“ለሚያልፍ ጊዜ የሚያስተዛዝበን ነገር መፈጸም ተገቢ አይደለም”- አቶ ዳንኤል ሚኤሳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ

50

በተለያዩ ጊዜያት ወቅትን እየጠበቁና እንዲሁም ምንም ዓይነት አስገዳጅ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጥ የሆኑ ምርቶችን የሚደብቁ ፣ ከዋጋቸው በላይ የሚሸጡ በርካታ ነጋዴዎችና የንግድ ድርጅቶች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል።
በተለይም በአገር ላይ ችግር ሲከሰት፣ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ሲመጡ አልያም ሰዎች መሰረታዊ የሚባሉትን የፍጆታ እቃዎች በብዛት ይፈልጋሉ ብለው በሚያስቡበት ወቅት የሚደበቀውና ዋጋው የሚያሻቅበቅው ምርት ይበዛል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር እነሱ በዚህ ሁኔታ ምርትን እንዲደብቁ ወይም ከዋጋው በላይ ጨምረው እንዲሸጡ የእኛም የሸማቾቹ አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑ ነው። የሸማቹ በዓል ነው ወይም ደግሞ ልክ አሁን እንዳለንበት የኮሮና ቫይረስ ስጋት ወቅት ምርቶችን በብዛት የመግዛትና የማከማቸት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አካሄድ ለእነሱ የተመቸ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮም ችግሮች ባጋጠሙባቸው ጊዜያት ሁሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። እርምጃውም እነዚህ ህገወጦች ለስራቸው የሚጠቀሙባቸውን የንግድ ድርጅቶች ከማሸግ ጀምሮ በወንጀል እስከ መጠየቅ የሚደርስም እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት አስታውቋል። የከተማዋን ወቅታዊ የንግድ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል።
በተለይም የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ፤ ምርቶችን በመጋዘን የደበቁ፤ ያለ ንግድ ፈቃድ ሲሰሩ በተገኙ፤ በድጎማ በቀረቡ የሸማች ዘይትና ስኳር ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉት ላይም ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል። ከዚህም በተጨማሪ ለንግድ ድርጅቶች የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያም ይሰጣል ። የመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦትን በተመለከተ ወርሃዊ ኮታ ስንዴ፤ ስኳር እንዲሁም የምግብ ዘይት በመቅረብ ላይም ነው። በተለይም በስንዴ ስርጭትን የዳቦ አቅራቢ ፋብሪካዎችና ስንዴውን ወስደው ወደ ዱቄት በመቀየር ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት እክል ሳይገጥማቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎት እንዲያሟሉም ይሰራል ።
የአዲስ ዘመን የዝግጀት ክፍል የተጠየቅ አምድም ንግድ ቢሮው ገበያን ለማረጋጋት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ እየታዩ ያሉ የዋጋ አለመረጋጋቶችን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ከሆኑት ከአቶ ዳንኤል ሚኤሳ ጋር ቆይታን አድርጓል።
አዲስ ዘመን ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በህግ የተሰጡት ስልጣንና ሃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ዳንኤል፦ ንግድ ቢሮው በዋናነት ከተሰጠው ሃላፊነት አንዱ የከተማዋ የንግድ ሥርዓት በህግና በደንብ መሰረት መካሄድ አለመካሄዱን መቆጣጠር ነው፤ በዚህ መሰረትም ህግ ተጥሶ ሲገኝ ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ ስልጣን አለው።
በሌላ በኩልም የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ቢሮ የሚመራባቸው ደንቦችና የአሰራር ሥርዓቶች መመሪያዎች አሉ፤ በዚህም መሰረት የንግድ ሥርዓቱ በሥርዓት መመራቱን ማረጋገጥም የቢሮው ተጨማሪ ሃላፊነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለንግድ ሥርዓቱ መሳለጥ ፍቃድ መስጠት ፣ የማደስ አካሄዱን የመቆጣጠር የመከታተልና የመደገፍ ስራዎችን ይሰራል።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህን ተግባርና ሃላፊነቶች እንደ ቢሮ ምን ያህል ተወጥታችሁታል ማለት ይቻላል?
አቶ ዳንኤል፦ ማንኛውም ስራ ሲሰራ ድክመትም ጥንካሬም ይኖረዋል፤ ይህም ቢሆን ግን ቢሮው መሰረት አድርጎ የሚሰራው የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ላይ ነው። ይህንንም ተግባርና ሃላፊነት ባሉት አዋጅና ደንቦች መሰረት የሚሰሩ ይሆናሉ። ንግድ ቢሮው ከማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ መኖሩና በዚህም ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለመሆን የሚደረገውን ጥረት እንደ ትልቅ የስራ ጥንካሬው የሚወሰድ ነው።
ሆኖም እንደ አሰራር በተለይም በቁጥጥር ስራው ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚና አናሳ መሆን እንደ ክፍተት የሚታይ ቢሆንም በህጉ ላይ የተቀመጠውን መስራታችን ግን ትልቅ እመርታ አድርጎ መያዙ ጥሩ ነው ።
አዲስ ዘመን፦ እንዳሉት ንግድ ቢሮው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ የሚሰራ ከሆነ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው ወቅትን የጠበቀና ያልጠበቀ ህገ ወጥ የንግድ ልውውጥ ምንጩ ምንድን ነው?
አቶ ዳንኤል፦ ህገ ወጥ የንግድ ልውውጥን ለመግታት ቢሮው የሚጠቀምበት የራሱ የሆነ የህግና የሥርዓት አሰራር አለው። በዚህም ወቅትን የጠበቁም ሆነ ያልጠበቁ ህገ ወጥ የንግድ ልውውጦች ሲያጋጥሙ አጥፊዎች ላይ የንግድ ሱቃቸውን ከማሸግ ጀምሮ በወንጀል እስከ መጠየቅ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል። ከዚህም በተጨማሪ ገበያውን ሊያረጋጉ የሚችሉ የአቅርቦት ማስተካከያዎችም ይደረጋሉ። ይህንን የመሳሰሉ ስራዎችን በማከናወን ህገወጥነትን የመዋጋት ስራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ወቅታዊ ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ችግር ጋር በተያያዘ በርካታ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ምርቶችን በመደበቅ፣ ከዋጋ በላይ በመሸጥ እንዲሁም ገበያው እንዳይረጋጋ የተለያዩ ውዥምብሮችን በመንዛት ላይ ናቸውና ፤ የቢሮው እርምጃ ምን ያህል ነው ተደራሽነቱ?
አቶ ዳንኤል፦ የኮሮና ቫይረስ ችግር ዓለም አቀፍ ነው፤ ሆኖም ግን እንደ አገር እኛም ጋር እየደረሰ በመሆኑ በዚህ የተነሳ በገበያው ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ለመቆጣጠርና ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ከተማ አቀፍ ግብረ ሃይል ተቋቁሟል። ግብረ ሀይሉም ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ እየሰራ ሲሆን በውስጡም የህግ ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አካላት፣ የነጋዴ ፎረም፣ የነዋሪ ፎረም፣ የመሳሰሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች የተሳተፉበት ነው ፤ በዚህም መሰረት በሽታው ወደ አገሪቱ ገብቷል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ግብረ ሀይሉም የንግድ እንቅስቃሴውንና አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን ከመቆጣጠሩም ባሻገር ገበያውን በጋራ የመወሰን ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙትን በመከታተል እንዲሁም የምርት ጥራትን ሊያጓድል የሚችል ተግባርን የሚፈጽሙ አካላትን ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ በኩል ሰፊ ስራን ሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፦ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ብቻ የታሸጉና የተዘጉ የንግድ ድርጅቶች ምን ያህል ናቸው?
አቶ ዳንኤል፦ በቢሮው የተቋቋመው ግብረ ሃይል ባለፉት ቀናት ውጤታማ ስራን የሰራ ሲሆን በዚህም መሰረት ከ14ሺ በላይ የንግድ ተቋም በቁጥጥርና ክትትል ግብረ ሃይሉ ተደራሽ ተደርጓል። በተገኘው ውጤት መሰረትም በ 11 የምርት አይነቶች ላይ እና 12 ፋርማሲዎችን ጨምሮ በ767 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል።
ለእርምጃው መነሻ የሆነው ደግሞ ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ በጋራ ዋጋ የመወሰን ምርት የማከማቸትና የመደበቅ ፣ በምርቶች ላይ ከፍተኛ ዋጋ የመጨመር እንዲሁም በተለያዩ ምርቶች የዋጋ ንረትና ሰው ሰራሽ እጥረት በሚያስከትሉ ስራዎች በተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ ነው ።
እርምጃው በወፍጮ ቤቶች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ተቋማት፣ ሸቀጣሸቀጥ መደብሮች ፣ መድሃኒት ቤቶችንና በበርበሬ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ያካትታል።
ወቅታዊ የዋጋ ንረት የሚታይባቸውን የፅዳት መጠበቂያ እቃዎች እንደ ሳኒታይዘር የመሳሰሉ ምርቶችን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በመደበኛ ዋጋ በ80 ብር በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው። በተጨማሪም የምርት አቅርቦትን ለማሻሻል ቢሮው ከክልሎች ጋር እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ እናንተ በህገ ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርቶ ያገኛችሁትን ነጋዴ ሱቁን ስታሽጉ በጎን እቃውን አውጥቶ በሩ ላይ ሲነግድ የሚታይበት ሁኔታ አለና እንደው ከማሸግ ባለፈ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ሃላፊነታችሁን እየተወጣችሁ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ዳንኤል፦ በዚህ ሰሞን ብቻ ከ 14 ሺ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትልና ቁጥጥር አድርገናል፤ በዚህም 767 የንግድ ተቋማትን አሽገናል። ከላይ እንደገለጽኩት፤ ከእነዚህ መካከል ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ወደ 361 እንዲሁም 329ኙ ደግሞ ያለንግድ ፍቃድ አጋጣሚውን ተጠቅመው ለመጠቀም ሲያስቡ የተያዙ ናቸው። በመደበቅና በማከማቸትም ከ 60 ያላነሱ ተቋማት ላይ እርምጃ የተወሰደበት ሁኔታ አለ።
ይህ የሚያሳየው እየወሰድነው ያለው እርምጃ ከሌላው ጊዜ በተለየ የተለየ መሆኑን ነው። ከዚህ በፊት የሚወሰደው እርምጃ አስተዳደራዊ እርምጃ ነው፤ አሁን ከዚህ ባሻገር አጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እስከመውሰድ ተደርሷል። በዚህም አጥፊዎችን እንደ ጥፋት አይነታቸው ፍርድ ቤት የመክሰስ ንብረቶቻቸውን የመውረስና ግብዓቶቹ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካይነት ወደተጠቃሚው እንዲደርስ የማድረግ ስራ በመሰራት ላይ
ነው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ቢሮው ከምን ጊዜውም በላይ የሚወስደው እርምጃ ጠንከር እያለ መምጣቱን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ይህ እርምጃ ወቅታዊውን የአገራችንን ችግር የተንተራሰ ነው። የንግድ ሥርዓቱ በህገወጦች የሚተራመሰው ደግሞ በየጊዜው ነውና ቢሮው ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት እርምጃዎች ለመውሰድ ነው የሚያስበው?
አቶ ዳንኤል፦ ዋጋ ጨምረዋልና መቀነስ አለባቸው የሚለው አስተሳሰብ መያዝ ያለበት አይመስለኝም። ምክንያቱም እንደ አገር የምንከተለው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን ነው። ስለዚህ ዋጋን የመወሰን ስልጣን ቢሮው የለውም። ነጋዴውም ያዋጣኛል ባለው ዋጋ ነው የሚሸጠው እየሸጠም ያለው።
እኛ የምንቆጣጠረው ነጋዴው ሲሸጥ ህጋዊ ሆኖ ደረሰኝ ተጠቅሟል ወይ የሚለውን እንጂ ዋጋ ጨምር ቀንስ የሚለው ስራ ላይ አንገባም። ሆኖም እጥረት ባጋጠማቸው ምርቶች ላይ አቅርቦትን የማጠናከር ስራን እንሰራለን። በተለይም አሁን ላይ አቅርቦቱን ለማጠናከር ከክልሎች ጋር ከፍተኛ ትስስርን እየፈጠረን ህብረት ስራ ማህበራትና የከተማው ህብረት ስራ ኤጀንሲ እንዲሁም ቢሮው በጋራ ከክልሉ ህዝብ ጋር ተሳስሮ ወደ ማዕከል ምርቶች እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው ።
በሌላ በኩልም የጽዳት እቃዎች ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በመደበኛ ዋጋ ለምሳሌ ወቅቱ የሚፈልገውን የንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) ህብረት ስራ ማህበራት በመደበኛ ዋጋው ማለትም በ80 ብር እንዲሸጥ እየተደረገ ነው። እንደዚህ ባለው መልኩ አቅርቦቱን የማጠናከር ስራውን አጠናክረን እንቀጥላለን።
አዲስ ዘመን፦ ቢሮው አቅርቦትንስ የማመቻቸት ስልጣን አለው ?
አቶ ዳንኤል፦ አዎ ህብረት ስር ኤጀንሲ ለንግድ ቢሮው ተጠሪ ተቋም ነው፤ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ደግሞ በስሩ በርካታ ህብረት ስራ ተቋማት ያሉት ሲሆን ከ 143 በላይ መሰረታዊ ማህበራትና 10 ዩኒየኖችን ያቀፈ ነው። በመሆኑም እነዚህን ዩኒየኖች ከክልል ዩኒየኖች ጋር አስተሳስረናል። በርካታ የግብርና ምርቶችም በእነሱ በኩል ነው የሚገቡት፤ አሁን ላይ እንደዚህ ኑሮ ተወደደ በሚባልበት ጊዜ ማህበራቱ ጋር ነጭ ጤፍ በ 33 ብር ፣ ገብስ 17 ብር ነው እየተሸጠ ያለው ስለዚህ አሁን የምርት እጥረት አልገጠመንም ያለውንም አውጥተናል፤ ሰሞኑንም ጠፉ የተባሉት እንደ ሎሚ ፣ ነጭ ሽንኩርትና መሰል ግብዓቶችንም በእነዚሁ ማህበራት አማካይነት እንዲገቡ ተደርጓል። በመሆኑም ይህንን ስራ መንግስት ያስተባብራል ይደግፋል ጎን ለጎንም ደግም ይቆጣጠራል። በዚህ መካከል አቅርቦቱ ሲጨምር የንግድ ሥርዓቱ ደግሞ የሚረጋጋ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ ሰዎች የንግድ ቢሮ ስራ የወረት ነው አንድ ነገር ተፈጠረ ሲባል ቀና ቀና ይልና ግብር ሃይል ያቋቁምን ችግሩ የተፈታ ሲመስል ደግሞ በዛው ይጠፋል ይባላል ፤ ከዚህ አንጻር ቢሮው የቁጥጥርና የክትትል ስራው ጠንካራ ነው ይላሉ?
አቶ ዳንኤል፦ እንግዲህ ንግድ ቢሮ ዋጋን የማስቀነስ ስራ መስራት ያለበት የሚመስለው ካለ እውነትም ቢሮው ምንም እየሰራ አይደለም ማለት ይቻላል። እየሰራ አይደለም ለማለት የማንችልበት አግባብ ደግሞ ዋጋ እንዲቀንስ የማድረግ ስልጣን ያለው አለመሆኑ ነው። ምንድን ነው ሊያደርግ የሚችለው ህጋዊ የንግድ አሰራርን ተከትሎ ነጋዴው እንዲሰራ ማድረግ ነው ይህ ደግም አንድ ነጋዴ ሲሸጥ ግብይቱን በደረሰኝ ያድርግ፣ ዋጋ በሚታይ ቦታ ይለጥፍ ህጋዊ የንግድ ፍቃድ ይዞ እንዲነግድና አላስፈላጊ ክምችት እንዳይኖር የማድረግ ስራ ነው የሚሰራው። ጎን ለጎን ደግሞ አቅርቦት ከላይ በገለጽኩት አግባብ በቅንጅት ወደ ከተማው እንዲገባ ያደርጋል።
ይህ መደበኛ ስራውና ሁሌም የሚሰራው ነው ፤ ከዚህ ውጪ ደግሞ ችግሮች ሲያጋጥሙ በተለየ ትኩረት ይሰራል። ለምሳሌ የበዓል ወቅት፣ አሁን እንዳለንበት አስቸጋሪ የጤና እክሎች ሲያጋጥሙ ልዩ ግብረ ሀይል ይዋቀራል። በዚህም ጠበቅ ያለ እርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ ይኖራል።
አንዳንድ ጊዜ እኮ ነጋዴው ላይ የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎች አስተማሪ የሚሆኑበት ጊዜ አለ ፤ ለምሳሌ የበርበሬ መነገጃ ቤቶች በብዛት ታሽገዋል በዚህ ጊዜ በርበሬው የመሻገትና የመበላሸት ሁኔታ ሊገጥመው ይችላል ፤ በዚህ ጊዜ በነጋዴው ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶ ነጋዴው ደግሞ ከቅጣቱ ተምሬያለሁ በመደበኛ ዋጋው እሸጣለሁ ካለ ይህንን አስተምረን ወደ ሥርዓት ማስገባት በራሱ ትልቅ ተግባር በመሆኑ ይህንን እንሰራለን። መደበኛ ስራችንም ነው።
የህብረተሰቡ ፍላጎት ሁል ጊዜ ዋጋ እንዲቀንስ ነው ግን መሰረቱ እሱ ሳይሆን አቅርቦቱን ከፍ ማድረግና የንግድ ሥርዓቱ ህግን መሰረት እንዲያደርግ ማድረግ ነው እንጂ ዋጋ ማስቀነስ አለመሆኑ መታወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፦ የቁጥጥር ባለሙያዎቻችሁ ከነጋዴው በተለይም ከህገወጦቹ ጋር ተመሳጥረው ህግ እንዳይከበር እንዳያደርጉና ሸማቹም እንዳይጎዳ ባለሙያዎቻችሁን ምን ያህል ትከታተሏቸዋላችሁ ?
አቶ ዳንኤል፦ ትክክል ነው የቁጥጥር ባለሙያዎች ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ አሉ ፤ እነዚህ ባለሙያዎች በተቻለ መጠን ስነ ምግባር ያላቸውና የተሰጣቸውን ሃላፊበነት በአግባቡ ይወጡ ዘንድ አንደኛ የሲቪል ሰርቪስ መመሪያ አለ በዚህም መሰረት አንድ የመንግስት ሰራተኛ ሊኖረው የሚገባው ሥነ ምግባር በግልጽ ተቀምጧል እሱን እንዲያከብሩ ይገደዳሉ ፤ ከዚያ ውጪ ደግሞ በተደጋጋሚ የሥነ ምግባር ስልጠናዎች ይሰጣሉ። በዚህ መሰረት ሁሉም ባለሙያዎች ለስራ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ላይ ህግንና መመሪያን እንዲሁም ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው ከአጭበርባሪዎች ጋር ሳይተባበሩ ስራቸውን ይሰራሉ ብለንም እናስባለን።
ከዚህ ውጪ ከሚገኙ ጥቆማዎች የሚነሱ አላስፈላጊ ነገሮች ሲመጡና በዚህ ውስጥም የገባ ሰው ሲገኝ በየጊዜው በሚደረጉ የሰራተኞች ግምገማ አማካይነት እርምጃ ይወሰዳል። ለምሳሌ በዚህ ዓመት በክፍለ ከተማና በወረዳ ላይ የሥነ ምግባር ጥሰት ባሳዩ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
እዚህ ላይ ግን ማንም ስላወራ ወይም የተለያዩ አሉባልታዎች ስለተነሱ የሚወሰድ እርምጃ ባይኖርም መረጃና ማስረጃን አጠናቅሮ በትክክል ጥቆማ የሚሰጥ አካል ሲመጣ ግን ቢሮውም የራሱን ማጣራት አድርጎ አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ የሚቆጠብበት ምንም ምክንያት የለም ።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ከተማ ቢሮው ትልቅ ሃላፊነት የተጣለበት ነውና እስከ አሁን እያከናወነ ያለው ተግባር የህብረተሰቡን ችግር ፈቷልስ ብሎ ያምናል?
አቶ ዳንኤል፦ ምንም ጥያቄ የለውም የህብረተሰቡን ችግር እየፈታና ህገ ወጦችን እየተቆጣጠርኩ ነው ብሎ ያምናል። ከአሁን በፊት የነበረበት ችግር የመዋቅር ነበር ይህ ማለት ምንድን ነው መዋቅሩ ታች ወረዳ ድረስ ቢኖርም ህብረተሰቡ የሚፈልገውን እርካታ ማምጣት ላይ ክፍተቶች ነበሩበት። ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን መዋቅሩ እየተስተካከለ አድማሱንም እያሰፋ መጥቷል። ለምሳሌ ነጋዴዎች በብዛት ያሉበት አካባቢ ላይ ሊኖር የሚገባው የቁጥጥር ባለሙያ ቀድሞ በጣም ትንሽ ነበር አሁን ግን ቁጥሩን የማሳደግ ስራ እየሰራን ነው። አሁን ላይ 2 ሺ 600 የሚደርሱ አዳዲስ ባለሙያዎችን ወደ ስራ አስገብተናል። ይህ የሚያሳየው ህብረተሰቡ ችግር ላይ እንዳይወድቅ የቁጥጥር ስራውን ማጠናከርና ህግን ማስከበር እንዲሁም ስራውን በታዓማኒነት ለመወጣት የሚያስችል ስራን ለመስራት እየተሞከረ መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ንግድ ቢሮው በመኖሩ ለከተማው ህብረተሰብ ይህንን አስገኝቷል ባይኖር ኖሮ ደግሞ ይህንን ዓይነት ችግር ይፈጠር ነበር የሚሉት ነገር አለ?
አቶ ዳንኤል ፦ አሁን ያለው ነጋዴ ለአገሪቱ ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው። ሆኖም ይህ ጠቃሚ ጎኑ የሚገለጸው ደግሞ ህጋዊ የሆነ ፍቃድ ኖሮት ህግን ተከትሎ ሲሰራ ደረሰኝ ቆርጦ ሲገበያይና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ነገሮች ሲኖሩ ነው። ከዚህ አንጻር ንግድ ቢሮው ባይኖር ህገወጥነቱ ይሰፋል፤ ማንም ነጋዴ ፍቃድ አውጥቶ አይሰራምም። ያለ ፍቃድ መነገድ ከቻለ ደግም ግብር የመክፈል ሁኔታው አይኖረም ይህ ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ ያደርገዋል።
ስለዚህ አሁንም ህገወጥነትን እንቆጣጠራለን ስንል በተወሰነ መልኩ የምናገኛቸውን ህገወጦች በአስቸኳይ እርምጃ እየወሰድንና ህጋዊ እያደረግን እየሰራን ነው ያለነው። በጠቅላለው ቢሮው ባይኖር ኖሮ ህገወጥነት ይስፋፋል የአገሪቱ ኢኮኖሚም በሚፈለገው ደረጃ አይሄድም ነበር።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻ እርስዎ ማሳሰብና ማስገንዘብ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎ፤
አቶ ዳንኤል፦ እኔ ማሳሰብ የምፈልገው ለህብረተሰቡ ነው፤ አሁን እንዳለንበት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ሰዎች በተረጋጋ መንገድ ችግሩን መረዳት ይኖርባቸዋል፤ ካልተረጋጋን ችግሮች ያጋጥማሉ።
ለምሳሌ አሁን ህብረተሰቡ ባልተጠናና ከመንግስት ውጪ በሆኑ መረጃዎች ላይ በመንተራስ በርካታ ምርቶችን ለመግዛት እየተነሳ ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው። መደበኛ የግዢ ሥርዓት አለ ። ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ ግን ሁሉም ማህበረሰብ ወደ ገበያ ወጥቶ የሚገዛ ከሆነ ነጋዴን አከማቸ ብለን ስንከስ ህብረተሰቡም በዚህ መንገድ ከሄደ በከተማው እንዲሁም በሌላው ሸማች ላይ የምርትና የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።
ስለዚህ መንግስት የአቅርቦት እጥረቱን ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ህብረተሰቡ ደግሞ ተረጋግቶ መንግስት የሚሰጠውን አቅጣጫ ብቻ እየተቀበለ መሰረታዊ ፍላጎቱን በተለመደው አግባብ ግዢ ቢፈጽም ገበያው ይረጋጋል። ስለዚህ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት እራሱን በመቆጠብ የግብይት ሥርዓቱን ላለመረበሽ መተባበር ያስፈልጋል።
ሌላው ነጋዴው ህብረተሰብ ሊያውቀው የሚገባው በተለይም አሁን እየተፈታተነን ያለው የኮሮና ቫይረስ የመጣው ለነጋዴ፣ ለሸማች፣ ለባለስልጣን አልያም ለሌላው ብሎ ሳይሆን ማንኛውንም ዜጋ በየትኛውም መልኩ ሊያጠቃ ነው። ስለዚህ ነጋዴው በሰወረው ምርትና ባጭበረበረው ልክ እየታየ ባለው የዋጋ ንረት ቢሳተፍ እሱን የሚምር አይደለም፤ በመሆኑም ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ታሪክ ጥሎ ማለፍ ተገቢ አይደለም። ህብረተሰባችንን የምናገለግልበት መንገድ ብንችል በመደበኛ ዋጋው ደግፈን በጋራ የመጣብንን ችግር በህብረት የምናልፍበትን መንገድ ማሰብ ይገባል። እንደዚህ ካልተባበርን ከችግሩ ለመውጣት በጣም ከባድ ነው።
ማንኛውም ነጋዴ በዚህ ወቅትም ይሁን በሌላው ጊዜ በፈጠረው ችግር ልክ የሚጠየቅ ሲሆን እጅግ ሥነ ምግባር ያላቸው ለህብረተሰቡ የሚያስቡ በመደበኛ ዋጋው እቃዎችን የሚሸጡም በአገሪቱ ላይ የመጣው ችግር የጋራ መሆኑን ተረድቶ ከመንግስት ጎን የቆሙትም ትልቅ ምስጋና የሚገባቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ዳንኤል፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012

እፀገነት አክሊሉ