ብልጽግና ኢትዮጵያን ካለችበት የሚያሻግር እውነተኛ ድልድይ መሆኑ ተገለፀ

31

• ውህደቱን የተቀበሉ እህትና አጋር ድርጅቶች የፊርማ ሥነሥርዓት ተከናውኗል

አዲስ አበባ፡- የብልጽግና ፓርቲ /ብልጽግና/ በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ወደብልጽግና የሚያሻግር እውነተኛ ድልድይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ውህደቱን የተቀበሉት የኢህአዴግ እህት እና አጋር ፓርቲዎች የፊርማ ሥነሥርዓት ትናንት ተከናውኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “የብልጽግና መለያ እውነትና እውቀት ነው፤ ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ ተስፋ የምትሆን፣ ለመኖር የምታጓጓ እና ሁሉም ዜጋ ደስተኛ የሚሆንባት ሀገር እንድትሆን በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርተን እንሰራለን” ብለዋል፡፡

ብልጽግናዎች እውነትና እውቀትን በመያዝ ምኞትና ስሜትን መቀነስ ይጠበቅብናል ያሉት ዶክተር ዓቢይ ምኞት በጥረትና ስኬት የሚከወን ካልሆነ ባዶ ተስፋ እንደሚሆንና፤ ባዶ ምኞትና ያልተገራ ስሜትም በኢትዮጵያ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሀገር ለመምራት ዘመኑን የሚመጥን አደረጃጀት፣ ራዕይና ብቃት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ያልገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩም ነገ በኢትዮጵያ ብልጽግና ላይ በጋራ ቆመን ወደኋላ ስንመለከት ይህ ውሳኔ በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ታላቋን ሀገር ወደሚገባት ቦታ የሚያደርሳት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀውና የሚያየው እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

 ዶክተር ዓቢይ በንግግራቸው ዴሞክራሲንና ልማትን አጣምሮ የያዘው የብልጽግና ፓርቲ የሆድ መሙላት ብቻ ሳይሆን ለአእምሮ ነፃነትም እኩል ቦታ የሚሰጥ፣ በነፃነት ማሰብ፣ መናገርና መንቀሳቀስ እንዲሁም ያልታሰረ ማንነትና ያልተቆለፈ አንደበት ያለውና ባገኘው ልክ የሚኖር ህዝብን እውን ያደርጋል ብለዋል፡፡

በህዝቦች መካከል እኩልነት ያስፈልጋል ብሎ የሚያምነው ብልጽግና ግልፅ የሆነና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚጠቀሙበት በብዙ ምክክርና ውይይት የተዘጋጀ ግልፅ ፕሮግራም ያለው ሲሆን ፕሮግራሙ ለመላው አባልና ህዝብ በግልፅ የሚሰራጭና ውይይት ተደርጎበት የሚዳብር ብሎም ሁሉም የሚታገልለት እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

ብልጽግና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልጽግና ምእራፍ እንድትሸጋገር እቅዱን በግልፅ ቋንቋ በርካቶችን በማወያየት ያዘጋጀ ሲሆን አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ ራሱን ከምኞትና ከስሜት በማራቅ አስቻይ ሁኔታዎችን አካቶ የሚመጣ ካለ ለመማር ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የብልጽግና ፕሮግራም አይተኬ ሳይሆን የተሻለ ሃሳብ ከመጣ ለመማር ዝግጁ መሆኑ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካስቀመጠው የአይተኬነት አላማ እንደ ሚለየውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

‘’ሌብነት ጥዩፍ ነው፤ የማይተጋና የማይሰራ ከእኛ ጋር መቀጠል አይችልም’’ የሚሉና መሰል በፅሁፍ የተቀመጡ ሀሳቦች በብልጽግና ውስጥ መካተታቸው በአንዳንዶች ዘንድ ጥላቻ እንዲያድር አድርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትጋት ለሚሰሩና ለውጥን ለሚናፍቁ ግን ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከመበልፀግ ብልጽግናን ድልድይ ሆኖ ከማሻገር የሚያስቆም አንዳች ኃይል አለመኖሩን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም ህዝቦች ይዘን ሀገራችንን ወደ ብልጽግና እናሸጋግራለን ሲሉም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

ብልጽግና በዜጎች እኩልነት የሚያምን፣ ለሁሉም ህዝብና ቋንቋ ክብር የሚሰጥ፣ እውነተኛ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ተሸክሞ የሚያሻግር ድልድይ በመሆኑ መላው የፓርቲው አመራሮችና አባላት ከዚህ በፊት ከነበረው በላቀና በተባበረ ክንድ በእውነትና እውቀት ሀገሪቱን እናሸጋግር ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለህዝቡ አማራጭ ሀሳብ እንጂ አማራጭ ስሜትና ምኞት ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ያሰመሩት ዶክተር ዓቢይ ኢትዮጵያውያን ነገን የማመንና ተስፋ የመሰነቅ፣ ያለጥርጥር ጨለማው እንደሚነጋ የመገንዘብ፣ ተግቶ የመስራት፣ ሌብነትን የመጠየፍና ሀገርን የማሸጋገር ዓላማ እንዲይዙም ጠይቀዋል፡፡

በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድን ጨምሮ የየፓርቲዎቹ ሊቃና መናብርት፣ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ስምምነቱንም ዶክተር ዓቢይ አህመድ ከኦዴፓ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ከአዴፓ፣ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ከደኢህዴን፣ አቶ አህመድ ሽዴ ከሶዴፓ፣ አቶ ኡመድ ኡጁሉ ከጋህዴን፣ አቶ ኦርዲን በድሪ ከሀብሊ፣ አቶ ሀድጎ አምሳያ ከቤጉህዴፓ እና ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ከአብዴፓ ፈርመውታል።

አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012

   ድልነሳ ምንውየለት