በዜማ የተቃኘች ሕይወት

34

የሰው ልጅ ሁሉም እያንዳንዱ አብሮት የሚገኝ ስጦታ አለው። ግን ይኽን ለይቶ አውቆ፤ አውቆም አጥብቆ ይዞ፤ በዛም ጸንቶ የሚያገለግልና የሚገለገልበት ብዙ ሰው አይደለም። የተሳካላቸውና ባወቁበት ሙያ ጸንተው የሚቆዩትን ታድያ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሳናነሳቸው አንቀርም። እነሆ ዛሬ ደግሞ ሕይወት እንዲህም ናት ስንል አንድ አንጋፋ ባለሙያን እንግዳ አድርገን ቀርበናል።

እንግዳችን ከመናገር ማዜም ይቀናቸዋል፤ ወግና ጨዋታቸውን ሁሉ መሰንቆ እየገዘገዙ፤ አልያም ክራር እየገረፉና በገና እየደረደሩ ቢሆን የሚጠሉ አይመስሉም። ምንአልባትም በሕይወታቸው ንግግር ካደረጉበት ጊዜ የሚልቀው ያዜሙበት ይሆናል። ዘመናቸውን ከክራር፣ መሰንቆና በገና ጋር አሳልፈዋል። የኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ራሳቸው ሳያውቋቸው ይቀራሉ?

በብዙ የዓለም አገራት መሣሪያዎቻቸውን፣ ሻከር ያለ ሳቢ ድምጻቸውን እና ከምንም በላይ አገራቸውን ይዘው ተንቀሳቅሰዋል። ዛሬም ጊዜን አሸንፈው ከእድሜና ግሳንግሱ ጋር እየተጋፉ ማልደው በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ጊቢ ይገኛሉ። የዛሬው የሕይወት እንዲህ ናት እንግዳችን «የአገርኛ ሙዚቃ አውራ» የሚባሉት ዓለማየሁ ፈንታዬ።

መልዕክተ ዮሐንስ

ቦታው በቀድሞው ወሎ ክፍለ አገር ዋግ ኸምራ ሰቆጣ ተብሎ የሚጠራ ነው። በክህነት አገልግሎት የሚሰጡትና በአካባቢው የታወቁት ቄስ መምሬ ፈንታዬ ወልደገብርኤል የበኩር ልጃቸው ፈለጋቸውን ተከትሎ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ይሆን ዘንድ ይጓጉና ይፈልጉ ነበር። እናም ዓለማየሁ ሲሉ ስም ያወጡለትን ልጃቸውን ወደ ከብት ማገድና እረኝነት  አልላኩትም። ይልቁንም ፊደል ይቆጥር ዘንድ ወደ የኔታ እንጂ።

በየኔታ ፊት ፊደል ተቆጠረ፤ መልዕክተ ዮሐንስ በቁጥርና በዜማ ተወጣና ንባብ ታወቀበት። ትንሹ ዓለማየሁ የዮሐንስን መልዕክት ቀሽሮ ከያዘ በኋላ ዳዊትን ከሚደግሙት ተርታ ተሰለፈ። ከዚህም በኋላ የዲቁና ማዕረግ ይቀበል ዘንድ ጊዜው ነበር። «ማዕረገ ዲቁና የተቀበልነው አቡነ ቄርሎስ ከተባሉ አባት ነው። የሁለት ቀን መንገድ አቋርጠን አዲስ የተሠራን ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ሊያስመርቁ ወደተገኙት አባት ሄደን በዛው ነው ዲቁናን የተቀበልነው» ይላሉ፤ ዓለማየሁ ፈንታዬ ዛሬ ላይ መለስ ብለው ሲያስታውሱ። ከዜማ ጋር ትውውቃቸው የጠነከረውም ለዲቁና አገልግሎት በተማሩትና ባገለገሉበት ዜማ ነው።

ጉዞ ወደ አዲስ አበባ

በቤተክርስቲያን አራት ዓመታትን በመቀደስ ካገለገሉ በኋላ ዲቁናቸውን አፈረሱ። በወቅቱም በአንድ በኩል ድቁናቸውን በማፍረሳቸው እጅግ አዝነው በሌላ በኩል ደግሞ በጓደኞቻቸው «ዜማና አቋቋሙን እንማራለን አይዞህ!» የሚል ቃል እየተጽናኑ፤

«እቱ በአንቺ ነገር በአንቺ የተነሳ፤

ድቁናዬም ቀረ ዳዊቱም ተረሳ።

እቱ ድቁናዬ ዳዊቴ አንቺ ነሽ፤

ብደግም ብደግም የማልሰለችሽ» እያሉ ከወዳጆቻቸው ጋር ያዜሙ እንደነበር በፈገግታ አወሱ። ከዚህ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር የቅኔ በኋላም የአቋቋም ትምህርት ለመማር ወሰኑ።

በቀድሞው የብሔራዊ ባህል ማዕከል የተዘጋጀ አንድ ሰነድ ስለእርሳቸው እንዲህ ሲል አስፍሯል፤ «…የቅኔ ትምህርታቸውን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ እረፍት በሚያደርጉበት በጎንደር ከተማ ፒያሳው ላይ አንድ ድምጽ ማጉያ በምሰሶ ላይ ተሰቅሎ የከተማው ሰው ሁሉ ተሰብስቦ ሲያዳምጡ ተመለከቱ። ዜማው ከየት እንደሆነ ሲጠይቁ ከአዲስ አበባ የሚተላለፍ ሬድዮ ነው ተባሉ።…በኋላም ይተላለፉ የነበሩት ሙዚቃዎች ልባቸውን እየገዛ እያሸነፈ ዘፋኞቹንም ለማየት ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው» ይላል።

ይህ ምንአልባት ዛሬ የደረሱበት ደረጃ የመጀመሪያ ጭረት ይሆናል። እርሳቸው ከዛ በኋላ የሆነውን ሲያስታውሱ ደግሞ እንዲህ ሆነ። አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አለቃ ሳህሌ ካሳዬ የተባሉ አጎታቸው ጋር ማረፊያቸውን አደረጉ። የልባቸውን በልባቸው እንደያዙ ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ግን ሳይርቁ በአዲስ አበባ ቆዩ።

ሰላም! አገር ፍቅር

«መኮንን ሀብተወልድ የሚባሉ አገር ፍቅርን ያቋቋሙ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፤ ለኪነጥበብ በጣም ጉጉ የነበሩና የአገር ባህልና ቅርስን ከፍተኛ ደረጃ አደርሳለሁ ብለው የተነሱ ሰው ናቸው። ካህናቱንና ዲያቆናትን ከየቤተክህነቱ እየፈለጉ፤ ከአዝማሪዎችም ችሎታ ያላቸውን እየመረጡ ሰብስበው አገር ፍቅርን አቋቁመው ጥሩ ይንቀሳቀሱ ነበር» ሲሉ የሚያስታውሱት ጋሽ ዓለማየሁ፤ ወደ አገር ፍቅር የመጡበትን ሁኔታ የሚጀምረው በዛ ነበር።

እርሳቸውም ተመርጠው ድምጻቸው ታይቶና ተፈትነው በ1950ዓ.ም በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተቀጠሩ። በአገር ፍቅር ጊቢ ውስጥ ቤት ተሰጣቸው፤ ደመወዛቸውም ሰላሳ ብር ሆነ። «እንደገባሁ ሥራዬ መጋረጃ መያዝና መላላክ ነበር። በቦታው በጣም ባለሙያ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፤ አዝማሪዎቹ እረፍት ላይ ሲሆኑና መሣሪያዎቹን አስቀምጠው ሲሄዱ እያነሳሁ ስለማመድ፤ እየተቀጣሁና እየተከሰስኩ ነው የለመድኩት። እንጂ አገር ፍቅር ስገባ ከቤተክህነት ዜማ በቀር ማጨብጨብ እንኳ አልችልም ነበር» ይላሉ።

በአገር ፍቅር ቴአትር  ቤት የአስር ዓመታት ቆይታቸውም በዚህ መንገድ ዜማውንና አሠራሩን በደንብ አውቀውበታል። እንደውም ደመወዛቸው በዓመቱ ከፍ ብሎ ስድሳ ብር ገብቶ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ታድያ በነዛ ዓመታት ውስጥ ዜማ መድረስ ችለዋል። «አፍሪካ አንድ ሁኚ፣ አዲስ አበባ ቤቴ፣ ወንደላጤ ከመባል» እና የመሳሰሉ ሥራዎችንም የሠሩት በአገር ፍቅር ቆይታቸው ነው።

የአገርኛ ዜማ መምህር

ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከባህር ማዶ ያሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችንና ዜማዎችን ለማስተማር ሲከፈት፤ የአገር ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንዲካተቱ ፈቃድ ተገኘ። እናም ተማሪዎችን ለመቀበል መምህራን ተፈለጉ፤ ለዚህ የተገኙት ደግሞ ዓለማየሁ ፈንታዬ ነበሩ። በ1960ዓ.ም በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የባህል የዜማ መሣሪያ መምህር ሆነውም ተቀጠሩ።

መምህር ዓለማየሁ በቤተክህነት ያልተራመዱ በትን መምህርነት በዜማ በኩል ተቀበሉት። በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትም ራሳቸው የማስተማሪያ መርሐ ግብር (ስርአተ ትምህርት) አውጥተው ከዛ ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ  እያገለገሉ ይገኛሉ። ታድያ ሰልጣኞችን በአራት ዓመት ያስመርቃል ተብሎ የተጀመረው የሙዚቃ ትምህርት ለእርሳቸውም ምቹ ሆነ። አራቱን ቅኝቶች በአራት ዓመት ከፍለው ለየዓመቱ በቅደም ተከተል ማስተማር እንዲችሉ አግዟቸዋል።

በተጓዳኝ በግላቸው የሠሯቸው የካሴት ሥራዎችም ነበሩ፤ በተለይም በመዲና እና ዘለሰኛ አጨዋወታቸው ነው ብዙዎች የሚያውቋቸው። «የምንጠቀመው እኛ ባንሆንም በርካታ ሥራዎችን ሠርቻለሁ» አሉ። ታድያ በፍቅር የሚሠሩትን እንጂ ለትርፍ ያልተጠቀሙበትን ሙያ በአስተማሪነት ለሌሎች ሲያቀብሉም በደስታ መሆኑን ያወሳሉ።

«አሁንም ሳስተምር ከተማሪዎቼ ጋር በፍቅር ነው። የማስተምረውም በድሮ ዜማዎች ነው። ተምረው የሚወጡ ልጆች በጣም ይጠቀሙበታል፤ እንደውም ከዘመናዊው ጋር እያያዙ ብዙ ይሠራሉ። ይህ ዘርፍ ገና ያልተነካ ሥራ ነው»  ሲሉ ይናገራሉ።

እኚህ የአገርኛ ዜማ አንጋፋ መምህር ከዚህ የሙዚቃ ነክ ሥራቸው በተጓዳኝ በቴአትሮችም ላይ ተሳትፎ ነበራቸው። አገር ፍቅር ገብቶ ቴአትር ሳይሠሩ በየት በኩል? እንደውም ሽለላና ፉከራ ይጫወቱ እንደነበር ይናገራሉ፤ ታትመው የቀሩ ፎቶግራፎች ደግሞ ይኽንን ይመሰክራሉ። እንደውም በጀግንነት ፉከራቸው ምክንያት «የዲያቆን ሸላይ» የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸውም ነበር። ታድያ ለሙያው ባላቸው ፍቅር የተነሳ ለአገራቸው የአገርኛ ሙዚቃ እድገት፤ የመሣሪያዎቹን አጨዋወት ጥበብ በማስተማር እንዲሁም በድምጻዊነት ሳይሰለቹ የሠሩ ቢሆንም፤ ጠርቶ ያመሰገነና እውቅና የሰጣቸው አልነበረም።

ከባህር ማዶ የተገኘ ክብር

ከመምህር ዓለማየሁ ማስተማሪያ ክፍል፤ ከሚቀመጡበት ወንበር ፊት ባለው ጠረጴዛቸው ላይ በርካታ በተለያዩ ቋንቋ  የተዘጋጁ ጋዜጦች፣ ፎቶግራፎችና ምስክር ወረቀቶች ይገኛሉ። ሁሉንም የሚያመሳስላቸው መምህር ዓለማየሁን በተለያየ መጠሪያ እያሞካሹ በአድናቆትና በክብር የተጻፉ መሆናቸው ነው።

«የውጭ ጉዞ ሲመጣ እኔ ቀርቼ አላውቅም» የሚሉት መምህር ዓለማየሁ፤ በውጭ ጉዟቸው የኢትዮጵያውያን ባህል ምን ያህል እንደሚደነቅና ክብር እንደሚያገኝ ያስታውሳሉ። እናም ታድያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ሲወጡ ያረፉባት አገር ሱዳን ነበረች። ይህም በ1957ዓ.ም ሲሆን፤ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት እያገለገሉ በነበረበት ወቅት ነው።

ከዚህ ይልቅ ግን ትዝታቸው ቀድሞ የሚመራቸው በ1959ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በሴኔጋል የተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ፌስቲቫል ላይ ወደነበራቸውን ተሳትፎ ነው። «የመጀመሪያው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ፌስቲቫል ተብሎ ሴኔጋል ተካሂዶ ነበር። በንጉሡ ምርጫ ነበር የሄድነው፤ የሄድነውም አሥራ ስድስት ነበርን» ይላሉ። እነዚህ አገራቸውን ወክለው በስፍራው የተገኙ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታድያ በስፍራው የነበረውን ታዳሚና የአገራት መሪዎችን ሳይቀር ያስደመመ ሥራቸውን አቀረቡ።

መምህር ዓለማየሁ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፤ «ንጉሡ በጊዜው በጣም ተደስተው ነበር። ሌሎቹም የእናንተ አገር አፍሪካ አይደለም እስኪሉ ድረስ ተደንቀው ነበር፤ አሳምረን ነበር የሠራነው። የዓለም መሪዎችም ቆመው አጨብጭበዋል»

ሥራቸውን አቅርበው ሲጨርሱ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማትና ግብዣ ተደረገላቸው። ንጉሡም እንዲህ አሉን ይላሉ፤ «ለካ እንዲህ ነው የምትሠሩት። እናንተ’ኮ የአገር መልክ ናችሁ፤ እናንተን ነው ዓለምን ማዞር፤ እኔ አላውቅም ነበር» ይህም የንጉሡ ቃል በተግባረ ተገለጠ። የአገርኛ ሙዚቃውን የያዙት ዓለማየሁና ባልደረቦቻቸው ቀጥሎም በ1960ዓ.ም ካናዳ በተካሄደ ዝግጅት /ኤክስፖ 67/ ላይ ለመሳተፍ እድል ተሰጣቸው።

«በካናዳ ልዩ የሆነ ጊዜን አሳለፍን፤ ሥራችንንም በየቦታው ሠርተን ተመለስን። ከዛ በኋላ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ አትሌቶቻችን ጋር አብረን ሄደናል። በሄድንበት ሁሉ አድናቆት እናገኛለን፤ አገራችንንም አስተዋውቀን ተከብረን እንመለሳለን። ከአገራችን ይልቅ በውጪው ነው የተከበርነው» አሉ በቁጭት።

በግላቸው እጅግ በርካታ የዓለም አገራትን አይተዋል፤ ጎብኝተዋል፤ ሥራቸውንም አቅርበዋል። «በአገራችን ሙዚቃ በኩል በተሰጠኝ ድርሻ ጥሩ ሠርቻለሁ ብዬ አስባለሁ» ይላሉ። በእርግጥ ከጥሩ በላይ ቃልና ገላጭ ከተገኘም የእርሳቸውን ሥራ ለመግለጽ ቢያንስ እንጂ አይበዛም። የባህላዊ ዜማ መሣሪያዎች ከመዘንጋት ያተረፏቸው አንድም የእርሳቸው መምህርነት መሆኑን ልብ ይሏል! እንጂ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለአገር ውስጥ ዜማና የዜማ መሣሪያ ትኩረት እንደማይሰጥ በተደጋጋሚ ይነሳል፤ የታወቀ ነገርም ነው።

የቀድሞው ብሔራዊ ባህል ማዕከል ትውስታ

ብሔራዊ የባህል ማዕከል በጥሩ ተነሳሽነት ለአንድ ዓመትና ጥቂት ወራት አካባቢ አንድ ጥሩ መርሃ ግብር ያካሂድ ነበር። ይህም «አርአያዎቻችን ላበረከቱት የከበረ ሥራ ሊወደሱና ሊመሰገኑ ይገባቸዋል!» የሚል መሪ ሃሳብ የነበረው ሲሆን፤ ምንም እንኳ የተቋረጠ ቢሆንም በርካታ አንጋፎችን ለማክበር፣ ለማወደስና ለማመስገን ያስቻለ እድልን ፈጥሯል።

ማዕከሉ «የአገርኛ ሙዚቃ አውራ» ያላቸውን ዓለማየሁ ፈንታዬንም በሰኔ ወር 2008ዓ.ም በማዕከሉ ጊቢ በተካሄደ ደማቅ መርሃ ግብር አመስግኖ ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ታድያ እኚህ የአገርና ባህላዊ መሣሪያዎችን አዋቂና የዜማ መምህር የሆኑ ሰው፤ በአገር ውስጥ ከተሰጣቸው ክብርና አድናቆት ይህኛውን አብለጠው እንደሚያስታው ሱት ያነሳሉ። በእለቱ ካደረጉት ንግግር ደግሞ እኛ እናስታውስ፤

«ሙያው የተረገመ ተብሎ የሚቆጠር፤ መሰደቢያ ሆኖ የቆየ ነው። እኔ ግን የአገራችን ቅርስ የሆነውን መሣሪያ በመያዜ  እንደዛሬ ተደንቄና ተከብሬ አላውቅም። ይህን ረቂቅ ሙያ እና የአገር ቅርስ እኛ አገር እንኳ ክብር ባይሰጠው በሌላው አገር የከበረ፤ በዛም ያለን አድናቆት ከፍተኛ ነበር። ሥራውን ጀምረን ከአገር በወጣን ጊዜ ንጉሡ በእኛ ተደስተው የሰጡን ማበረታቻ በአእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ስለነበር፤ ስድብና ትችት ከየአቅጣጫው ቢኖርም አልተቀበልኩትም። የሙያውን ስነምግባር በመጠበቅ በተለይ ደግሞ በመምህርነት ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ» ብለው ተናግረዋል።

ቤተሰብ

ጋሽ ዓለማየሁ ትዳር ይዘው ቤተሰብ መሥርተዋል። የአምስት ልጆች አባትና የሁለት ልጆች አያት ሆነዋል። በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ መሆናቸው ከገጻቸው ላይ ይነበባል። ከእርሳቸው ወንድሞችና እህቶቻቸው መካከል የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ወደ ኪነጥበቡ ወይም ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባ ባይኖርም፤ እርሳቸው ግን ፈለጋቸውን የተከተሉ ልጆችን አፍርተዋል። መለስ ብለው ታሪኩን እንዲህ ሲሉ ነበር ያስታወሱት፤

«በኢህአፓ ወቅት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበሩ። ያኔም እንዳይወሰዱብኝ ሰግቼ ልጆቼን ወደማስተምርበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አመጣኋቸውና ይማሩ ጀመር። አራቱን ዓመት ተምረውም በዲፕሎማ ተመረቁ። ከዛም ሁለቱም የትምህርት እድል አግኝተው ቡልጋርያ ሄዱ። አሁን እዚሁ እያስተማሩ ይገኛሉ።» ብለው አጫወቱን።

በአገር ሆኖ ስለማገልገል ያነሱት ጋሽ ዓለማየሁ፤ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አፍሪካ የመቃብር ቦታ ነች ማለታቸውን አስታውሰው ተከታዩን ይናገራሉ። በሌላ አገር ሠርቶና ገንዘብን አስቀምጦ በመጨረሻ አገሬ ቅበሩኝ ይሉት ነገር አይዋጥላቸውም። «እኔ ዓለም ዞሬ አይቻለሁ፤ ከአገር የሚበልጥ ነገር የለም። ማየት ጥሩ ቢሆንም አገርን የመሰለ ነገር ግን የለም»  ይላሉ።

እናም እርሳቸውም ልጆቻቸው ውጪ ሄደው ከተማሩ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው አገራቸውን እንዲያገለግሉ አሏቸው እንጂ «እዛው ይሻላችኋል!» አላሉም። ልጆቻቸውም መጡ፤ ሴት ልጃቸው ፒያኒስት ወንዱ ደግሞ ቫዮሊን ተጫዋች ሆነውም በዛው በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤተ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። የተቀሩት ሶስት ልጆቻቸው ደግሞ በተለያዩ ሙያ ተሰማርተዋል።

ዋ ዜማ!

«ሙዚቃ ራሱን የቻለ ቋንቋ ነው። ነፋስ አይታይም፤ ግን ዛፉን ሲያወዛውዝና ሲያስጨፍር ይታያል። ሙዚቃም እንደዛው ነው። ሙዚቃ ቀስቃሽ ነው፤ አዝናኝና አስተማሪ፣ ታሪክና ሁለተኛ ቋንቋ ነው። ሙዚቃችን በጣም ዋጋ ያለው ነው» ይላሉ፤ ዜማን እንደ አየር የሚተነፍሱት የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃና ዜማ አውራ ዓለማየሁ ፈንታዬ።

ያለዜማ ሃሳብም አይመጣላቸውም፤ እርሳቸውም ያንኑ ነው የሚሉት። ከሙዚቃና ዜማ ርቀው አያውቁም። ከ1960ዓ.ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ከቆዩበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ጡረታ ወጥተው ነበር። ያኔም ለስምንት ዓመታትም ከትምህርት ቤቱ ርቀው ይቆዩ እንጂ ከዜማና ከአገርኛ የሙዚቃ ሥራቸው አልተነጠሉም። ብቻ ግን ትምህርት ቤቱም መልሶ በኮንትራት ቀጥሯቸው እነሆ ከጡረታ መልስ አስር ዓመታት አስቆጠሩ።

ዕድሜያቸው ሰማንያ ሁለት እንዳለፈ እርግጠኛ ናቸው። ነገር ግን እንደ ሰማንያ ዓመት አዛውንት አይደሉም፤ ቀልጠፍ ብለው ይንቀሳቀሳሉ፤ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበልም ክፍት እንደሆነው በራቸው በፈገግታ ይጠብቃሉ። በየቀኑ አዲስ እንደተቀጠረ መምህር በደስታ እንደሚያስተምሩ ያስታውቃሉ። ለዚህ ቃለመጠይቅ ቢሯቸው በተገኘሁ ጊዜ እንኳ ተማሪዎቻቸው ሲመጡ፤ «እንግዲህ ምን ላድርግሽ! አሁን ተማሪዎቼ መጥተዋል!» ብለው ከወንበራቸው ተነስተዋል።

ዕድሜያቸውን አንስቼ «እንደ እድሜዎ ግን አይደለም፤ ጠንካራ ነዎት» ስላቸው፤ «ሙዚቃው ነዋ! ሙዚቃ ያጠነክራል» አሉኝ። ስለሙዚቃ ይልቁንም ስለዜማ ሲያነሱ የሚሉት ተከታዩን ነው፤ «የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ሀዘንና ደስታ አይለየውምና፤ በዛ ሁሉ የሚገኝ ነው፤ ዜማ። ሙዚቃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለተኛ ቋንቋው ነው። ደስ ሲለው ይዘፍናል፤ ሲከፋው ያንጎራጉራል»

ታድያ እንደ እርሳቸው እይታ መሰንቆ በንጉሥ ዳዊት ዘመን የነበረ ነውና፤ ስለዜማና ሙዚቃ ጥናት ማድረግ ከአምስተኛውም ክፍለ ዘመን ወደኋላ አርቆ የሚወስድ ነው። ዜማም አስቀድሞ የሕዝብ እንደነበር፤ ሕዝብም በሚገባ እንደተገለገለበት ይጠቅሳሉ።

ስለፍቅር፣ ስለሥራ፣ ስለአገር፣ ስለነጻነትና አንድነት፤ እንዲሁም ጀግና በሚያስፈልግበት ሜዳ ድንበር ሲወረርና ሲደፈር በሰንጎ መገን፣ ጉሮ ወሸባዬና ፉከራ እንዲሁም ቼ በለው ሕዝብንና አገርን ያገለገሉ ዜማዎች ናቸው። ለመንፈሳዊ አገልግሎትም መዲና እና ዘለሰኛ አለ፤ ተፈጥሮን በማድነቅ የሚዜምም እንዲሁ። የዚህ ሁሉ ዜማ ደራሲው ታድያ ሕዝብ እንደሆነ ነው መምሕር ዓለማየሁ የሚናገሩት።

እናም ቀጥለው፤ «የአገራችን ሙዚቃ በጣም ሰፊ ነው፤ ከሰማንያ በላይ ቋንቋ የሚናገሩ ወገኖቻችን ሁሉ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ግጥሙን እየገጠሙ በዜማ መልክ የሚያንጎራጉሩት ከአራቱ ቅኝት ውጪ አይደለም። ይህንንም ጊዜ ወስዶ ተንትኖ ማስረዳት ይቻላል» ያም ሆኖ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ለመናገር ብዙ ጥናትና ምርምር እንደሚያስፈልግ ያምናሉ።

በሙዚቃና ዜማ ሥራ ላይ የእርሳቸው ተማሪ የነበሩ እንዲሁም አዳዲስ በሚወጡ ባለሙያዎችም ኩራት እንደሚሰማቸው ያነሳሉ። ጥቂት የማይባሉት ባህሉን ከዘመናዊ ጋር በአንድ እንዲሄዱ ማድረግ መቻላቸውም ለፊቱ የአገርኛ ዜማን በስፋትም በጥልቀትም ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።

መልዕክታቸውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። ሕዝቡ የአገሩን ሁለተኛ ቋንቋ፤ የስሜቱ መግለጫ የሆነውን፤ ስለአገርና ስለአንድነት እንዲሁም ስለነጻነት የተዘፈነውና የተዘመረውን የአገሩን ሙዚቃ እንዲያከብርና እንዲያጠናው ይጠይቃሉ። እንደውም ከሆነልንና ከተቻለ ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነውና በጽሑፍ ወይም በሙዚቃ ቋንቋ በኖታ እየተጻፈ ለትውልድ እንዲተላለፍ፤ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ዓለም ሁሉ አንብቦ እንዲረዳው ማድረግ የምንችልበት ደረጃ መድረስ አለብን ባይ ናቸው።

እናበቃ! በትህትና ከተመሉት፤ ሥራቸውን ወዳድና አክባሪ ከሆኑት የባህል ሙዚቃ አውራ ከሆኑት ዓለማየሁ ፈንታዬ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንዲህ ነበር። የእርሳቸው ልምድና ተሞክሮ ከዚህ እንደሚልቅ የታወቀ ነው። እኛ ግን መጥነን እንዲህ አቀረብን። ሰላም!

አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011

ሊድያ ተስፋዬ