ዜጋ ተኮሩ የውጭ ግንኙነት ተግባር ይጠናከር!

20

 ዳያስፖራው ጠንካራ የስራ ባህል በመገንባት፣ የግል ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ፣ ንግድ፣ ትምህርትና መሰል የልማት ስራዎች እንዲጎለብቱና ገንዘብ ለቤተሰቡ በመላክ ለአገር ዕድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ እንዲሁም ፍትህ እንዲነግስ፣ የፖለቲካና ሲቪል መብቶች እንዲከበሩም ከውጭ አገራት የቀሰመውን ልምድ በማካፈል ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ህንድ ባሉ አገራት በተጨባጭ የታየና ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡

ብዙ ኢትዮጵያውያን በአገራችን በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። እነዚህ ወገኖች የተሰደዱትና እየተሰደዱ ያሉት ደግሞ የስልጣኔ ማማ ላይ ደርሰዋል ወደ ተባሉት ምዕራባውያን ሀገሮች ብቻ ሳይሆን ወደ አረብ አገራት ጭምር ነው። ሀገራቱ ደግሞ በሳይንስም ፤ በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ልቀው የሄዱ ናቸው። ከዚህ አኳያ በእነዚህ ሀገራት ሲኖሩ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮችና በትምህርት ተቋማት ቢሰማሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ማበርከት እንደሚችሉ እሙን ነው።

መንግስት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የወጣቱን ጉልበት፤ እውቀት በመጠቀም ሁለተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ዳያስፖራውን ማሳተፍና ማወያየት ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ላይ ናት። ለኢትዮጵያ የብልጸግና ጉዞ ለማፋጠን ደግሞ ዳያስፖራዎች ለአገራቸው ከሚልኩት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ ፤ በውጭ ሀገራት ቆይታቸው ወቅት የቀሰሙት ክህሎትና የስራ ባህልም ለህዝቡ፣ ለኩባንያዎችና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡

ይህን እንዲያደርጉና በአገራቸውና በመንግስታቸው ክብርና ኩራት እንዲያድርባቸው የእነሱንም ጥቅም፣ መብትና ተሳትፎ ማስከበርና ማሳደግ የመንግስት ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል ዳያስፖራው በኢኮኖሚው እንዲሳተፍ ጥረት ማድረግ እንጂ በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ደህንትና ተሳትፎ የሚጨነቅ መንግስት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ለኢኮኖሚ ልማትና ኢንቨስትመንት ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡

በመሪ ደረጃም በውጭ የሚኖረውን ዳያስፖራ ሀሳብ አድምጦ የሚያሳትፍና ችግሩን ለመፍታት የሚጥር መሪ አልታየም፡፡ መሪዎች ለስራና ለጉብኝት ወደ ውጭ አገራት ሲሄዱ የሚያተኩሩት ኢንቨስትመንትን መሳብ እንጂ በእነዚያ አገራት የሚገኙ ዜጎቻቸውን በአገራቸው የሚኖራቸው ተሳትፎና በውጭ እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችን አድምጠው ለመፍታት ያደረጉት ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ለውጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውያንን ማወያየትና በውጭ ታስረው የነበሩ ዜጎችን አስፈትቶ ይዞ የመምጣት ዜጋ አኩሪ ተግባር እያሳዩ ይገኛሉ፡፡

እንኳን ለጉብኝት በሄዱባቸው አገራት ቀርቶ ለዚሁ ዓላማ ብለው ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓና ደቡብ አፍሪካ አቅንተው በእነዚህ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በአገራቸው ሁለንተናዊ ልማት በሚኖራቸው ተሳትፎና በውጭ አገራት በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ በሄዱባቸው አገራትም በእስር ቤት ታስረው የቆዩ ዜጎችን ይዘው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳዑዲ አረቢያ፣ በሱዳን በግብጽና በሌሎችም አገራት ጉዞዎቻቸው በማረሚያ ቤት የነበሩ ዜጎች ከእስር አስፈትተው አብረዋቸው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሂደቶች ከተከናወኑ በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተከታታይ ሥራ በመስራቱ 120 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱና የማቋቋም ሥራው እንዲቀጥል እየተደረገ መሆኑን ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክተሪያት ገልጿል፡፡

የዜጎች ክብር በሚለው የመደመር መርህ መሰረት መንግስት በጉዳዩ ላይ አሁንም ሰፊ ስራ እየሰራ ነው። በአገር ውስጥ የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠርና ህጋዊነትን በማጎልበት ዜጎችን ከስደት የመታደግ ሥራ ከመስራቱም በተጨማሪ፤ ወደ ውጭ አገር በሄዱበት ወቅት የሚገጥማቸውን ችግር ከአገራቱ ጋር በመነጋገርና በመተባበር ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ነው፡፡

ከዚሁም ጋ በተያያዘ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለማወያየትና ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከትናንት በስቲያ ወደ የተባበሩት ኤሜሬትስ አቅንተዋል፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባርም በውጭ ያሉ ዜጎችን መብት፣ ደህንነታቸውንና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትና የሚሳተፉበትን አቅጣጫ እየተከተሉ ስለመሆኑ ዐብይ ማስረጃ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባርም ከለውጡ ወዲህ አዲስ በተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጭምር የተደገፈ መሆኑ ደግሞ ጥረቱን ተስፋ ሰጪ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመንግስት የተሰጠው ትኩረት ይበልጥ መበረታት የሚገባው ነውና ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል እንላለን፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012