ከፋይናንስ ግብረ ኃይሉ የ‹‹ጥቁር መዝገብ›› መውጣት ትሩፋት

16

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ኃይል Financial Action Task Force፣ ውልደት እኤአ 1989 የቡድን ሰባት አባል አገራት ጉባኤ በፈረንሳይ ፓሪስ ሲካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ ይስተዋል የነበረበውን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመፋለም፡፡

ግብረ ኃይሉ እኤአ የተለያዩ 40 ምክረ ሃሳቦችን በማውጣት የሀገራትን ሁኔታ በየጊዜው የሚገመግም ሲሆን እኤአ በ2001 ደግሞ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር በመጨምሮ ተግባሩን ከፍ አድርጎታል፡፡

በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የፋይናንስ አንቀሳቃሽ የሆኑ 39 አገራትን በአባልነት ያካተተው ግብረ ኃይሉ፣ ምክረ ሃሳቦችን ለማስፈፀምም ወንጀሉን በመከላከል ረገድ ደካማ የሆኑ አገራትን በጥቁር መዝገቡ ውስጥ ያካትታል። ኢትዮጵያም ተቋሙ ካስቀመጣቸው ምክረ-ሃሳቦች አንፃር ጉልህ ክፍተት እንዳለባት በመታመኑ ስሟ እኤአ ከ2011 ጀምሮ በዝርዝር ውስጥ ተካቶ ለዓመታት በተቃሙ ድረ- ገፅ ላይ ሰፍሮ ቆይቷል፡፡

ይሁንና ግብረ ኃይሉ አገሪቱ ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስርዓቷን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻለች ስለመሆኗ በማጋገጥ ‹‹ከጥቁር መዝገቡ›› እንዳስወጣት ከቀናት በፊት አሳውቋል። ለመሆኑ የዚህ ውሳኔ ትሩፋት ምን ይሆን፣ ቀጣይ ተግባራትስ በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለያዩ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ከአስተያት ሰጪዎቹ አንዱ ናቸው፡፡

አቶ ዘመዴነህ እንደሚገልጸት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ ደህንነትን ለማስጠበቅ በርካታ ህጎች አሉ፡፡ በተለይ የአውሮፓ ህብረትና ዩናይትድ እስቴትስ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር በጣም ጠንካራ ህጎችን አርቀዋል፡፡ እኤአ ከ2001 የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት በኋላ ዩናይትድ እስቴትስ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ለመከላከል ጠንካራ ህግ አውጥታለች፡፡

ይህን ህግ ተግባራዊ በማድረግ ረገድም በአሁን ወቅት ማናቸውም ባንኮች ለአንድ ደንበኛ የሒሳብ ቁጥር ከመክፈታቸው አስቀድሞ ከግለሰብ እስከ ኩባንያ ድረስ ደንበኞቻቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያስገድድ ህግ አለ›› የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣ አንድ አገር በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት፣ ሽብርተኝነትንና በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር፣ ደካም ከሆነ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር በትብብር ለመሥራት እንደሚቸገር ያስረዳሉ፡፡

የዓለም የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በእጅጉ በተሳሰረበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በዝርዝር ውስጥ መሆኗ ሌሎቹ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውንም ሆነ የሚወጣውን ገንዘብ ለመቀበል እንዲያመነቱ እንደሚያደርጋቸው የሚያስረዱት አቶ ዘመዴነህ፣ በመስል የፋይናንስ ደህንነት ህጎች ሰለባ ከሆኑ አገራት መካከል በአሜሪካን መንግሥት በተጣለባት ገደብ ኢኮኖሚዋ የታነቀባት ኢራንን መመልከት በቂ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በመሰል ዝርዝሮች ውስጥ መግባት በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጥቁር ጠባሳ በማሳረፍ ረገድ በተለይ ባለሀብቶች በኢንቨስትመን ለመሰማራት እምነት እንዳይኖራቸው፣ ቱሪስቶች ገንዘባቸውን እንደፈለጉ ለመገልገልም ሆነ አጠቃላይ በመንግሥት እንቅስቃሴ ላይ ከባድ ራስ ምታት እንደሚፈጥር ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹አገሪቱ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወንጀሉን ለመከላከል ተቃማዊ በሆነ መልኩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የቁጥጥር ተግባራት ማከናወኗንም በመገምገግ ከጥቁር መዝገቡ እንድትወጣ መደረጉም ሁለንተናዊ ፋይዳው የላቀ ነው›› ይላሉ፡፡

በተለይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት የሚኖረው ድጋፍ ከፍተኛ እንደመሆኑ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ኢንቨስተሮች፣መልካም የሚባል ዜና ስለመሆኑ አፅንኦት የሚሰጡት አቶ ዘመዴነህ፣ የአገሪቱ ባንኮች ከድንበር ተሻጋሪ ባንኮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቀየር አጋርነታቸውን እንደሚያጎለብተው ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከጥቁር መዝገብ መውጣት ማለት ለአንዴና መጨረሻ ጊዜ ሁሉም ፋይል ተዘጋ ማለት አለመሆኑን መረዳት የግድ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ግብር ኃይሉ የአገሪቱን ሁኔታ ሁሌም መከታተሉን እንደማያቋረጥ በመገንዘብ ወንጀሉን መከላከልን መቆጣጠር ተግባር ይበልጡን ማጠናከር ይገባል ነውም›› ያሉት፡፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ መምህር ረዳት ፕሮፈሰር ብርሃኑ ደኑ፣ የፋይናንስ ደህንነትን ማረጋገጥ አለመቻል የሚፈጥረው ከባድ ራስ ምታት ከአገር እስከ ህዝብ አለፍ ሲልም እስከ ግለሰብ የሚዘልቅ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡

ከጥቁር መዝገብ መነሳትም ሌሎች አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ቁጥጥርና ክትትል እንዲያነሱ በማድረግ በተለይ የአገርን መልካም ስም በማጉላትና ለኢኮኖሚያው የሚያበረክተው ፋይዳው የላቃ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በተለይ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ ያለ ጥርጥር እንዲገቡ የሀገሪቱ ባለሀብቶች በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች ያለጥርጣሬ እንዲታዩ እንደሚያግዝ ይስማሙበታል፡፡

‹‹ይህ ሲሆን መሰል መልካም ውጤቶችን ማስቀጠል ግዴታ መሆኑን መረዳት ነጋሪ አያሻውም›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ስምን መልካም ስም ማስጠራት በሌሎች ዘንድ የሚፈጥረው አዎንታዊ ትሩፋት ለመቋደስ ጥቁር ስሞችን ማፅዳት የተበላሸ ማስተካከል ግድ ስለመሆኑ ነው ያሰመሩበት፡፡

መሰል የኢኮኖሚ እድገት ማነቆዎችን በማስወገድ ረገድ ለውጭ ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥ የቤት ሥራዎችም ትኩረት መስጠት ግድ መሆኑን ሳያስገነዝቡ የማይልፉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ለአብነትም የውስጥ የገንዘብ አያያዝ፣ ታክስ አከፋፈልንና አሰባሰብ በአግባቡ መፈተሽ ይገባል ነው›› ያሉት፡፡

ምንም እንኳን በመንግሥት ከፍተኛ ጥረት ህገወጥነቱ በተደጋጋሚ ሲጋለጥ ቢስተዋም በአሁን ወቅት የሚስተዋለው ከፍተኛ የኮንትሮባንድ በተለይ ገንዘብ ዝውውርም ወንጀሉን የመከላከሉ ተግባር የግድ መጠናከር እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ ናቸው፡፡

ኢንቨስተሮች መዋእለ ነዋያቸውን ለማፍሰሳቸው አስቀድሞ አንድን አገር ከሌላው የሚያነፃፀሩ እንደመሆኑ ውሳኔው ኢኮኖሚን በማነቃቃት የሚንጫወተው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚስማሙበት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ይሁንና ኢንቨስትመንት ለማበራታታት የውጭ ባንኮችን ወደ አገር መጋበዝን የመሳሰሉ አስፈላጊ የሆኑ የውስጥ የቤት ሥራዎችን መሥራት ሁሉን ለማሳመር ወሳኝ ስለመሆኑም አስምረውበታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ውሳኔው፣ መሰል ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱም አስፈላጊውን ተግባር እንደሚከወን ማረጋገጫውን ሰጥተዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትን ያካተተ ብሄራዊ የክትትል ቡድን በማቋቋም በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን በማስገንዘብም የሀገርን ገጽታ መገንባት፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን መጋበዝ እና የገቢ እና ወጪ ንግዱን በመደበኛ የፋይናንስ ቁጥጥር ስርዓት እንዲሆን የማድረግ ሥራ በቀጣይ የሚሠሩ ተግባራት ስለመሆናቸው በማስገንዘብ፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 9/ 2012 ዓ.ም

ታምራት ተስፋዬ