የአብሮነት በዓል

9

በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አንድነት ሥር እንዲሰድ የሚያደርግ የኢትዮጵያውያንን ልዩነት ብቻ ሳይሆን አንድነትን የሚያሳይ ነው። በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውንና ቱፊታቸውን ለሌላው ብሔር የሚያሳዩበት እርስ በእርስ የሚተዋወቁበትና የሚተሳሰሩበት ነው። ይህ የአብሮነት በዓል ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ልዩ፣ ክቡር፣ ውድ፣ አስደናቂ፣ ኅብረ ብሔራዊ ባህሎችና ማንነቶች እንዳሏቸው የሚያሳዩበት ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተዛመዱ፣ የተጋመዱ፣ የተወራረሱ፣ የተሠናሠሉ፣ መሆናቸውም የሚታይበት በዓል ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለ14ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በአስተላለፉት መልዕክት ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸው ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ አላቸው። የተለያዩ ቢሆኑም አብረው፣ ተባብረው የኖሩ፣ ኢትዮጵያ የምትባለውን ቤት በጋራ የገነቡ፤ አብረው ድል ያደረጉ፣ አብረው የተጨቆኑ፣ አብረው ብሔራዊ ገዥዎችን የታገሉ፣ አብረው ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከኩ ናቸው። ስኬቶችንና ድሎችን ብቻ ሳይሆን መከራዎችንና ግፎችን ተካፍለዋል።

ባህሎችንና ዕሴቶችን አንዳቸው ከሌላቸው ወርሰዋል። ተጋብተውና ተዋልደው በደም ተሳስረዋል። አንድ ቦታ መኖር ብቻ ሳይሆን ለአንድ ዓላማ በአንድ ግንባር ተሰዉተዋል፤ በአንድ መቃብር ተቀብረዋል።›› ሲሉ መግለጻቸው በዓሉ የህዝቦች ልዩነት የሚጎላበት ሳይሆን አብሮነታቸውን ይበልጥ ከፍ አድርገው የሚያሳዩበት የአብሮነት በዓል መሆኑ አመላካች ነው።

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለፍትሐዊነት በአብሮነት ታግለዋል። ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ባህልንና ቋንቋን የማበልጸግ መብትለማግኘት በጋራ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል መስዋዕትነት ሲከፍሉባት የኖረች አገራቸው በመሆኗ ሁሉም እኩል የሚጠቀምባት አገር እንድትሆን ከገዥዎች ጋር ተናንቀዋል። ይህ የዘመናት ትግላቸው በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና አግኝቶ ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ተረጋግጧል።

በተግባር ሲፈተሽ ግን የተዘረጋው ሥርዓት ትግላቸውን በተሟላ ሁኔታ የሚመልስ፣ መብታቸውንም በእኩልነት የሚያስከብር አልነበረም። በሕዝብ መራራ ትግል የሕዝቡን ሉዓላዊነትና መብት ለማስከበር የወጣው ሕገ መንግሥት እየተሻረ የጥቂቶች አገዛዝ ሰፍኗል። ሰብዓዊ መብት ተጥሶ፣ የዜጎች ክብር ጠፍቶ ኢትዮጵያ የጨለማ እሥር ቤቶችና የማሰቃያ ሥፍራዎች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች።

ይህ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ወደ ዳግም ትግል ከቷቸዋል። ሕገ መንግሥቱ በልኩና በመጠኑ እንዲተገበር ሲሉ አሁንም የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። ይህ የሚያሳየው የሃገራችን ህዝቦች አብሮነት ዛሬም እንዳለ ነው። ስለሆነም ወደፊትም ቢሆን አብሮነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ስሙ ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲፈፀም ይፈልጋሉ። አንድነታቸውን አጥብቀው ቢፈልጉም ልዩነታቸው ሳይጠቀልል፤ ልዩነታቸውም አንድነታቸውን ሳይሸረሽረው አብረው መኖር ይሻሉ።

ኢትዮጵያውያን በአብሮነት ዘመናቸው ብዙ ነገሮችን ተወራርሰዋል። አገራዊ አንድነት ከብሔር ማንነት ጋር በተመጣጠነ መልኩ መቅረብ እንዳለበት ያምናሉ። ይህ በዓልም የልዩነት ብቻ ሳይሆን የአንድነት በዓል ሆኖም እንዲያልፍ አጥብቀው ይፈልጋሉ። በቀጣይ ባህሎቻቸው፣ ቋንቋዎቻቸው፣ ዕሴቶቻቸው፣ የሚጠፉበት ሳይሆን የሚበለጽጉበት ዘመን መሆን ይሻሉ። አንድነታቸውን፣ አብሮነታቸውን፣ ወንድማማችነታቸውን ከሚያበለጽጉባቸው መንገዶች መካከል ይህ በዓል አንደኛው ነው። ቀጣዩ ዘመን በፍትሕ፣ በሰላም፣ በጋራ ደኅንነት የሚኖሩበት ዘመን መሆን አለበት።

በበዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያውቁበት ያላቸውን የጋራ ባህልና እሴት የሚያሳድጉበት የሚተሳሰሩበት ሲሆን፤ በልዩነት ውስጥ ያለው አንድነታቸው ጎልቶ ይወጣል። ይህ በዓል ሲታሰብ ስላለው ልዩነት ብቻ ሳይሆን ስለቆየው አብሮነት ማሰብንም ይጠይቃል።

በደፈናው ልዩነት የለም አንድነት ብቻ ነው መባል የለበትም። አንድነት የለም ሁላችንም የተለያየን ብቻ ነን ማለትም አይገባም። ልዩነት ቢኖርም የሚያስተሳስር አንድነት አለ። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የብሔረሰቦችን ቁጥር ከማሳየት ባህል ቱፊታቸውን ከማስተዋወቅ በዘለለ አብሮነታቸውንም የሚያጎሉበት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። የአብሮነት በዓል ነውና።

አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012