ሳይንሳዊ ግንዛቤ በኢትዮጵያ – መገናኛ ብዙኃንን እንደማሳያ

30

በዚህ ዘመን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሰው ልጆች የየትኛውም ችግር መፍትሄ ስለመሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ለማንኛውም ጉዳይ፣ በማንኛውም ቦታና ሁልጊዜም ሳይንስና ቴክኖሎጂን መጠቀም ለማኅበረሰባዊ ችግሮች የመፍትሄ አካል አድርጎ መውሰድም ተለምዷል፡፡ ዓለም ላይ ግብርናው፣ ትምህርቱ፣ የእለት ተዕለት ህይወት፣ማኅበራዊ ኑሮው ኢኮኖሚው ወዘተ የላቀ እምርታ ለማሳየት ብሎም ለውጥ ለማምጣት የሳይንስና ቴክኖሎጂ እገዛ የግድ ያሻዋል፡፡ ይህ በምርጫ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን ለውጥን የፈለገ ሁሉ የግድ ሊከተለው እንደሚገባ በርካታ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሃያላን አገራትና ወደ ፊትም የዓለምን ኢኮኖሚ ይዘውሩታል የሚባሉት የእድገታቸው ዋነኛ ምስጢር ይኸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውም ይበልጥ አዋጭና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት ዋነኛ ምስጢር ሆኗቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ይበልጥ በማጠናከር መስራት እንደሚገባት የሌሎች አገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ እድሎችና ሥራዎች በዙርያዋ እንዳሉ እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሌሎች የዓለም አገራት እኩል ተወዳዳሪ ለመሆን ሳይንስ አወቅ ማኅበረሰብ ከመፍጠር አንጻር ጉድለቶች እንዳሉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ይህንኑ ችግር ለማቃለል በተይም «የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሳይንሳዊ መረጃ አሰጣጥ ዙሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂን እሳቤዎች መገንዘብ ይኖርባቸዋል» ሲል የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከመገናኛ ብዙኃን ለተወጣጡ ጋዜጠኞች በቅርቡ ሳይንሳዊ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል መድረክ አመቻችቶ ነበር፡፡

በመድረኩ ሳይንስ አወቅ የሆነ ማኅበረሰብ ከማፍራት አንጻር የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምንድነው? በኢትዮጵያ ያለው ሳይንሳዊ ግንዛቤስ ምን ይመስላል? የሚለው ዳሰሳ በምሁራኑ ቀርቧል፡፡በመድረኩ የዳሰሳ ጽሁፍ ካቀረቡት ውስጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ቀጣዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሳይንሳዊ ግንዛቤ
ሳይንሳዊ ግንዛቤ ሲባል በማህበረሰቡ ህይወት የዕለት ከዕለት ኑሮ ውስጥ ምን ያህል ሳይንስ ወለድ ግንዛቤ ተግባራዊ እናደርጋለን አሊያም እንጠቀምበታለን ምን ያህልስ ህይወታችን ያሻሽለዋል የሚለው ነው፡፡ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ምንጮች የሚሰሙት ግን በተለይ ባልተማረው የህብረተሰብ ክፍል ላይ አገር በቀል የሆኑና ነገር ግን አዋጭ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ይበዛሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንዱ ጠቃሚ ቢሆንም በትምህርት መለወጥ የሚገባቸው ነገሮችም እንዳሉ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የትምህርትና የልማት ደረጃው ሲታይ ዝቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መረጃዎች እየለሙ እንዳሉ አገራት አይደሉም፡፡ ሳይንስ የቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ የኑሮ ጉዳይን የያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ሳይንሳዊ አስተሳሰቦችና ግንዛቤዎች ቢያስፈልጉንም በሚፈለገው መጠን ተገኝቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡

የግንዛቤ ችግሮች ለመፈጠራቸው ዋናው የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ ከፖሊሲ ጀምሮ መስተካከል አለበት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ መጣ እንጂ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደ ቅንጦት ይታይ ነበር፡፡ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይ መሠረታዊ እንዳልሆነ ፍላጎትና እንደ ሩቅ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ነበር፡፡ አሁን ላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለኑሮ ወሳኝ መሆኑ ሲታመንበት ማህበረሰቡ እየገባው መጣ፡፡
የቀደሙት መንግሥታት የጀመሩት ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አልቀጠሉበትም፡፡ ተጀምረው የተቋረጡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነክ ብዙ ፕሮግራሞች ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጭምር ይተላለፍ የነበረና ብዙ አድማጭ የነበረው ‹‹ከሳይንስ ማህደር›› ፕሮግራም እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት በስፋት የሚደመጥ ቀጣይነት ያለው ፕሮግራም አሁን ላይ ብዙ የለም፡፡ በአንዳንድ ጣቢያዎች የጤና ባለሙያዎች ጭምር የሚሳተፉበት ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ሚና
በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእርግጥ በየጊዜው የሚታዩ ነገር ግን ቀጣይነት የማይታይባቸው ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ በአሁኑም ወቅት ተስፋ ሊሰጡ የሚችሉ ነገሮች በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ይታያሉ፡፡ ይህ ግን አገሪቷ ካላት የህዝብ ብዛትና መረጃ ከመፈለግ አንጻር በቂ አይደለም፡፡ በሚዲያው በኩል እየተሰራ ያለው ሥራ በቂ አይደለም የሚለውን የሚያረጋግጠው ዛሬ ላይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች የሚወጡበት ፍጥነት ከፍተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ስለዚህ የሚጀውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን በወቅቱ በፍጥነት እየደረሰ አይደለም፡፡ ብዙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ አያረጅም፡፡ ጠቀሜታው ሥላለ ሁልጊዜም ለህብረተሰቡ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከብዛት አንጻር ሳይነገሩ ሊያልፉ የሚችሉ ነገሮች ስላሉ ሚዲያው በትኩረት መስራት አለበት፡፡

የግል የሚዲያዎች ሳይንስ ቴክኖሎጂ ነክ ዘገባዎችን ለኅበረተሰቡ ሲያቀርቡ ይታያል፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች በመሠረታዊነት እንደ ንግድ ተቋምነታቸው ለማኅበረሰብ ይጠቅማል በማለት ሳይንሳዊ ግንዛቤዎች እንዲኖሩ ማድረጋቸው ይበረታታል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በጀት የሚደጎሙ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እሳቤዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ የበለጠ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ህብረተሰቡ ለኑሮ ማሻሻያ የሚፈልገው አንዱ የሳይንስ እውቀት ስለሆነ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ መላቀቅ
ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደ ሌሎች መረጃዎች እኩል ሽፋን ሊያገኙ ይገባል፡፡ አብዛኞቹ ሚዲያዎች በፖለቲካው ስለሚጠመዱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው፡፡ ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ህብረተሰብ ግን እዚያው ያለ ስለሆነ ሳይንስም ከህብረተሰቡ ኑሮ ጋር የተቆራኘና አብሮት የሚቆይ በመሆኑ ከፖለቲካው ተጽዕኖ ወጥቶ ተገቢውን ሽፋን መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ሚዲያዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ምን ያህል ነጻነት አላቸው ተብሎ በዴሞክራሲ ማዕቀፍ ውስጥ በማስቀመጥ መታሰብ አለባቸው፡፡ ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሲሆኑ በማኅበራዊ ኃላፊነት መርህ እየተመሩ ሙያዊ በሆነው መነጽር ብቻ ነገሮችን በመመልከት የህብረተሰቡን የልብ ፍላጎት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነጻነት በሌለበት ጊዜ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት ይቀንሳል፡፡

ባለሙያዎች ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ካለባቸው ትኩረታቸውም፣ ዓይናቸውም፣ አቅማቸውም ይዳከማል፡፡ ከውጭ ከየትኛውም ቡድን ማለትም በስልጣን ላይ ካለው መንግሥትም ሆነ ከሌሎች አካላት ተጽዕኖ የሚያሰድሩ ነገሮች መኖር የለባቸውም፡፡ በሳይንሳና ቴክኖሎጂ ዙርያ ህብረተሰቡ ለሚጠይቀው ሁሉ በቂ ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ ህብረተሰብ ነጻነት ከመጣ በኋላ ሚዲያው ምን ሰራልን ብሎ መጠየቅ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ በማኅበራዊ ኃላፊነት መርህ እየተመራ ለህብረተሰቡ ካልሰራሁ ያስጠይቀኛል ብሎ መስራትን ይጠይቃል፡፡

አገር በቀል እውቀትና የሳይንቲስቶች ሁኔታ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ ወደ ውጭ ማማተሩ ተለምዷል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ መጥፎ አይደለም፡፡ ሌሎችም አገራት የሚከተሉት ነገር ነው፡፡ ሁሉ ነገር የግድ ከባዶ መጀመር የለበትም፡፡ አንዳንዱን ነገር ከውጭ በመቀበል ለህዝብ እንደሚበጀው በማድረግ ማስተላለፉ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን አገር በቀል የሆኑ ሳይንስ እውቀቶች መፈጠር አለባቸው፡፡ ወደ ህብረተሰቡም መድረስ አለባቸው፡፡ አገር በቀል ሳይንሳዊ እውቀቶች ሲበረክቱ ከውጭ ከሚመጣው ይልቅ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡ በራስ ሳይንቲስቶችና አጥኚዎች ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተጠና የራስን ህዝብ ኑሮና አውዱን ከግምት ውስጥ ያስገባ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ አገር በቀል ሳይንሳዊ እውቀት ከሁኔታዎች ጋር መስማማት ስለሚችል ቶሎ ተቀባይነት ያገኛል፡፡

በብዙ መልኩ ማስተዋል እንደሚቻለው አገር ቤት ያሉት ሳይንቲስቶች በብዛት እውቀትን አያመርቱም፤ በቅጡ ህብረተሰቡ ሊቀበል በሚችለው መልኩ ቀለል አድርገው እያደራጁም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት አሊያም በሌሎች መንገዶች ወደ ህዝቡ ለማድረስ በቂ ጥረት አያደርጉም፡፡ ‹‹የኛ ሥራ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ አትኩረን መስራትና እውቀትን መፍጠር እንጂ ማሰራጨት አይደለም›› ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ኃላፊነቱንም ለጋዜጠኞች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኞች ደግሞ በሁሉም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በቂ ዝንባሌም በቂ እውቀትም ላይኖ
ራቸው ይችላል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንደየሁኔታውና እንደየአስፈላጊነቱ ብቻ ሊሆን ይቻላል የሚያነሱት፡፡ ይህ አስተሳሰብ አይደገፍም፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011

ሰሎሞን በየነ