በሀይማኖት መቻቻል የተጋመደ ሕዝብ እንዴት ይለያያል?

በኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች መካከል የቆየው ትስስር ጤነኛ ሆኖ እንዲቀጥል በወረቀት ላይ የተጻፉ ህጎችና ያልተጻፉ እሴቶች የየራሳቸው ሚና አላቸው። በተለይም ያልተጻፉ እሴቶች በብሄሮች መካከል ያለው ትስስር ቀጣይነት ያለው እንዲሆን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያዊያን እንዳይነጣጠሉ አድርጎ ካጋመዳቸው አንዱ በተለያዩ ሀይማኖቶች መካከል ለዘመናት የኖረው መቻቻል ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህን ኢትዮጵያዊያንን ያጋመዳቸውን ድርና ማግ ለማናጋት የእምነት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።

ኢትዮጵያውያን ቀና ብለው ለማየት እንኳ በሚፈሩት የእምነት ተቋማት ላይ ዘግናኝ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ማየት የተለመደ ሆኗል። ከኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ የሀይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት ሲፈጸም በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት አነስተኛ መሆን ወይም እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ችግሩን እጅግ አሳሳቢ አድርጓል። የዚህ ችግር መነሻ፣ መፍትሄና አሳሳቢነቱ ምን ያህል ነው? የሚለው የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ነው።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዱ መሃመድ አሊ እንደሚገልፁት፤ በአሁኑ ወቅት በሀይማኖት ተቋማት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችና በሀይማኖቶች መካከል የሚታየው ሹክቻ በአንድ ማግስት የተፈጠሩ ቅጽበታዊ ክስተቶች አይደሉም ይላሉ። ከሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት በፊት ጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ያነሳሉ። አሁን በሀይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ችግሩ ጫፍ ላይ ለመድረሱ አመላካች ነውም ሲሉ ያስረዳሉ።

ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያራምዷቸው አመለካከቶች አገር ውስጥ ድረስ የዘለቀ ነበር። ይህን ተከትሎም በአገር ውስጥ የተቋቋሙ ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶችና ማህበራት ለመመስረት መንስኤ ሆኑ። በእነዚህ ሁለቱ ተፃራሪ ዓላማ አራምጅ ድርጅቶችና ማህበራት ፉክክሩ ጠንክሮ ወጣ። እነዚህ ማህበራትና ድርጅቶች ስለ ሀይማኖት አብሮነት ሳይሆን ስለራሳቸው ሀይማኖት መልካምነትና ስለሌላኛው መጥፎነት በመስበክ ላይ የተጠመዱ ናቸው። በእነዚህ ድርጅቶች መካከል ፉክክሮችና ፍትግያዎች መጧጧፋቸው የእምነት ተቋማትን ሰለባ እንዲሆኑ የበኩሉን ስለማበርከቱ የሚያብራሩት ዶክተር አብዱ በእነዚህ መካከል ሲደረግ የነበሩ ፉክክሮች በአንዳንድ አካባቢዎች ለተፈጠሩት የሀይማኖት ግጭቶች የበኩሉን ሚና እንደተጫወተ ምሁሩ ይጠቁማሉ።

በሀይማኖቶች ስም በተደራጁ ድርጅቶች መካከል ያለው ፉክክርና ፊትጊያው ጫፍ ላይ ከመድረሱ በተጓዳኝ ለሶስት አስርት ሀገሪቱን ሲመራው በነበረው በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አሁን በእምነት ተቋማት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት የበኩሉን እያበረከተ ነው ይላሉ። በግንባርነት ተደራጅተው ሀገሪቷን በመሯት ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ህገ ወጥ ተግባራት አበርክቶ አለው። በድርጅቶቹ መካከል የተፈጠረው ችግር ማዕከላዊ መንግስቱ ህግን እንዳያስከብር እና ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ቀድሞ እንዳያመክን አድርጓል። ይህን ክፍተት ተጠቅመው በሀይማኖቶች መካከል ችግር ለሚፈጥሩ ሁሉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል ባይ ናቸው።

እንደ ዶክተር አብዱ ማብራሪያ፤ የሀይማኖት መሪዎች ሚናቸውን መዘንጋታቸው ለዚሁ ችግር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። የሀይማኖት አባቶችና መምህራን የስነ ምግባርን በማስረፅ ሚናቸው የጎላ ነው። ነገር ግን አሁን በሚታየው ሁኔታ የአብዛኞቹ የሀይማኖት መምህራን ስነ ምግባር ሲታይ በተለይ አንዳንዱ ከሞራል በታች እና ከህግ በላይ ሆኖ እየታየ ነው። የሀይማኖት መሪዎችና መምህራን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀይማኖቶች መካከል ለሚፈጠረው ግጭትና የእምነት ተቋማት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ለመሆኑ ምመንም ጥርጥር የለውም ሲሉ ይከራከራሉ።

አንዳንድ የሀይማኖት መምህራን ለሀይማኖታቸው የተቆረቆሩ በመምሰል ከሀይማኖት አንጻር ሀጢያት፣ ከህግ አንጻር ወንጀሎችን ሲፈፅሙ ጭምር ታይተዋል የሚሉት ዶክተር አብዱ፤ የሀይማኖት መምህራን መንገዳቸውን ቆም ብለው ሊመለከቱት ይገባል በማለትም ይመክራሉ። የሀይማኖት መሪዎችና መምህራን ችግሮችን የማቀጣጠልና የማባባስ ሚና ሲጫወቱ ዝም ሊባል አይገባም በማለት መንግስትን ይወቅሳሉ።

ፖለቲካ ማለት ለስልጣን የሚደረግ መስዋዕትነት ነው የሚሉት ዶክተር አብዱ፤ የትኛውም ፖለቲከኛ የመጨረሻ ግቡ ስልጣን መቆጣጠር ነው። በህገ መንግስቱ ሀይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው ቢባልም፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፖለቲካ ሀይማኖት ውስጥ እየገባ ነው። ሀይማኖትም ፖለቲካ ውስጥ እየገባ ይስተዋላል። በሁሉም ሀይማኖቶች ውስጥ ተቋማቱን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም የሚፈልጉ አካላት ቁጥር እያሻቀበ በመምጣቱ ጉዳዩ ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባው ያነሳሉ። አብዛኛው ህዝብ ግን ይህን ላይረዳው ቢችልም አሁን አሁን ግን በዕለት ተዕለት የህዝቦች መስተጋብሮች ላይ ጥቁር ጠባሳ እየተወ በመጓዝ ላይ በመሆኑ የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም ሲሉ ለጉዳዩ አፅንኦት ይሰጣሉ።

ፖለቲከኞች ወደ ስልጣን ለመውጣት ማንኛውንም አይነት መወጣጫ መሰላል ሊጠቀሙ ይችላሉ። በመሆኑም ሀይማኖትንም እንደመሰላል ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አሁን አሁን በተግባር የሚታዩት ድርጊቶች ያሳብቃሉ። በተለይም የራስን የፖለቲካ ግብ ለመምታት አንዱን ሀይማኖት ከፍ አንዱን ዝቅ አድርጎ፤ አንዱን ገዥ፣ አንዱን ተገዢ፤ አንዱን ሰላማዊ አንዱን ሳይጣናዊ አድርጎ በመሳል ሁኔታውን ከሀይማኖት ጋር እየገመዱት መጓዛቸው ከፍተኛ ችግር ይሆናል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ባልሰለጠነ ማህበረሰብ ውስጥ ሀይማኖትን ፖለቲካ ውስጥ መቀላቀል አደጋው እጅግ የከፋ ውጤት እንዳለውም አብራርተዋል።

የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳግማዊ ተስፋዬ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሀይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሀይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረግ ጥረት አካል ነው። ይህም ሀገራዊ አንድነትን አደጋ ውስጥ የመጣል አቅም አለው። ምክንያቱም ሀይማኖት የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አንድ ላይ ካጋመዱት እሴቶች አንዱ ነው። ይህን እሴት ለማናጋት እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት በስፋት በመስራት ላልተገባ ጥቅም እያዋሉት ነው። ይህ ደግሞ ለአገር ግንባታ መጥፎ ምሳሌና ውጤት ያስከትላል ይላሉ፤ ዶክተር ዳግማዊ።

በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር በቅርበት የሚከታተሉ ሌሎች ምሁራንም የዶክተር ዳግማዊን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የእምነት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በድንገት እየተፈጠሩ አይደሉም። አንድን ብሄር ለሆነ ሀይማኖት ጠቅልሎ የመስጠት እና አንዱን ሀይማኖት ደግሞ ለአንድ አካባቢ ጠቅልሎ በመስጠት አንድ ብሄር በአንድ ሀይማኖት ብቻ እንዲገለጥ የመፈለግ አዝማሚያ ይታያል። ይህም የተለያዩ ብሄሮች አንድ ላይ የሚያጋምዳቸውን እሴቶችን፣ ማህበራዊ ህይወትንና መስተጋብሮችን ያናጋል ይላሉ።

ምሁራኑ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ምልክቶች በእንጭጩ ሊቀጩ የሚገቡ ናቸው። ሁሉም አካል በአንድ ላይ በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ ሊረባረብ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ከሁሉ በፊት ግን ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት በቅድሚያ እውነት መነጋገር መጀመር አለበት። በጉዳዩ ላይ አድበስብሶ ማለፍ መቆም አለበት። አድበስብሶና ለችግሩ የተለያዩ ማልበሻ ምክንያቶችን እየደረደሩ መሄድ ችግሩ ስር እንዲሰድ ያደርጋል ብለዋል።፡

ሁሉም ሀይማኖቶች ውስጥ በእኩይ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ እና የሚያበረታቱ አካላት እንደ ጀግና ሳይሆን እንደ ጥፋተኛ መቆጠር መጀመር አለበት። ከየትኛውም ሀይማኖት ይሁን ብሄር አጥፊን አጥፊ ማለት መለመድ አለበት ይላሉ ምሁራኑ።

እንደ ምሁራኑ ማብራሪያ ሁሉም አካል ኢትዮጵያን በቅጡ ሊረዳ ይገባል። ሁሉም አካል የሚሰራው ስራም ሆነ የሚያስበው አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት። የመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ የምሁራን ትርክቶች የኢትዮጵያን እውነተኛ ማንነት የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ሀይማኖት ሀገር ነች። በተለይም የመንግስት ትርክቶች ሁል ጊዜም ብዝሃነትን እውቅና የሚሰጡና የሚያከብር መሆን አለበት። የሀይማኖትም ሆነ ሌሎች አይነት ብዝሃነቶችን ለሀገር ስጋት አድርገው ሊያቀርቡ የሚሞክሩ አካላትን መንግስት አደብ ማስገዛት እንዳለበት መክረዋል።

ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚፈጽመውን ወንጀል የአንድ እምነት ተከታይ የሚፈጽመው አድርጎ የመመልከት አዝማሚያዎችም ሊታረሙ እንደሚገቡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አንድን የሀይማኖት ተከታይን በአጠቃላይ ከአንድ መጥፎ ድርጊት ጋር ማያያዝ መዘዙ አደገኛ ነው። በመሆኑም ጥፋቱን የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠያቂ መደረግ አለባቸው። የአንድ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ብቻ መፈረጅ ተገቢ አይሆንም ይላሉ ምሁራኑ።

እንደ ዶክተር አብዱ ማብራሪያ፤ የሀይማኖቶች መምህራንና መሪዎች ቢችሉ ችግሮችን ማረጋጋት አለባቸው። ከመስመር የሚወጡ ነገሮችን ወደ መስመር የመመለስ ስራ ሊሰሩ ይገባል፡፡ ማረጋጋት ካልቻሉ ግን የችግሮች አካል ሊሆን አይገባም፡፡ ለችግሮች ሰበብ ሲሆኑ ደግሞ መንግስት አደብ ሊያስገዛቸው ይገባል ይላሉ።

“የጥቂቶች ጥፋት የብዙሃን የዝምታ ውጤት ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱ፤ ብዙሃኑ ዝምታን

 መምረጡ ለሚፈጠሩ እምነት ተኮር ግጭቶች አስተዋጽኦ ማድረጉን ያብራራሉ። በመሆኑም ብዙሃኑ ጥቂቶችን ሃይ ሊል ይገባል። በዚህ ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ብዙሃን ዝምታ መቀጠል የለበትም። በዚህ ወቅት ዝምታን መምረጥ ወንጀል ነው። ዜጎችን በሀይማኖት፣ በብሄርና በፖለቲካ አመለካከታቸው ልየነት የሚፈጥሩ አጥፊዎችን በቃችሁ ሊባሉ ይገባል። መጠየቅ ያለባቸው በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የብዙሃን መገናኛ አውታሮች ከወገናዊነት ነጻ መሆን አለባቸው። የብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች ከምንም በላይ ጋዜጠኝነታችን ይቀድማል ሊሉ ይገባል። እምነታቸውን ሳይሆን ሙያቸውን ሊያስቀድሙ ይገባል። ሀይማኖቶችን ሳይለዩ ሁሉንም ማስተናገድ አለባቸው። የአንዱን ችግር ዘግበው የሌላውን ሊተው አይገባም። ከመዘገባቸው በፊት የክስተቶቹን እውነተኛነት ማጣራት ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው።

ከወገናዊነት ነጻ በሆነ መልኩ የችግሮች ሰበብ የሚሆኑትን የማጋለጥ፤ በጎ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ መንገድ መክፈት እንዲሁም ሀይማኖት ለፖለቲካ ማስፈጸሚያ ሊውል እንደሚችል ለህዝብ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም ያብራሩት ምሁሩ፤ መገናኛ ብዙሀኑ ከህግና ስርዓት ውጭ ሆነው ሲሰሩ ደግሞ መንግስት ቁጥጥር ማድረግ አለበት። በተለይም ሆን ብለው የሀይማኖት ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መገናኛ ብዙሀንን ሊታገሳቸው አይገባም ብለዋል።

ዶክተር አብዱ እንደሚሉት አሁን በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየውን በጊዜያዊነት በሚሰሩ ስራዎች ብቻ ሊቀረፉ አይችሉም። በዘላቂነት ሊፈታ ይገባል ባይ ናቸው። በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው ድህነትንና ድንቁርናን ማስወገድ ሲቻል ነው። ድህነትንና ድንቁርናን ማጥፋት ሳይቻል መሰል ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ከባድ ነው። ሁሉም ዜጋ ድህነትንና ድንቁርናን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አንድ ላይ በመሆን ለችግሩ መፍትሄ ያብጁለት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ዳግማዊ በበኩላቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ የሚታየው ሀይማኖት ነክ ግጭቶች መንስኤውና መፍትሄው በጥናት ሊለይ ይገባል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ለምን ሀይማኖቶች እንደ መሳሪያዎች እየሆኑ መጡ? የሚለውን በጥናት መለየት ትኩረት ሊሰጥ የሚገባ ጉዳይ ነው። የችግሩ ምንጭ የሆነው አስተሳሰብ ተለይቶ እንዲታከም ሊደረግ ይገባል።

ከዲሞክራሲ እሴትና አስተሳሰብ ባፈነገጠ መልኩ የሀይማኖት ብዝሃነትን አለመቀበልና የራስን ብቻ ለማግነን የሚደረጉ ጥረቶችን መንግስት ከምንጩ ለማድረቅ ሊሰራ ይገባል። መንግስት ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ አለበት። በብሄርና በማንነት ምክንያት ለአጥፊዎች ሽፋን መስጠት ችግሩ እንዲቀጥል ከማድረግ ጋር ቀጥተኛ ትርጉም እንደሚሰጠው አብራርተዋል።

የሀይማኖት አስተማሪ ሆነ ተከታይ አጥፊ ሆኖ ከተገኘ ሊጠየቅ ይገባል። ይህ ካልሆነ እንዲቀጥል እንደመፍቀድ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ አጥፊን ለህግ ከማቅረብ ጎን ለጎን አብሮነትን የሚያጠናክሩ ትምህርቶች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

እንደ ዶክተር ዳግማዊ ማብራሪያ ለዚህም የህግ የበላይነትን ማስከበር ላይ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባው ቢታመንም ችግሩ በመንግስት ጥረት ብቻ አይፈታም። የሀይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቁጭ ብለው ተነጋግረው ሁኔታውን በማገናዘብ አሁን ያለውን ሁኔታ በመገምገምና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት መርዳት አለባቸው።

የሀይማኖት አባቶች መደራጀት አለባቸው። የሁሉም የእምነት አባቶች ለማህበረሰቡ እና ለሀገር ጥቅም ሲሉ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተጠናከረ መልኩ በአንድነት ሊደራጁ ይገባል። የሚደራጁት ግን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ ሊሆን ይገባል። የእነሱ አንድ መሆንና መቀራረብ ለሀይማኖቶቹ አብሮነት መጠናከር አይተኬ ሚና አላቸው።

ዶክተር ዳግማዊ እንደሚያብራሩት ፈጣን የመረጃ ፍሰትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች ምክንያት በአንዳንዱ ጉዳዮች ላይ የእምነት ተከታዮች ከሀይማኖት ተቋማት አስተሳሰብ በንቃት ከፍ ብለው ይታያሉ፡ የእምነት ተቋማት ከህብረተሰቡ ንቃት ጋር አብሮ መሄድ ያልቻሉባቸው ሁኔታዎች ይታያሉ። በተለይም የሀይማኖቶቹ እሴቶችና የሚሰሩ ስራዎች የሚቃረኑ ሆነው ሲታዩ ህዝቡ መጠየቅ ጀምሯል። ይህም የሀይማኖት ተቋማት ራሳቸውን መፈተሸ እንዳለባቸው አመላካች ነው።

በቅርቡ በሞጣ ከተማ በመስጊድ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያን የቆየ የሃይማኖቶችን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል የሚፃረሩ ጽንፈኛ አካሄዶች አሁንም በኢትዮጵያ ቦታ የላቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በእምነት ተቋማት ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶች አጥብቀው አውግዘዋል። መላው ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያንም የመከባበርና አብሮ የመኖር ጥልቅ እውቀታቸውን እንዲያጋሩ ጥሪ አቅርበዋል። ከፋፋይ አጀንዳዎችን መረዳትና መጠየፍ የጋራ ዕድገታችንን ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የመጀመሪያውን የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ሰሞኑን ያካሄደው ብልጽግና ፓርቲም በዚሁ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጓል። የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ያካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በሃይማኖት ተቋማት ላይ በቡድንና በተናጠል በተደራጀ መልኩ ጥቃት የማድረሱ ዘመቻ እየተባባሰ መጥቷል። ይህ እኩይ ተግባር የኅብረተሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ እንደሚከት ስራ አስፈፃሚው ገምግሟል። በወንጀሉ የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድም አቅጣጫ ተቀምጧል።

‹‹በወንጀሉ በተሰማሩ አካላት በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት እና የፍትህ ተቋማት እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ ተላልፏል›› ያሉት የዋና ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ፤ የአገሪቷንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል። ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር መንግስት ከመግለጫ በዘለለ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። የእምነት ተቋማት፣ መምህራን፣ አባቶች እና የሁሉም እምነት ተከታዮች የመንግስትን ጥረት ሊያግዙ ይገባል።

አዲስ ዘመን  ታህሳስ 30/2012

መላኩ ኤሮሴ

Ad Widget

Recommended For You

About the Author: teshome

Leave a Reply