ጥምቀት እና ሰርግ

32

«ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ» የሚለው የኖረ አባባል ለእለቱ የሚሰጠውን ልዩ አትኩሮት ያሳያል፡፡ በእለቱም የሚተጫጩ በርካቶች በመሆናቸው አምሮና ደምቆ ለመታየት፣ ሌሎችን ለመማረክ ጥረት ይደረጋል። ቀኑ ብዙዎች በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ጫወታ የሚደራበት፣ ትውውቅ የሚፈጠርበትና ፍላጎት ይፋ የሚሆንበት ነው። ሎሚም ከዘወትር አገልግሎቷ በተለየ መልኩ የፍቅር ጥሪ ማስተላለፊያ ትሆናለች፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ዘፈን ትዝ አለኝ። ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት እገምታለሁ። የዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ዘፈን ነው።
ሎሚ ብወረውር አሃ አሃ
ደረቱን መታሁት አሃ አሃ
አወይ ኩላሊቱን አሃ አሃ
ልቡን ባገኘሁት አሃ አሃ የሚለው። ልብም ሆነ የልብ ሰው የሚገኘው በዚህ ቀን እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ። ምክንያቱም አምሮና ተውቦ ከልቡ አጋር ፈልጎ የሚወጣ ስለማይጠፋ ነው። ለእዚህም ዛሬ ዛሬ ቢጠፋም በጥምቀት የሎሚ ውርወራም ይደራ ነበር። አሁን ኋላ ቀር ባህል ነው ተብሎ እየቀረ መጥቷል። እውነት ኋላ ቀር ባህል ይሆን? መልሱን ለእናንተው ልተወው።

ባህል እውነት፣ እምነትና አመለካከት የታከለበት ነው። ስለዚህም ለሚያምኑት መታመንና ከልብ መውደድን ያላብሳል። ይህ ደግሞ በሎሚ ውርወራ የሚያገኛት እንስት በእጅጉ የሚወዳትና እጣ ክፍሌ ናት የሚላት በመሆኑ ይታመንላታል፤ ይታዘዝላ ታልም። ይሁንና ባህሉ ቀርቶ ምርጫ የማይሳካበት መንገድ መከተሉ ሰፍቶ እያለ ይህ ኋላቀር ባህል ነው ይባላል። ለማንኛውም በጉዳዩ ላይ ብዙ ሃሳብ መስጠት ይከብዳልና ወደዚያው ወደ ቀደመው ነገሬ ልግባ።

በጥምቀት በርካታ ሰርግ በየአካባቢው ባህልና ወግ ዘንድ ይስተናገዳል። የታጨው የሚያገባበት፤ ለማግባት ደግሞ ዝግጁ የሆነው የሚያጭበት እለት ነው። በእርግጥ ይህ ጉዳይ እንዴት በማህበረሰቡ ዘንድ ሰርጾ ቀረ፤ የሰርግ ወቅት ይህ ብቻ ነው እንዴ፣ ለምንስ ተመረጠ? የሚል ጥያቄ በአዕምሯችን ዘወትር እንደሚያቃጭል አስባለሁ። አንዳንድ አባቶች እንደሚሉት ይህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድምታ አለው። በቃና ዘገሊላ ጌታ በሰርግ ቤት ገብቶ ውሃን ወደወይን ቀይሮ እድምተኛው ተደስቶ የወጣበት በመሆኑ ዘወትር የተቸገሩ እንኳን በዚህ እለት በሌሎች የሚታገዙበት ጊዜ ስለሆነ ተመራጭ ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ወቅት መኸር የሚሰበሰብበትና ምድሪቱ ጥጋብን የምታስተናግድበት ጊዜ ስለሆነ ደስታና ፌሽታ ለማድረግ ምቹ ነው ይባላል።

ማንም ደግሶ የማያፍርበት፤ የመጡትን እንግዶች በልተው ጠጥተው መርቀው የሚሸኙበት ጊዜ ነው። ስለዚህም በሞላ ጊዜ መደሰት የኢትዮጵያውን ባህል ነውና ድግሱ የተትረፈረፈና የሚያስደስት ለማድረግ ሲባል ጥምቀትን በሰርግ ማሳለፍ የተለመደ ሆኗል። በተመሳሳይ ይህ ወቅት የብርድ በመሆኑ በጨዋታ ሁሉ ነገር ይሞቃልና ሰብሰብ ብሎ ጊዜን ለማሳለፍ ደግሞ እንደ ሰርግ ተመራጭ አውድ የለምና ጥርን የሰርግ ወቅት ማድረግ የተጀመረው ከዚህም አንጻር እንደሆነ ይነገራል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰርጋቸውን ጊዜ በዚህ ወቅት ለያውም በጥምቀት እለት ያደረጉ ጥንዶችን ማናገር ችያለሁና ይህንን ወቅት የመረጡበትን ምክንያት እንዲህ ሲሉ አጫውተውኛል። ከ12ቱ ወራት ጥቂቶቹ አብዛኞቻችንን በጋራ የሚያስማሙ የራሳቸው የሆነ መገለጫ እና ትውስታን ይዘውብን ይመጣሉ። አስቀምጠውብንም ያልፋሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የመጀመሪያው ጥር ወር ነው ይላል ወጣት ዘመን አስጨንቅ። ምክንያቱ ጥር ወር ቤቱን የመሰረተበት፤ ልጅ ወልዶ አባት የሆነበት ጊዜ ነው። በተለይ ዕለተ ጥምቀት ለእርሱ ባለውለታው እንደሆነ ይናገራል።
«ከከተራ ጀምሮ አይኖቼን በውብ ሴቶች ላይ አማትር ነበር። ምክንያቱም ልቤን የምትማርከዋን እንስት ለማግኘት ነው። በዚህ ቀን ማጨትም ሆነ ማግባት እፈልግ ነበር። ስለዚህም ምንም ሳላቅማማ በጠዋት ጸሎቴን አድርጌ ነበር በከተራ እለት ታቦታቱን አጅቤ ወደ ኮተቤ ሜዳ የተጓዝኩት። አምላኬም ልመናዬን ሰማና ዓይኗ ከብለል ከብለል የሚል እንስት ላይ ልቤም አይኔም አረፈ። በተለይም አለባበሷ እርሷን እንዳላልፍ አድርጎኝ ነበር» አለ ወጣቱ ዘመን።

ከሴት ጓደኛዋ ጋር እየተጓዘች ነበርና ዝም ብሎ ተጠጋና የንግግር መክፈቻ የሆነውን አብሮ የመጫወት ጥያቄ አቀረበ። እንስቶቹም ጥያቄውን ተቀብለውት አብረውት ቆዩ፤ ልዩ ትዕይንቷን እንዳትረሳ የምታደርገው የኮተቤ ጥምቀተ ባህርም ለከርሞ እንዲናፈቅ አድርጋ አስተናገደችው። እዚህም እዚያም ክብ ሰርተው በተመስጦ ከሚዘምሩት ምዕመናን ጥቂት ሜትሮች ፈንጠር ብሎ ወጣቶች ተሰብስበው ‹‹አርሞኒካ›› በሚባል የሙዚቃ መሳሪያ እስከሚጫወቱት ድረስ እየተዘዋወሩም ተዝናኑ። አሁንም ፍላጎቱ የቤት አድማቂው አጋሩ ማድረግ ነውና ሊነጠላቸው አልፈለገም። እናም ያው በተለመደ የአንለያይ ጥያቄው «ስልክሽን ታውሺኝ» አለ አይኑ ያረፈባትን ሴት ለብቻ ነጥሎ።

በአርሞኒካ ጨዋታ ላይ ወንድና ሴቱ በጋራ ለመጨፈር መተዋወቅ መስፈርት እንዳለመሆኑ ሁሉ እርሱም አጠገቡ ያለችዋን እንስት ጎተት አድርጎ ወደ ስብስቡ መሃል ማስገባት ምርጫው አደረገና ልብሽን ለልቤ አለ። እርሷም ብትሆን ሳትማረክበት አልቀረችምና ጥያቄውን ተቀበለችው፤ ስልክ ቁጥሯን ሰጠችው። የአለባበሱም ጉዳይ እንደዛው ከባህላዊው ያፈነገጠ አልነበረምና ወደዋለች። ይህ የፍቅር ጊዜም ከኮተቤ ጥምቀተ ባህር አልፎ ቤት ገባ።

መጀመሪያ የከተራ ዕለት ተዋወቁ። ከዚያም በዕለተ ጥምቀት ተገናኝተው ተጫወቱ። በሦስተኛው ቀን በቃና ዘገሊላ የፍቅርን መንገድ አሃዱ ብለው ጀመሩ። ስለዚህም በሎሚ ውርወራ ፋንታ በርካታ ወዝ ያለው ንግግር ተነጋግረው ቤትሽ ቤቴ ይሁን በማለት ለሁለት ዓመት ከቆዩ በኋላ ያችኑ የተዋወቁባትን ቀን ጠብቀው ጋብቻቸውን አደረጉ። ምክንያቱም ይህ ቀን መሰረታቸው ነው። የትዝታ ቤታቸውም ነው።

እናም ዘመን አለ «የተጋቢ ሙሽሮቹ የሰርግና ምላሾቻቸው እለቶች ቢሆን የምመርጠው ከተራ ነው፤ በእነዚህ የወሩ ሳምንታት ከሳምንቱም አራቱ ቀናቶች የከተማይቱ ጆሮዎች የሰርግ ዜማና የመኪና ጡሩንባ ሳይቀር የሚፈጥረው ትዝታ ዘላለም የማይጠፋ በመሆኑ ሁልጊዜ የሰርግ ጊዜያችን እንዲታወስ ያደርገናል። ይህንን ቀን አለማስታወስ አይቻለንምም። ስለዚህ እኔ እንዳደረኩት እነርሱም ቢጠቀሙበት እመርጣለሁ» ብሏል።
ባለቤቱ ወይም የትዳር አጋሩ ወይዘሮ ገዳምነሽ ምትኩም ከባሏ ጋር በእጅጉ ትስማማለች። «ይህ እለት ለእኔ የትዳር ቤቴን ማቆሚያ ብቻ አይደለም። የልጆቼንም የልደት በዓል ማክበሪያ ነው። ሁለቱም ልጆቼ የተወለዱት ጥምቀት በሚከበርበት ጊዜ ነው። እናም ይህ ቀን ለእኛ የሰርጋችን ዓመታዊ በዓል ሲሆን፤ የልጆቼ ደግሞ ልደታቸው ነው። በዚህም ሰው የማይረሳውን ትዝታ ማስቀመጥ ያለበት እንዲህ ባለው አጋጣሚ ነው» ትላለች።

ጥምቀት ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የሚደረግበት ብቻ አይደለም። ህይወት መስጫና ራስን ማወቂያም ጭምር ነው። ላወቀበት በትክክል ይጠቀምበታል። ኋላቀር ነው ብሎ ላሰበ ደግሞ ሌሎች ልምዶችን ይወስድበታል። በተለይ ከመሰባሰቡ ጋር ተያይዞ ጥሩ ቁምነገር የሚጨበጥበትና ማንኛውም ሰው ራሱን የሚገነባበትን አማራጭ የሚያገኝበት እንደዚህ ቀን ያለ አይመስለኝም። ያለልዩነት ራስን ማወቂያም ጭምር ነውና እንደኛ ህይወትን መለወጫ እለት እንዲያደርጉት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደምትመኝ አጫውታኛለች።

ይህንን ሀሳቧን ስሰማ አንድ ነገር አስታወስኩ ኋላ ቀር የሚባለው ነገር ምን ይሆን የሚለውን። ብዙ ሰዎች ባህላችን የሚገኙ የማይጎዱ እንደውም ማንነታችንን የሚገነቡ ነገሮችን ኋላቀር እንደሆኑ ይነግሩናል። ለምሳሌ ሎሚ መወርወር ኋላ ቀር ነው ይባላል። ዘመን ግን ትዝታ ነው፤ እንደውም ትክክለኛ ምርጫን የሚያሳይና ከልብ የመነጨ ባህል ይላል። ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ላይ የምንናገረውና የምንኖረው አይገናኝም።

በሎሚ ውርወራ ተመስርቶ ወደ ትዳር የሚያመራው ህይወት ባህልን መነሻ አድርጎ ስለሚቆምና የሌላ ወገን ጣልቃ ገብነት ስለማይበዛበት ሁሉ ነገር በፍቅር ይጠናቀቃል። ባህሉን የሚያምነው ማህበረሰብም ይመርቃቸዋል። ከዚህ በላይ ፍቅር አጠንካሪ ነገር ምን አለ ሲልም ይጠይቃል። እርግጥ ትንሽ እውቀት ትልቁን ድንቁርና ታረግዝና በባዶ መጀነንን ትወልዳለች። ከዚያም የዓለምን የእውቀት ጫፍ የነካን ይመስለንና በራሳችን ዛቢያ ላይ ብቻ እየተሽከረከርን የራሳችንን ማሞካሸት የሌሎችን መንቋሸሽ እንጀምራለን። ይህ ነው ለውድቀት የሚዳርገው።

ሊገባን የሚገባው ግን ቁምነገር ባወቅን ቁጥር ያልገቡን ነገሮች እንደሚገቡን ነው። አዋቂነት ማለት አላዋቂነትን ማስፋፋት ማለት አይደለም። ማወቃችን የሚጠቅመን ችግሮችን ለመፈብረክ ከሆነ ዝንተ ዓለም ሳያውቁ መኖር ይሻላል። እናም ኋላ ቀር ምንድነው የሚለውን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን አላወቅንምና እንጠንቀቅ። ለምታገቡ የአብርሃምና የሳራ ጋብቻ ይሁንላችሁ፤ ለምታጩ ደግሞ መልካሙን፣ መልካሟን ያጋጥማችሁ አልኩ። ሰላም!

አዲስ ዘመን ጥር 12/2011

ጽጌሬዳ ጫንያለው