ለተሰንበት ግደይ የዓለም ክብረወሰን አሻሻለች

27

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ለተሰንበት ግደይ የዓለም አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ክብረወሰንን መጨበጥ ችላለች፡፡ ለተሰንበት ከትናንት በስቲያ በኔዘርላንድስ ‹ሰቨን ሂልስ ረን› በተባለ የጎዳና ላይ ውድድር ክብረወሰኑን ያሻሻለች ሲሆን ውድድሩን ያጠናቀቀችበት ሰዓት 44፡20 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከወር በፊት በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአስር ሺ ሜትር አስደናቂ ብቃት በማሳየት የብር ሜዳሊያ ማሸነፍ የቻለችው ለተሰንበት በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና በወጣቶች ምድብ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ቻምፒዮን እንደነበረች ይታወሳል፡፡

ለተሰንበት የዓለም የአስራ አምስት ኪሎ ሜትር ክብረወሰንን ከአንድ ደቂቃ በላይ ያሻሻለች ሲሆን ይህ ክብረወሰን ከሁለት ዓመት በፊት በኬንያዊቷ ጆይስሊን ጂፕኮስጌ 45፡37 በሆነ ሰዓት በፓራጓይ ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ የተመዘገበ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ ድረ ገፅ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የሃያ አንድ ዓመቷ አትሌት ለተሰንበት ከውድድሩ በኋላ ‹‹ገና ለውድድሩ ዝግጅት ሳደርግ በጥሩ አቋም ላይ እንዳለሁ አውቅ ነበር፣ በውድድሩም ላይ ምቾት ተሰምቶኛል፣ እውነቱን ለመናገር የቀድሞውን ክብረወሰን በምን ያህል ሰዓት እንዳሻሻልኩኝ ለማየት ጓጉቼ ነበር›› በማለት የዓለም ክብረወሰን ስለመጨበጧ እርግጠኛ እንደነበረች ተናግራለች፡፡

ለተሰንበት ውድድሩን ከማሸነፏና የዓለም ክብረወሰን ከማሻሻሏ ባሻገር የመጨረሻዎቹን አስር ኪሎ ሜትሮች የሮጠችበት ፍጥነት የአትሌቲክሱን ቤተሰብ ያስደነቀና ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ እንዲጣልባት ያደረገ ነበር፡፡ ለተሰንበት የመጨረሻዎቹን አስር ኪሎ ሜትሮች 29፡12 በሆነ ሰዓት ያገባደደች ሲሆን ይህም አልማዝ አያና በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ የአስር ሺ ሜርት የዓለም ክብረወሰንን ስታሻሽል ካስመዘገበችው 29፡17፡45 ሰዓት የፈጠነ ነው፡፡

የአስራ አምስት ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ 2009 ላይ በተመሳሳይ ውድድር በጥሩነሽ ዲባባ ተሻሽሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጥሩነሽ በወቅቱ የርቀቱን ክብረወሰን 46፡28 በሆነ ሰዓት ስታሻሽል ከእሷ በፊት ክብረወሰኑ 46፡55 በሆነ ሰዓት በጃፓናዊቷ ካዮኮ ፉኩሺ የተያዘ ነበር፡፡ ጥሩነሽ ይህን ክብረወሰን ባስመዘገበችበት ውድድር በወንዶች ባለቤቷ አትሌት ስለሺ ስህን ከዩጋንዳዊው ኒኮላስ ኪፕሮኖ ጋር እስከ መጨረሻ አንገት ለአንገት ተናንቆ በተመሳሳይ ሰዓት በመግባት አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ለተሰንበት በነገሠችበት የዘንድሮው ዓመት ውድድር በስቶች ኬንያዊቷ ኢቫሊን ቺርቺር 46፡32 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ሌላኛዋ ኬንያዊት ኢቫ ቺሮኖ 48፡14 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ፈፅማለች፡፡ በወንዶች መካከል የተካሄደውን ውድድር የሃያ ሦስት ዓመቱ ዩጋንዳዊ ስቲፈን ኪሳ 41፡49 በሆነ ሰዓት ማሸነፍ ችሏል፡፡ እሱን ተከትለው ኬንያውያኑ ኤድዊን ኪፕቶ በሁለት ሰከንድ ዘግይቶ ሁለተኛ፣ ሞሰስ ኮይች በ42፡05 ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡

አትሌት ለተሰንበት ግደይ ክብረወሰን ከማሻሻል ባለፈ ያሳየችው አስደናቂ አቋም ተስፋ እንዲጣልባት አድርጓል፣

አዲስ ዘመን ህዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም

ቦጋለ አበበ