“በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት የሚያስችል ተግባር አላገኘንም”አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአምስት ወራት የሚቆይ ነው። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባለፈው ወር መባቻ ላይ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰጠው ማብራሪያ መሰረት ውሳኔው በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ከመሆኑም በላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችንም በዝርዝር ነበር ያስቀመጠው።
በዚህም ቋሚ የመብት እገዳዎችንና እርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ እንዳስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት እገዳዎችንና እርምጃዎችን እንዲደነግግ ስልጣን ሰጥቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነትን በተመለከተ የሚኖሩ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎችን ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ነው በወቅቱ የገለጸው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማንኛውም ሰው በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባለው አካል የሚሠጥን ሕጋዊ ትዕዛዝ፣ መመሪያ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። በሌላ በኩልም የፌደራልና የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማትና ሌሎች በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ሁሉ ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም በአዋጁ መሰረት ይፋ የተደረጉ የመብት እገዳዎችንና እርምጃዎችን የማስፈጸም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያ ወይም ትዕዛዝን ሆን ብሎ የጣሰ ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችልም በአዋጁ ተደንግጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነትን በተመለከተ የሚኖሩ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎችን ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ፤ በተወሰነው መሰረትም ሚያዚያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ክፍሎችን ይዞ ወጥቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካስቀመጣቸው ክልከላዎች መካከልም ማንኛውም ሀይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድሮች፣ ደቦዎችና ሌሎችም ከአራት ሰው በላይ የሚያሳትፉ ነገሮች ሁሉ ክልክል መሆናቸውና የህግ ታራሚዎችንም በተመለከተ ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚደረግና ጥየቃ ለሚሄዱ ሰዎች ግን ከታራሚዎች ጋር መገናኘት የማይፈቀድ መሆኑን ያብራራል። ከሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተለይም ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፣ ባንኮች፣ የገበያ ቦታዎችና ትራንስፖርት ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንዲጠቀም አዝዟል።
የአዋጁን አፈጻጸም፣ እየታዩ ባሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ ከአቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ የአዋጁን አስፈላጊነትና ከታወጀበት ጊዜ አንስቶስ ምን ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንደተደረጉ ቢገልጹልኝ?
አቶ ጴጥሮስ፦ አዋጁ የታወጀው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ እያደረሰ ካለው ተጽዕኖ አንጻር ሊደርስብን የሚችለውን ጉዳት በመገመት ከወዲሁ የመከላከሉን እርምጃ መንግሥትም ህዝብም በተቀናጀ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ለማስቻል ነው። በተለይ ከዚህ ቀደም የምናውቃቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ይወጡ የነበረው ህግና ስርዓትን ለማስከበር ሳይቻል ሲቀር እንዲሁም መንግስት የአስተዳደር ስራውን በአግባቡ ማካሄድ የማይችልባቸው ግርግሮች ሲኖሩ ነበር።
አሁን ግን በአገሪቱ ላይ አመጽ ወይም ሌላ ለመንግስት አስተዳደር ምቹ ያልሆነ ነገር ተፈጥሮ ሳይሆን ከሰው ህይወት ጋር የተያያዘ ጥፋትን ሊያስከትል የሚችል ወረርሽኝ በመከሰቱ የታወጀ በመሆኑና በሽታውን ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ ከህብረተሰቡ ጋር መግባባትና መደማመጥን የሚጠይቅ ስለሆነ ሰዎችን ከጥፋት ለማዳን የታወጀ ነው።
አዋጁም ህገ መንግስቱ በሚያዘው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ተቋቁሞለት ስራውን የጀመረ ሲሆን በተጨማሪም ቦርዱ የሚመራበት መመሪያ እንዲሁም መንግስት የሚያወጣቸው ደንቦችን በመከተል ተፈጻሚነቱም በተቻለ መጠን የሰዎችን ሰብዓዊ መብት አክብሮ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲባል ብዙ እንቅስቃሴዎችን ይገድባል፤ ይህ አዋጅ የታወጀው ህይወት ለማዳን ከመሆኑ አንጻር ከሌሎቹ ይለያል፤ እናም ይህንን በህብረተሰቡ ውስጥ የማስረጽ ስራው በሚገባ ተሰርቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ጴጥሮስ፦ አዋጁ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ለመጠበቅ የወጣ እንጂ ሌሎች መብቶችን ለመገደብ የወጣ እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፤ ቦርዱም አዋጁን ለማስፈጸም መንግስትንና ህዝብን አግዞ መከላከሉ ላይ አብረን ተሳትፈን በዚህ ሂደት ደግሞ የሚፈጠሩ ችግሮች ሲኖሩ ለመቆጣጠርም በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው።
አዋጁ ከመታወጁ አስቀድሞ መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ነበር። አዋጁ ከታወጀ በኋላም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያግዙ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመራ በማድረግ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ ይህ አደረጃጀት በክልሎችም እንዲቋቋም ተደርጎ ወጥ የሆነ የመከላከል አካሄድ እንዲኖር ተደርጓል። የተሰሩ ስራዎች ህብረተሰቡን ያሳተፉ እንዲሁም ግንዛቤን ከፍ ያደረጉ መሆናቸውንም በየጊዜው መገምገም እንዲቻል ስርዓት ተቀምጦ ስለተገባ በዚህ ልክ እየተሰራና እየሄደ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ አዋጅ አካሄድ የመጡ መልካም ጅምሮችንና ውጤቶችን እንዴት ይገልጿቸዋል?
አቶ ጴጥሮስ፦ ከጠንካራ ጎኖቹ መካከል ህዝቡ በተቻለ መጠን ከመንግስት ጋር ለመስራትና የሚሰጡ መረጃዎችን ለማዳመጥ ጥረት እያደረገ ነው:: የሀይማኖት ተቋማት በትልልቅ የበዓላት ቀናት ሳይቀር የአምልኮ ፕሮግራሞች ቀርተው ሁሉም ምዕመን በቤቱ እንዲጸልይና እንዲሰግድ በማድረግ በኩል የታየው መተባበር ሌላው የጥንካሬው ማሳያ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ አሁን ላለንበት የተረጋጋ የመከላከል ስራ ትልቅ አዎንታዊ ሚናን ተወጥቷል።
አዲስ ዘመን፦ ችግሮቹስ እንዴት ይገለጻሉ?
አቶ ዼጥሮስ፦ አሁን ባለንበት ሁኔታ ጫፍ የወጣ ችግር አላጋጠመንም። በሽታው በድንገት የመጣ እንደመሆኑ የለይቶ ማቆያ (ኳራንታይን) ዝግጅት በቂ ያለመሆንና በበሽታው ተጠርጥረው ለሚገቡ ሰዎችም የምግብና የማረፊያ ሁኔታዎችን እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ከማሟላት አንጻር ክፍተቶች ነበሩ። በሌላ በኩልም ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች በቶሎ ለይቶ ህክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ከማመቻቸት አንጻርም ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን ችግሮቹ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ አልነበሩም።
ቫይረሱ ወደ አገራችን በገባበት ወቅት በርካታ ሰዎች ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ ይመለሱ ስለነበር ይህንን ለመቆጣጠር መንግስት እንዲሁም በየደረጃው የተቋቋሙ ኮሚቴዎች በጥሩ ጥንቃቄ ስራዎችን በማከናወናቸው ዜጎቻችን ሳይጉላሉ በተቻለ ፍጥነት ወደተዘጋጀላቸው ማቆያዎች እንዲገቡ ሆኗል።
እንደ ችግር ሊነሳ የሚችለው አገራችን ከሌሎች አገራት ጋር የምትጋራቸው ድንበሮች በሁሉም አቅጣጫዎች በጣም ሰፋፊ መሆናቸው በእነዚህ አካባቢዎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ቁጥር በጣም እየጨመረ መምጣቱ ለእኛ ስጋት ነው። በመሆኑም ከእነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች በሽታውን እንዳያስፋፉ ስጋት አለ። በመሆኑም ድንበርን ሙሉ በሙሉ ማጠር ሊታሰብ የሚችል ነገር ስላልሆነ በአካባቢው ያሉ ህዝቦች ከሰራዊቱና ከፖሊሱ ጋር ተባብረው በእግር ሊታለፉ የሚችሉ ቦታዎችን ነቃ ብለው እንዲጠብቁ እየመከርን ነው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ደግሞ በሽታውን ለመቆጣጠር አቅም እናገኛለን።
አዲስ ዘመን ፦ ህብረተሰቡ የቫይረሱን አስከፊነት ተረድቶ እራሱንና ሌላውን በመጠበቁ በኩል እያደረገ ያለውን ተግባር እንዴት ያዩታል?
አቶ ጴጥሮስ ፦ የህብረተሰቡ ቸልተኝነት በጣም ሰፊ ነው፤ ለምሳሌ አዋጁ ከሚያዘውና በቀላሉ ሊደረጉ ከሚችሉ ነገሮች ብንነሳ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አለማድረግ፣ ተዘጋጅቶ በቀረበ ውሃና ሳሙና እጅን ለመታጠብ ማቅማማት፣ ርቀትን ጠብቆ ለመሄድም ሆነ ለመቀመጥ ፍቃደኛ አለመሆን የቸልተኝነቱን መጠን ስለሚያሳይና ‹‹እኔን አይነካኝም›› ብሎ ማሰብ በኋላ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ በመሆኑ ከዚህ ቸልተኝነት መውጣትና እንደሀገርና ህዝብ ይህንን ወቅት በጋራና በትብብር ለማለፍ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ይህ እናንተ የተመለከታችሁትን የህብረተሰቡን ቸልተኝነት የተመለከቱ አንዳንድ አካላትም ‹‹መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያወጣም ማስፈጸም አልቻለም›› ይላሉ፤ የእርስዎ ሀሳብ ምንድን ነው?
አቶ ጴጥሮስ፦ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠ አድርገው የወሰዱ አሉ፤ እስካሁን ወደ 694 የሚሆኑ አቤቱታዎችን ስንቀበል ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ‹‹መንግሥት ቸል ብሎናል፤ ክልከላውን የማይጠብቁ ሰዎች እየተያዙና እየተቀጡ አይደለም›› የሚሉ ናቸው። መንግሥት ደግሞ ኃይል መጠቀም ከቫይረሱ ስርጭት አንጻር ሌላ ችግር መፍጠር ነው የሚል አቋም የነበረው በመሆኑ እስካሁን ሰዎች አዋጁን ተላልፈው ሲገኙ ከመምከርና ከመገሰጽ ያለፈ እርምጃ ሳይወሰድ ቆይቷል።
አሁን ግን በተለይም ተመክረው ውጤት አላመጣ ያሉንትና እራሳቸውንም ሆነ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል አደጋ ላይ ሊጥሉ የተዘጋጁትን መስመር በማስያዝ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት አግባብ ያለውን ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። እዚህ ላይ ግን የመንግስት ትዕግስት ያልገባቸው እንዲሁም የወረርሽኙን በፍጥነት መዛመት ቸል ያሉ አካላት መንግስት አዋጁን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ የሰብዓዊ መብታችን እየተረገጠ ነው እያሉም ነውና ሁሉንም አቻችሎ ለመሄድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንዳለ እኛ እንደቦርድ ዕያየን ነው።
በመጀመሪያው አካባቢ ሁሉም ክልሎች ተደናግጠው በሮቻቸውን ዘግተው ነበር፤ ግን በዚህ ድህነታችን ላይ ትራንስፖርትን እንዲሁም የሰዎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሁኔታን መዝጋት ወይም መገደብ አዋጭ ባለመሆኑ በሮቹ ተከፍተው የትራንስፖርት አጠቃቀሙና የህዝብ አጫጫኑ 50 በመቶ እንዲሆን ተወስኖ ወደ ስራ ተገብቷል። ሆኖም 50 በመቶ ጫኑ ሲባሉ ከዚያ በላይ መጫንና እንዲቀበሉ ከተቀመጠላቸው ታሪፍ በላይ ማስከፈል፤ ህብረተሰቡም አዋጁን ተከትሎ በዚያው መሰረት መጓጓዝ ሲገባው ራሱን የህገወጥ ድርጊታቸው ተባባሪ አድርጓል። ይህ ደግሞ አዋጁን መጻረር በመሆኑ በዚህ ልክ የሚያጠፉ ሰዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጀምሯል፤ ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል። እዚህ ላይ ግን በተለይም እርምጃ መውሰድ ሲጀመር የሰብዓዊ መብት ተጣሰ እየተባለ ነው። እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ተይዘው በምክርና በፊርማ ተለቀዋል፤ ለ24 ሰዓታት እንኳን ታስረው የሚቆዩት ጥቂት ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ የእነዚህ ጥቂት ሰዎችስ ሰብዓዊ መብት ሳይጓደል ስለመታሰራቸው እንደቦርድ ያያችሁበት ሁኔታ አለ?
አቶ ጴጥሮስ፦ እንቅስቃሴ ስለተገደበ ታሰሩ ይባል ይሆናል እንጂ እነዚህ ህግ ተላላፊ ሰዎች አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አይሄዱም፤ የሚቆዩትም ለዚሁ በተዘጋጁ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፤ በቆይታቸውም ወቅት ተራርቀው እንዲቀመጡ፣ ሲያድሩም በአንድ ክፍል ውስጥ ሶስትና አራት ሰዎች እንዲሆኑ ነው እየተደረገ ያለው። እኛም ይህንን ተዟዙረን ተመልክተናል።
ሆኖም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ‹‹የሰዎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ›› ሲባል እየሰማን ነው፤ እስካሁን ግን የለም። ወደፊትም ከተከሰተ እየተከታተልን እንዲታረም ለማድረግ እንሰራለን። ምክንያቱም የቦርዱ መቋቋም ዋና አላማና ስራው አዋጁን በማስፈጸም ወቅት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዳይኖሩ መከታተልና ተፈጽሞም ሲገኝ እንዲታረም ማድረግ ነው። ይህንን የፈጸሙ አካላትም እንዲጠየቁ የማድረግ ስልጣንም ስላለን ስራችንን ከዚህ አንጻር እየሰራን ነው ።
በአንድ ወር ውስጥ በተሰሩ ስራዎች እንዲሁም እስካሁን የታሰሩ ሰዎች ምክንያታቸውና ማንነታቸውን በተመለከተ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ጋር ተወያይተናል፤ ጥሩ መግባባት ላይም ደርሰናል። በዚህም በአዋጁ አፈጻጻም ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት የሚያስችል ተግባር አላገኘንም። ይህም ቢሆን ግን ከሚደርሱን ጥቆማዎችና ከሚሰጡን አስተያየቶች በመነሳት ችግሮች ሲያጋጥሙ የምንፈታበት አካሄድ ይኖራል። በመላው አገሪቱ ያለው የአዋጁ አፈጻጸም ግን አገራዊ መልክ ይዞ እየተመራና መንግሥትም ዜጎችን ለመጠበቅ ያደረገው ጥረት ተገቢ መሆኑን አይተናል።
አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ በሰዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው የሚል መግለጫ ማውጣቱስ መነሻው ምንድን ነው?
አቶ ጴጥሮስ፦ ቦርዱ የታሰሩ ሰዎችን በአካል በማግኘት አነጋግሯል፤ በዚህም አንድም ሰው ‹‹ሰብዓዊ መብቴ ተጥሷል›› ብሎ ቅሬታ አላቀረበም። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይህንን መረጃ ወደ መገናኛ ብዙኃን ይዞ ከመቅረቡ በፊት ጉዳዩን ወደእኛ ይዞ መጥቶ ብንወያይበት ጥሩ ነበር፤ አሁንም ቢሆን ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ቦርዱም የማይፈልገው በመሆኑ በአንድ ሰው ላይ ቢሆንም በዚህ ልክ የተፈጸመ ችግር ካለ አምርረን የምንታገለውና የማንታገሰው ነገር ነው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አዋጁ እንደወጣም ከማስፈጸሚያ ደንብ ጋር የሚያያዙ ጥያቄዎች ነበሩት፤ ሆኖም ጉዳዮቹን ፈጥኖ ወደ ሚዲያ ከማውጣት ይልቅ ቁጭ ብሎ መንግስትም እንዲሁም እኛ እንደ ቦርድ የአዋጁን አፈጻጸም የምንመረምር በመሆኑ በጋራ ቁጭ ብለን መነጋገርና ችግሮችን መፍታት እንችል ነበር።
እዚህ ላይ ምክር ቤቱ አዋጁን ሲያወጣ አስፈጻሚው አካል ክፍተቶችን እንደ ነባራዊ ሁኔታው እያየ እያስተካከለና እያሻሻለ እንዲሄድ ስልጣንም ስለሰጠው በደንቡ ላይ ሰብዓዊ መብትን የሚነኩ ነገሮች ካሉ የማይሻሻሉበት ምክንያት የለም።
ምክንያቱም አንድ ሀሳብ ሲነሳ ሙሉ በሙሉ ወስነን ‹‹እኛ ያልነው ነገር ብቻ ትክክል ነው›› ብለን መሄድ አንፈልግም። በመሆኑም ‹‹ኮሚሽኑን ቅር ያሰኘው ምንድን ነው? ምናልባት እኛ ባላየነው መንገድ አይቶት ይሆን?›› ብለን እያሰብን ነው።
አዲስ ዘመን፦ኮሚሽኑ አዋጁን ለማስፈጸም ከወጣው ደንብ ጋር ተያይዞ ቅሬታ እንዳለው ካወቃችሁ እስካሁን ለመነጋገር አልሞከራችሁም?
አቶ ጴጥሮስ፦ ከኮሚሽኑ ጋር መድረክ ፈጥረን እንወያይ። እነሱ የሚሉት ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለ ለመታረም ያስረዱን፤ ባለው ሁኔታ ደግሞ የመንግስትን የመከላከል ጥረት የሚያደበዝዝና ህብረተሰቡንም የባሰ ለበሽታው ተጋላጭ እንዳያደርግ እስኪ እንወያይ በማለት እየተዘጋጀን ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥም ቦርዱ መድረክ አመቻችቶ ኮሚሽኑም የመጣለት አቤቱታ ካለ እንዲያስረዱን እናደርጋለን። በዚህም ተጨባጭ ነገር ከተገኘ እንዲታረም ማድረግ ያስፈልጋል። ምናልባትም ስጋት ከሆነ ደግሞ ስጋቱን በመጋራት እንዳይቀጥል ለማድረግ እንሞክራለን።
ሰው ለማዳን እየተደረገ ያለውን ጥረት መደገፍና ተጋግዘን ይህንን ጊዜ ማለፍ ሲኖርብን ድክመቶች እንኳን ቢኖሩ ወደ ውይይት መምጣት ሲቻል በዚህ መልኩ መግለጫዎችን መስጠት ተገቢ አይደለም የሚል የግል አስተያየት አለኝ። ሆኖም አሁንም ቢሆን ችግሩ እውነት ከሆነ ለማረም ጊዜ ሳንሰጥ የውይይት መድረኩን እናመቻቻለን፤ እነሱም ፍቃደኛ ሆነው ይሳተፋሉ የሚል እምነት አለኝ።
እስካሁን ባለን መረጃ ግን የኮሚሽኑ ሪፖርት እውነት ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፤ እንዲያውም በህግ አስከባሪ ፖሊሶች ላይ በጉልበተኞች እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ ሰምተናል። ሆኖም ፖሊሶቻችን ህጉን ለማስከበርና በሽታውን የመከላከል ስራ ለመደገፍ ራሳቸውን ሰጥተው ዜጎች ላይም እርምጃ ሳይወስዱ እየሰሩ እንዳሉም ታዝበናል። ይህንንም ኃይል ለመልካም ስራው እያመሰገንን ነው መሄድ ያለብን።
አዲስ ዘመን፦ አዋጁ የሰዎችን ህይወት ለመታደግ የወጣ ነው፤ እስካሁንም ተላላፊዎችን በምክርና በተግሳጽ እንዲሁም በማስፈረም እየታለፈ እንዳለ ነግረውኛል። ይህ አዋጅ ጠንከር ብሎ ይፈጸም ቢባል ምን መልክ ሊኖረው ይችላል?
አቶ ጴጥሮስ፦ አዋጁን ተከትሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ደንብ ቁጥር 466/2012 ላይ 27 የሚሆኑ የተከለከሉ ተግባራት አሉ፤ የተጣሉ ግዴታዎችም አሉ፤ በዚህም መሰረት ይህንን ተላልፎ የተገኘ አካል ቅጣት ይጣልበታል። አዋጁና ደንቡ ከዚህ በፊት ያሉትን የወንጀል ስነ ስርዓት ህጎችን በዚህ አዋጅ ጉዳይ ላይ እንዳይፈጸሙ አድርጎ አግዷቸዋል። ይህ ማለት አንድ ሰው በአዋጁ ውስጥ የተጣሉትን ግዴታዎች ተላልፎ ከተገኘ ይያዛል። ‹‹በ48 ሰዓት ውስጥ ለምን ፍርድ ቤት አላቀረብከኝም?›› ብሎ ግን መከራከር አይችልም፤ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ሰዎች ሊያዙ ስለሚችሉ በ48 ሰዓት ውስጥ አለማቅረብ ሊኖር ስለሚችል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰው በመደበኛ ሁኔታ ወደ ፍርድ ቤት እንዳይሄድ በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤቶች ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ ዝግ ናቸው፤ ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ለሚታሰሩ ሰዎች ብቻ ነው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት። ይህም በመሆኑ በፍጥነት ውሳኔ ማግኘት ላይ መጓተቶች ይኖራሉ ።
በዚህ መሰረት ፍርድ ቤት የቀረበ ሰው ደግሞ በቀላል እስራት እስከ ሦስት ዓመት እንዲሁም በገንዘብ ከ አንድ ሺ እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር ድረስ ይቀጣል። በመሆኑም አገሩንና ቤተሰቡን የሚወድ ሰው እስሩን ወይም ቅጣቱን ሳይሆን መፍራት ያለበት ለሚወዳቸው ሁሉ ሲል የራሱን ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልገው።
ሞራል ያለው ሰው እስሩንም ሆነ የገንዘብ ቅጣቱን ከመፍራት ይልቅ በሌሎች አገሮች በአንድ ቀን ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ መቃብር እንደወረዱ በመገንዘብ ወደእኛ አገር እንዳይመጣ መፍራት ነው ያለበት። ሆኖም በዚህ ልክ ማሰብ ያቃታቸው ሲኖሩና ቸልተኛ ሆነው የሌላውንም ዜጋ ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ከሆነ አዋጁን የማስፈጸም ግዴታችንን እንወጣለን።
አዲስ ዘመን፦ አዋጁን ተገን በማድረግ የግል ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚጥሩ የጸጥታ ሀይሎች እንዳሉ ይሰማልና ቦርዱ የሚያደርገው ክትትል ምን ይመስላል ?
አቶ ጴጥሮስ፦ እንደ አገር የጸጥታው ሁኔታ እንዴት ነው እየተመራ ያለው? በሽታውን በመከላከሉ ስራስ? የሚለውንና እንደ ሉአላዊ አገር ሁሉም ዜጎች መብቶቻቸው ተከብሮላቸው በሰላም መኖር ስላለባቸው ይህንን የሚያደርጉ የጸጥታ ሀይሎች እንዴት እያገዙ ነው? የሚለውንም እንከታተላለን።
በየሳምንቱ በሁሉም የአገሪቱ ክልል ካሉ የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር እንወያያለን። በዚህ መሰረት በምናገኛቸው መረጃዎች በተለይ በአዲስ አበባና ወጣ ባሉ ከተሞች ላይ ውስን የሆኑ የጸጥታ አካላት ከወንጀለኞች ጋር የመሻረክ ነገር ተገኝቷል።
አዲስ ዘመን፦ ከወንጀለኞች ጋር መሻረክ ሲባል ግን ምን ማለት ይሆን?
አቶ ጴጥሮስ፦ ለምሳሌ መጠጥ ቤት፣ ሺሻ ቤቶችና ሌሎችን አዋጁን ተላልፈው ሲሰሩ አንዳንዱ ላይ እርምጃ መውሰድ ሌላውን ደግሞ አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ሲሆን፤ የዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ተባባሪ የሆኑ ህግ አስከባሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው። እርምጃውም ሌላው እንዲማርበትና ወረርሽኙን ለመከላከል ስራው ህይወታቸውን ሰውተው እየሰሩ ያሉት ስማቸው እንዳይጎድፍ የሚያደርግ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ባለሙያዎች ትንበያ ቀጣዮቹ ወራት የወረርሽኙ ስርጭት ከፍ የሚልበት ጊዜ ነው የሚል ስጋት አለና ህብረተሰቡ ለራሱ ብሎ እንዲጠነቀቅ ለማድረግ አዋጁም ጠንከር ብሎ ተፈጻሚ እንዲሆን ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
አቶ ጴጥሮስ፦ ቀጣዩ ጊዜ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተገምቶ በመንግስትም በኩል የመከላከል ስራውን ጠንካራ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አሉ፤ ከዚህ ወር በኋላ ባሉ ወራቶች የተጠቂዎች ቁጥርም ከፍ ሊል እንደሚችል ትንበያዎች አሉ፤ አንድና ሁለት ሰው ከተያዘብን ጊዜ ጀምሮ እያደረግን ያለው ጥረት አለ፤ አሁን ደግሞ በስጋት መጠኑ ልክ ለመቋቋም የሚያስችል ዝግጅት በመንግስት በኩል እየተደረገ ነው፤ ህዝቡም በዚህ ረገድ ተባብሮ ለመስራት ያሳየው ፍላጎትና ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው።
ቀጣዮቹ ወራት እንደትንበያው አስፈሪ ቢሆኑም መጀመሪያ ተደናግጠን እጅ መስጠት አይገባም፤ የምንችለውን ያህል መጠንቀቅ፣ ከዚህ በላይም ከመጣ ደግሞ መንግስት ከትልልቅ ከተሞች እስከ ወረዳና ጎጥ ድረስ ህዝቡን ለመታደግ ሰፊ ስራን እያከናወነ በመሆኑ መጠንቀቅ እንጂ መፍራት አያስፈልግም።
በሽታው ጥንቃቄን ነው የሚፈልገው፤ ይህንን ማድረግ ካልተቻለና ቸልተኝነቱ ከቀጠለ መንግስት ደግሞ ሳይወድ በግድ ህጎቹን ጠበቅ ወደማድረግና ክልከላዎቹን ወደ ማስፋት ይሄዳል ።
አዲስ ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ጴጥሮስ ፦እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
እፀገነት አክሊሉ

Recommended For You