የሥጋ ዝምድና የገደበው የኩላሊት ልገሳ

47

የኩላሊት ንቅለ ተከላ  በቅርብ ዘመድ ልገሳ ብቻ እንዲከናወን በህግ በመወሰኑ  ዘመድ ባልሆኑ ሰዎች ልገሳ መዳን የሚችሉ ዜጎች ለሞትና ለስቃይ እየተዳረጉ መሆኑ ይገለጻል፡፡

አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በኩላሊት ህመም ህይወቱ ላለፈው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ማሳከሚያ ገንዘብ አሰባሳቢ ነበር፡፡ እርሱ እንደሚለው ለአርቲስት ፍቃዱ የኩላሊት ህክምና የሚውል ገንዘብ ተገኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የቅርብ ዘመዶች መካከል ለእርሱ የሚገጥም ኩላሊት አልተገኘም፡፡ ከዘመዶቹ ውጪ የሚለግስ ሰው ተገኝቶ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመሄድ ዶክተሮቹን ‹‹ከቻላችሁ አክሙኝ›› ብሏቸው ነበር፡፡

ይሁን አንጂ፤ ዶክተሮቹ በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ኩላሊት መለገስ የሚችለው የቅርብ ዘመድ ብቻ እንደሆነ፤ ከዚያ ውጪ ግን የኩላሊት ንቀለ ተከላውን ማድረግ እንደማይችሉ መንገራቸውን ይገልጻል፡፡ በዚህም የተነሳ አርቲስት ፍቃዱ አምልጦናል ይላል፡፡

አርቲስት ቴዎድሮስ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ፤ ኩላሊት የሚለግሳቸው ዘመድ ያልሆነ ወገን እያላቸው በአሁኑ ወቅት እየሞቱ ነው፡፡ ሌሎችም  በኩላሊት እጥበት ህክምና እየተሰቃዩ ነው፡፡ መንግሥት ይህን በማየት የተሻለ ያለውን  አማራጭ በማጥናት የሚሰቃዩ ወገኖችን መታደግ ይገባዋል ሲልም ይማጸናል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ህጎች በህግ ከተወሰኑ ጥቂት የአካል ልገሳዎች ውጪ የሰዎችን አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነት ለጉዳት የሚጥሉ ጉዳዮች ፍጹም የተከለከሉ ናቸው፡፡ በማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2009 አንቀጽ 7 የሕብረተሰቡን አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነት ለጉዳት የሚያጋልጥ ድርጊት ማስታወቂያ ይከለክላል፡፡ በአንቀጽ 34 ክልከላውን የተላለፈም ከ20 ሺ እስከ 150 ሺ ብር እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

በወንጀል ህጉ አንቀጽ 573 መሰረት፤ ገንዘብ አሊያም ሌላ ጥቅም ለማግኘት ብሎ የሰውነት አካሉን የሰጠና ያስተላለፈ ከአምስት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይም፤ በፍትሕ ብሔር ህግ ቁጥር 18 ላይም፤ ሙሉ አካልነትን የሚያቃውስ ማንኛውም በሰውነት ክፍሎች ላይ የሚፈፀም ተግባር የተከለከለ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በውል ህግ አንቀጽ 1678 እና 1716  ደግሞ፤ አንድ ውል ህጋዊ ውጤት የሚኖረው የውለታው ጉዳይ ህጋዊና ሥነ-ምግባርን የማይቃረን ሲሆን እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሰረትም በኩላሊት ሻጭና ገዢ መካከል የሚደረገው ውል ዋጋ አልባ እንደሆነም ያመላክታል፡፡

የምግብ፤ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 በአንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 2 አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ወይም ህይወቱ ካለፈ በኋላ የአካል ክፍሎቹንና ህብረ-ህዋሳቱን በልገሳ ለማስተላለፍም ሆነ በምንም መልኩ እንዳይወሰዱ ለመከልከል ያልተገደበ ነፃነት መሰጠቱን ያብራራል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወጣው መመሪያም እንደሚያመለክተው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለሚደረግላቸው ሰዎች ኩላሊት መለገስ ያለበት የቅርብ ቤተዘመድ መሆኑንም ይደነግጋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሃኪምና መምህር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን ታደሰ፤ በኢትዮጵያ ስለእያንዳንዱ ሰው የተጠናቀረ መረጃ የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቅርብ ዘመድ ውጪ ኩላሊት እንዲለገስ መፈቀድ የኩላሊት ሽያጭ እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ ይህም ወደማንወጣው ችግር ውስጥ ያስገባናል ይላሉ፡፡

በሰለጠነው ዓለም ጓደኛ ይለግሳል፡፡ በገንዘብ አለመሸጡን የሚያረጋግጥ ስርዓትና  ባለሙያዎችም አሏቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ግን ጥብቅ ህግ ነው መዘርጋት ያለበት፤ ጥብቅ ህግ የሚወጣው ሰዎችን ለመጉዳት ሳይሆን ጉዳዩ ይዞት ከሚመጣው  መዘዝ ዜጎችን ለማዳን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ፤ ድርጊቱ ከአገሪቱ ዜጎች ሃይማኖትና  ባህልም ጋር  የሚቃረን ነው፡፡ ህጉ ጥብቅ ሆኖ እንኳን የኩላሊት ንቅለ ተከላ በሚካሄድበት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ታካሚ ሆኖ በመግባት ለመደለል የሚሞክሩ እንዳሉ በማንሳት አሁን ያለው ህግ ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት ያብራራሉ፡፡

በአንድ ቤተሰብ ብዙ ልጆች በሚወለድበት አገር፤ ከዚያም አለፍ ሲል ከአክስትና ከአጎት ልጅ ኩላሊት በመለገስ ችግሩን እስከ 95 በመቶ መፍታት እየተቻለ ይህን ህግ አላልቶ ዜጎችን ችግር ውስጥ ማስገባት አይገባም፡፡ መሆን ያለበት ይልቁንም በመመሪያ ደረጃ ያለውን ህግ በማጥበቅ የተለያዩ አካላት ተወያይተውበት በፓርላማ ደረጃ አዋጅ ሆኖ ማውጣት ነው ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ዶከተር መሀሪ ረዳኢ፤ ማንም ሰው ኩላሊት አምጥቶ ተኩልኝ ብሎ መቀየር የሚችል ከሆነ ዜጎች እየታፈኑ በመወሰድ ለዕርድ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ያነሱና፤ ጥናት አድርጎ  በኩላሊት ችግር ለሚሞቱ ሰዎች አማራጭ ማየቱ ግን ተገቢ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡

ዶክተሩ፤ ኩላሊት ከማንም መለገስ እንዲቻል ህጉን ክፍት ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ቢያምኑም ኩላሊት ከዘመድ ብቻ ይወሰድ ተብሎ የማይገጥም ከሆነ ንቀለ ተከላ አለማድረግ ግን  ስጋ ሰጥቶ ቢላዋ እንደመከልከል ነው፡፡ ስለሆነም፤ በሩን ዝግ ከማድረግ የሁሉንም ችግር ከግምት ውስጥ ያስገባ፤ ለሁሉም ጠቃሚ የሆነ አሠራር እንዲዘረጋ ባለሙያዎች ጥናት አድርገው ህጉን ለማሻሻል መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

የኩላሊት ህመምተኞች ዕጥበት የበጎ አድራጎት ድርጀት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ በበኩላቸው፤ ከዘመድ ብቻ ኩላሊት መለገሱ ዓላማው ህገ ወጥ የኩላሊት ንግድን ለማቆም ነው፡፡ ህጉ በዚህ ደረጃ ጥብቅ ሆኖም እንኳን ሰዎች ተጠናንተው በመምጣት በግዥ ለመለገስ የሚሞክሩ አሉ፡፡ በእኛ አገር ደረጃ ህጉ የሚላላ ከሆነ በዜጎች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት፤ በህዝብ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪም ለጋሹ ዘመድ ካልሆነ የመግጠም ዕድሉም አነስተኛ ነው፡፡ መግጠም አለመግጠሙ የሚረጋገጠው ደግሞ በጀርመን አገር ስለሆነና ከፍተኛ ወጭም ስለሚጠይቅ  ተግባራዊ ለማድረግ ችግር መሆኑንም ያመላክታሉ፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን ችግሩን ለማቃለል ከዘመድ ውጪ የኩላሊት ልገሳ እንዲፈቀድ ሰዎች ሲሞቱ ኩላታቸውን እንዲለግሱ በማድረግ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ይህን እንዲፈቀድ ግፊት ማድረግ እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የህግ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ ወሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በአስቸኳይ ወደ ሥራ በመግባት በህመሙ የሚሰቃዩ ዜጎችን እንደሚታደግም ያመላክታሉ፡፡ የሚለከታቸው አካላትም ሥራቸውን በማጠናከር መቀጠል አለባቸው ይላሉ፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ2 ሚሊዮን በላይ የኩላሊት ታማሚዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ወስጥ ወደ 600 ሺህ ታካሚዎች የኩላሊት እጥበት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለእነዚህ ታካሚዎች ለአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት 3 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ዜጎች በየዓመቱ እየሞቱ መሆኑን መረጃው ያትታል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎች በኩላሊት በሽታ እየተሰቃዩ ነው፡፡ መንግሥት ችግሩን ለማቃለል በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቀለ ተከላ ህክምና ጀምሯል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንጻር እስከአሁን ንቀለ ተከላ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር ውቅያኖስን በጭልፋ ያህል ቢሆንም ውጤት ግን ተገኝቷል፡፡ በጅምሩ ደግሞ የኩላሊት ልገሳው በዘመድ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዲሆን በህግ በመታሰሩ የተወሰኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም፡፡ እናም እንደ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሳይነገርላቸው በየቤታቸው የሞቱና የሚሰቃዩ አሉና አሁንም አካሄዱን ለማስተካከል ጉዳዩን በጥበብ መነጽር መመልከት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 1/2011

በአጎናፍር ገዛኽኝ