‘ከዚህ በኋላ እንደ አገር የወረቀት ፈተና እድሜ አይኖረውም” – አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

62

 የሀገራቱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና ስርዓተ ትምህርትን መሠረት ያደረጉ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን በማዘጋጀትና በማስተዳደር የውጤት ሪከርዶችን የመያዝና ብሎም የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመስጠት በመንግስት ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎችን መመደብ እና የትምህርት ብቃት ምዘና ጥናትና ምርምር ማካሄድ ለአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የተሰጠው ኃላፊነት ነው፡፡ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር ምን እያከናወነ ነው ስንል ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር ጋር ቃለ ምልልስን አድርገናል።

አዲስ ዘመን፦ ወደ ኤጀንሲው መቼ መጡ?

አቶ አርአያ ፦ ቀድሞ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆኜ ከውጭ ከማየው በቀር ውስጡ ገብቼ አልሰራሁም ግን እንደ ፈታኝም እንደ ተቆጣጣሪና የፈተና ጣቢያ ሀላፊ ሆኜ አይቼዋለሁ። ወደ ኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ ሆኜ የመጣሁት ግን በ2002 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ነው።

አዲስ ዘመን፦ በቆዩባቸው ዓመታት ግን የኤጀንሲው ፈተናዎች ምንድን ናቸው ይላሉ?

አቶ አርአያ፦ የኤጀንሲው ትልቁ ፈተና ፈተናን በወረቀት አባዝቶ በየክልሉ መላክ መድረሱን መቆጣጠር በተቻለ መጠን አንጻራዊ በሆነ መልኩ በጊዜው በበይነ መረብ ተማሪዎች ውጤታቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ሲሆን ሌላው ከ 2002 ዓ.ም ጀምሮ እየሰራ ያለው ተማሪዎችን መመደብም በጣም አስቸጋሪ ነው።

ፈተና በእጅ ( ማንዋሊ) የሚሰራ በመሆኑ በየዓመቱ የተማሪዎች ቁጥር በጨመረ መጠን የመጨረሻ የአገሪቱ መዳረሻ ላይ መድረስ ነው። በነገራችን ላይ በፈተና ታሪክ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ አንድም የአገሪቱ አካባቢ ላይ ጎድሎ አያውቅም። በጣም ሰፊ የሆነ የእጅ (የማንዋል) ስራ መኖሩ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ምናልባትም የሰራተኞቹ ጥረት የፌዴራል ፖሊስና አታሚው ድርጅት በጣም ተጠባብቀንና እስከ ሶስት ወር በሚፈጅ ሁኔታ አደራጅተን እያንዳንዷን ትምህርት ቤት መዳረሻ ለይቶ ጭኖ መሄድ በጣም ፈተና ነው።

ፈተና ማጓጓዝ ራሱን የቻለ ፈተና ነው። አንዳንድ ቦታ ላይ በመሬት ውስጥ ለውስጥ ቆፍረው ይሰርቃሉ፤ በኮርኒስ ይገባሉ፤ ከዚህ አንጻር የደህንነቱና የጥበቃው ጉዳይ ያስጨንቃል። እጅግ በጣም ጥሩና ስነ ምግባር ያላቸው ሰዎች በየትኛውም ዘርፍ እንዳሉት ሁሉ ከተማሪ፣ ከወላጅም ከጸጥታ ሰራተኞችም ሳይቀር በጣም የሚፈታተኑ ተማሪዎችን አደራጅተውም ውጤታቸው በተለየ መንገድ እንዲሰራ የሚፈልጉ አልፎ ተርፎም መምህራኖቻችን ፈተና ሰርተው ካልሰጡን አንፈተንም የሚሉም ስላሉ ማስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ጫና አለው።

ህብረተሰቡ ውስጥ የእገሌ ልጅ ዩኒቨርሲቲ ይግባ ሳይሆን የሰራ ይግባ የሚል አመለካከትን ማስረጽ በጣም ከባድ ነው። እዚህ ላይ የሚጠፋው ሁለት ነገር ነው፤ አንዱ በተረጋጋ ሁኔታ ሊፈተን የሚችለውን ተማሪ ፈተና ካልሰጠኸን በማለት ማሰቃየት አለው፤ ይህንን እንናገራለን ግን እያንዳንዱ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር፣ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና ተማሪዎች ከእኔ እከሌ ይሻላል ብለው ተዛዝነው የሚሄዱበትን አካሄድ ካልፈጠርን ቀጣዩም በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

እዚህ ላይ በቴክኖሎጂ የሚቀነሱ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ ፤ አስተዳደራዊ ጫናውንና ሌሎች ነገሮችን ግን መቀነስ የማይቻልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። እናም ከፍተኛ ፈተና ሆኖብን የነበረው የፈተና ደንብ ጥሰት አሰራሩና አካሄዱን እየቀየረ በየጊዜው እየተቀያየረ ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ ላይ ያጋጠመን ልጆች ፍርድ ቤት ድረስ ሄደው ስማቸውን ይቀይራሉ፤ ለምን ቢባል ጎበዝ ከሆነው ተማሪ ጎን ለመሆን፤ ለምሳሌ ዘሪሁን የሚባል ተማሪ ጎበዝ ከሆነው አበራ የሚባለው ልጅ ጎን ለመቀመጥ ‘ዘአበራ’ ብሎ ስሙን የሚጽፍበት አጋጣሚ ነበር፤ ይህ በእርግጥ በመረጃቸው ይያዛል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፈተናው ኮምፒተራይዝድ መሆኑ ችግሩን ቀለል የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ ማንም ለማንም ተቀምጦ አይፈተንም።

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ያሉን ነገር ያው አሰራራችን ዘመናዊነትን የተከተለ አለመሆኑን ተከትሎ የተፈጠረ ችግር ነውና እንደው ኤጀንሲው ራሱን በቴክኖሎጂ ለማብቃት ምን እየሰራ ነው?

አቶ አርአያ፦ ባለፉት አመታት ኤጀንሲው በተለያየ ደረጃ እድገት አሳይቷል፤ ትልቁ ውጤቱም አገልግሎቱን ‘አውቶሜት’ ለማድረግ እያካሄደ ያለው ስራ ነው፤ በአሁኑ ወቅት ለዘመናት በኤጀንሲው በወረቀት ተቀምጠው የነበሩ የትምህርት መረጃዎች ተደራጅተው በአውቶሜሽን እንዲቀመጡ ሆኗል። ስለሆነም ማንኛውም ወደኋላ ሄዶ መረጃን የሚጠይቅ ባለጉዳይ ሲመጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትምህርት መረጃውን የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

በሌላ በኩልም በየዘመኑ የነበሩት የእርማት ሂደቶች ሳይንሳዊ ይዘት ኖሯቸው በእጅ ንክኪም ስህተቶችን ለማረም የሚደረጉ ጥረቶች ሙሉ በሙሉ ተቀርፈው ኮምፒተራይዝድ አሰራር ከመጀመሩም በላይ እርማቱ ሁሉ በኮምፒውተር ሆኗል። ይህንንም ለማድረግ ያስችል ዘንድ በቴክኖሎጂ የዘመነና እኤአ የ 2018 ምርት የሆነ ማሽን በሥራ ላይ ይገኛል።

ኤጀንሲው ራሱን ዘመናዊ ለማድረግ ከሄደባቸው ርቀቶች አንዱ ፈተናዎችን ኮምፒውተራይዝድ በሆነ መልኩ ለመፈተን ማቀዱ ሲሆን ይህም ከወረቀት በመውጣት’ አይፓዶችን’ ና ላፕቶፖችን በመጠቀም ፈተናዎችን የምንፈትንበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። በተለይም ሙከራዎቹና ጥረቶቹ ከተሳኩ ተማሪዎቻችን በአይፓድ ፈተናዎችን የሚፈተኑበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

አዲስ ዘመን፦ ይህንን ቴክኖሎጂ እንደ አገር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለን?

አቶ አርአያ ፦ ዘንድሮ 4 መቶ 50 ሺ የሚጠጉ የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች እንዳሉን እንገምታለን፤ ከዚህ አንጻር ተጨማሪ ወጪ አክለው ሌሎች መሟላት የሚገባቸው ነገሮቸም አሉ፤ ሆኖም የመንግስት ትኩረት በዚሁ ከቀጠለ እነዚህ ግብዓቶች አሟልተን ዘንድሮ ተማሪዎቹም እንዲለማመዱበት ሆኖ ወደ ስራ የምንገባበት ሁኔታ ነው ያለው።

በእርግጥ ከጀርባው ሊሟሉ የሚገባቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ፈተናን በአይፓድ መፈተን እንደምንችል ያረጋገጥንበት ወቅት ላይ ነን ፤ እዚህ ላይ ግን የሁሉም ተሳትፎ ተከታታይ ስልጠና ያስፈልጋል ፤ በመሆኑም የጎደሉ ነገሮችን አሟልቶ ለመገኘት ከፍተኛ የሆነ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፦ ይህ ቴክኖሎጂ እንደተባለው ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል ለኤጀንሲው ምን ያስገኝለታል እንደ አገርስ የሚታዩትን ችግሮች ከመቅረፍ አንጻር አቅሙ ምን ያህል ነው?

አቶ አርአያ ፦ ይህ ቴክኖሎጂ ወደ ስራ ገባ ማለት ለኤጀንሲው ትልቅ እመርታ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አገር በፈተና ዙሪያ ከእርማት፣ ፈተናውን ከማስተዳደር እስከ ፈተናውን እስከ መፈተንና ውጤት አገላለጽ ድረስ ሂደቱን ዘመናዊ ከማድረጉም በላይ ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ ስለሚሆን አስተማማኝነቱ የጎላ ይሆናል።

ሌላው ከዚህ በኋላ እንደ አገር የወረቀት ፈተና እድሜ አይኖረውም በተጨማሪም ማርክ አስተካክሉልኝ የሚል ጥያቄም ቦታ ያጣል።

አዲስ ዘመን፦ ቴክኖሎጂ የሚሰጠውን ጥቅምና የሚያቀለውን የስራ ጫና ያህል የጎንዮሽ ችግሮችም አብረውት አሉና እነዚህ ጥናት ተደርጎባቸዋል?

አቶ አርአያ፦ እድገት አይደል እንግዲህ የሚመጡትንም ችግሮች በየጊዜው የምናያቸው ይሆናሉ፤ ችግሮችም ሲያጋጥሙ ከስር ከስር እየፈታን ወደፊት የምንሄድበት ሁኔታ ነው የሚኖረው።

በነገራችን ላይ ፈተና በአንድ አገር አቀፍ ደረጃ ይዘጋጅ እንጂ ተሳትፎ የሚያደርጉት ብዙዎች ናቸው። ባለፈው 2011 ዓ.ም እንኳን ብናይ ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ መምህሩ፣ ፈተና አስተዳደሩ፣ የአካባቢው ማህበረሰብና ወላጅ ተማሪዎች በጠቅላላው 70ሺ ሰው ነው የተሳተፈበት። ስለዚህ ይህ ሁሉ ፍላጎት አለው፤ የዚህ ሁሉ ፍላጎት ወደ አንድ አምጥተን የምንመዝናቸው ልጆች ውጤታቸውን መሰረት አድርገን ወደሚቀጥለው ደረጃ እንዲሄዱ በአግባቡ ስራውን ካልሰራን የሚመረጡትና ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ተማሪዎች የማይሆኑ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ሙስና ነው፤ ከዚህ የበለጠ ሌብነትም የለም።

አዲስ ዘመን፦ ይህንን ሁኔታ ለመከላከል ቴክኖሎጂው አንድ አጋዥ ሊሆን ይችላል፤ሆኖም እንዴት ነው ከዚህ ችግር ሙሉ በሙሉ መውጣት የሚቻለው?

አቶ አርአያ፦ ይህንን ለመከላከል ከላይ እስከታች በአመለካከት አንድ መሆን ያስፈልጋል፤ ኤጀንሲው ፈተናው በተቻለ መጠን ሳይንሳዊ ይዘት ኖሮት ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እያዘጋጀ ነው፤ ግድፈትና ሌሎች ስህተቶች እንዳይኖሩ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል ፤ ሌላው ባለድርሻ አካልም በዚህ ልክ ሚናውን ሊወጣ ይገባል።

የሚገርመው ከሁለትን ሶስት ዓመት በፊት የ12 ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ሲካሄድ ፈርቼ አላውቅም ነበር፤ እንደውም ከብዛቱ አንጻር የ10ኛ ክፍል ፈተና ሌብነት ይኖርበታል ብዬ እሰጋ ነበር። አስረኛ ክፍል ግን በሚገርም ሁኔታ እየተስተካከለ መጥቶ 12ኛ ክፍል ፈተና ነው ችግር እያስተናገደ ያለው። ዘንድሮ ደግሞ የ10 ኛ ክፍል ፈተናም ስለቀረ አሁን ከደረስንበት ቴክኖሎጂ አንጻር ችግሩ ቀለል ይላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ።

አዲስ ዘመን ፦ከዚህ ቀደም የነበረው የፈተና አወጣጥ ግን ምን ይመስል ነበር?

አቶ አርአያ፦ ፈተና መነሻ አለው ፤ ዝም ብሎ አይደለም የሚጻፈው፤ አንደኛ በስርዓተ ትምህርቱ መሰረት የሚማሩትን የትምህርት ይዘትና በትንሹ ሊይዙት የሚችሉትን እውቀት መሰረት አድርጎ ሊመዝን ይችላል ወይ? ሊለይ ይችላል ወይ ? አስተማማኝ ነው ወይ? የሚሉትን ነገሮች ከትምህርት ስርዓቱ ጋር አወዳድረን ነው የምናዘጋጀው።

ድሮ ፈተናን መጻፍ ነበር አሁን ግን ቢያንስ አራት ደረጃዎችን ማለፍ አለበት ብለን በማሰብ ይጻፋል፤ ኤዲት ይደረጋል፤ ሪቪው ይደረጋል፣ አገባቡ ልክ ነው አይደለም የሚለው ይታያል፤ ከትምህርት ይዘቱ ጋር ያለው መስተጋበር ይለያል እነዚህ ሁሉ ተለክተውና ታይቶ ነው ፈተና የሚሆነው። አጋጣሚ ዘንድሮ 10 ኛ ክፍል ቀረ እንጂ እሱ ደግሞ አንድ እርምጃ ወደፊት ይሄዳል በዚህም የሙከራ ፈተና ተሰጥቶ ውጤቱም በዛው መሰረት ተለክቶ ነበር ወደ ቋት የሚገባው። ወደፊትም ቢሆን አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ስላለ በዛ አደረጃጀት መሰረት የትምህርት ይዘቱን በሚሰራው ስርዓተ ትምህርት እንቃኛለን።

የፈተና መነሻው ስርዓተ ትምህርት ነው፤በዚህም ስርዓተ ትምህርቱ አንድ ተማሪ ሊያገኝ የሚገባው ብሎ የሚጠብቃቸው ነገሮች አሉ ፤ ይህንንም መሰረት አድርገን

 ነው በመለኪያ እየመዘንን የምንሰራው። በኮምፒውተር የሚሰጠው ፈተና ተፈታኙን ይለየዋል አንዱ ለአንዱ ሊቀመጥ አይችልም ፤አሻራ አለ ፤ በዚህም አንዱ ለአንዱ ሊፈተን ይገባ የነበረውን ሌብነት እናስቀራለን ማለት ነው። ይህም ቢሆን ግን የሰው ልጅ አእምሮ ለጥሩም ለመጥፎም የሰላ በመሆኑ የሚያጋጥመው ነገር አይታወቅም ሲሆን ደግሞ ቀድመን የምንገኝበትን ነገር እናያለን። ግን ትልቁ ነገር ውጤት በስራ ነው መገኘት ያለበት ፤ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ያለፉ ልጆች ደግሞ የድካማቸውን ውጤት ማግኘት አለባቸው ፤ ይህንን ለማድረግ ደግም በትምህርት ሴክተሩ ላይ የተሰማራነውን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎውን ካላረጋገጠ አስቸጋሪ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው ከፈተና ጋር በተያያዘ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት እያጋጠሙት ያሉት ችግሮችና እየሄደባቸው ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎች ሰዎች እምነት እንዲያጡበት ያደረገ ይመስለኛል፤ በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው ?

አቶ አርአያ ፦ እውነት ለመናገር ባለፉት ዓመታት የተበላሹ ነገሮች አሉ፤ ሆኖም እኛን እዚህ ደረጃ ያደረሰን ፈተናዎቹ ከእጃችን ከወጡ በኋላ ያጋጠማቸው ችግር ነው። እስከ አሁን ፈተናን በማዘጋጀት ሂደት ላይ ችግር አጋጥሟል የሚል መረጃ የለኝም፤ ለምሳሌ አምና ያጋጠመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ችግሩ ጥያቄው ላይ የተፈጠረ አይደለም። ሆኖም ልጆቹ ሊያገኙ የማይገባቸውን ውጤት ነው ያገኙት ይህ ደግሞ በመካከል የገባ መልስ አለ ማለት ነው። ከዚህ አንጻር እኛም ባደረግነው ፍተሻ ሁለቱ ኮድ የተዘበራረቀና አንዱ ለአንዱ የተሰጣጣ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም ወዲያውኑ ይቅርታ በመጠየቅ እንዲስተካከል ሆኗል።

አዲስ ዘመን፦ ችግሩ የተፈጠረበት ምክንያት ግን ታውቋል?

አቶ አርአያ፦ አዎ ታውቋል። ችግሩ ወዲያው እንደተ ፈጠረም ችግሩ የተፈጠረበትን ክፍል ነው የጠየቅነው። ምክንያቱም እኛ ጋር ነው እንዳንል እኛ የመልስ ቁልፉን አናውቀውም ስለዚህ ችግሩን ተማምነን እንዲያስተካክሉ አደረግን በዛ መሰረትም ይቅርታ ተጠይቀናል። ይህም ቢሆን ግን አጋጣሚው ጥሩ አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ አጋጣሚ ነው ብሎ ማለት ግን ይቻላል? እርስዎ አጋጣሚ መሆኑን ያምኑበታል?

አቶ አርአያ፦ ስህተት ነው። አጋጣሚም ነው። ሁለቱ ኮድ እኮ ትክክል ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ ጥያቄዎቹ ችግር የለባቸውም ማለት ነው ። የሁለቱ ኮድ መልስ ነው የተዘበራረቀው፤ እኛ በእርማት ሂደት ላይ የተሰጠንን መልስ ነው የምናስገባው ኮምፒውተሩ ደግም የተሰጠውን ነው የሚቀበለው በዛ ምክንያት ደግሞ ይበላሻል።

እዚህ ላይ ግን ስህተቱ ባይፈጠር ጥሩ ነበር፤ ግን ደግሞ ከተፈጠረ በኋላ ማዕከሉ ስህተቱን አምኖ ትክክለኛውን መልስ ባይሰጠን ኖሮ ምናልባትም ችግሩን በቶሎ ማረም እንቸገር ነበር።

ከዚህ ሌላም ፈተና ላይ እስከዚህ ድረስ መሮ አይሂድ እንጂ በየትምህርት ቤቱ በሚሰራው ስራ ራሱ የሚያጋጥሙ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ በዛን ወቅትም የምንወስዳቸው እርምጃዎች አሉ፤ ይህ ጥሩነቱ በተማሪዎቹ ውጤት ላይ ምንም ጫና አያመጣም።

አዲስ ዘመን፦ ከተፈጠሩ ችግሮች ትምህርት ወስደናል የሚል እምነት አለኝ፤ ወደፊትስ እንደዚህ አይነት ነገሮች እንዳያጋጥሙ የተቀመጡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

አቶ አርአያ፦ ይህ እንዳይደገም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ፈተናዎችን አዘጋጅቶ ቋት ውስጥ ማስገባት ይገባል። ቋቱ ደግሞ የመመዘን አቅሙን መጥኖ ነው የሚሄደው ፈተናውም ተለክቶ ነው የሚሰጠው፤ በዚህ በዚህ መንገድ የፈተናን ዝግጅትና የፈተና አወጣጣችን ሳይሆን ችግር የሆነ የፈተና አስተዳደሩ ነው። ለምሳሌ አምና የጋሸበ ውጤት አለ ተብሏል። ይህ ውጤት አንድ ዞን አካባቢ ያለ ተማሪ ወይም 124 ትምህርት ቤቶች አንድ አይነት ውጤት በአንድ የትምህርት አይነት ላይ ማምጣታቸውን እንዴት መቀበል ይቻላል።

ይህ ምንልባት የፈተናው አወጣጥ ሊሆን ይችላል እኔ አላውቅም ፤ ግን በጋራ ሰርተዋል የሚለው መያዝ አለበት ይህን እንግዲህ ባለፈው ዓመት ሪፖርት ቀርቦ የተሻሉ ናቸው የተባሉ አራት የትምህርት ዓይነት ውጤት ተወስዶ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ሆኗል ። ምክንያቱም ሌላው የተበከለ በመሆኑ ነው ይህ ምናልባትም ተማሪው ብቻ ላይሆን ይችላል ያደረገው በትምህርት ቤቱ ከአስተዳደር ጀምሮ ያሉ የትምህርት ማህበረሰቦች ተባባሪ ናቸው። እነሱ ባይተባበሯቸው ኖሮ እንደዚህ ዓይነት ውጤት አይመጣም።

ሌላው በ 2008 ዓ.ም ፈተና ተሰርቋል። ሁላችንም በሁኔታው አልቅሰናል ፤ሶስት ወር ሙሉ እንቅልፍ ያጣሁበትን ስራ በአንድ ቀን ሲያመክኑት ምንም ማድረግ ስለማይቻል ፈተናው ተሰርዟል፤ ኤጀንሲው ግን እልህ ውስጥ ገብቶ ቀላል ባይሆንም እንኳን በአንድ ወር ውስጥ እንደገና ፈተና አዘጋጅቶ ተማሪዎች እንዲፈተኑ ሆኗል። ቀጣዩ የትምህርት ጊዜም አልባከነም። በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በቀጣይ ሊያጋጥሙን አይገባም በማለት መንግስትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ኮምፒውተርን መሰረት ያደረገ ፈተና ያዘጋጀው። ከዚህ በኋላም ለእናንዳንዱ ተማሪ ላፕቶፕ በመስጠት እናስፈትናለን ይህም በጣም አስተማማኝ የኤጀንሲውንም ታሪክ አንድ ርምጁ ወደፊት የሚያስኬድ ስራ ነው ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፦ ህብረተሰቡ በኤጀንሲው ላይ ያሳደረው የተሸረሸረ እምነት መገንባት ይቻላል?

አቶ አርአያ ፦ ኤጀንሲው ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ነው፤ ውስጣችንን ማሳየት አልቻልንም እንጂ በጣም ዘመናዊ ስራን እየሰራን ነው። የተሻሉ ነገሮች እንሰራለን ካልናቸው ነገሮች መካከል ደግም ከ 15 እስከ 20 ደቂቃ ውስጥ ባለጉዳዮች የትምህርት ማስረጃቸውን አግኝተው እየሄዱ ነው። ሌላውንም አገልግሎታችንን በተመሳሳይ ዘመናዊ ለማድረግ እየሞከርን ነው። የፈተና አቅማችንንም በተለይ የወረቀቱ አለ በሚባልን የጥራት ደረጃውም የተረጋገጠ እኤአ የ 2018 ምርት ነው። ውጤትም ከዚህ በኋል አስተማማኝ ይሆን ዘንድ ከእጅ ንክኪ የጸዳ አሰራርን ተግባራዊ አድርገናል።

በቀጣይ ያለፉትን ዓመታት ስራዎቻችንን የበለጠ ፈጣንና ዘመናዊ በማድረግ ሰዎች ውጤታቸውን ወዲያውኑ አይተው የሚሄዱበት ሁኔታ ይመቻቻል። ከምንናገረው በይበልጥ ደግሞ ወደፊት ለውጣችንን ማየትና እምነትን ማጽናት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ በአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተና አወጣጥ ራሳችንን ከሌሎች አገሮች ጋር ስናወዳድር የት ላይ ነን?

አቶ አርአያ፦ በየዓመቱ የፈተናው ሂደቱ ውጤት የተለካበት ሪፖርት አለ ፤ ባለፉት ዓመታት የነበረው ነገር በተለይም በ2008 ዓ.ም ያጋጠመው የፈተና ስርቆት ሂደቱን ጥቁር ነጥብ አስያዘው እንጂ ከዛ ውጪ የነበረው ነገር ከየትኛውም የአፍሪካ አገር የተሻለ ነው።

አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን አሁን በፈተና በአጠቃላይ በመማር ማስተማሩ ላይ ያለው ችግር እየጨመረ አልሄደም?

አቶ አርአያ፦ ጥፋቱማ በጣም እየጨመረ ነው። በነገራችን ላይ በበይነ መረብም በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘዴዎችም ስናይ በሌሎች አገሮች የሚካሄደው የፈተና ስርቆት የሚታይ ነው። በመሆኑም እኛም መጠንቀቅ እንዳለብን ሆኖ በ 2008 ዓ.ም ያጋጠመው ግን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቁር ነጥብ እንዲያዝባት ያደረገ ነው። አሁን ደግሞ ተስፋ አደርጋለሁ እንወጣለን።

አዲስ ዘመን፦ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረግ ምደባ በክልሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭቅጭቅ እያስነሳ አንዳንዶችም የእኔ ተማሪ እዚህ አይሄድም የሚሉትም ነገር አለና እንደው ለዚህ ላይ እርስዎ ምን ምላሽ አለዎት?

አቶ አርአያ፦ ምደባን ከመንግስትም ከሌላም አካል የሚመጡ መመሪያዎች አሉ እኛም እነሱን መሰረት አድርገን ነው የምንሰራው፤ መረጃው ተማሪው ውጤቱ አለ እኛ ጋር በዚህ መሰረት ወደ ከፍተኛ ትምህርት የመግባት አቅማቸው ሲለይ እንለያቸዋለን፤ በግል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው መማር የሚችሉ ካሉም እነርሱንም እናያለን።

ሆኖም የእኔ ክልል ተማሪዎች ሌላ ቦታ ሄደው አይመደቡብኝ የሚለው አባባል በጣም የሚገርመኝ ነው። በነገራችን ላይ እንደዚህ የሚሉት አንዳንድ ክልሎች አይሄዱም የሚሏቸውን ተማሪዎች እነሱ ጋር ብናስቀር ለማስተናገድ የሚሆን አቅም የላቸውም። አሁን መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሰላም አጡ እንጂ የትምህርት አካባቢ ከሆኑ የትስ ቢኬድ ከኢትዮጵያ ውጪ ይኬድ የለም እንዴ ? ውጪ አገር ነጻ የትምህርት እድል ያገኘ ሰው እኔ እዚህ አገር አልሄድም ብሎ ይቀራል? አይቀርም። ስለዚህ ዲግሪ ለመማር በመላ አገሪቱ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምት የሚሰጡት ትምህርት አንድ አይነት ነው ስለዚህ መሄድ ግዴታ ነው።

እኔ እንደ ትምህርት ባለሙያ አልመርጥም ዩኒቨርሲቲዎች መንግስት ያቋቋማቸው ሀብት ናቸው ማንኛውም ተማሪ የእኔም ልጅ ቢሆን ሄዶ ሊማርባቸው ይገባል። ስለዚህ ድልድሉን ፍትሀዊ ለማድረግ መሞከር ይገባል፤ ከህክምና፤ ከወሊድ፤ ተመሳሳይ መንትዮች አንጻር የሚታዩ ልዩ ሁኔታዎች ይኖራሉ። በተረፈ ግን እዚህ አልሄድም ወይም አይሄዱም የሚለው ሀሳብ መጥፎ ስለሆን እንደ አገር ተስማምተን ልጆቹን በማስቀረት ሳይሆን ሰላማዊና ጸጥታው የተጠበቀ የትምህርት አካባቢ ፈጥረን እንዲማሩ ድጋፍ ማድረግ ነው የሚሻለው።

ይህ ሁኔታ ለነገሩ ጊዜያዊና ምክንያታዊ ያልሆነ የሚጠፋ ነው፤ ዛሬ አልሄድም ያለበት ቦታ ነገ ለምኖና ፈልጎ የሚሄድበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህ ቀደም የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እኮ ሳይጣሉ ቀርተው አይደለም ግን ጸባቸው በድንጋይና በዱላ ሳይሆን በሀሳብ ነው የሚፋጩት ያንን መሰረት አድርገው ደግሞ ስለ አገራቸው ነገም ይጨነቁ ነበር።

አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ምን ያህል ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ነው?

አቶ አርአያ ፦ ስራው ሙያዊ ነው፤ እድሜ ልኬን በትምህርት ስራ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት፤ ወደ ኤጀንሲውም የመጣሁት ከትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርነት ነው፤ የእኛ ትልቁ ስራ ፈተና ማውጣት አይደለም? በዚህ ላይ ደግሞ እንኳን ሌላ ፖለቲከኛ ተሿሚ ጣልቃ ሊገባ ቀርቶ እኛም እንደ አመራር ባለሙያዎቹ ውስጥ ገብተን ይህ ይሁና ያ ይቀነስ ልንል አንችልም። እዚህ ላይ ግን እንደ ሌላው መንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኛው የራሱ የሆነ አቋም ሊኖረው ይችላል፤ ግን እንደ አሰራር ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የሌለበትና ነጻ ሆኖ የሚሰራ መስሪያ ቤት ነው።

አዲስ ዘመን፦በተያዘው ዓመት ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ ከዋና ዋና ከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች ላይ የተለየ የጸጥታ ስጋት ቢያጋጥም ፈተናውን በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ የእናንተ ዝግጁነት ምን ያህል ነው?

አቶ አርአያ፦ ባለፈው ጊዜ ፈተናን ስናንቀሳቅስ በአገሪቱ አለ የሚባል የጸጥታ ሀይል ነው አብሮን የነበረው፤ በወታደር ፈተናን አጅበን ያሳለፍንበት አካባቢም ነበር። አሁንም በጣም አስጊ የሆኑ ነገሮች ካሉ ከማህበረሰቡ በየደረጃው ካለ አስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር ጋር እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ ካሉ የጸጥታና የደህንነት ሰራተኞች ጋር በጋራ የምንሰራ ይመስለኛል።

ጉዳዩን ትምህርት ሚኒስቴርም በበላይነት ስለሚይዘው የእያንዳንዱ ክልል አስተዳዳሪዎች በተለይም ፈተናው እንዳሰብናው ሳይሳካ በወረቀት የምንሰጥ ከሆነ ይደግፉናል ብለን እናስባለን። ኮምፒውተርን መሰረት አድርገን የምንሰጥ ከሆነ ገን ሳይንሳዊ የመከላከል ስራን ከማከናወን በዘለለ ሌላ ችግር አያጋጥመንም።

አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ ከኤጀንሲው ምን እንጠብቅ?

አቶ አርአያ፦ በቢሮ ውስጥ የሚሰራ የፈተና ዝግጅት እኔን አሸንፎኝ አያውቅም። በጥሩ ትጋትና እምነት ነው የምሰራው ፤ ሁሉም ጓደኞቼ መምህራን ናቸው ሳይንሱም አለ፤ በተለይም ከ 2002 ዓ.ም ወዲህ እየተሰራ ያለው ስራ የአለም ባንክ ባለሙያዎች ሳይቀሩ የገቡበትና አስተማማኝ ነው። ከዚህ ባለፈም በየክልሉ የሚዘጋጁትን የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲወጡ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ እየፈተሽንና በጋራ እየሰራን ነው። ጥሩ ደረጃ ላይም ነን።

ህብረተሰቡ ፈተናዎቻችንን በማየት ልፋቱን ሊለካ ይገባል፤ ቀድሞ በፈተና ላይ በጣም አስቸጋሪው የነበረው አንዱ ለአንዱ መፈተን፣ መኮረጅና ወረቀትር መቀባበል ነበር ፤ አሁን ግን ፈተናው ውጪ ወጥቶ ተደራጅቶ ሰርቶ መግባት ሆኗል፤ ይህንን ደግሞ በአቅራቢያው ያሉት ሰዎች ካልረዱን ምንም ማድረግ አይችልም።

በጠቅላላ ይህ ስራ የሰው ሃብት ልማት ስራ እንደመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣና ሊደግፈን ይገባል፤መገናኛ ብዙሀኑን ትክክለኛውን በመውሰድ ስህተቱን አጉልቶ ማውጣትና መናገር ይገባቸዋል።

አዲስ ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ አርአያ ፦ እኔም አመሰግናለሁ

አዲስ ዘመን የካቲት 18 / 2012

 እፀገነት አክሊሉ