ተደራሽ ያልሆነው የፓርኪንሰን  ህክምና

41

መንቀጥቀጥ፣ የሰውነት መድረቅ፣ የሰውነት ሚዛን መሳትና ዘገምተኛ እንቅስቃሴ ማሳየት የህመሙ ምልክቶች ሲሆኑ  ድብርት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ለመፃፍ እና ለመናገር መቸገር፣ የምራቅ መዝረብረብ፣ የሆድ ድርቀትና የማሽተት ችሎታ መቀነስ ደግሞ ተጨማሪ የህመሙ ምልክቶች ናቸው፡፡  የፓርኪንሰን በሽታ፡፡

የፓርኪንሰን ህመም በዶፓሚን ንጥረ ነገር እጥረት የሚከሰትና እየባሰ የሚሄድ የአንጎል /ነርቭ/ ህመም መሆኑን እና ከ80 በመቶ በላይ በሽታው የሚከሰተውም ንጥረ ነገሩን የሚፈጥሩት የነርቭ ሴሎች ሲሞቱ እንደሆነ በዘርፉ ምርምር ያካሄዱ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ዶፓሚን የተሰኘው ንጥረ ነገር የሰውነት እንቅስቃሴን የሚቆጣጠርና የነርቭ ሴሎች እንዲንቀሳቀሱ የሚረዳ ኬሚካል በመሆኑም የንጥረ ነገሩ ከአንጎል ውስጥ ማለቅ የፓርኪንሰን ህመምን ያስከትላል፡፡

የፓርኪንሰን ህመም ምክንያቱ ባይታወቅም ለህመሙ መከሰት ብዙ አጋላጭ ሁኔታዎች እንዳሉ የህክምና ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ በተለይም እድሜ፣ፆታ፣ዘርና ለመርዛማ ኬሚካሎች መጋለጥ እንደ ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በተለይም እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች  በፓርኪንሰን ህመም የመጠቃት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡  በህመሙ የተጠቃ የቤተሰብ አባል ካለም በዘር የመተላለፍ እድል ይኖረዋል፡፡ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ለህመሙ የበለጠ ታጋላጭ ሲሆኑ ለመርዛማ ኬሚካሎች/ፀረ -አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች/ በተደጋጋሚ መጋለጥ አጋጣሚም ሌላው ተጋላጭነትን የሚጨምር ነው፡፡

በበሽታው ዙሪያ በርካታ ምርምሮች የተካሄዱ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ማስታገሻና የህመሙን ምልክቶች ለማከም  እንጂ ፈዋሽ መድሃኒት አልተገኘለትም፡፡ ሌቫዶፓ እና ዶፓሚን የተሰኙት የመድሃኒት አይነቶች ደግሞ በአብዛኛው የፓርኪንሰን ህመም ምልክቶችን ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የታማሚዎችን ትክክለኛ አሀዝ ለመለየት የተሰራ ጥናት ባይኖርም ከ200 እስከ 300ሺ የሚጠጉ ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ግን ይገመታል፡፡ የፓርኪንሰን ታማሚዎችን በመደገፍና የመድሃኒት አቅርቦት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ስፖርት ኦርጋናይዜሽን  ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ሲሆን የጤና ሚኒስቴርም በአእምሮ ጤና ስትራቴጂ ውስጥ በማካተት መጠነኛ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የህክምና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን፣ የመድሃኒት አቅርቦት ዝቅተኛነት ሁሌም ከታማሚዎች የሚነሳ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ስፖርት ኦርጋናይዜሽን መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ክብራ ከበደ እንደሚሉት፤ማህበሩ ህሙማንን በማሰባሰብ በ2003 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 550 አባላት አሉት፡፡ ማህበሩ ለህሙማን፣ለጤና ባለሙያዎችና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ግንዛቤ ማስጨበጫና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በተለይም ለህሙማን ድጋፍና እንክብካቤ ከማድረጉም በላይ  አስታማሚዎችም የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው የበኩሉን ማበርከቱን ይናገራሉ፡፡

እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ ፤ማህበሩ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን ህሙማን ስለ እግራቸው በቂ መረጃ እንዲያገኙ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ መድሃኒት እንዲገዙ በማድረግ ትልቅ እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡

በማህበሩ ድጋፍ ብቻ ለታማሚዎች መድሃኒት ማቅረብ እንደማይቻል የሚገልፁት ስራ አስኪያጇ፣ መንግስት የታማሚዎችን አቅም ባገናዘበ መልኩ የተሻሉና ወቅታዊ መድሃኒቶችን በማስገባት፣ ህሙማን መድሃኒቶቹን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ አማካይ ቦታዎች ላይ እንዲሸጡ በማድረግ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ስራ አስኪያጇ እንደሚሉት ፤የፓርኪንሰን ህመም የእድሜ ልክ በመሆኑና ሁሌም የህክምና ክትትል የሚጠይቅ ነው ፤ለዚህ ደግሞ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ህክምናው በተሟላ ባለሙያዎችና መሳሪያዎች እየተሰጠ ባለመሆኑ በቀጣይ በጤና ጣቢያ ደረጃም ጭምር  ማስፋትና ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ አቶ አበባው አየለ እንደሚገልፁት፤ የፓርኪንሰን ህመምን ልክ እንደሌሎቹ የአእምሮ ህመሞች ሁሉ  በአእምሮ ጤና ስትራቴጂ ውስጥ በማካተት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በህመሞቹ ዙሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቀየር የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባሮች በስፋት ተከናውነዋል፡፡ ፓርኪንሰንን ጨምሮ ሌሎች የአእምሮ ጤና  አገልግሎት አሰጣጦችን ተደራሽ የማድረግና ከሌሎች ህመሞች ጋር አቀናጅቶ አገልግሎቱን የመስጠት ተግባራት መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡

እንደ ቡድን መሪው፤ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ አሃድ የአእምሮ ጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው፤ይህም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንዲሁም የአእምሮ ጤና ደግሞ በቅርቡ በተጀመረው የትምህርት ቤት ጤናና ስርአተ ምግብ ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተትም ሆኗል፡፡

እየተሰጡ ያሉት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የታሰበውን ያህል ጠንካራ ባይሆኑም ከፓርኪንሰን ፔሸንትስ ስፖርት ኦርጋናይዜሽን ጋር በመሆንና የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም  እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ለፓርኪንሰን ታማሚዎች የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በአብዛኛው  የነርቭ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ባሉባቸው ሆስፒታሎች  ብቻ መሆኑን የሚጠቅሱት ቡድን መሪው፤ በሃገሪቱ ያሉ የነርቭ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ቁጥር ውስን በመሆኑ የህክምና አገልግሎቱን በጤና ጣቢያዎች ደረጃ ማስፋት አልተቻልም ይላሉ፡፡ ሆኖም በማህበሩ ድጋፍ ለጤና ባለሙያዎች የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት አገልግሎቱ በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ቡድን መሪው እንደሚሉት፤ ከፓርኪንሰን ህመም ጋር በተያያዘ በፕሮግራሙ ውስጥ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ውስን መሆን፣ተቀናጅቶ አለመስራት ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በቂ አለመሆንና  ዝቅተኛ የመድሃኒት አቅርቦት ችግሮች ለህሙማኑ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት  የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ናቸው ፡፡

ታማሚዎቹ የሚወስዷቸው መድሃኒቶች ሙሉ በሙሉ የሚፈውሱ ሳይሆኑ የተሻለ ህይወት እንዲኖሯቸው የሚያስችሉና በየእለቱ ሳይቆራረጡ የሚጠቀሙባቸው ናቸው የሚሉት ቡድን መሪው በበቂ ሁኔታ ላለመቅረባቸው ዋናው ምክንያት ደግሞ በሃገሪቱ ምን ያህል የፓርኪንሰን ታማሚዎች እንዳሉ አለመታወቁ ነው ይላሉ፡፡

በጤና ሚኒስቴር በኩል የፓርኪንሰን ህክምና አገልግሎት በሆስፒታሎች በይበልጥ  ተደራሽ እንዲሆንና በተዋረድ ባሉ የጤና አግልገሎት መስጫ ተቋማት እንዲሰጥ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው የሚሉት ቡድን መሪው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ህሙማን ሌሎች የቴራፒና የመድሃኒት አገልግሎቶችን  እንዲያገኙ ይሰራል ፡፡ታማሚዎች የተሻለ የህክምና፣ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ  እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ እንደ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሁሉ  የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል አጋርነት በመፍጠር ይሰራል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የነርቭ ሃኪም ዶክተር ግርማ ደልታታ የፓርኪንሰን ህመም ስርጭትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ጥናቶች እንዳልተደረጉ ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በግለሰቦች ተነሻነት በአዲስ አበባ ከተማ በተወሰኑ አካባቢዎች በፓርኪነሰን ህመም ዙሪያ ጥናት መደረጉን ያመለክታሉ፡፡ ስርጭቱም በአማካይ ከ100 ሺ ሰዎች ውስጥ ከ 7 እስከ 10 ሰው የፓርኪንሰን ታማሚ ነው ተብሎ ይገመታል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የነርቭ ሃኪሞች ከ 36 እንደማይበልጡና የአለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈረት በታች መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር ግርማ፤ ቁጥራቸው በቂ ባለመሆኑ ለፓርኪንሰን ታማሚዎች በሚፈለገው መጠን የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዳልታቻለ ይገልጻሉ፡፡  ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት  የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  የነርቭ ህክምና ትምህርት ክፍል በተቻለው አቅም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡

በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ አሸናፊ እንደሚገልፁት፤ ቀደም ሲል ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች የማህበረሰቡ ዋነኛ የጤና ችግሮች በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራባቸው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ፓርኪንሰን ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የወቅቱ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች እየሆኑ በመምጣታቸው  ለመከላከልና ለህበረተሰቡ ግንዛቤን ለማስጨበጥ የተለያዩ ስራዎች በጤና ሚኒስቴር በኩል ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ኃላፊው እንደሚሉት፤የጤና ሚኒስቴር ከፓርኪንሰን ህመም ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች እንዳሉ ያውቃል፡፡ ደረጃ በደረጃ ለመፍታትም ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን በተለይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ስትራቴጂ በመቅረፅና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡

የፓርኪንሰን ህመምን በተመለከተ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ውስን በመሆኑ አገልግሎቱን ለማስፋት በተቻለ አቅም ግብአቶችን የማቅረብና ሙያተኞችን የማሰልጠን ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አሁን ካለው የታማሚዎች ቁጥር አኳያ አገልግሎቱ  በቂ ባለመሆኑና በጤና ሚኒስቴር በኩልም በርካታ የሚቀሩ ስራዎች በመኖራቸው ከህሙማኑ ማህበርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመስራት ከፓርኪንሰን ህመም ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011

አስናቀ ፀጋዬ