በዓላት እና ኪነ ጥበብ

26

 

ምግብ ያለ ጨው በዓላት ያለ ኪነ ጥበብ ጣዕም የላቸውም፡፡ በዓላትን አድማቂው፣ ክብረ በዓልን አስናፋቂው ኪነትን  ከበዓላት ነጥሎ መመልከት አዳጋች ነው፡፡ አስቲ አስቡት በዓላትን ያለ ኪነጥበብ ማክበር አይከብድም?  ገናን «አሲናዬ አሲና ገናዬ» ሳይባል አዲስ ዓመትን ህጻናት እንቁጣጣሽን «አበባ አየሽወይ… ለምልም» ሳይሉ ቢያልፉ በዓሉ የጎደለ አይመስልም፡፡ በዓል ያለ ኪነ ጥበብ ይፈዛል፡፡ በዓልን በዓል የሚያስመስለው የሚያደምቀው ጥበብ ነው፡፡ የበዓላትን ድባብ ከፍ የሚያደርገው ኪነት ነው፡፡

ኪነ ጥበብ ከስፋትና ፋይዳው አንጻር መገኛው ከጓዳ እስከ መድረክ ነው፡፡ እናቶች ለበዓላት ዝግጅት ሲያደርጉ ማህበረሰባዊ ዜማዎች በጋራና በተናጥል ያዜማሉ፡፡ ልጆች  ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቀው ተለምዷዊ የማህበረሰብ ዜማና ክዋኔ በመፈጸም ለበዓሉ ድምቀት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህ የኪነትና የበዓላት ትስስርን የጠበቀ ስመሆኑ ማመላከቻ ነው፡፡

ጥበብን ባማረ ዜማ ይቀኙታል፡፡ ስራቸውን በኪነት አጅበው ያበጁታል፡፡ አባቶች በየ ስራ መስካቸው ጥበብን እየተቀኙ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ይከናውናሉ፡፡ ማህበረሰቡ ታሪክ ያቆየለትን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ጥበቡን በክብረ በዓሉ ይቀኛል፡፡ ሀገሩ በኪነ ጠበብ ታጅቦ በሚውለው ክብረ በዓል ይደምቃል፡፡

ዛሬ ላይ በዓላት በመጣ ቁጥር መደበኛ ያልሆኑ ግብይቶች እየተለመዱ መተዋል፡፡ እነዚህ ዘምነውና ተሽለው የሚቀርቡ መገበያያዎች /ባዛርና አውደ እርዕዮች/ በኪነ ጥበብ ታግዘው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉና እየሰፉ ይገኛሉ፡፡ ኪነ ጥበብም የሁነቶች ማስጌጫ ቅመም፤ የሁነቱ ተሳታፊ መጥሪያ ጭምር ነው፡፡ በክብረ በዓላት ምክንያት የሚዘጋጁ አውደ እርዕዮችና ባዛሮች የሚያደምቀው ኪነ ጥበብ ነው፡፡  በኪነ ጥበብ ለመሰብሰብና የሚፈልጉትን መልዕክት  ለማስተላለፍ ኪነ ጥበብ ሁነኛ መንገድ ማድረግ ተለምዷል፡፡ ክውን ጥበባቱ በመድረክ ታግዘው የሻጭና ገዢ መገናኛ ሰበብ ናቸውና በኪነ ጥበብ ያልታጀበ ባዛርና አውደ እርዕይ የተሳታፊው ቁጥር የሳሳ መሆኑ የማይካድ ነው፡፡

ሰሞኑን በኢግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለው የገና ባዛር ብዙ የጥበብ ባለሙያዎች እንደተሳተፉና ለኪነ ጥበብ ባለሙያው ትልቅ ጠሜታ መፍጠር እንደቻለ ተሳታፊ አርቲስቶች ይገልጻሉ፡፡ በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ በሚገኘው እና ዛሬ በሚጠናቀቀው የዘንደሮው የገና ባዘር ከ100 በላይ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ሰባት የሙዚቃ ባንዶች፣ የዳንስ ቡድኖች፣ ልዩ ልዩ ትርኢት እቅራቢዎችና ኮሜዲያንን ተሳታፊ ናቸው፡፡ ኮሜዲያን ደምሴ ፍቃዱ /ደምሴ ዋኖስ/ ከተሳታፊዎቹ አንዱ ነው፡፡ ኪነ ጥበብ ነገሮችን ማጣፈጫ በመሆኑ የባዛሮች ማድመቂያ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የባህል ልብሱን ተጎናጽፎ  ወደ መድረክ ሲያመራ ያገኘሁት ኮሜዲያን ደምሴ «ኪነ ጥበብ ያላካተተ ዝግጅት ቀለም እንዳልተቀባ ቤት  ይደበዝዛል» ይላል፡፡ በዓልን ምክንያት አድርጎ የሚዘጋጁ ባዛሮች ለኮሜዲያን ደምሴና ለሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከህዝቡ ጋር ለመገናኘት እድል እንደፈጠረላቸው ይናገራል፡፡

በዓላትን ምክንያት አድርገው የሚዘጋጁ አውደ እርዕይና ባዘሮች ለኪነ ጥበቡ እድገት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡የኢግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጀው የገና ባዘር አዘጋጅ የሆነው ሀበሻ ዊኪሊ ባለቤት አቶ አዶኒክ ወርቁ  ከ5 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ ለኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ብቻ በጀት ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ያለ ኪነ ጥበብ የተሳካ ዝግጅት ለማድረግ ማሰብ  እንደሚያስቸግር የሚናገሩት አቶ አዶኒክ በድርጅታቸው የተዘጋጀው የባዘር ዝግጅት ኪነ ጥበባዊ ድግሱ ከፍ ያለ እንዲሆን  የተደረገው ታስቦበት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዝግጅቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገቢን ከፍ ማድረጉ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው በማጠናከርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግም ያግዛቸዋል፡፡ በተለይ በዳንስና በልዩ ልዩ ትርዒትና ተስጥዖ ተሳታፊ የሆኑ አዳዲስ ተሳታፊዎች ጥሩ ልምድ እንዲቀስሙም ባዛሩ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ያምናሉ።

ብሩክ ጥጋቡ በዚሁ ባዛር ላይ በድምጽ ተስጥዖ ውድድር ለመካፈል የተገኘ ወጣት ነው፡፡ መድረኩ የመጀመሪያው መሆኑን የሚናገረው ብሩክ የገና ባዘር ተስጥዖውን ህዝብ ፊት ቀርቦ ማሳየት አስችሎታል፡፡ በበዓላት ምክንያት የሚዘጋጁ አውደ እርዕዮችና ባዛሮች እንደ ብሩክ ያሉ ጀማሪ ተሳታፊዎችን ወደ ኪነ ጥበብ በማቅረብ የጎላ ሚና እንዳለው እሙን ነው፡፡

ኪነ ጥበብ ለባይተዋሩ ባለ ውለታው ነው፡፡ የአውድዓመት ድባብ ፈጥሮለት ሀገሩ ላይ የተገኘ ያህል ልዩ ምናባዊ አውድ ይፈጥርለታል፡፡ ሳይኖር በምዕናብ የሚሳል አረንጓዴ መስክ፤ እንደ ትኩስ ሙልሙል ዳቦ የሚገመጥ፤ በፍቅር  የሚያጣጥ ሙት፤ እንደ ልዩ ማዕዛ የሚምጉት፤  የአውድዓመት የእናት ጓዳና ሳሎን የሚያውድ ሽታ  በኪነጥብብ ውስጥ ይፈጠራል፡፡ ይህም የኪነ ጥበብ ሃያልነት ማሳያ የጥበብ ትልቅነት መግለጫ ሌላ ማሳያ ነው፡፡

ዮናታን አርዓያ ስራው ሙዚቃ ማጫወት /ዲጄነት/ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል መድረክ ላይ ከመድረኩ ዙሪያ የሚለቃቸውን ጣዕመ ዜማዎች ለማድመጥ በከበቡት ታዳሚያን ፊት ቆሞ ከማጫወቻው ሙዚቃ ሲመርጥ አገኘሁት፡፡ መድረክ ላይ ሁኖ የታዳሚን ስሜት እየተከተሉ የተለያዩ ሙዚቃ ስልቶችን ማጫወት ለመድረኩ ድባብ ማማርና ለዝግጅቱ መድመቅ ወሳኝ መሆንኑ ያስረዳል፡፡ «ያለ ሙዚቃ ባዛርም ሆነ አውደ እርዕይ የለቅሶ ያህል ነው» የሚለው ዮናታን ሙዚቃ አውድን አድማቂ ሁነትን አሳማሪ መሆኑን ያምናል፡፡

ኪነ ጥበብ ከሩቅ ይጣራል፤  ከፍ ባለ ድምጽ ስሜትን ይቆጣጠራል፤ ጥበብ እሩቅ ሆኖ በምዕናብ ሀገር  ያደርሳል፡፡  ከሀገሩ የራቀን ውቂያኖስ  አቋርጦ  የሚኖርን ሰው በኪነ ጥበብ ናፍቆትና ትዝታውን ያስታግሳል፡፡  ከአድማስ ማዶ ያለውን የሀገሩን ናፍቆት መወጫው የቀዬውን ትዝታ መላሹ መሳሪያ ኪነ ጥበብ ነው፡፡ ባህላዊ ዜማውን ሲሰማ፤  ማህበረሰባዊ ትውፊቱን ስያይ፤  እሩቅ ሆኖም በአካል የተገኘ ያህል ይሰማዋል፡፡ ኪነ ጥበብ ውስጥ ሀገሩን ባህሉን ማንነቱን ያያል፡፡ ባለበት ሀገር ኪነ ጥበብን ማስጌጫ አድጎ በዓሉን ያከብራል፡፡

የኪነ ጥበብ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍተኛ መሆን በማሳያ የሚገልፀው ኮሜዲያን ደምሴ ከአምስቱ ሀገራዊ የሙዚቃ ቅኝቶች ውስጥ አንዱ የሆነው  አንቺ ሆዬ ከበዓል ውጪ እንኳን ሲሰሙት የበዓልን ድባብ ይፈጥራል። ኪነ ጥበብ በምዕናብ ምስል ከሳች የሆነ የትዝታ ፈረስ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በዓላት በመጡ ቁጥር በዓል በዓል የሚሸቱ ሙዚቃዎችና እቤታችን በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ባይኖሩ በዓሉ እንዴት ሊደበዝዝ እንደሚችል መገመት ከባድ አለመሆኑንም ያስረዳል፡፡

በመዲናችን የዘንደሮውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ከተዘጋጁ ባዘርና አውደ እርዕዮች መካከል በጆርካ ኤቨንት የተዘጋጀውና በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደው ሌለኛው ነው፡፡ በዚህ የባዛር ዝግጅት ላይም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን በማቅረብ ለዝግጅቱ ድምቀት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአምስት የተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች የታጀበው ድግስ ከ26 ያላነሱ የባህልና ዘመናዊ ሙዚቃ ተጫዋቾችን አሳትፏል፡፡

በድርጅቱ የሁነት ማስተባበር ኃላፊ የሆኑት አቶ ብሩክ ዘነበ የባዛሩ ድምቀት የኪነ ጥበብ ነውና በዝግጅት ወቅት ልዩ ትኩረት መስጠታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ኪነ ጥበብ በባዛርና አውደርዕይ ላይ ለማድመቅ መገኘቱ የተዘጋጀው አውደእርዕይ አላማውን ያሳካል፡፡ በሌላ በኩልም አውደእርዕዩ ወይም መድረኩ ለኪነ ጥበቡ ጥሩ እድል ፈጥሮለታልና የተሻለ እድገት ያሳያል፡፡ ጥበብ አውድ ካላገኘ ምንም ስላልሆነ በባዓላት ምክንያት በባዛርና አውደ እርዕይ እድል ማግኘቱ መልካም አጋጣሚው ነው፡፡ በዓላት ኪነ ጥበብን ይደግፋሉ፤  በአንጻሩ ደግሞ ኪነ ጥበብ በዓላትን ያደምቃል፡፡

መሰል ዝግጅቶች ለኪነ ጥበብ ባለሙያውና ለኪነ ጥበቡ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል። የተባለበት ምክንያት ከላይ የተጠቀሰውና በርካታ ፋይዳዎችን መጥቀስ ያስችላል፡፡ የጥበብ ስራ ለማህበረሰቡ ቀርቦ የሚፈለገው ጠቀሜታ መስጠት ካልቻለ ምንም ነው፡፡ ለጥበብ ባለሙያው የጥበብ ስራውን የሚያቀርብበት መሰል መድረኮች መስፋፋትና እድሎችን መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011

ተገኝ ብሩ