የተስፈኞቹ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራና ስጋት

26

የዓለማችን ኃያላን ሀገሮች ቀደም ብለው ወጣቱን ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ዘርፍ ኮትኩተው በማሳደግ ለችግሮቻቸው መፍትሄ የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን በየትምህርት ተቋማቱ እንዲሠሩና ትምህርት እንዲቀስሙ በማስቻላቸው ዛሬ ላይ የቴክኖሎጂው ማማ ላይ የደረሱ ሲሆን፤ በፈጠራ ሥራቸውም ከራሳቸው አልፎ በዓለም ዙሪያ ለገጠሙ ችግሮች ሁሉ አይነተኛ መፍትሄን ጀባ ሲሉ ይስተዋላሉ።

በሳይንስና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎች ከፍተኛ ደረጃ የደረሱት ዓለምን ወደአንድ መንደር በማምጣት ላይ ናቸው። ታዲያ አህጉራችን አፍሪካ ብሎም ሀገራችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራና ግንዛቤ ገና ዳዴ በማለት ላይ ይገኛሉ። ከአፍሪካ ምድር እንዲሁም ከሀገራችን ጦርነት፣ ችግር፣ ርሀብ፣ ሥራ አጥነትና ኋላቀርነት ከሥራቸው እንዲነቀሉ ከተፈለገ፤ ወጣቱን ኃይል ወደፈጠራ ሥራው እንዲገባ በማድረግ የሀገሩን ችግር በራሱ የፈጠራ ሥራ መፍታት የውዴታ ግዴታ መሆኑ ተገቢ ይሆናል።

በሀገራችን የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ዝንባሌያቸውንና እውቀታቸውን ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው ያለውን እምቅ እውቀትና ሀብት ለማህበረሰቡ በማድረስ በመማር ማስተማር ሂደቱ ተጨማሪ እውቀት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውና ከፍተኛ የፈጠራ ሥራ የመሥራት ብቃት ላላቸው ተማሪዎች ደግሞ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ከሐምሌ 2007 ዓ.ም ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ በማስተማር ላይ ይገኛል።

ተማሪዎቹም በተግባር የተደገፈ ትምህርት በማግኘታቸው የተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሥራት ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው። የካምፓሱ ተማሪዎች በቡድን ከሠሩት የፈጠራ ሥራዎች መካከል አንዱን ባለፈው ሳምንት ይዘን የቀረብን ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ ሁለተኛውን የፈጠራ ሥራ ይዘን እነሆ ብለናል፡፡ የቡድኑ ተወካይ ቤዛዊት ተስፋዬ ስለፈጠራ ሥራቸው ገለፃ አድርጋልናለች።

«አልትራ ቫዮሌት የሚባለውን ጨረር በመጠቀም ሙሉ ለሙሉ ለመጠጥነት የማይውል ቆሻሻ ውሃን በማጣራት ለመጠጥነት እንዲውል የሚያደርግ የውሃ ማጣሪያ ማሽን ነው የሠራ ነው። ይህንንም የፈጠራ ሥራ አንድ አይነት ፍላጎትና ተነሳሽነት ያለን አራት የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነን የሠራነው በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ነው» በማለት የፈጠራ ሥራቸውን ጠቀሜታ ገልፃለች።

በከተማችን አዲስ አበባ ብዙ ወንዞች፣ የውሃ ጉድጓዶች፣ ኩሬዎችና ምንጮች በተለያዩ ቆሻሻዎችና የኢንዱስትሪ ፍሳሾች ተበክለው እናስተውላለን። ታዲያ እነዚህ የውሃ አካላት በጣም ቆሻሻ በመሆናቸው ለማህበረሰቡ ምንም አይነት ግልጋሎት ሳይሰጡ በከንቱ የሚባክኑ መሆኑ ቁጭት በማሳደሩ በከንቱ የሚባክኑ የውሃ ሀብታችንን ማህበረሰቡ ለመጠጥነትና ለተለያዩ አገልግሎት እንዲያውላቸው ለማስቻልና በከተማይቱ የሚስተዋለውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጦት ለመቅረፍ በማሰብ ይህን የውሃ ማጣሪያ ለመሥራት እንደቻሉ ቤዛዊት ትናገራለች።

« ምንም ጥቅም ሳይሰጡ የሚባክኑ የውሃ ሀብታችንን በቀላሉ የውሃ ማጣሪያውን በመጠቀም ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ሠርተናል። በዚህም የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንድንጠቀም በማድረግ፤ የሀብት ብክነትን መከላከል፣ ማህበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ማስቻል፣ ለውሃ ወለድ በሽታ እንዳይጋለጥ ማድረግ ጤንነቱን በመጠበቅ ላላስፈላጊ የህክምና ወጪ እንዳይጋለጥ የሚታደግ ነው፡፡

«ብዙ አይነት የውሃ ማጣሪያዎች ገበያ ላይ አሉ። ነገር ግን የኛ የውሃ ማጣሪያ ለየት የሚያደርገው፣ ጨረርንና ተፈጥሮአዊ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም አገልግሎት ላይ የማይውሉ ቆሻሻ ውሃን ሙሉ በሙሉ ከበሽታ አምጭ ተህዋስያን እና ከተለያዩ ኬሚካሎች የጸዳ በማድረግ ለመጠጥነትና ለአገልግሎት እንዲውሉ የሚያደርግ ነው። በተጨማሪም ሰዎችን ለጎንዮሽ ችግር የሚያጋልጡ ኬሚካሎችንና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ባለመጠቀማችን፤ ንጹህና ደረጃውን የጠበቀ ውሃ ማህበረሰቡ እንዲያገኝ በማስቻል ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ያስችላል» በማለት ገበያ ላይ ካሉ ሌሎች የውሃ ማጣሪያዎች የሚለይበትን ነገሮች ቤዛዊት ታስረዳለች።

የፈጠራ ሥራው ጥቅም ላይ ከዋሉ የውሃ መያዣ ፕላስቲኮች፣ ንኬሎች፣ አልሙኒየም ብረቶች፣ ጥቃቅን የፕላስቲክ ቱቦዎች ወ.ዘ.ተ የሠራ ነው። የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት ብዙ ወጪ አልጠየቀም። ችግሮችም አልገጠሙም የምትለው ተማሪዋ፤ የፈጠራ ሥራውን ሠርቶ ለመጨረስ ሁለት ሳምንት ጊዜ ብቻ መውሰዱን ታብራራለች፡፡

«ይህ የውሃ ማጣሪያ በፋብሪካ ውስጥ ጥራትና መጠኑ ዳብሮና ተሻሽሎ ቢሠራ አንድ የውሃ ታንከር ለአንድ ሰፈር በመትከል ማህበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል። ይህ ካልተቻለ ግን የመገናኛ ብዙኃን በኩል ህብረተሰቡ እንዴት አድርጎ የውሃ ማጣሪያውን መጠቀምና መሥራት እንደሚችል ሥልጠናውን በመስጠት በቀላሉ የውሃ ማጣሪያውን ህብረተሰቡ በየቤቱ በመሥራት አገልግሎቱን እንዲያገኝ ማድረግ እንችላለን» በማለት የፈጠራ ስራውን ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ጠቁማለች።

«ሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ ከማስተማርና ከማበረታታት ባለፈ ለፈጠራ ሥራው የሚያስፈልገንን አንዳንድ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጎልናል። እንዲሁም መምህራኖች በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የፈጠራ ብቃታችን ከፍ እንዲል እየረዱን ነው። እኛም በመተባበር በቡድን ሥራዎችን በመሥራታችን በብዙ መልኩ መተጋገዝ ችለናል። እንዲሁም ይህን የፈጠራ ሥራ ስንሠራ ወላጆቻችን በተለያየ መልኩ ድጋፍ አድርገውልናል። በሠራነው የፈጠራ ሥራ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ተበርክቶልናል። በተጨማሪም ባለፈው ዓመት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባካሄደው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ውድድር የፈጠራ ሥራችን አንደኛ በመሆኑ የላፕቶፕ ሽልማት ለማግኘት ችለናል።

«መንግሥት ለእኛ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ትምህርታችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንድከታተል እያደረገን ነው። ትምህርታችን በዚህ ደረጃና በዩኒቨርሲቲ መምህራን መማራችን የተሻለ እውቀት እንድንቀስም የሚረዳን ነው። ነገርግን ከዚህ ትምህርታችን ከጨረስን በኋላ ይህን የፈጠራ ሥራችን አጠናክረን ለማስቀጠል የሚያ ስችል ቅድመ ሁኔታ አልተፈጠ ረልንም። በተለይም ነገ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ስንመደብ በጋራ ስንሠራቸው የነበሩትን የፈጠራ ሥራዎቻችንን ወደ ተግባር ቀይረን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንቸገራለን። እንዲሁም በምንሄድባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የምንፈልገው ዘርፍ ላይ ተሰማርተን የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያ ስችሉ መሰረተ ልማቶች ላይሟሉ ይችላሉ። ስለዚህ የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንቸገራለን» ስትል የፈጠራ ባለሙያዎቹን ስጋት ትገልፃለች፡፡

«በአሁኑ ወቅት የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎትና ብቃት ያለን ተማሪዎች በአንድ ላይ በመማርና በመሥ ራት ላይ ነን። በዚህም ከፍተኛ የውድድር መንፈስ እንዲኖረን አስችሎናል። ይህም ሁሌም የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት በጣም ያግዘናል። ስለዚህ መንግሥት እነዚህን የፈጠራ ሥራዎችን አንድ ላይ የምናስቀጥልበትና ይህ ከፍተኛ የውድድር መንፈሳችንን ይዘን በፍላጎታችን የምንሠራበት አንድ እራሱን የቻለ እኛን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ዩኒቨርሲቲ ቢኖር ጥሩ ውጤት በማምጣት ለህብረተሰቡ ችግር ፈች የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለናል» ብላለች።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የመማር ማስተማርና የተጓዳኝ ትምህርት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ጥበቡ በላይ፤ ይህ የተማሪዎቹ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የተማሪዎቹ ወላጆች ሁሌም የሚያነሱትና እኛም መልስ ለመስጠት የተቸገርንበት ከመሆኑ በላይ የኛም ጥያቄ ነው ብለዋል።

አቶ ጥበቡ እንደገለጹት፣ ከ2007ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ መንግሥት ይህን ፕሮግራም ከፍተኛ በጀት ፈሰስ አድርጎ ነው እያከናወነው ያለው። ስለዚህ አንድ ገበሬ ዘሩን ዘርቶ ዘሩ ፍሬያማ ሆኖ ምርቱን እስኪሰበስብ ድረስ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርገው ሁሉ እነዚህ ተማሪዎች ላይ የዘራነው ዘር ፍሬያማ ሆኖ እስክንሰበስበው ድረስ ክትትልና እገዛ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ይህ ዘር ደግሞ እየተዘራ ያለው ትውልድ ላይ እንደመሆኑ መጠን ትውልድን የማብቃትና ውጤት ላይ የማድረስ ኃላፊነት የሁሉም ሴክተሮችና የሁሉም ዜጋ ነው ብለዋል።

በእኛ በኩል ተማሪዎቹን ከእስከ 12ኛ ክፍል ድረስ አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ በማድረግ በጥሩ ውጤትና የፈጠራ ብቃት ለመገንባት ችለናል። ነገር ግን ተማሪዎቹ በቀጣይ ደግሞ በተደራጀ መልኩ የፈጠራ ሥራቸውን የሚያስቀጥሉበትና ፍላጎታቸውን መሰረት አድርገው ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት አንድ ዩኒቨርሲቲ ወይም ልዩ ተቋም ያስፈልጋቸዋል በማለት ምክትል እርሰ መምህሩ ያስረዳሉ።
ይህ ደግሞ ለእነዚህ ተማሪዎች ቢደረግላቸው ቢያንስ እንጂ አይበዛባቸውም። ምክንያቱም የነገ የሀገር ተስፋዎች የሚሆኑ በርካታ ተማሪዎች ቀርቶ አንድ ተመራማሪ እንኳን ብቻውን ዓለምን መለወጥ ይችላል። እነዚህ ተማሪዎች ደግሞ ሰለቸን ደከመን ሳይሉ ለወገን ብርሃን ለመሆን ራሳቸውን ካልባሌ ቦታ አርቀው በመሥራት ላይ በመሆናቸው ይህንን ራዕያቸውን የሚስቀጥሉበት ተቋም ስለሌለ የነገ ተስፋቸውን የሚያጨልም ነው ብለዋል አቶ ጥበቡ።

ተማሪዎቹ ነገ ላይ ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተበታትነው ውጤታቸውን ሳናይ እንዳንቀር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ቢሰጡትና አንድ መፍትሄ ቢፈጠር እንደሚሻል ያሳስባሉ።
ተማሪዎቹ ስለሠሩት የፈጠራ ሥራና ስላስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት በብዙ መገናኛ ብዙኃን የተገለጸ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጥበቡ፤ የተማሪዎቹን ራዕይና ብቃት ያላወቀ ከፍተኛ የመንግሥት አመራርና የሚመለከታቸው ተቋማት የለም ብዬ አላስብም ከፍተኛ የመንግሥት አመራር፣ የትምህርትና ሌሎች ሴክተሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሊረዱን የሚገባበት ጊዜው አሁን ነው በማለት የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

«ይህ ፕሮግራም በእኛ ብቻ ታጥሮ እንዳይቀር ለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ልምዳችንን በማካፈል ሥልጠናና የአሰራር ማንዋላችንን በመስጠት ወደሥራ እንዲገቡ በማድረግ፤ እንደ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ አዲግራት፣ አክሱምና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራሙን ጀምረዋል። ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራሙን ለመጀመር በሂደት ላይ ናቸው፡፡ ባጠቃላይ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ዓላማውን ወደውና ፈቅደው ተቀብለውት ወደሥራው ገብተዋል» በማለት ምክትል እርሰ መምህሩ ገልጸዋል።

አዲስ ዘመን ጥር 10/2011

ሰለሞን በየነ