«ከፍታ ማለት በገንዘብና በሥልጣን ወደታች ወርዶ ሕዝብን ማገልገል ነው»ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ

40

አቡዳቢ፡- ከፍታ ማለት በገንዘብና በሥልጣን ወደታች ወርዶ ሕዝብን ማገልገል መቻል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ተወካዮች ጋር ትናንት ማታ በአቡዳቢ ሲወያዩ እንደገለጹት፤ ከፍታ ላይ መድረስ ማለት በገንዘብና በሥልጣን ወደታች ወርዶ ሕዝብን ማገልገል መቻል ነው።

ለዚህም የቀዳማይ እመቤት ጽሕፈት ቤት በሁሉም ክልሎች 20 የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ያስገነባውና እያስገነባ ያለው በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የአቡዳቢ ልዑል ሼህ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ወላጅ እናት የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ልዑሉም ቢሆኑ አፋርና ባሌ ውስጥ ለሚሰሩ የውሃ እና ትምህርት ቤት ሥራዎች ድጋፋቸውን እያደረጉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ትልቅ ትምህርት የሚሠጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

በውይይቱ ከተወካዮቹ ወቅታዊ የኢትዮጵያን የፀጥታ ሁኔታ፣ ለእምነት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ግንባታ ቦታዎችን ከማግኘት እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።

 በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ያለውን የእምነት ተቋማት የግንባታ ስፍራ ጥያቄ ትኩረት በመስጠት በተሰራው ሥራ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚሆን የግንባታ ቦታ መፈቀዱንና ለሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው አሁን በኢትዮጵያ የብሔር ግጭቱ እየረገበ ሲሄድ ወደ ሃይማኖት ግጭት ለመቀየር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልሰከነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሮች መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።

«መልካም ነገርን ማየት ያቃታቸው ሰዎች የኢትዮጵያ ብልፅግና የሚደናቀፍ አስመስለው ቢያወሩም እውነትን ስለያዝንና ጊዜውም የኢትዮጵያ በመሆኑ ወደ ብልፅግና የምናደርገው ጉዞ ፈፅሞ አይደናቀፍም» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ትናንት አመሻሽ አቡዳቢ ሲደርሱ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲያብ መሀመድ ቢን ዛይድ ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ዛሬ ከተባበሩት አረብ አሚሬቶችና ከመካከለኛው ምሥራቅ ከተውጣጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዱባይ ከተማ ሸባብ አልአህሊ ክለብ በአልመክቱም ስታዲያም በመገኘት መልዕክት ያስተላልፋሉ።

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012

ድልነሳ ምንውየለት