ኪነጥበብ ማበረታቻ ለምን ተነፈገው?

13

ኪነጥበብ የአንድን ህብረተሰብ የካበተ ዕውቀትን፣ ዕምነትን፣ አስተሳሰብን፣ አመለካከትን፣ ሥነ-ጥበብን፣ ፍልስፍናን፣ ሥነ-ምግባራትን፣ ወጎችን፣ ሥነ-ቃሎችን፣ እሴቶችን፣ የአኗኗር ዘይቤውን፣ ልማዶቹን፣ የፈጠራ ችሎታውን እንዲሁም ሌሎች ቁሳዊና ቁሳዊ ያልሆኑ የማንነቱ መገለጫዎችን በአንድነት በማምጣት የሰው ልጅን ህይወት ይቀይራል። ይሁን እንጂ በዚህ ልክ ትኩረት የተቸረው እንዳልሆነ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ አዋጁ ብቻ መመልከት ይቻላል።

ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አመለካከቶችን ለመግራት በሚፈለገው ልክ ኪነጥበብ ወሳኝ መሆኑን መንግሥት እንዳልተረዳም ይነገራል። ይህንን አስመልክቶም ባለፈው ሳምንት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዘርፉ በኢንቨስትመንት ኮድ ውስጥ እንዲካተት ለማስቻል የተዘጋጀ መነሻ ጽሁፍ አሰናድቶ ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ተወያይቶበታል። በተለይ ኢንቨስትመንት ማበረታቻውን በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

አገሪቱ የተረጋጋ ኢኮኖሚ፣ ተስማሚ የአየር ፀባይ እና የተፈጥሮ ሃብት፣ ሰፊ የአገር ውስጥ ገበያ፣ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ኃይል፣ እያደገ ያለ መሰረተ ልማት፣ ነፃ ገበያ፣ የህግ አስተማማኝ ጥበቃ እንዲሁም ለተመረጡ ዘርፎች የሚደረግ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች አሏት። ይህ ሁሉ በሌለበት አገር እንኳን ባህልና ኪነጥበብ ትልቅ ኃይል ኖሯቸው አገርን በኢኮኖሚ ይገነባሉ። ሆኖም በአገር ደረጃ ግን ማበረታቻ እንደማያስፈልገው ተቀምጦ እንዳይሰራ ተደርጓል ይላል የመነሻ ጽሁፉ።

ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የሚደረገው የቀረጥ፣ የገቢ ግብር፣ የጉምሩክ ቀረጥ ማበረታ ቻዎች… ወዘተ የኪነጥበቡን ኢንዱስትሪ አያካትትም። በዚህም የግል ባለሃብቶች በዘርፉ በስፋት እንዳይሰማሩ ሆኗል።  እይታዊ እና ትዕይንታዊ ጥበባት ስር የሚመረቱ ምርቶች እና የሚሠጡት ግልጋሎትም ቀንሷል። በተለይም  የመልቲሚዲያ ኢንዱስትሪውን አቅፈው የያዙት ዘርፎች በእጅጉ እንዲዳከሙ ዕድል አመቻችቷል ይላል መነሻ ጽሁፉ።

ለዘርፉ የተሰጠው አነስተኛ ግምት፣ የመስሪያ ቦታ እና ገንዘብ ችግር፣ የጥራትና የዲዛይን ችግር እንዲሁም የመረጃ ችግር ዘርፉ እንዳያድግና የታቀደው ላይ እንዳይደርስ ከማድረጉም በላይ ዘመንኛን የተከተለ አሰራር ለአገር እንዳያበረክት ገድቦታል። በእርግጥ በህግ ደረጃ ከህገ መንግሥቱ እስከ ኪነጥበብ ዘርፉ ድረስ አጋዥ የሆኑ ነገሮች ተቀምጠውለታል። ለአብነት በህገመንግስቱ አንቀጽ 91 ንዑስ አንቀጽ 1ላይ «መንግሥት መሠረታዊ መብቶችንና ሰብዓዊ ክብርን፣ዴሞክራሲንና ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ ባህሎችና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ኃላፊነት አለበት፤ ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ደግሞ መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ኪነጥበብን፣ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ግዴታ አለበት» ተብሏል።

በፊልም አዋጁ ላይም እንዲሁ ማበረታቻ እንዴት እንደሚያስፈልገው የተቀመጠ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ፊልሞችን ለማምረት የሚያስችሉ የተለያዩ መሳሪያዎች በአገር ውስጥ በቀላሉና በብዛት እንዲገኙ መፍቀድ፣ ለፊልም ማምረቻ የሚሆን የስቱዲዮ መንደር በግል ዘርፉ ወይም የገበያ ክፍተቱን ለመሙላት በሚያስችል የመንግሥት ተሳትፎ እንዲገነባ ማስቻል፣ የፈጠራ፣ የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች እንዲከበሩ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መንግሥት ያደርጋል» ይላል።

ለፊልም ማምረት ሥራ ደረጃቸውን የጠበቁ የፊልም ስቱዲዮች ለሚገነቡ ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ከሀገር ውስጥ ፊልም አምራቾች ጋር በጥምረት ለሚሰሩ የውጭ ፊልም አምራቾች ተገቢ ድጋፍ ይደረጋል፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራልና በዘርፉ መሰረተ-ልማቶችን ለማስፋፋት ፍቃድ ለሚጠይቁ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣል ብሏል።

ወደ ዘርፉ የሚመጡም ሆነ በዘርፉ ያሉ ሲኒማ ቤቶች፣ የፊልም አሰራጮች፣ አታሚዎች፣ ፕሮዲዩሰሮች፣ እንዲሁም የፊልም የትምህርት ተቋማት አቅማቸው እንዲጎለብትና እንዲጠናከሩ የብድር አገልግሎት ያገኛሉ፤ የዘርፉ የትምህርት ተቋማት ለብቁ ስልጠና የሚጠቅሙ ዘመናዊ ቁሶች ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡ የቀረጥ ማበረታቻ ያገኛሉ ይላል። ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነና ነገሩ ሁለቱ ሀሳቦች በእጅጉ ተራርቀው ነው የሚገኙት።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የፊልም ሰሪዎች ማህበር አባል የሆነው ጋሻው ሞላ አንድ ሃሳብ ያነሳል። የፊልም አታሚዎች፣ አሰራጮች እና አሳይዎች በተጠናከሩ ማህበራት መመራት እንዲችሉና በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ ዕድል ይመቻቻል ተብሎ በስንት ግፊት ተነግሯል። ግን በምንም መልኩ ይህ ዕድል አልተሰጠም። የሁለትና የሦስት ሰዎች ሥራ እስኪመስል ድረስ እዚህ ቦታ ገብታችሁ ሥሩ ነው የሚባለው። በ1998 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ባሳተመው መጽሄት የኢንቨስትመንት የትኩረት መስኮች ተብለው የተለዩ ነበሩ። በዚህም መንግሥት ድጋፍ ይሰጣቸው ያለው በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር በአነስተኛ ወለድ፣ ወደ ውጭ ለሚልኩ (ምርታቸ ውን/ ማበረታቻ )፣ የግብር መክፈያ የዕፎይታ ጊዜ፣ በተመጣጣኝ የሊዝ ክፍያ ቦታ መሰጠቱ፣ የቴክኒክ ዕገዛ ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁንና ኪነጥበብ ዘርፉ አያስፈልገውም ተብሎ በአዋጅ ተቀምጧል። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ዘርፉ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ጀምሮ ትኩረት እንዳልተቸረው ነው።

ኢንቨስትመንት በልማት መስክ ለመስራት የሚያስችል የአስተዳደርና የሀብት ቅንጅት እውቀትና ጥበብ በማጐልበት በኩል የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም። ነገር ግን በኪነጥበቡ ዘርፉ ካልታገዘ ውጤታማ መሆን አይችልምና ማበረታቻው ከሌሎች ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ለዚህ ዘርፍ እንደሆነ ይናገራል።  ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በወጣው አዋጅ ላይ የኢንቨስትመንት ዓላማዎች ተብለው ከተጠቆሙት ውስጥ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ልማት ማፋጠን፣ የግሉን ዘርፍ ሚና ማሳደግ ነውና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት እንዲኖርና ከላይ የተጠቀሱት ተፈጻሚ እንዲደረጉ ከተፈለገ ከኪነጥበብ የበለጠ ኃይል ያለው የለምና ልብ ይባል ይላል።

አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ፤ የግል ባለሀብቱ በዘርፉ ተሠማርተው የመንግሥትን ሸክም በመጋራት እራሳቸው ተጠቅመው አገራቸውንና ህብረተሰቡን የሚጠቅሙበት ሁኔታ እንዳይፈጥር በኪነጥበቡ ዘርፍ ማበረታቻ አይደረግም ተብሏል። ይህ ደግሞ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንዳይሰሩ የሚያደርግና እንዳያድጉ በችግር ውስጥ አልፈው ሁልጊዜ እንዲሰሩ የሚያደርግ እንደሆነ ይናገራል።

በሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ቁጥር 84/95 ስለ ኢንቨስትመንት ማበረታቻ እና ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ስለተከለከሉ የሥራ መስኮች ባወጣው ደንብ አንቀጽ 10 ላይ ‹‹የጉምሩክ ቀረጥ ነፃ መብት የማይፈቅድላቸው›› በሚል ርዕስ ስር ‹‹የማስታወ ቂያ ሥራ አገልግሎት፣ የፊልምና መሰል ሥራዎች፣ የሲኒማ እና ቴአትር ቤቶች አገልግሎት ንግድ ሥራ›› በሚል ኪነጥበቡ በማበረታቻው ተጠቃሚ እንዳይሆን ገድቦታል የተባለው ደግሞ በእጅጉ የሚያሳዝንና አሳፋሪ ነው ይላል።

ለዚህም ምክንያቱ ኢንቨስትመንት ማለት በአዋጅ ቁጥር 28ዐ/1994 መሰረት አዲስ ድርጅትን ለማቋቋም ወይም ነባር ድርጅትን ለማስፋፋት ወይም ለማሻሻል በባለሀብት የሚደረግ የካፒታል ወጪ ነው፤ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚና ባህል ለማሳደግ ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች መካከልም ይጠቀሳል። ገንዘብን ከሰው ጉልበት፣ ከመሬት፣ ከጥሬ ዕቃ… ወዘተ ጋር በማቀናጀት በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ምርትን ለማምረት ወይም አገልግሎት በማቅረብ ትርፍ ማግኘት ላይ የሚያተኩርም ነው። ነገር ግን የፈጠራ ሥራን ትቶ ማደግ እንዴት እንደሚቻል ያልተገነዘበው አካል ዘርፉ ማበረታቻ አያስፈልገውም ብሎታል።

ኪነጥበብ በሌሎች አገሮች የባህልና የወግ ሥራዎችን እየሰራ ነው፤ ገንዘብ ወደሚያመጣው ቦታም እየተጓዘ ይገኛል። አገሩ ላይ ግን ከአመለካከት ጀምሮ መስራት ያለበትን አልሰራም። ለዚህ ተጠያቂው ደግሞ ቃል የገባውን መንግሥት አለማድረጉና በአዋጅ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ አያስፈልገውም መባሉ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ደግሞ አገር ባላት ጥበብ እንዳትጠቀም ከማድረጉም በላይ በባህል መገንባት እንዳይቻል ያደርጋል። ዜጋውም ሁልጊዜ ውጪ ናፋቂነትን እንዲላበስና በባህል የተገነባውን እውቀት ለማስተማር ሲሞከር አይመቸኝም የሚል እንዲበዛ ዕድል ያመቻቻል ይላል። የአገር ማንነት በውጪው ዓለም መተካቱ ደግሞ ምን ያህል መውደቅ እንደሆነ ማሰብ ይገባል ባይ ነው።

«ኢንቨስትመንት ልማትን ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ተስማሚ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትም ይጠቅማል። ይህ ደግሞ በተለይ በኪነጥበቡ ላይ ሲታይ ሰፊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል» የሚለው አርቲስት ደሳለኝ፤ ለአብነት በአንድ ፊልም ላይ ብቻ በርካታ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። በዚህም የሥራ ዕድል በመፍጠር አገር በልጆቿ እንድትገለገል ያደርጋታል። ይሁን እንጂ ይህ ዘርፍ ከመዝናኛ ያለፈ ተግባር እንደሌለው በመታሰቡ ማበረታቻ አይሰጠውም መባሉ ትክክል አይደለምና መታሰብ እንዳለበት ያስገነዝባል።

«ከጉምሩክ ቀረጥ 100 በመቶ ነፃ መሆን፣ ዕቃዎችና መሣሪያዎችን በነፃ ማስገባት፣ ከውጭ ከገባው መሣሪያ 15በመቶ ባልበለጠ የመለዋወጫ ዕቃዎች ማስገባት፣ ከ2 እስከ 7 ዓመት የሚደርስ የገቢ ግብር ቅነሳ እንደ የኢንቨስትመንት ዓይነቱ የሚወሰን ቢሆንም ለዘርፉ ምንም አይነት ማበረታቻ አልተደረገም» የሚሉት ደግሞ ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደመጡ የገለጹት አቶ አዲሱ ታምሩ  ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኪነጥበቡ ወደ ውጭ የሚልከው ምርት ብዛት፣ ኪሳራን ለማካካስ የእፎይታ ጊዜ መስጠትን ይፈልጋል። የቀረጥና የግብር ሥርዓቱ በሥነ ጥበብ ላይ የጣለው የመዝናኛ ግብርም ከሌሎች በርካታ የታክስ ጫናዎች ጋር ተደማምረው ኢንዱስትሪው ላይ በስፋት እንዳይገባ ያደርጉታልና ይህ መታየት አለበት። ከዚያ ባሻገር የቴአትር፣ የሙዚቃ፣ የስዕል መሳሪያዎች ላይ የሚጣሉት ከፍተኛ ቀረጥ በአገር ውስጥ አስመጪዎች ላይ ያለው ጫና ከፍተኛ መሆኑና የኪነጥበብ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ በማዕከላት ግንባታ፣ በትምህርት እና ስልጠና፣ በማምረት እና ከውጭ አገር በማስገባት… የግል ባለሀብቱ በስፋት እንዳይሰማራ አድርጓልና በማበረታቻው ማገዝ የአገሪቱ የቤት ሥራ መሆን አለበት።

በኢንቨስትመንት ህጐችና ደንቦች ውስጥ ኪነጥበብ በአግባቡ አለመገናዘቡ የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን ተሳትፎ እየገደበው መጥቷል ያሉት ደግሞ በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክቶሬት የባህል ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተፈሪ ተክሉ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የባህል ኢንዱስትሪ ትልቅ ካፒታል የሚጠይቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው። አንድ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለው ስቱዲዮ ለመገምባትም ሆነ ለዛ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለመግዛት ትልቅ ካፒታል ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት ማበረታቻውን መፍቀድ ግዴታው ነው። በዘርፉ የሌሎች አገራትን ባለሃብቶች ተሳትፎ በማሳደግ ወደ ውጭ የሚወጣ ሃብት እንዲኖር ማድረግ ላይ መሰራት አለበት። ሰፊ የሰው ኃይል የሚጠይቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሆኑም ዘርፉን ተጠቅሞ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ይህ ዕድል መታለፍ የለበትም ይላሉ።

ኪነጥበብ መልካም እሴቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ባህልን ያዳብራል። መሰረታዊ ትምህርት ያላገኙ ዜጎችን እንኳ ለመድረስ ዘርፉ ትልቅ ፋይዳ አለው። እናም የዘርፉ አቅም ለመጠቀምና አገልግሎት ላይ ለማዋል ኢንዱስት ሪውን ማነቃቃት ተገቢ ነውና ከመንግሥት የላቀ ድጋፍ ይጠይቃል ይላሉ።  የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ የመዝናኛ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባትም ኪነጥበቡ በማበረታቻው መደገፍ እንዳለበት መታመን አለበት።

ኪነጥበብ በአገር የሚመጡ ቱሪስቶች ገንዘባቸውን አሟጠው በአገሪቱ ላይ እንዲያውሉ ኃይል አለው። በዚህም የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ነው። ስለሆነም ለዘርፉ ማበረታቻው ወሳኝ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበትና  የኢንቨስትመንት ማበረታቻን እንደ አንድ ችግር መፍቻ መሳሪያ ተወስዶ ዘርፍ ዘለል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል። በተጨማሪም መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ሙስናንና የስነ-ምግባር ጉድለትን ማረቅ፣ የአገርን ወይም የአካባቢን ገፅታ ለመገንባት ማዋል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011

ጽጌረዳ ጫንያለው