የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላቱ ተሳትፎ ይጎልብት

19

 የሀገራችን ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ሀገሪቱ ግብርና መር የኢኮኖሚ ስትራቴጂን ስትከተል ቆይታለች። በዚህ ስትራቴጂ መሰረት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባሮች የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል። ግብርናው እስከ አሁንም ድረስ ለሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ዘርፎች አንጻር ሲታይ ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል።

በግብርና የሚመራውን ይህን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንስቶ እየሰራች ትገኛለች። ይሁንና ኢንዱስትሪው ግብርናውን ይረከባል ተብሎ ቢታሰብም በኢኮኖሚው ላይ የመጣ መዋቅራዊ ለውጥ ግን የለም።

እንዲያም ሆኖ ግን ኢኮኖሚው በተለያዩ ዘርፎች የሚታገዝበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው፣ የአገልግሎት ዘርፉና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ለሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እየጨመረ መጥቷል።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ብንመለከት መሬት ላይ ያለው እውነታም ሆነ መረጃዎች የሚያመለክቱት እውነታ በእድገት ላይ መገኘቱን ነው። ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ እያበረከተ ያለው እስተዋጽኦም ተጠቃሽ ለመሆን በቅቷል። ኢንዱስትሪው ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመክፈትም ይታወቃል።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመንም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አፈጻጸም 27 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም በያዝነው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያ ሶስት ዓመታት በአማካይ 20 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም ከ9 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ደርሷል።

ኢንዱስትሪው ይህን ሁሉ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው ግን በርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ነው። ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ ፕሮጀክቶች የሚጓተቱበት እና ከተያዘላቸው ጊዜ በእጅጉ እየዘገዩ የሚጠናቀቁበት፣ ከተያዘላቸው በጀት በላይም ከፍተኛ በጀት እየጠየቁ የሚጠናቀቁበት፣ የጥራት ጉድለት በከፍተኛ ደረጃ የሚስተዋልበት መሆኑ ይገለጻል። የግብአት አቅርቦት በበቂ አለመኖር፣ የቴክኖሎጂ ውስንነት፣ የዘርፉ የሰው ሀይል እጥረት ፣ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግርም ሌሎች የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው።

እነዚህ የዘርፉ ተግዳሮቶች ቢፈቱ ደግሞ ኢንዱስትሪው ለሀገር ሊያበረክት የሚችለው አስተዋጽኦ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። የግንባታ ስራው በወቅቱ ተጠናቀቀ ማለት በራሱ ትልቅ ትርጉም አለው። የመንግስት ፍላጎት ይሞላል፤ የህብረተሰቡ ጥያቄ ይመለሳል። በመሆኑም ዘርፉን ከነዚህ ተግዳሮቶች ለመታደግ አሰራር መቀየስ ያስፈልጋል። በተለይ ከግዥ ጋር ተያይዘው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ስራውን በቀጥታ ለኢንዱስትሪው ማስረከብ ይገባል።

ይህ ዘርፍ ከሀገሪቱ ካፒታል በጀት 60 በመቶውን የሚያንቀሳቀስ እንደመሆኑ ዘርፉን ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት መታደግ ማለት ይህን የህዝብና የመንግስት ሀብት መታደግ ማለት ነው። ግንባታ በመጓተቱ ሳቢያ ሊኖር የሚችል የሀብት ብክነትም አይኖርም። በመሆኑም ችግሩ በአሰራር የሚፈታ ነውና መንግስት ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ይህን የዘርፉን ነቀርሳ መንቀል ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በተካሄደ የኮንስትራክሽን ንቅናቄ መድረክ ላይ እንዳሉት ፤ መንግስት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በጥናት ለይቷል፤ እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ይሰራል።

በቀጣይ 10 ዓመታት የግንባታው ዘርፍ በሀገሪቱ እድገት ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። የግንባታው ዘርፍ ለሙስና እና ለስርቆት የተጋለጠ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከስርቆት ነጻ የሆነ የግንባታ ዘርፍ በሌለበት ሁኔታ ብልፅግና ላይ መድረስ አዳጋች መሆኑን አስረድተዋል።

የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም ከመንግስት ጎን በመሆን በተለይ ሌብነትን በመጠየፍ ዘርፉ እያስመዘገበ ያለውን እድገት የላቀ ደረጃ ለማድረስ መስራት ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እና መንግስት ችግሩን አንዳቸው ወደሌላኛው ከመወርወር ይልቅ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል።

አዲስ ዘመን ጥር 5/2012