በጉጉት የተጠበቀው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ

40

የሲዳማ ምድር ሽር ጉድ ላይ ነች፡፡ ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሁሉም በየፊናው ዝግጅቱን እያጧጧፈው ነው፡፡ ይህን ያህል ይሆናል ብሎ በቁጥር ለመገመት የሚያዳግት የሲዳማ ህዝብና በሲዳማ የሚኖሩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግ በማላ ሲዳማና በሃዋሳ ከተማ የድንኳን ተከላ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በድንኳኖቹ አጠገብ የተሰቀሉት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎች ለድምፅ መስጫዎቹ ልዩ ውበት አጎናጽፈዋል፡፡ በጸጥታው አካል በየቦታው የሚደረገው ፍተሻና ጥበቃ ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሲዳማ ምድር ልጇን ልትድር የተዘጋጀች እናትን ትመስላለች ማለቱ ይቀላል፡፡

የሲዳማ ዞንና የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎችም የድምፅ መስጫ ቀኗን በጉጉት እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ “ለሠርግ የተዘጋጀሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ ቀኑን በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቅኩ ነው፡፡” በማለት የዝግጅቷን መጠን የገለጸችው በሃዋሳ ከተማ በመነሃሪያ ክፍለ ከተማ በጉ ቀበሌ የሰላም መንደር ነዋሪዋ ወይዘሪት ደራሮ አርገታ ናት፡፡

ካርድ ያልቃል የሚል ስጋት አድሮብኝ ስለነበር የመራጮች ምዝገባ በተጀመረበት በመጀመሪያ ቀን ነው ካርድ በመውሰድ የድምፅ መስጫ ቀኗን በጉጉት ስጠብቅ የነበርኩት የምትለው ወይዘሪት ደራሮ፤ ያለ ማንም ጫና በካርዴ የነገ ዕድሌን እወስናለሁ ብላለች፡፡ በካርዴ የምወስንበትን ዕድል በማግኘቴና የዚህ ትውልድ አካል  በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ስትል ገልጻለች፡፡

በቅስቀሳ ሂደትና የመራጮች ምዝገባ ወቅት ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚሉ አሉባልታዎች ሲናፈሱ ስለነበር ስጋት ገብቷት እንደነበር የተናገረችው ወይዘሪት ደራሮ ምዝገባውና ቅስቀሳው ያለ አንዳች እንከን መጠናቀቅ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባት ትናገራለች፡፡ እስከአሁን ባለው ነገር እጅግ ደስተኛ መሆኗን በመግለጽ የድምፅ አሰጣጥ ሂደትና የድህረ ድምፅ ሂደቱም ሰላማዊ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብላለች፡፡

እንደ ወይዘሪት ደራሮ የመንግሥት የጸጥታ አካል ብቻውን ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ ሊያደርግ  አይችልም፡፡ የህዝብ ድጋፍ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚመጡ ችግሮች ካሉ እንኳ በመመካከር ብቻ መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ብዙ የተለፋበት ህዝበ ውሳኔ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ እኔ እንደ አንድ ግለሰብ ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፡፡ የምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምን ለመቀበልም ዝግጁ ነኝ በማለት ተናግራለች፡፡

አቶ ጉደታ ግንዶ በሃዋሳ ከተማ የመንግሥት ሠራተኛ ሲሆኑ በሂጣታ ቀበሌ ለህዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጫነት የሚያገለግል ድንኳን ሲተክሉ ነው ያገኘኋቸው፡፡ ይህ ህዝበ ውሳኔ ለሲዳማና በሲዳማ ለሚኖሩ ለሌሎች ህዝቦች ልዩ ትርጉም ስላለው ሥራ አስፈቅደው በመቅረት ህዝበ ውሳኔው በተቀላጠፈ መልኩ እንዲከናወን ለማስቻል ድንኳን የመትከል ሥራ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ድምፅ የመስጠቱ ሂደት በተባለበት ወቅት ያለ አንዳች እንከን እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት አቶ ጉደታ፤ ቅስቀሳና የመራጮች ምዝገባ ስኬታማ እንዲሆን ህዝቡ ያደረገውን ትብብር በድምፅ መስጫ ሂደትም በመድገም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

“ድምፅ ለመስጠት ያለኝን ዝግጁነት በቃላት መግለጽ አልችልም፡፡” በማለት በከፍተኛ የደስታ ስሜት የተናገሩት ደግሞ በታቦር ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ተሻለ ግርማ ናቸው፡፡ በህይወት ዘመኔ ስመኛቸው ከነበሩት ነገሮች አንዱ በሲዳማ ጉዳይ ድምፅ መስጠት ነው ይላሉ፡ ፡ ይህ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ቀን ከሌሊት ሲለፉ የነበሩ በርካቶች ማየት ሳይችሉ እሳቸው ለዚህ ዕድል በመብቃታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመነሃያ ክፍለ ከተማ ሌላኛው ነዋሪ አቶ አሰፋ ደንሰሞ በበኩላቸው የሲዳማ ህዝብ ለረጅም ዓመታት ለተለያዩ መንግሥታት በተለያዩ መንገዶች ራሱን በራሱ የማስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርብ መኖሩን ያስታውሳሉ፡ ፡ የብሄሮችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በህገ መንግሥቱ ከተረጋገጠ ወዲህ ባሉ ዓመታትም የሲዳማ ህዝብ ባነሰው ጥያቄ ዙሪያ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጥያቄ በማንሳታቸው የብሄሩ ተወላጆች ብዙ ችግሮችን ማስተናገዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ህዝበ ውሳኔ ባለመዘጋጀቱ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ለሚጠቀሙ አካላት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ መቆየቱን የሚያስታውሱት አቶ አሰፋ፤ ብዙዎችም የችግር ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ያለው የመንግሥት አካል የህዝቡን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ህዝበ ውሳኔ በማዘጋጀት ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁነቱን በመግለጹ ደስተኛ መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡

እንደ አቶ አሰፋ ምብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም በደፈናው ጥያቄው የህዝብ አይደለም የጥቂቶች ነው በማለት ሲጣጣል ነበር፡፡ ጥያቄው የማን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችለው ይህ ህዝበ ውሳኔ ለሲዳማና በሲዳማ ለሚኖሩ ብሄሮች ልዩ ትርጉም አለው፡፡ መንግሥትም የከዚህ ቀደሙ አካሄድ ስህተት እንደነበር በማመን ህዝቡ ፍላጎቱን የሚገልጽበትን ዕድል በማመቻቸቱ ሊመሰገን ይገባል፡፡

በህዝበ ውሳኔው ሲዳማ ክልል የሚሆን ከሆነ በክልሉ የሚኖሩ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችን ያቀፈችና የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የተከበረባት ሲዳማን ማየት እንደሚሹ አቶ አሰፋ አብራርተዋል፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት ህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ላይ ትኩረት በማድረጉ ብዙ ጊዜ፣ ዕውቀትና ሀብት ባክኗል የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ይህ ህዝበ ውሳኔ ይህ ብክነት የሚካካስበት እንዲሆን እንደሚመኙም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፤ ሲዳማ የሲዳማ ብቻ ሳትሆን በውስጧ የሚኖሩ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ነች፡፡ አሁን በውስጧ ካሉት ብሄሮች በተጨማሪ ሌሎች ብሄሮችም መጥተው የሚበለጽጉባት፣ ሠርተው የሚለወጡባት፣ ሰላሟ የተረጋገጠ እንድትሆንም እሻለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት የበኩሉን የሚወጣ እንዲሁም ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ደግሞ ኢትዮጵያን ትልቅ ለማድረግ የሚሠራ ክልል እንዲሆንም ምኞታቸው ነው፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012

መላኩ ኤሮሴ