አደራን በታማኝነት ማስቀመጥ ያለው ፋይዳ

23

 

ሰላም ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ያሳለፍነው ሳምንት የበዓል ወቅት እንዴት አለፈ? በተለይ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆናችሁት የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚከበርበት የገናን በዓል በድምቀት እንዳከበራችሁት ተስፋ አደርጋለሁ። ሌሎቻችሁም ብትሆኑ ከክርስቲያን ጓደኞቻችሁ ጋር አክብራችሁት እንደምታልፉ አልጠራጠርም። ከሳምንት በኋላ ደግሞ በመላው አገሪቱ በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የሚከበረው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዓመታዊ ክብረ በዓል አለ። በዓሉ ምን እንደሆነ አስታወሳችሁ አይደል? አዎ የጥምቀት በዓል ነው።

ጥምቀት በኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅ በዓል ነው። በተለይ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቱ በጣም ደስ ይላል። ታቦታቱ በከተማም ሆነ በገጠሩ ክፍል በሚገኙ ሰዎች ታጅበው በተለያዩ የባህል አልባሳት ደምቆ ዝማሬ እየተሰማ የሚያከብረው እለት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ አያቴ ነበረች ስለ ጥምቀት በዓል በዝርዝር ያስረዳችኝ። ከዚያ በፊት  ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብበት ከመሆኑ በዘለለ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አልረዳም ነበር። ሆኖም አያቴ ሁል ጊዜ ስለ በዓላት አከባበር እና ስለ አስተማሪ ታሪኮች እንደምትነግረኝ ሁሉ ስለ ጥምቀት በዓል አከባበርም እንዲሁ በዝርዝር ነግራኛለች።

እርሷ በጊዜው እንዲህ በማለት ነበር የእለቱን ድባብ እና ስነ ስርዓቱን የገለፀችልኝ። በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ባህር ወይም ውሃ ያለበት ቦታ ይሄዳሉ። ይህም በየጥምቀተ ባሕሩ ተገኙ ያስብላቸዋል። በዚህ ደግሞ ሀገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብን ይፈጥራሉ። ቱሪስቶችም በስበቡ ይሰባሰባሉ፤ ጥቁርና ነጭ፣ ቀይና ቢጫ የዓለም ዘር፣ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ያከብረዋል።

የምዕመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ ፍፁም በሚማርክ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁል ጊዜ አዲስ ነው። እንዴት ነው ታዲያ ከዚህ ቀደም ከምታውቁት የጥምቀት በዓል አከባበር የተለየ መረጃዎች አገኛችሁ? መልካም በዓሉ ሲደርስ ይህን እያሰባችሁ ወደ ስፍራው እንደምትጓዙ እና ባህላችንን በጠበቀ መንገድ እንደምታከብሩት እገምታለሁ። በበዛሬው አምዳችን ላይ ደግሞ አያቴ ይህን የጥምቀት በዓል አከባበር ስነ ስርዓት ምንነት ባስረዳችኝ ወቅት የነገረችኝን ጣፋጭ ታሪክ እተርክላችኋለሁ። መቼም የአያቴ አስተማሪ እና ጣፋጭ ታሪኮች ናፍቃችኋል። እኔም እንደናንተ በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ታሪኮቹን እያጫወተችኝ ሁሌም እንደ አዲስ ይናፍቁኛል።

ሳምንቱ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ወቅት ነበር። አያቴ እና እኔ በግቢያችን ውስጥ ቁጭ ብለናል። እርሷ በጠዋት ቤተክርስቲያን ስማ ነበር የተመለሰችው። በሰፈራችን ጥምቀት በልዩ ሁኔታ ስለሚከበር እና ታቦት የሚያድርበት ሰፊ ሜዳ እኛ አካባቢ ስለሚገኝ ሁሌም በየዓመቱ ሰፈራችን ይደምቃል። እኔም በዚህ ወቅት ልዩ የደስታ ስሜት ይሰማኛል። እኔና አያቴ በግቢው የዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለን ስለ ጥምቀት በዓል አከባበር እና ምንነት ስታስረዳኝ እናቴ ደግሞ ለበዓሉ የሚሆን የቤት ውስጥ ስራ እየሰራች ነበር።

በእለቱ ከበዓሉ ድባብ በላይ ዝርዝር መረጃ ስለ ጥምቀት ስላገኘሁ ደስ ብሎኝ ነበር። ከዚያ በተጨማሪ እጅግ አስተማሪ የሆነ ታሪክ እንደ ምርቃት ጨመረችልኝ። ታዲያ ጥምቀት በመጣ ቁጥር ይህን ታሪክ አስታውሰዋለሁ። ዛሬ ደግሞ ለእናንተ በዚህ መልኩ ተረኩላችሁ። በደንብ አንብቡት እሺ?

ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት መገርሳ ዱኪ የሚባል በምዕራብ ወለጋ የሚኖር ከነጋዴ ቤተሰቦች የተወለደ ጎልማሳ ሰው ነበር። ይህ ሰው የንግድ ስራን ከቤተሰቦቹ ቢወርስም ስኬታማ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው የንግድ ስራ በጣም ተቀዛቅዞ ነበር። በዚህ ምክንያት የተሻለ ስኬት ለማግኘት ከተማውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ መምጣት እንዳለበት ወሰነ። ሆኖም ለጉዞ እና ለተወሰነ ጊዜ እራሱን እስኪያቋቁም ለምግብ የሚሸፍንለት ገንዘብ ማግኘት ፈለገ።

መገርሳ ከብዙ ዓመታት በፊት ቤተሰቦቹ እጅግ ውድ ዋጋ የሚያወጣ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የነበረ ሚዛን በስጦታ አበርክተውለት ነበር። ይህን ውድ እቃ ቢሸጠው ጥሩ ገንዘብ ማግኘት ቢችልም ማስታወሻውን አሳልፎ ለሌላ ሰው መስጠት ግን አልፈለገም። አንድ ውሳኔ ላይ የማይደርስ ከሆነ ግን ያሰበውን ማሳካት እንደማይችል ተረዳ። በዚህም ውዱን የብረት ሚዛን ከመሸጥ ይልቅ በቅርብ ለሚያውቀው ሌላ ነጋዴ በመያዣ መልክ አስቀምጦ ብድር ሊቀበል ወሰነ።

ለነጋዴው ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ  ንግድ ላይ ለመሰማራት ማሰቡን አስረድቶ የሚፈልገውን ብድር ጠየቀው። በመያዣነትም ሚዛኑን ሰጠው። ነጋዴውም ሚዛኑ ውድ ዋጋ እንደሚያወጣ በማወቁ መገርሳ የጠየቀውን ብድር ሳያቅማማ ሰጠው። ገንዘቡን በአጭር ጊዜ እንደሚመልስ በመንገር ከገንዘብ በላይ እጅግ ውድ ክብር የሚሰጠውን ሚዛን በአደራ እንዲያስቀምጥለት ተስማምተው ተለያዩ። ከዚያ መገርሳ ወደ አዲስ አበባ መጣ።

በአጭር ጊዜ ውስጥም ገብስ እና ሌሎች የጥራጥሬ እህሎችን በመነገድ እንዲሁም የቁም እንስሰሳት ንግድ ላይ በመሰማራት ስኬታማ ነጋዴ ሆነ። የሚፈልገው ስኬት ላይ ደረሰ። ይሄ የሆነው በአጭር ዓመታት ውስጥ ነበር። በሁኔታው እጅግ ደስተኛ የሆነው መገርሳም ወደ ትውልድ መንደሩ ምዕራብ ወለጋ በመሄድ ከቤተሰቦቹ በስጦታ መልክ የተሰጠውን ሚዛን ለመውሰድ እና ያለበትንም ብድር ለመመለስ ውሳኔ ላይ ደረሰ።

ወደ ትውልድ መንደሩ በመምጣቱ እጅግ ደስተኛ የነበረው መገርሳ፤ አካባቢው ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው ብዙም ልዩነት አልነበረውም። የመንደሩ ሰው በሙሉ አግኝቶ ሰላምታ ሰጠ። ከዚያም ከዓመታት በፊት ብድር የሰጠውን ባለውለታውን ለማግኘት ወደ ቤቱ አመራ። ሰውዬውን አግኝቶትም ሰላምታ ተለዋወጠና ላደረገለት ውለታ ምስጋና አቅርቦ የተበደረውን ገንዘብ እስከ ወለዱ መለሰለት። ከዚያም በአደራ እና በመያዣነት ያስቀመጠውን ሚዛን እንዲሰጠው ጠየቀው።

በብድር መያዣነት ውዱን የብረት ሚዛን እንዲያስቀምጥ በአደራ የተቀበለው ነጋዴ ግን ለመገርሳ ጥሩ ዜና ይዞ አልጠበቀውም። ይልቁንም እጅጉን የሚያሳዝነው አስደንጋጭ ነገር ነው የነገረው። ከዓመታት በፊት ያስቀመጠው ሚዛን አደጋ እንዳጋጠመው አስረዳው። ለብዙ ጊዜያት እቃውን  እየበሉ ያስቸገሩት አይጦች የብረት ሚዛኑን እንደበሉት ነገረው። በሁኔታው መገርሳ እጅጉን ተደናገጠ። ከአያት ቅድመ አያቶቹ ሲተላለፍ የቆየው እና በአደራ መልክ እርሱ ጋር የደረሰው ሚዛን ጠፍቷል መባሉ አሳዘነው። ነገር ግን ነጋዴውን ምንም አልተናገረውም ነበር። ይልቁንም ይህ አይነት ነገር ሊያጋጥም እንደሚችል ነግሮት በሁኔታው ምንም አለማዘኑን አስረዳው። ነገሮቹ መረጋጋታቸውን ሲያውቅ ግን ሰውየውን አንድ እርዳታ ጠየቀው።

‹‹ወዳጄ ከአዲስ አበባ ረጅም መንገድ አቋርጬ እዚህ የደረስኩት ገና አሁን ነው በጣም ደክሞኛል ወደ ወንዝ ወርጄ ገላዬን መታጠብ እፈልጋለሁ። ስለዚህም ልጅህ አብሮኝ ሄዶ እኔ እስክታጠብ እቃዬ እንዳይሰረቅ እንዲጠብቅልኝ ብትፈቅድልኝ›› በማለት እርዳታውን ጠየቀው። ሰውየውም የመገርሳን ጥያቄ ተቀብሎ ልጁ አብሮት ሄዶ ንብረቱን እንዲጠብቅለት አዘዘው። ወደ ወንዝም ወረዱ። እንዳለውም ባገኘው ንፁህ ወራጅ ውሃ ገላውን ታጥቦ ጨረሰ። ልጁም እቃውን እንዳይሰረቅ ጠበቀለት። ነገር ግን መገርሳ በድንገት ልጁን ሳያስበው በገመድ አስሮ በአካባቢው በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ከተተው።

በትላልቅ ድንጋይም ዋሻውን ዘግቶት ወደ መንደሩ ተመለሰ። በዚህ ጊዜ የልጁ አባት መገርሳ ብቻውን መመለሱን አይቶ ደነገጠና እንዲህ ሲል ጠየቀው። ‹‹ልጄን የት አደረከው?›› መገርሳ የአባትየው ጥያቄ ብዙም ሳያስጨንቀው ወንዝ ዳር በነበሩበት ወቅት ልጁን አንድ ፍላሚንጎ የምትባል ቅልጥመ ረጅም ወፍ ሳያስበው ይዛው እንደበረረች ነገረው። ሰውየው በመገርሳ ምላሽ እጅጉን ተበሳጨ። «እንዴት ልጅ የሚያህል ነገር ይቺ ወፍ ይዛ ትሄዳለች» በማለትም አምርሮ ሞገተው።

ልጁን አውቆ እንደደበቀበት እና የሰጠው ምክንያት ከእውነት የራቀ እንደሆነ አመነ። በጉዳዩ ሲጨቃጨቁ የአካባቢው ሰው ተሰባሰበ። አንድ ሽማግሌ ሰውዬም በምን ምክንያት እንደሚጨቃጨቁ ሲጠይቃቸው የልጁ አባት የሆነውን ሁሉ በዝርዝር አስረዳቸው። በዚህ ጊዜ ሽማግሌው በመገርሳ አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት በተመሳሳይ ተበሳጩ። «እንዴት አንዲት ወፍ ህፃን ልጅን ተሸክማ ልትበር ትችላለች» ሲሉ ጥያቄ አቀረቡለት።

መገርሳ በተረጋጋ መንፈስ ሆኖ በመንደሩ ለተሰባሰቡ ሰዎች እና ለሽማግሌው ሰውዬ ‹‹አንድ አይጥ የብረት ሚዛን ከበላች እንዴት አንድ ወፍ ህፃን ልጅ ተሸክማ መብረር ያቅታታል›› በማለት በነጋዴው እና በመገርሳ መካከል ስለተፈጠረው ነገር ሁሉ በዝርዝር ነገራቸው። በተለይ እጅግ የሚወደውን እና በአደራ ከቤተሰቦቹ የተበረከተለትን ሚዛን በምን መልኩ ጠፋ እንዳለው እና ለራሱ ደብቆ እንዳስቀመጠው ነገራቸው።

ልጁንም ሆን ብሎ በዋሻው ውስጥ እንደደበቀው ተናግሮ ምክንያቱን አስረዳ። በዚህ ጊዜ ነገሩ የተጋለጠበት ነጋዴው በተፈጠረው ነገር ሃፍረት ተሰማው። መገርሳን ይቅርታ ጠይቆም ደብቆት የነበረውን ሚዛን ከነበረበት አውጥቶ ሰጠው። እርሱ በአደራ የወሰደውን ገንዘብ ከነወለዱ በታማኝነት ሲመልስለት በምላሹ ታማኝ መሆን ስላልቻለ ተፀፅቶ መገርሳን ይቅርታ ጠየቀው። በተፈጠረው ሁኔታም የአካባቢው ሰው ትልቅ ትምህርት አገኘ።

የሰው አደራን በታማኝነት ማስቀመጥ መልካም መሆኑን ሁሉም ተገነዘቡ። መገርሳም ልጁን ከደበቀበት ዋሻ በማውጣት ለአባቱ አስረከበ። በማለት አያቴ ትልቅ አስተማሪ የሆነ ታሪክ በጥምቀት ዋዜማ አጫወተችኝ። እኔም ይህን ታሪክ የህይወት መመሪያዬ አድርጌ እስካሁን ድረስ ቆይቻለሁ። ልጆች እናንተም ታሪኩ እንደመሰጣችሁ እና በብዙ እንዳስተማራችሁ እምነቴ ነው። የሳምንት ሰው ይበለን!

አዲስ ዘመን ጥር 5 /2011

ዳግም ከበደ