አንድ ሁለት ስለ ገና ጨዋታ

46

የባህል ስፖርት ለሰው ልጅ ከአኗኗር ዘይቤ አንፃር በየአካባቢው የሚያከናውናቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ነው። ባህል የአንድ ህብረተሰብ ልዩ ልዩ ማህበራዊ መተዳደሪያ ሥርዓቶችን፤ የኀዘንና የደስታ ስሜት መገለጫ የሆኑ ልዩ ልዩ ስነ ቃሎች፣ ጭፈራዎች ዳንኪራና አልባሳትን ያካተተ ሲሆን፣ ሲጠቃለል የሕዝቦች ማህበራዊ ህይወት ማሳያና የማንነት መገለጫ ነው። የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ የሚችሉና ብሔር ብሔረሰቦች የበለጠ እንዲቀራረቡ በማድረግ፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህላቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ ጉልህ ሚና አለው። የባህል ስፖርት የሰው ልጅ በተፈጥሮ በለገሰው ነገር ህልውናውን ለማኖር በሚያደርገው የዕለት ተዕለት ውጣውረድና እንቅስቃሴ አማካኝነት የተፈጠረ ማህበራዊ ጨዋታና እንቅስቃሴ ነው። የባህል ስፖርት በአዝጋሚ ለውጥ ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር እያደገና እየዳበረ የመጣ የህብረተሰብ ወጉና ማዕረጉ የሱነቱ መገለጫ ከሆኑ ቅርሶቹ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛውና  ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በፊት በተለያዩ አካባቢዎች፤ በመንደር፤ በቤተሰብና በደብር የተመሰረተ የባህል ስፖርት ጨዋታ በኢትዮጵያ እንደነበር የባህል ስፖርቶች የውድድር ሕግ በሚል ሰኔ 2006 በባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ተዘጋጅቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ድጋፍ የታተመው መጽሐፍ ያስረዳል። በዓለም አቀፍ ደረጃ «ሆኪ» ተብሎ የሚታወቀውን የገና ጨዋታ ኢትዮጵያውያን ከሦስት ሺ ዓመት በፊት ይጫወቱት እንደነበር  የዓለም ሆኪ ፌዴሬሽን በድረ-ገጹ ከሦስት ዓመት በፊት ያሰፈረው ጽሁፍ ያስረዳል። ያም ሆኖ ሆኪ አሁን ያለበት ደረጃና የኛው የገና ጨዋታ ለንጽጽር እንኳን የማይበቃ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ማንም መናገር ይችላል። የሆኪ ስፖርት መነሻው ከገና ጨዋታ መሆኑ ግልፅ ነው። ነገር ግን ይህን ተወዳጅ ስፖርት ማበልፀግና ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን ማጎልበት ባለመቻላችን ምዕራባውያኑ የግላቸው አድርገው አሁን ላይ መነሻ የሆነው የገና ጨዋታ በሆኪ ተውጦ እናገኘዋለን።

የገና ጨዋታ በሀገራችን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው፣ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ጨዋታ እንደሆነ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

መምህር ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር የተባሉ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ፤ ስለ ገና ጨዋታ ታሪካዊ አጀማመር ሁለት ትውፊቶች ተደጋግመው እንደሚነገሩ አስቀምጠዋል። ክርስቶስ ሲወለድ እረኞች ከመላዕክት ጋር አብረው እንደዘመሩና በወቅቱም የገና ጨዋታ መጫወት እንደጀመሩ አንደኛውን ትውፊት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡

ሁለተኛው ትውፊት ደግሞ ከሰብዓ ሰገሎች ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ንጉስ ሄሮድስ የሚባለው የዘመኑ ንጉሥ አዲስ የሚወለደው ህፃን የበለጠ ዝናና ክብር እንደሚያገኝ የሰማው ትንቢት ስላስደነገጠው በዚያን ጊዜ የተወለዱ ወንድ ህፃናት በሙሉ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ እያሳደደ ያስገድል እንደነበር ይወሳል። ሄሮድስ ታዲያ ክርስቶስ ሊወለድ መሆኑ ተነግሮት ስለነበር የት እንደሚወለድና ስለ አጠቃላይ ሁኔታው በቅርበት ለማወቅ በመፈለጉ አንድ ሰላይ የሰብዓ ሰገሎች ዓይነት ልብስ አስለብሶ፣ ከእነሱ ጋር እንዲቀላቀል ይልካል፡፡ ሰላዩ ከሰብዓ ሰገሎች ጋር ተቀላቅሎ ጌታ ወደሚወለድበት ሥፍራ ሲጓዙ፣ ይመራቸው የነበረው ኮከብ ድንገት ቀጥ ይላል፡፡ ይሄኔ ተጠራርተው መሃላቸውን ሲፈትሹ፣ ሰላዩን እንዳገኙት ይኸው ትውፊት ያስረዳል፡፡ ከዚያም ሰብዓ ሰገሎቹ ሰላዩን ይገድሉና ራሱን ቆርጠው እንደ አሁኑ የገና «እሩር» እየተቀባበሉ ተጫወቱበት ይላል – ሁለተኛው ትውፊት፡፡ ከዚያም በመነሳት የገና ጨዋታ ተፈጠረ ይላሉ፤ የታሪክ ተመራማሪው፡፡  ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለው፣ እስከ አሁን የቀጠለው የገና ጨዋታ፤ በየዓመቱ በታኀሣሥ ወር በተለይ በኢትዮጵያ የገጠሩ ክፍል ከብት  እረኞች በድምቀት ይጫወቱታል።

ከክርስቶስ ልደት በኋላም በተለያዩ ጊዜያት በወቅቱ ነግሰው በነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት ጊዜ፤ በመሳፍንት፤ በሹማምንቱ፤ በሎሌዎች፤ በሕዝቡ መካከል በሰንበትና በአውድ ዓመት የባህል ስፖርት ጨዋታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ውድድርና ፉክክር በማድረግ ይዝናኑበት እንደነበር በተለያዩ ጽሑፎች ተገልጿል።

በአፄ ቴዎድሮስ፤ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥታት ወቅት በራሳቸው ንጉሶቹ አዘጋጅነትና ዳኝነት በከፍተኛ ሁኔታ የባህል ስፖርት ጨዋታዎች ይካሄዱ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያኖችን ጥንካሬና ጀግንነት ለውጭ አገር ዜጎች ለማሳየት የኢትዮጵያ ጎበዝ ታጋዮችን ከውጭ አገር ከመጡ ዜጎች ጋር በራሳቸው ዳኝነት የትግል ውድድር በማወዳደር ላሸነፉ ኢትዮጵያኖች ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ይሸልሙ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል። አፄ ምኒልክ ደግሞ የራሳቸው የገና ተጫዋቾች በማደራጀት ከእቴጌ ጣይቱ ቡድን ጋር የገና ጨዋታ ውድድር ያደርጉ ነበር። እቴጌ ጣይቱም በስማቸው የከፈቱትን ሆቴል ለማስተዋወቅ የገበጣ ጨዋታ አዘጋጅተው ያጫውቱ ነበር።

በአሁኑ ወቅትም በገጠር የሚኖረው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አካላዊ ብቃቱን ከሚያዳብርባቸውና መንፈሳዊ እርካታን ከሚጎናፀፍባቸው እሴቶች መካከል የሱነቱ መለያ፤ ባህልና ልምዱን ወግና ማዕረጉን ከሚገልፅባቸው መንገዶች አንዱ የባህል ስፖርት ነው። በተለይም የተዳከመ አዕምሮውንና የዛለ አካሉን የሚያነቃቃባቸውና የሚያፍታታባቸው፤ በትርፍ ሰዓቱና በበዓላት ቀናት ማህበራዊ ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት መሳሪያው የባህል ስፖርት ነው። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የባህል ስፖርቶች በተለይም በበጋው ወራት የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ገና በትክክል በአገራችን መቼ እንደተጀመረ በጽሑፍ የተደገፈ መረጃ ባይገኝለትም እንደሌሎቹ የባህል ስፖርቶች ከክርስቶስ ልደት በፊት ይዘወተር እንደነበር በአፈታሪክ ይነገርለታል። በእዚህም የክርስቶስ ልደት ወይንም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ እረኞች የገና ጨዋታን ከታህሳስ ጀምሮ እስከ ጥር ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ይጫወቱ እንደነበር የቀድሞ አባቶች ይናገራሉ።

በተለይም  የገና ጨዋታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚካሄደው መኸር በተሰበሰበበት አካባቢ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ ከሰዓት በኋላ እሩሩ ለዓይን መታየት እስከተቻለበት ጊዜ ድረስ  ነበር። ጨዋታው የሚካሄደው በሁለት የቡድን አባቶች አማካኝነት እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተለየ ስም እያስመረጡ ወደ ቡድናቸው ይቀላቀላሉ።ይህም የሚሆነው ሁለት  ቡድኖች ከአንድ መንደር ወይም ቀበሌ ከሆነ ብቻ ነው።

ሌላው ከፍተኛ የውድድር ዓይነት ደግሞ የቡድን አባቶች የተመደበው ደብር ከደብር፤ የላይ አምባ ከታች አምባ፤ የአንዱ ቀበሌ ከሌላው ቀበሌ ከሆነ ብቻ ነው።እንዲሁም ባገቡና ባላገቡ መካከል ተካፍለው የጨዋታውን ዓይነት በስምምነት የሚፈፀም ነው።በዚህ የጨዋታ ዓይነት ለመንደር ወይም ለደብር ገና ለመጫወት የፈለጉ ሁሉ የሚሳተፉበትና እንዲመጣ ለቡድኑ መግባት የሚችልበት የተጫዋች ቁጥር ማዕቀብ የሌለውና ሊበላለጥ የሚችል የትርምስ የገና ጨዋታ ሲሆን አንድ ተጫዋች ሲወጣና ሲገባ የቡድኑ አባላት የማይጠየቅበት ነበር። ሌላው በቡድኑ አባቶች በምርጫ የሚጫወቱ ገና ግን አንዱ በጨዋታው ተጎድቶ ቢወጣ ወይም አዲስ ለመግባት ቢፈልግ ለቡድኑ አባት ለጎበዝ አለቃ ወይም ለአጫዋቾች ተናግሮ ሲፈቀድለት የሚገባበት ነው። የገና ጨዋታን ይጫወቱበት የነበረው ዱላ ከጫፉ ቀለስ ያለ የእንጨት ገና ሲሆን የመጫወቻ ሩሯም (ጥንጓም) ከቆዳ ወይም ከዛፍ ስር ድቡልቡል ሆኖ የተዘጋጀ ሩር በመምታት፣ በማንከባለልና በመለጋት ነበር። አለባበሳቸውም ጉልበት ላይ የሚቀር ሱሪ፣ እጀ ጠባብ፣ ከወገቡ ላይ የሚጠመጠም ድግ ለብሰው ይጫወቱ ነበር። በአንዳንድ አካባቢ የገና ጨዋታ በሚደረግበት ጊዜ አንድ የጎበዝ አለቃ ከአማካሪዎቹ ጋር ከመሃል ሜዳ አቆራቋዥና ጨዋታውን የሚመሩ አራት የድንበር ጠባቂዎች ይደረግለት ነበር። የጨዋታው ፍፃሜም በግብ ወይም በነጥብ የሚለይ ነበር።

የገና ጨዋታ ብዙ ዓይነት ውድድር ይደረግበት ነበር። ለምሳሌ ያህልም ቁርቁዝ፤ ሙጭ፤ ቀልቦ መለጋትና አፍሶ መለጋት ይጠቀሳሉ። አፍሶ መለጋት ከባድ የአውዳመት ጨዋታ ሲሆን አፍሶ በመለጋት የሚጫወቱት ነው። ህግና ሚና በሚከበርበት ጊዜ ደግሞ ቀልቦ መለጋት ጨዋታ ላይ ይውላል። ሙጭ ጨዋታ በመጥረግ ብቻ እንጫወት ብለው በስምምነት ያገኙትን የሰውንም እግር ሆነ ጥንጉን በመጥረግ የሚጫወቱት ነው። ቁርቁዝ የተባለው አጨዋወት ህግን በመከተል በሚናህ በማለት ጥንጓን በኃይል ሳይጫወቱ ወይም ሳይመቱ በማንከባለል ብቻ የሚጫወቱት ጨዋታ ነበር።

በቀድሞው የገና ጨዋታ ጊዜ ጨዋታው የሁሉም መሆኑን ለመግለፅ « በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ» እየተባለ በሚደርሰው አደጋ ምንም ዓይነት ቂም መያዝና አደጋ መፍጠር ወይም ጠብ የማያስከትል እንደነበር ይወሳል።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011

ቦጋለ አበበ