ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ የተዘረጋው የቦረናዎች ጥበብ

46

የቦረና ኦሮሞዎች በረሃማ የአየር ንበረት ባለው አካባቢ ለዘመናት ባህላቸውን ጠብቀው የኖሩ ህዝቦች ናቸው። በተለይ የገዳ ስርዓትን ጥንታዊ ትውፊት በመጠበቅና ለትውልድ በማስተላለፍ ከሁሉም የተለዩ መሆናቸው ይነገርላቸዋል። የቦረና ኦሮሞዎች ኢትዮጵያ ውስጥም ኬንያ ውስጥም የሚገኙ ሲሆን፤ ሞያሌ ከተማን ለሁለት የከፈለው የድንበር ኬላ የኬንያውን ቦረና በዚያኛው ማዶ የኢትዮጵያውን ቦረና ደግሞ በዚህኛው ማዶ አድርጓቸዋል።

ቦረናዎች ድንበር የላቸውም፤ ለከብቶቻቸው የሚመች ቦታ እስካገኙ ድረስ 300 ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛሉ። አብዛኛው የቦረና ሰው አርብቶአደር በመሆኑ ባለረጃጅም ቀንዳም ከብቶቹን እየነዳ ካሻው ስፍራ ውሎ ካሻው ስፍራ ያድራል። በኬንያ ጋብራ ቦረናዎች ሲኖሩ በኢትዮጵያ ደግሞ እንደነገሌ ቦረና እና ሞያሌ አካባቢዎች ይኖራሉ። ቦረናዎች ድንበር አካባቢ መኖራቸው ግን ከተለያዩ ጥቃቶች እንደታደጋቸው ይነገራል።
በአካባቢው ባህል እና አኗኗር ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ እንደሚናገሩት፤ በመላ ኢትዮጵያ የገባር ስርዓት ሲዘረጋ ቦረናዎች ድንበር ላይ በመሆናቸው አንቀበልም ብለው ነበር። የገባር ስርዓት ለንጉሥ እና አስተዳደሮቹ ካመረተው ወይም ካለው ሀብት ላይ እንደግብር የሚሰጥበት ስርዓት በመሆኑ አልፈለጉትም። ስለዚህም ወደኬንያ በመሄድ በወቅቱ ቅኝ ገዥ ከነበረችው እንግሊዝ ስር ሆኑ። ይህም ቢሆን ለእነርሱ ምቹ አልነበረም። በኬንያ እንግሊዝ የከፋ የህግ እና የቁጥጥር ስርዓት አውጥታ ቦረናዎችን በታክስ አጎሳቁላቸዋለች።

የሚሸጡ ንብረቶቻቸውን ዋጋ በማውረድ በኢኮኖሚውም እንዲጎዱ አድርጋለች። ይህ አልበቃ ብሎ በቦረናዎች ዘንድ የተለመደውን የአንድ አለቃ የእንስሳት ውሃ ጉድጓድ አጠጪ ሰው ስልጣንን ነጥቃ ነበር። ቦረናዎች አደን ማካሄድ እንዳይችሉ የእጅ ብረት መሳሪያዎቻቸውንም ነጥቃቸዋለች። በዚህ የተማረሩት ቦረናዎችም ወደ ኢትዮጵያ የቀድሞ አካባቢያቸው ተመልሰው ድንበሩን እየተጠቀሙ ሲያሻቸው ወደኬንያ ሲያሻቸው ወደኢትዮጵያ እየተመላለሱ መኖራቸውን ይገልጻሉ።

እንደ ፕሮፌሰር አስመሮም ገለጻ፤ እንግሊዝ የኬንያ ድንበር እንዲለይ ከኢትዮጵያ ጋር የጋራ የድንበር ካውንስል አቋቁማ ስትሠራ አብዛኛው የቦረናን ክፍል ነጣጥላ ወደኬንያ ወስዳለች። በዚህ ጊዜ አፄ ምኒልክ ቦረና አብዛኛው ክፍሉ ወደኢትዮጵያ መሆኑን በማስረዳት መነጣጠል እንደሌለባቸው በመናገራቸው ሰፊ ግዛት ያለው የከረዩ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ወገን እንዲሆን አደረጉ። ጋብራ፣ ሳሃይ፤ ገሪ እና አጁራን ደግሞ ወደኬንያ ተጠቃለሉ። አሁን ድረስም የኬንያ እና የኢትዮጵያ ቦረናዎች ዋናው መለያቸው ገዳ በኢትዮጵያ በመሆኑ የገዳ ስርዓቱ አመራር በኢትዮጵያ በኩል መሆኑ ነው።

በኬንያም ሆነ በኢትዮጵያ የቦረና ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ ሶማሌዎችም እየኖሩበት እንደሚገኝ በርካታ አጥኚዎች ይናገራሉ። ቦረናዎች ምቹ መሬት ፍለጋ ለወራት ያክል ከአካባቢያቸው ርቀው ይነቀሳቀሱ እንጂ የኦሮሞ ገዳ ስርዓትን ሳያስታጉሉ እየተገበሩት ለአሁኑ ዘመን ያደረሱ ናቸው። አይደለም ረጅም ቦታ ለሚንቀሳቀስ አርብቶአደር ማህበረሰብ ይቅርና በአንድ ቦታ ተወስኖ ለኖረ ህዝብ ትውፊቱን ከልጅ ልጅ የማስተላለፉ ሥራ ከባድ ነው። ይሁንና ቦረናዎች ዓለም የመሰከረለትን ገዳ ስርዓትን፣ የስነከዋክብት ዕውቀትን እና የዕጽዋት ቅመማን ለልጆቻቸው አውርሰዋል።
በቦረና ገዳ ስርዓት ለበርካታ ክፍለዘመናት ሲተገበር የቆየነው። የቦረና ገዳ ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች ደግሞ ከዘመናዊው ፓርላማ የተለየ አካሄድ አላቸው። ፓርላማ ላይ ቋንቋ ያሳመረ እና ሌሎቹን ያሳመነ ሰው ሃሳቡ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል። ካልሆነም የድምፅ ብልጫ ተደርጎ አሸናፊው ሃሳብ ይለያል። በቦረና ግን የጋራ ሃሳብ እስካልተፈጠረ ድረስ ኃያሉ የሚያሸንፍበት ውይይት የለም።

«ጉሚ» በተባለው ትልቁ ስብሰባ ላይ ለሚመጡ ሰዎች «ጮሌ ንግግር ካላችሁ መሬት ላይ ትታችሁ ግቡ ተብሎ» ይነገራል። ስለዚህ ክርክር ቢነሳም ወሬ አሳምሮ እና ተንኮል ሠርቶ ሃሳብን ማስረጽ አይቻልም። ይሁንና የጋራ ስምምነት በመፍጠር ክርክሮች እንዲፈቱ ይደረጋል። ነገርግን የትኛውንም ያህል ጊዜ ፈጅቶ ክርክሩ ካላበቃ አባቶች ተነስተው ቡራኬ ያቀርባሉ። የተራራቀ ሃሳብ ያላችው ወደአንድ መምጣት እንዳለባቸው ተናግረው ቡራኬ ያቀርባሉ። «አንተም ወደዚህኛው ሃሳብ አንተም ወደዛኛው ሃሳብ ተቀራረቡ» ብለው የሚበጀውን መርጠው በቡራኬና ምርቃት ይቋጩታል።

ማንኛውም ግጭት ሲነሳ ደግሞ ጉሚ ላይ በዕርቅ ይፈታል። ካልሆነ ደግሞ በድርድር ስልት ይሞከራል። ድርድሩም ካልሠራ በፍርድ ይወሰናል። የሐይማኖት መሪዎች ደግሞ ውሳኔዎችንም ሆነ አጠቃላይ ክንውኖችን ከስነምግባር እና ከህሊና ጋር አያይዘው ማስተካከያ ይለግሳሉ። ቆንቆ ጉሚ /የሕዝብ ድምፅ/ የተባሉ አካላት ፖለቲከኞች ያጠፉት ስህተት ካለ እና ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር እያዩ ለችግሮች መፍትሔ የሚያበጁ የቦረና ኦሮሞ አባቶች ናቸው።

ቦረናዎች ተዝቆ የማያልቅ የባህልና ዕውቀት ባለቤት ናቸው። ከዚህ ውስጥ የስነከዋክብት ምርምር ችሎታቸው አንዱ ነው። በተለይ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የኩሽ ህዝቦች ይጠቀሙበት የነበረው የቀን መቁጠሪያ /ካሌንደር/ ባለቤት ናቸው። የቦረናዎች ቀን መቁጠሪያ 12 ወራት እና 354 ቀናትን የያዘ ነው። የቀን አቆጣጠሩም የጨረቃ እና የከዋክብትን ግንኙነት አመሳጥሮ ይጠቀማል። ዛሬ ቀኑ አምስት በመሆኑ በቦረናዎች አጠራር «ሶርሳ» ይባላል። እንደ የቦረና ኮከብ አዋቂ በከፍታማ ቦታ ላይ ወጥቶ በየቀኑ የወጣችውን እያንዳንዷን ኮከብ እና የጨረቃ ግንኙነት በመመልከት የወሩን እና ቀኑን አቆጣጠር ሊደርስበት ይችላል።

ቦረናዎች ከጊዜ ዑደት ጋር ያላቸው ቁርኝት ከፍተኛ ነው። ታሪክ እራሱን ይደግማል የሚል እምነት አላቸው። በገዳ ስርዓት በየ360 ዓመቱ የተከናወኑ ጉዳዮች ተመልሰው እንደሚመጡ ማጥናታቸውን ቦረናዎች ይናገራሉ። ያኔ ጦርነት ከተካሄደ ወይም ድርቅ ከነበረ አሁን ላይ ለዚያ የሚሆን ዝግጅት ያደርጋሉ። ነገርግን ችግር ወይም የከፋ ነገር ያለፈው ጊዜ ተከስቶ ከነበረ በጸሎት እና የእንስሳት መስዋዕት በማድረግ ችግሩ እንዲያልፍ በቅን ልቦና አምላካቸውን ይጠይቃሉ። በጎ ሥራ ከሆነ ግን ያንን ለመድገም ዝግጅታቸውን ያጧጡፉታል።

እንደ ፕሮፌሰር አስመሮም ገለጸ፤ በ1980ዎቹ ላይ የነበረው ጅሎ አጋ የተባለው የቦረና ገዳ መሪ የስምነተኛው ትውልድ የዘር ግንዱ የቦረናን ህግ ደንጋጊ ሲሆኑ፤ ወጣት ሆኖ ይህን ታሪክ ስለሰማ እና ከ360 ዓመት በኋላ ያንን ታሪክ የሚደግም ሥራ እንደሚያከናውን ስለተነገረው ዝግጅት አደረገ። በመሆኑም ታሪክ እራሱን ይደግማል በሚለው ብሂል እርሱ ደግሞ የአባ ገዳ አመራረጥ ስርዓትን ወደቀድሞ አሠራሩ የሚመልስ ህግ አወጣ። በቀድሞ ጊዜ አባገዳዎች በሙሉ ተሰብስበው ገዳውን ይመርጡ የነበረውን ሂደት ትቶ ምርጫው ለወረቃሉ ወይም ለሐይማኖት አባቶች ተሰጠ። በዚህም ምክንያት ጥንቁቁ ጅሎ አጋ ደግሞ ምርጫ የማካሄድ ስልጣኑን ወደአባገዳዎች የሚመልስ ህግ ደነገገ።

ቦረናዎች አሁንም በእያንዳንዱ የህይወት ክንውን ውስጥ ድግግሞሹ መኖሩን የሚያወሳ የጊዜ ቀመራቸውን ጠንቅቀው የያዙ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዴቨሎፕመንት ስተዲ የዶክትሬት ተማሪና የአካባቢው ተወላጅ አቶ ገልገሎ ጠቃ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ቦረናዎች የከብት እርባታ ችሎታቸው የሚደነቅ ነው። ከብት ሲያዳቅሉ ጥሩውን ዘር መርጠው ከጥሩ ዘር ጋር ነው። ልክ እንደዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈሃሳብ መጥፎው እየሞተ ጥሩው ብቻ እየዳበረ ይሄዳል የሚል እምነት አላቸው። በዚህም መሰረት ሰባት ዓይነት የጥሩ ዘር መምረጫ መስፈርት አውጥተው ለዘመናት ምረጦቹን ብቻ ሲያዳቅሉ ኖረዋል። የጥጃዋን ሽታ ጠልታ የምትራገጠውን ወይም በረሃብ ቶሎ የሚዳከመውን በመጥፎ ዘር ውስጥ ሲመድቡት። መንታ የምትወልደውንና ጠንካራ ሥራ የሚያከናውነውን ደግሞ ከጥሩዎቹ መድበው ይይዟቸዋል። የማይፈልጓቸውን ዘሮች ደግሞ ለገበያ አቅርበው ምርጥ ዘሮቹን ያዳቅላሉ። በዚህም ዘመናዊ የከብት ማርቢያ ድርጅቶች ጭምር ተመራጭ ሆነዋል።

በኬንያ በእርባታ ሥራ የተሰማሩ የውጭ ድርጅቶች የቦረናዎችን ከብቶች እየተጠቀሙ ይገኛሉ የሚሉት አቶ ገልገሎ፤ ቦረናዎች ስለከብት በሽታ በባህላዊ መንገድ ምርምር ያካሂዳሉ። አንድ እንስሳ ከሞተባቸው አይበሉትም፣ ግን አርደው ሆድዕቃውን ይፈትሻሉ። የትኛው ክፍል እንደተጠቃ ለይተው ባህላዊ መድሃኒት ያዘጋጃሉ። ቅጠላቅጠሎችን በመቀመም ከውስጥ ደዌ እስከ ቆዳ በሽታዎችን ሲከላከሉ ኖረዋል። አሁን ላይ ዘመናዊ ህክምና በገባባቸው አካባቢዎች ቦረናዎች የከብቶቻቸውን በሽታ በደንብ ስለሚያውቁ ተናግረው ብቻ መድሃኒት ይወስዳሉ። ከዚያም ቤታቸው ሄደው መድሃኒቱን ሲሰጧቸው ይፈወሳሉ። በዚህ መንገድ ለሌላ አካባቢ ነዋሪዎች መድሃኒት ባይሰጥም ለቦረናዎች ግን ካላቸው የእንስሳት በሽታ ዕውቀት የተነሳ ከመደብሮች መድሃኒቶችን እንዲወስዱ እንደሚደረግ ይናገራሉ።

በዕጽዋት ዕውቀት ቦረናዎች እስከ አራት መቶ የሚደርሱ ዝርያዎችን ጥቅም ለይተዋል። ለአብነት በድርቅ ወቅት «ሰፈራ» የተባለውን ተክል ቆፍረው ተደብቆ የኖረውን ትልቅ ስሩን ያወጡታል። በፀሐያማው አካባቢ ለተነቃቃው ጉሮሯቸው የሚሆን ፈሳሽ ከተክሉ ስር በመጭመቅ ለመጠጥነት ይጠቀማሉ። ሲያሻቸው ደግሞ ስሩን ከትፈው ለእንስሳቶቻቸው ምግብነት ያውሉታል። በዚህም እንስሳቶቻቸው ሳይሞቱ በርካታ የድርቅ ጊዜያትን እንዳሳለፉም ያስረዳሉ።

በአጠቃላይ ቦረናዎች ከጥንት ጀምሮ ሲወራረስ እና ሲዳብር የመጣ የበርካታ ጥበቦች ባለቤት ናቸው። በመሆኑም በአገባቡ ተጠንተው ከዘመናዊው ስርዓት ጋር የሚጣጣሙበትን መንገድ በመፈለግ ለተሻለ ጥቅም ማዋል ይገባል መልዕክታችን ነው። ሰላም!

አዲስ ዘመን ጥር 5/2011

ጌትነት ተስፋማርያም