የጨቅላ ሕፃናት ጤናን ያሻሻለው – የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት

48

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጤና አገልግሎት ላይ ያከናወነቻቸውን ሰፋፊ ተግባሮች ተከትሎ በእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ አመርቂ መሻሻል መታየቱን በቅርቡ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡ ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ የእናቶች፣ የጨቅላ ሕፃናትና ልጆች ሞት እየቀነሰ መምጣቱ በሀገሪቱ የእናቶች፣ ጨቅላ ሕፃናት እና ልጆች ጤናን ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ የህክምና ሥራዎችን ለመገምገም እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማዳበር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የእንግሊዝ እስኩል ኦፍ ሐይጅንና ትሮፒካል ሜዲስን በቅርቡ ባዘጋጁት የምክክር ጉባኤ ላይ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ የእናቶችን፣ አራስ/ጨቅላ/ ሕፃናትን እና ሕፃናትን ጤና ለመጠበቅ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አገልግሎቱን በጤና ኬላዎችና ቤት ለቤት የሚሰጡበት ማኅበረሰብ ተኮር እንክብካቤ አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት የሚል ፕሮግራም በፈረንጆች አቆጣጠር በ2013 በይፋ መጀመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዘጠኝ ክፍሎች የተከፋፈለው ይህ ፕሮግራም እስከ ሁለት ወራት ለሚሆኑ አራስ ሕፃናት ከባድ በሽታን ጨምሮ የፀረ ተሕዋስያን መከላከያ በማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞች የሚሰጥበት ነው፡፡

የከባድ በሽታዎች ምልክቶችን ጨምሮ የሚያንቀጠቅጡ ህመሞች፣ የምግብ ፍላጎት አለመኖር ወይም መቀነስ፣ የሙቀት መጠናቸው ከ37 ነጥብ 5 የበለጠ ወይም 35 ነጥበ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች የሆኑ ሕፃናት ጤና ፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ እንቅስቃሴ አልባ ወይም የተወሰነ እንቅስቃሴና ከባድ የደረት ህመም ያለባቸው ሕፃናት ጤና ጉዳዮችም በፕሮግራሙ ማህበረሰብ ተኮር የህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡

የእናቶችንና ጨቅላ ሕፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ የሚያስችለው የመጀመሪያው ዙር ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮግራም በ2014 በሀገሪቱ አራት ክልሎች 176 ወረዳዎች ነው መተግበር የጀመረው፡፡ ሁለተኛው ዙር ፕሮግራምም በቀጣዩ ዓመት ሲተገበር በአራቱ ክልሎች ባልተሸፈኑ ቀሪ ዞኖች ላይ ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡

የለንደን ስኩል ኦፍ ሐይጅን እና ትሮፒካል ሜዲስን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ማህበረተሰብ ተኮር የጨቅላ ሕፃናት ክብካቤ ሲጀምር የዳሰሳ እንዲሁም በ2017 ያለውን ለውጥ ለማየትም ተመሳሳይ ቅኝት አድርጓል፡፡ በ2014 የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የኅብረተሰቡ አጋሮች ወይም ሴት የልማት ሠራዊት መሪዎች የኅብረተሰብ ተኮር የአራስ ሕፃናት ክብካቤ አገልግሎት ሰጥተዋል። በአራት ክልሎች በሁለት ዙር በሁለት ወረዳዎች ብቻ በ101 የኅብረተሰብ ተኮር የአራስ ሕፃናት ክብካቤ አገልግሎት ላይ ቅኝት ተካሂዷል። በዚህም በያንዳንዱ የቅኝት ዓመት ሃምሳ ቤተሰቦች በአንድ ቤተሰብ ተመድበው 206 የቤተሰብ ቡድኖች ተዳሰዋል፡፡

በዚህ መለስተኛ የስነ ህዝብ እና ጤና ሀገር አቀፍ ዳሰሳ ጥናት ላይ እንደተጠቀሰው፤እኤአ በ2000 ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ሕፃናት ሞት ከአንድ ሺህ ሕፃናት 166 የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ዓመት የጨቅላ ሕፃናት የሞት መጠን ከአንድ ሺህ ሕፃናት 49 ነበር፡፡ ይህ አሀዝ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆነ ከአንድ ሺህ ሕፃናት 55 ሞት ያጋጠመ ሲሆን፣በተመሳሳይ አመት የጨቅላ ሕፃናት ሞት ደግሞ ከአንድ ሺህ ወደ 30 ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም ባለፉት ሃያ ዓመታት የሕፃናት የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ እንደተናገሩት፤ የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ጤናን ለመታደግ በሚል ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርስ የተደረገው የህክምና አገልግሎት የእናቶችና ሕፃናትን ጤና በመጠበቅ ከህመምና ሞት መታደግ አስችሏል፡፡ የእናቶችንና የሕፃናት ጤናን በተሻለ መልኩ ከመጠበቅ አኳያ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ገና እያደገች እንደመሆኗ የተገኘውን ውጤት ጠብቆ ለመሄድና በቀጣይም በጣም ከፍተኛ ለውጥ ለማስመዝገብ ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ የጤና ሚኒስቴርና አጋሮች የጤና ልማቱን አጠናክረው በመቀጠል የሕፃናት እና ጨቅላ ሕፃናት ሞትንና እንግልትን ለመቀነስ እየተሠሩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አመጣ ተብሎ የሚጠቀሰው ትልቁ ሥራ የጤና ባለሙያዎች ያከናወኑት ተግባር እንደሆነም ጠቅሰው፣ለባለሙያው የሚሰጠውን ሥልጠና በተሻለ መልኩ በመምራት በተለይ በጤና ኬላዎች እና እናቶች የሚኖሩበት አካባቢ ድረስ በመዝለቅ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ትልቅ ግምት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡ በተለይ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ ባለፉት 15 ዓመታት የኢትዮጵያ መለያ ተብሎ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የታወቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎቹ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የተለየ ሥልጠና በመስጠት ክህሎታቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣የጤና ኬላዎችን በተሻለ መልኩ እናቶችንና ሕፃናትን በተጨማሪ ለሌሎች ማኅበረሰቦች አገልግሎት በሚሰጥ መልኩ ማደራጀት እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ፡፡ የጤና ኬላ ግንባታው መሻሻል አለበት ተብሎ እየተሠራ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ፋካልቲ ዲን ዶክተር ሙሉእመቤት አበራ የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት እና ልጆች ጤና ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰው፣ቀደም ሲል የእናቶች እና ሕፃናት ሞት በስፋት ይታይ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ይህ ገጽታ መቀየሩንና የእናቶችና ሕፃናት ጤና እየተሻሻለ መሆኑን እንደሚያመለክቱ ያብራራሉ፡፡ የተመድ የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካት በተከናወኑ ተግባሮ በእናቶች ጤና የተገኙ ስኬቶችን ለማስጠበቅ ጥናትና ምርምሮች መደረጋቸውንም ጠቅሰው፣ በዚህም በዩኒቨርሲቲዎቹ ከለንደን ስኩል ኦፍ ሐይጅን ትሮፒካል ሜዲስን፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በጤና ሚኒስቴርም ውጤቶቹን ለማስቀጠል እንዲቻል የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ይጠቁማሉ።

ጉባኤውም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚጠቀም ይገልጻሉ፡፡ በጅማ አካባቢ በዚህ ልዩ ፕሮጀክት ላይ ሁለት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች አሉ የሚሉት ዶክተር ሙሉእመቤት፣ ተማሪዎቹ በእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት አሰጣጥ እና የጤና ኤክስቴንሽኖች የማከም እና የህክምና አገልግሎት የመስጠት ብቃት ምን ይመስላል በሚሉት ላይ ጥናት እያካሄዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በእናቶች፣ ጨቅላ ሕፃናትና ልጆች ጤና አገልግሎት ላይ የተሠሩ ሥራዎችን በማጠናከር ከእርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ እናቶች የሚያጋጥማቸውን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በዘላቂነት መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በጤና ኬላዎችና ቤት ለቤት ለነፍሰጡር እና ለወላዶች እንዲሁም ለጨቅላ ሕፃናት እና ሕፃናት በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚሠጠው የማኅበረሰብ ተኮር ጤና ክብካቤ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፤ለእዚህም መንግሥትና አጋሮች በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2012

 ኃይለማርያም ወንድሙ