ሕገ-ወጡ ተግባር በሕገ-ወጥ ገንዘብ ማሸሽ ሲገለጽ

22

ከመነጋገሪያ አጀንዳ ሠንጠረዥ ላይ ወርዶ የማያውቀው ሙስናና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት ሙሰኞች ሰሞኑንም በዓለም የመወያያ ርዕሰ-ጉዳይነታቸው እንደቀጠሉ ይገኛሉ። ይህ ጽሁፍ ለጋዜጣ አምድ የተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን ጉዳዩን አይን ከሰበከት እያገላበጠ ማሳየት የሚችል አይሆንም፤ ባንጻሩ፣ «ሙስናን በጭልፋ» ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ጽሁፍ ነው።

በተለያዩ ታዋቂ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እየተነገረ፣ እየተብጠለጠለና እየተተነተነ ያለው ሙስና ዓለማችንን ከአፅናፍ እስከአፅናፍ እየናጣት ይገኛል። ይህ ከግለሰቦች ጀምሮ፣ ድርጅቶችን አስታኮ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን በቁልፍ ተዋናይነት እያሳተፈ ያለው የሙስና ወንጀል ዓለማችንን እርቃኗን እያስቀረ፤ የኗሪዎቿን ሥጋ አሟጥጦ አጥንታቸውን እየጋጠ ይገኛል። ይህ ከመጠን ያለፈ ተግባር ልማትን እያስተጓጎለ፣ ሚሊዮኖችን ጦም እያሳደረ፣ የመንግሥታትን ካዝና ባዶ እያስቀረ የመሆኑ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም ዓለም ትተባበር፣ መንግሥታት እጅ ለእጅ ሊያያዙና በተዋናዮቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዱ ዘንድ እያስገደደ ይገኛል።

የሙስና መጠነ ጥፋት
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ይፋ እንዳደረገውና በመገናኛ ብዙኃን እንደተነገረው ዓለም በሙስና፤ በተለይም በገንዘብ ማሸሽ ምክንያት በየዓመቱ ከ600 ቢሊዮን እስከ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች።

ፒደብሊውሲ (2018) የተባለው የጥናት ተቋም ይፋ እንዳደረገው በዓለማችን ከሚገኙ ተቋማት 49 በመቶዎቹ በኢኮኖሚያዊ ወንጀል ይጠቃሉ፡፡ በጥቃቱም 64 በመቶ የሚሆኑት እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ሀብታቸውን ያጣሉ፤ 52 በመቶዎቹ በራሳቸው ድርጅት ሠራተኞች ማስፈራራትና ስጋት ይደርስባቸዋል፤ 31 በመቶ የሚሆኑት በሳይበር አማካኝነት በሚፈጸም ኢኮኖሚያዊ ወንጀል ተጠቂዎች ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላው አስደንጋጭ ዜና የምንሰማው ደግሞ ከወደ አፍሪካ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ በሙስናና በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ የማሸሽ ወንጀል ሲነግስ እንጂ ሲቀንስ አይታይም። ይህ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት እየጎዳው፤ ልማቷን እያጨናገፈው የሚገኘው ዘረፋ ግዙፍ ነው የሚለን ኤፍቲዶትኮም ድረገጽ፤ በአህጉሪቱ በተንሰራፋው ኢኮኖሚያዊ ወንጀል ምክንያት አፍሪካ በዓመት በተለያዩ ስርቆቶች 148 ቢሊዮን፤ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ደግሞ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች። ከ2002 እስከ 2006 በየዓመቱ ከ859 ቢሊዮን እስከ 1.06 ትሪሊዮን ዶላር ያጣችው አፍሪካ በዚህ አልበቃትም። እንደ ዘ ጋርዲያን ዘገባ አፍሪካ በ2008 ብቻ 1.8 ትሪሊዮን ዶላር ያጣች ሲሆን፤ ይህም ከእያንዳንዱ አፍሪካዊ 989 ዶላር (649 ፓውንድ) የተወሰደበት መሆኑን ያሳያል።

ከ1980-2009 ባሉት ዓመታት ከ1.2 እስከ 1.4 ትሪሊዮን ዶላር በሕገወጥ ገንዘብ ማሸሽ ምክንያት ያጣችው አፍሪካ፤ በ2015 ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት ብቻ 41 በመቶ ሕዝብ በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኝባታል። ገንዘቡ በሀገራዊ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም ይህ ሁሉ የአሁን ጊዜ መከራ በህዝብ ላይ ባልደረሰም ነበር።

በአፍሪካ የሙስናው ዘርፍ በርካታ ሲሆን፤ ጉቦ ተቀባዩ ባለሥልጣን የፍትሕና የፀጥታ አካላት ቁጥር ከአንድ ጤነኛ ግምት የዘለለ ነው። እንደዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት መረጃ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከ75 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጉዳዩን የሚያስፈጽመው ጉቦ በመስጠት ነው። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ድርጊቱ ባህል ወደመሆን እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ ጉቦ የለም ማለት ፍትሕ የለም እስከ ማለት የተደረሰበት ደረጃ ነው ያለው፤ ጉቦንና ፍትህን መንትዮች አድርጎ እስከማየት ድረስ እየተሄደ ነው።

ለድህነቱ ዋናው ምክንያት ስር የሰደደ ሙስና መሆኑን የሚያስገነዝቡት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሰነዶች አህጉሪቱ በ2014 በትንሹ ከ800 ሚሊዮን እስከ ሁለት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር (ከዓለም ጂዲፒ ከ2-5 በመቶ የሚሆነውን) በሕገወጥ መንገድ ከአህጉሪቱ በሚወጣ ገንዘብ አማካይነት ታጣለች።

በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ የማሸሹ ድርጊት በ1977 አንድ ብሎ የጀመረባት ኢትዮጵያስ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
በ2015 በወጣ ዘገባ እንደተመለከተው፤ ከ1970-2008 ባሉት ዓመታት በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር አማካይነት ኢትዮጵያ 16.5 ትሪሊዮን ዶላር አጥታለች።

በከፍተኛ ደረጃ ሕገወጥ ዝውውር ከሚካሄ ድባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የገለጸውንና ከአንድ ዓመት በፊት የተካሄ ደውን የ«ትራንስፓረንሲ ኢንተርና ሽናል» ዘገባ ይዘን ወደ «Global Financial integrity» ጥናት ስናልፍ የምናገኘው መረጃ ደግሞ ከ2010ጀምሮ ከኢትዮጵያ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሕገወጥ መንገድ ካገር እየወጣ መሆኑን ያሳየናል።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በ2017 ባካሄደው ጥናት ኢትዮጵያ ከ17 አገራት 107ኛ የሙስና ደረጃ ላይ መገኘቷን የገለፀ ሲሆን፤ ከ2000 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት በአማካይ 109.5ኛ ደረጃ ላይ መሆኗን፤ በተለይ በ2007 138ኛ ደረጃ ላይ ደርሳ እንደነበረ፤ በ2002 59ኛ ደረጃን በመያዝ ዝቅተኛ ሙስና የተካሄደበት ወቅት መሆኑን አመልክቷል።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ቃለመጠይቅ ካደረገላቸው አፍሪካውያን 58 በመቶ፤ በተለይ የዓለምን 90 በመቶ ማዕድን በምታቀርበው ደቡብ አፍሪካና በመሳሰሉት አገራት ከአምስት መላሾች መካከል አራቱ (83 በመቶ) ባለፉት ዓመታት ሙስና እየባሰበት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ከዓለም በነዳጅ ምርት 10ኛ በሆነችው ናይጄሪያ ⅔ ህዝብ በረሀብ እየተሰቃየ መሆኑንም እንደማሳያ ያቀርባሉ።

እንደ ጥናቱ ከሆነ፤ የአፍሪካ መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት ያላቸው ቁርጠኝነት እጅጉን አናሳ ነው። ጥናት ከተደረገባቸው ከ28 መንግሥታት 18ቱ ምንም ዓይነት ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አይደሉም፡፡ ወንጀሉም ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ ይመስላል። በአህጉሪቱ የፖሊስ አባላት፣ የቢዝነስ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የፍትህ አካላት ሳይቀሩ በሙስና የተዘፈቁ ናቸው። በተለይ ወሳኝ የሆኑት የፖሊስ አካላት በከፍተኛ ደረጃ በድርጊቱ መሳተፍ ችግሩን የበለጠ አስከፊ አድርጎታል ሲልም ጥናቱ አስፍሯል። 22 በመቶ አፍሪካውያን የሚገባቸውን ማህበራዊ አገልግሎት ለማግኘት እጅ መንሻ ለመስጠት የተገደዱ ሲሆን፤ በተለይ ናይጄሪያን በመሳሰሉት 69 በመቶ የሚሆኑት የወንጀሉ ሰለባ ናቸው።

ከአምስት ዓመት በፊት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ30 ዓመታት ውስጥ 50 በመቶውን የዓለም የወርቅ ፍጆታ የምታቀርበው ደቡብ አፍሪካ 183 ቢሊዮን፤ ግብፅ 130 ቢሊዮን፤ ናይጄሪያ 252.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሙስና ብቻ አጥተዋል።

ጉዳዩን አስገራሚ የሚያደርገው ይህ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ሙስናን ለመከላከል አገራት እያወጡት ያለው ግዙፍ በጀት ነው። ደቡብ አፍሪካን እንኳ ብንወስድ ሙስናን ለመዋጋት በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን እንረዳለን። ይህም አልበቃ ብሎ በዚህ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ሌላ የ12 በመቶ ጭማሪ ማድረጓ ነው። ከመንግሥት ሌላ በአገሪቱ የሚገኙ ትላልቅ ተቋማት 16.7፤ አነስተኞቹ 0.67 ሚሊዮን፤ ከመንግሥት ጋር በጥምረት የሚሠሩት ተቋማት ሁለት ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ያወጣሉ። የሙስና ችግር እዚህ ድረስ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።

ምን እየተደረገ ነው?
ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ቆርጠው የተነሱ ይመስላል፤ ለዚህም በርካታ ማሳያዎች መጥቀስ ይችላል። በደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ባንክ ለዝርክርክነትና ለገንዘብ ወንጀል በራቸውን በከፈቱ ተቋማት ላይ እርምጃ እየወሰደ መገኘቱ፤ የሐሰት የገንዘብ ተቋማት በየቦታው እየተመነጠሩ መሆኑ፤ ማላዊ፣ ኦስትሪያ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ እና የመሳሰሉት አገራት ርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ መጀመራቸው፤ ቦትስዋና፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሌሴቶ፤ እንዲሁም ሴኔጋልን መሰል አገራት ህዝብን ያሳተፈ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸው፤ ችግሩን ከአፍሪካ ምድር ማስወገድ የሚቻል ስለመሆኑ ተስፋ ያለው ይመስላል።

በቅርቡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአጠቃላይ በዓለማችን ከድህነት ወለል በታች 815 ሚሊዮን ወገኖች መኖራቸውን፤ እነዚህን ለመታደግና ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በየዓመቱ 30 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2011

ግርማ መንግሥቴ