልቅ በውጭ ለመኖር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ፈረንጅ የሚፈልገውን ሁሉ ስለሚያደርጉ እየታገዙም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰላማዊት የያዘችው አቋም የሚቀጥል ከሆነ የምርም የጥበብ ሰው ናት፤ ጥበብ ተደብቃ አትቀርምና የሰላማዊት አልበም ዕድል አግኝቶ ይሰራጭ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011

ዋለልኝ አየለ