ብሔር ብሔረሰቦች እና መደመር

14

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊነታቸው መገለጫ የሆነውን ህገ-መንግስት ልዩ ልዩ ባህሪያት ከሚባሉት መካከል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የስልጣን ባለቤት ማድረግ፣ ሃይማኖትና መንግስት በግልፅ የተለያዩ መሆናቸው፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ማስቀመጡ ተጠቃሾቹ ናቸው።

ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የመናገር፣ የመጻፍ፣ ባህላቸውን የማሳደግና የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብት እንዲጠቀሙ ያደረገ መሆኑም ሌሎቹ ተጠቃሾቹ ጉዳዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ህዳር 29 ቀን በአመቱ ሲያከብሩ ልዩነታቸውን ጠብቀው በአንድነት፤ በፍቅር እና በመቻቻል እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው የጋራ እሴት እንዳላቸው ለዓለም አቀፍ ማህረሰብ ለማስተዋወቅ እድል ፈጥሮላቸዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የግለሰብ መብቶች ከቡድን መብት እኩል እየታየ አለመሆን ችግሮችን እያባባሰ መጥቷል። ለአብነት ባለፉት ሶስት ዓመታት የብሔር አክራሪነት ባመጣው መዘዝ ዜጎች ንብረታቸውን የማጣት፣ የመፈናቀልና የሞት አደጋ ገጥሟቸዋል።

የማህበራዊ ሳይንስ መምህሩ አቶ ቢንያም ኤሮ እንደሚናገሩት፤ አሁን በአገሪቱ ያለው የቡድን መብት ሲታይ በብሔር ብሔረሰብ ላይ ተተኩሮ እንዲሰራ በመደረጉ ምክንያት የብሔር አክራሪነት እንዲፈጠር አድርጓል። የብሔር አክራሪነት ደግሞ አገር ወደ መበተን እንዲያመዝን አድርጓል። የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ግን የቡድን መብትን እና የግለሰብ መብትን አንድ ላይ ያስከብራል የሚል እምነት አላቸው።

እንደ አቶ ቢንያም፤ የቡድን ወይም የብሔር መብቶች ተጠብቀው አገራዊ አንድት ለመገንባት የግለሰብ መብቶች መከበር አለባቸው። ለሁለቱም እኩል እውቅና ሰጥቶ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ከግለሰቦች ጋር እኩል እንዲሆን የሚያደርግ ፍልስፍና መደመር ውስጥ ይገኛል። በመደመር አገራዊ አንድነት ጠብቆ አገሪቱ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የሚከበሩባት እንድትሆን ያደርጋል።

መደመር ሁሉንም ነገር አማካይ ላይ ሆኖ የሚያይ ሲሆን በተለይ አገራዊ አንድነትና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በእኩል መስመር የሚያስቀምጥ ነው። ቀደም ብሎ ግን አንድነት ላይ ባለመሰራቱ አክራሪ ብሔርተኝነት ውስጥ ተገብቶ ነበር ይላሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማካሪ የሆኑት አቶ ዮናስ ዘውዴ እንደሚናገሩት፤ ኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰብ መብቶችን ለማስከበር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ሁሉም ብሔር በራሱ ቋንቋ ተጠቅሞ እራሱን እንዲያስተዳድር ስራዎች ተሰርተዋል። ነገር ግን እውቅና የተሰጣቸው ብሔሮች እንዳሉ ሁሉ እውቅና የተነፈጉ ብሔረሰቦችም ይገኛሉ።

እንደ አቶ ዮናስ፤ በኢህአዴግ አስተዳደር ውስጥ ሁሉም ብሔር እኩል እየታዩ አይደለም። ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ ብዙ ብሔሮች በአንድ ታጭቀው እንዲቀመጡ ተደርጓል። ለምሳሌ የሲዳማን፣ የወላይታ፣ የሀድያ እንዲሁም የሌሎችን የክልልነት ጥያቄ ሲታይ ኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ በከፊል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አለመመለሱን ያሳያል።

ወደ መደመር ሃሳብ ሲመጣ መደመር የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በአንድነትና በልዩነት መካከል ሚዛናዊነትን ማምጣት እንዴት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዮናስ፤ በመደመር ላይ የሚነሱት ትችቶች ከግምት ያለፉ አለመሆናቸውንና መደመር ለብሔር ብሔረሰቦች ትልቅ እውቅና የሚሰጥ እንጂ ጨፍላቂ አለመሆኑን ያመለክታሉ። የመደመር ሃሳብ በማንኛውም ክልል ውስጥ የሚገኝ እውቀት ያለው ሰው አገር ማስተዳደርና መምራት ይችላል የሚል እውቅና የሚሰጥ ሃሳብ የያዘ አስተሳሰብ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

መደመር አሀዳዊነትን የሚያመጣ ባለመሆኑ ፌዴራሊዝምን አያጠፋም። መደመር አንድ መሆን ወደ አንድ መምጣት ማለት አይደለም። የመደመር ሀሳብ ያሉትን እውነታዎች በመመልከት በእውቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችን አይጨፈልቅም። ለአገሪቱ እድገት ለማምጣት በፉክክርና በትብብር መካከል ሚዛኑን ለማስጠበቅ መደመር ይሰራል እንጂ ጨፍላቂ አለመሆኑን አቶ ዮናስ ያስረዳሉ።

እንደ አቶ ዮናስ ገለፃ፤ በመደመር ሀሳብ ክልሎች ጋር ያለውን የተለያየ እውቀትና ጥበብ ወደ አንድ በማምጣት ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ መስጠት ይቻላል የሚል እምነት አለው። ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በመደመር ውስጥ ሀሳባቸው ሳይጨፈለቅ ለአንድነት እንዲሰሩ ይደረጋል። ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን ባህል፣ ቋንቋና እሴት ወደአንድ ጨፍልቆ የሚመጣበት ምንም አይነት ሂደትም ሆነ አሰራር የለም።

በመደመር ውስጥ የቡድንና የግለሰብ መብቶች በእኩል መንገድ ይታያሉ። አንዳንድ ሀሳቦች ከቡድን ተነስተው ወደ ግለሰብ ሲመጡ አንዳንዶቹ ሀሳቦች ደግሞ ከግለሰብ ተነስተው ወደ ቡድን ይመጣሉ። የቡድን መብት የሚከበረው የግለሰብ መብት መከበር ሲችል መሆኑን አቶ ዮናስ ያብራራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት «መደመር ማለት ትናንት ከኖርንበትና ዘመናት ከገፋንበት የእርስ በእርስ ሽኩቻ፣ ጥላቻ፣ ትንቅንቅ፣ መጠፋፋት፣ መወነጃጀል፣ የቂም በቀል ኋላቀር ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በመውጣት፤ ሁሉንም የትናንትን መጥፎ ቅሪቶች በማራገፍና በመርሳት በአዲስ መንፈስ፣ ለአዲስ አገራዊ ግንባታ በሰላም፣ በፍቅር፣ በወንድማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በመነሳት ወደቀድሞው ገናናነት መወንጨፍ እንችል ዘንድ የሚያሸጋግረን መወጣጫ መሰላል ነው» ብለው ተናግረዋል።

በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መድረኮች ስለ መደመር ፅንሰ ሀሳብ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። ስለ መደመር ካነሷቸው ነጥቦች ውስጥ ‹‹የመደመር ምሥጢር በፍቅር ለይቅርታ ብቻ ይሁን። ለክፋት፣ ለመግደል አንደመርም። የእኛ መደመር ለሌሎች ተስፋ እንጂ ጭንቀት አይሆንም። ብዙዎች የመደመር ፍልስፍናን ከመሠረታዊ የሂሳብ መሪ ቀመር ጋር ያገናኙታል። ይሁንና የእኛ የመደመር መሪ ሃሳብ ከስሌታዊ ንድፈ ሃሳብ በመጠኑ ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ምክንያቱም በማቲማቲክስ ፕሪንስፕል ቦዲ ማስ ይባላል። መጀመሪያ ቅንፉን ማፍረስ፣ እኛ ግንቡን ማፍረስ ነው። የእኛ የመደመር እሳቤ ከሂሳቡ ስሌት መሠረት የላቀ ነው። በዚህም የእኛ የመጀመሪያ ቅንፍ ሰበራው የጥላቻ ግንብን ማፍረስ ነው።›› ይገኝበታል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል፤ መደመር ከተራው የሂሳብ ስሌት የሚልቅበት ዋናው ሃሳብ ‹‹እኔና አንተ፣ እኔና አንቺ ስንደመር እንደ ሂሳብ ስሌቱ ሁለት አንሆንም። እኛ ነው የምንሆነው። የእኛ የመደመር መሪ ሃሳብ የሚቀንሰው በደል፣ ቂም፣ ክፋት፣ ጥላቻ፣ ስንፍና፣ ቀማኛነት፣አገር አለመውደድ፣ ሕዝብን አለማገልገል ይቀነሳሉ። የመቀነሻው መሣሪያ ደግሞ የማስሊያው መሣሪያ ደግሞ ይቅርታ፣ ምህረት፣ ደግነት፣ ፍቅር ይባላሉ።

የእኛ የመደመር መሪ ሀሳብ ማካፈልም አለው። የምናካፍለው ፍቅር፣በጎ ቃል፣ጥበብ፣ ነዋይ ይሆናል። መልካሙን ስናካፍል፣ መልካሙን ስናብቃቃ መከፋፈል ሳይሆን መደመር ይሆንልናል። ክፉ ተግባር ቀንሰን ተባዝተን በጎ በጎውን አካፍለን በአፍሪካ ቀንድ ስንደመር መደመር ለእኔ ሳይሆን፤ ለእኛ ነውና ሁሌም እኛ ከእኔ ይልቃል። የምንደመረው ነገን በጋራ ለማነጽ፣ እንግዶቻችንን በፍቅር ለመቀበልና ለማስተናገድ፣ ደካማውን ለማገዝ፣ ያለንን ለማካፈል፣ ተግተን ለመስራት፣ የበደሉንን ይቅር ለማለት፣ በፍቅር ሁሉን ለማሸነፍ፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ከመበላላት መረዳዳት፤ ከመገፋፋት መተቃቀፍ እንዲሆንልን ነው።››

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ‹‹በመደመር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን እንሰራለን። ሳንደመር ስንቀር ኪሳራው ብዙ ነው። መልካችን፣ ፍቅራችን፣ ደግነታችን፣ ጀግንነታችንም አንድ ዓይነት ነው። ነገር ግን የእኛ መደመር ለሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ስጋት ሳይሆን ተስፋ፤ ጦርነት ሳይሆን ልማት፤ የሚቀንስ ሳይሆን የሚጨምር ነው። ጤንነታችን እንዳያመልጠን፣ ዴሞክራሲያችን እንዳያመልጠን፣ ሰላማችን እንዳይወሰድብን ሁላችንም በአንድ ልብ ተደምረን ዘብ ልንቆም ይገባል። ምክንያቱም አንድ ሰው ቤተሰብ አይሆንም፤ አንድ ቤተሰብ ብቻውን ከተማ ሊሆን አይቻልም። አንድ ቡድንም እንዲሁም ሙሉ አገር ፈጽሞ ሊሆን አይቻለውም። አንድ አገርም ያለ ሌላ አገር ብቻውን አገር ተብሎ ሊጠራ አይቻለውም። ሌላ ድንበር የለምና።››

መደመር ለኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነትን የሚያጠናክር፣ዴሞክራሲን የሚያጎለብት ሰላምን የሚያጠናከር በመሆኑ በአሉ በመደመር እሳቤ ሊከበር ይገባል።

አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012

መርድ ክፍሉ