«አገር የሚለውጥ የካሪኩለም ሥራ ቢኖረኝም መንግሥት ሊመለከተው አልቻለም»- ፕሮፌሰር መኮንን አሰፋ

38

የ75 ዓመት አዛውንት ናቸው። አሁንም ከሥራ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መስርተው ይኖራሉ። እንደወጣት ሮጠውና ተግተው ይሰራሉ። በዚህም ብዙዎች ይቀኑባቸዋል። በተለይ በምርምርና ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ አንቱታን ያተረፉ በመሆናቸውና አሁንም እያስተማሩ በመገኘታቸው ግዴታን መወጣት እንደእርሳቸው ይባልላቸዋል። ከ40 በላይ ጤናንና ስርዓተ ትምህርትን የሚመለከት ምርምር በማድረግ ይታወቃሉ። በአማካሪነትም የተለያዩ ተግባራትን የከወኑ ናቸው። ጅማ ዩኒቨርሲቲና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ደግሞ በእጅጉ መሪያችንና መምህራችን ናቸው ይሏቸዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት አገልግሎትን የጀመሩ ስለመሆናቸውም ይነገርላቸዋል። በጅማ አካባቢ የሚገኘውን የግልገል ጊቤ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ማዕከልን ካቋቋሙት መካከል አንዱም ናቸው። ትምህርታቸውን በተለይም ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከአገር ውጪ በአሜሪካና እንግሊዝ ያጠናቀቁም ቢሆንም አገራቸውን በጣም ስለሚወዱና መለወጥም ስለሚፈልጉ በእነዚህ አገራት መቆየትን ሳይፈልጉ በአገራቸው እየሰሩ አሁን ያሉበት ላይ ደርሰዋል። የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን ፕሮፌሰር መኮንን አሰፋ። የዕድሜ ባለፀጋው እንግዳችን ብዙ ቁምነገሮች በውስጣቸው አለ። ስለዚህም ተሞክሯቸውን ተቋደሱ ስንል አቀረብንላችሁ። መልካም ንባብ።

የጎንደሩ እንቦሳ
የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አመለካከት ይመስጣቸዋል። ለዚህም ምክንያታቸው የማህበረሰብን ፍላጎት በማንኛውም መልኩ ማሟላት ግዴታ ነው የሚለው እምነታቸው ነው፡፡ ሰው በሰውነቱ ተከብሮ የሚፈልገው ማህበራዊ ጉዳይ ሊሟላለት ይገባል የሚል አመለካከትም አላቸው። ስለዚህም ከራስ የሚጠበቅ ነገር እንዳለ ስለሚረዱ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለአገር ባለውለታ፤ ሰርቶና ተምሮ የሚኖር ሰው መሆንን ይፈልጋሉ።

ታሪክ አዋቂና ፖለቲከኛ መሆንም የሁል ጊዜ ምርጫቸው ነው። ትውልዳቸው በቀድሞው አጠራር በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ጉና ተራራ አካባቢ ነው። በ1936 ዓ.ም ነበር እናት ልጃቸውን የዛሬውን የ75 ዓመት አዛውንት ፕሮፌሰር መኮንንን ያገኙት። እናም እንደማንኛውም የአካባቢው ነዋሪ ልጆች ቦርቀው፤ ተጫውተው፤ ያሻቸውን አግኝተው አድገዋል። የቄስ ትምህርትም የቆጠሩት በዚህ ስፍራ ነው። በልጅነታቸው ከብት አግደዋል፣ ቤተሰቦቻቸውን በቻሉት መጠን አግዘዋል። ይሁንና ሁል ጊዜ አላማ ተኮር ስለነበሩ ለዘመናዊ ትምህርት ልዩ ፍቅር ነበራቸው። በዚህም ቤተሰቦቻቸው በሚገባ አገዟቸውና በወቅቱ በቅርባቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በእግራቸው ጭምር እየተጓዙ እንዲማሩ ሆኑ። ልጅነታቸውን በይበልጥ የሚያስታውሱት በትምህርት ላይ ማሳለፋቸውን ብቻ እንደሆነ አጫውተውናል።

ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ እንግሊዝ
ባለታሪካችን ስለትምህርት ጉዳይ በእጅጉ ማውራት ያስደስታቸዋል። በዚህም ከአንዱ ወደ አንዱ እንዴት እንደተዘዋወሩና ትምህርታቸውን እንዴት ጠንክረው እንደተማሩ በስፋት ይናገራሉ። ያሳለፏቸውን የትምህርት ጉዞዎችና እንዴት ለዚህ እንደበቁም ተሞክሯቸውን ያጋራሉ። ፕሮፌሰር መኮንን ከቄስ ትምህርቱ ገፋ ሲሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል በዚያው በተወለዱበት ቀያቸው ደብረታቦር ከተማ የቆዩ ሲሆን፤ አጼ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባል ነበር የተማሩበትም ትምህርት ቤት።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ደግሞ ወደ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት አቅንተዋል። በዚያም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተብሎ በተሰየመው ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ በወቅቱ ትልቅ ህልም ነበራቸውና በሚገባ ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ አድርገዋል። ጎበዝ ከሚባሉት ተርታም ይሰለፉ ነበር። ይህ ታታሪነታቸው ደግሞ ብዙ ውድድርን የሚጠይቀውን የትምህርት ጉዞ እንዲያልፉ አስችሏቸዋል። ይሁንና አሥራ ሁለተኛ ክፍልን ጨርሰው የዩኒቨርሲቲውን ምደባ እየተጠባበቁ ሳለ ያላሰቡት ነገር ገጠማቸው።

ምደባው የሚደረገው አዲስ አበባ በመሆኑ እርሳቸውና ጓደኛቸው ወደ ቦታው ከቤተሰባቸው የተለገሳቸውን 150 ብር ይዘው ተጓዙ። ግን ብሯ ከተማው ውስጥ ብዙ ልታቆያቸው አልቻለችም። ስለዚህም መጠለያ ጠፋ። ምግብም ለማግኘት ተቸገሩ። ይህ ሁኔታቸው ደግሞ የቀያቸውን ሰው ፍለጋ እንዲገቡ አስገደዳቸው። በስመ ጎንደሬነት ተጠግተው የሚቀመጡበትን ቤት ሻቱ። እኒህ ጎንደሬ በወቅቱ ደጃዝማች ከበዱ ይባሉ ነበር። በእንጦጦ አካባቢ ይኖራሉ።

እንግዳችንም ይህንን መረጃ ይዘው ከጓደኛቸው ጋር ወደ ቦታው አቀኑ። ጎንደሬነታቸውን ነግረውም ባላባቱ በቤታቸው እንዲያስጠልሏቸው ጠየቁ። ፈቃደቻው ተሰጥቷቸው መኖር ሲጀምሩ ግን የፍልሰታ ጾም ገባና መጀመሪያ ሲሰጣቸው የነበረው የምቾት ምግብ ቀረ። ሠራተኛዋ ሽሮ ማቅረቧን ቀጠለች። ይህ ያናደዳቸው ባለታሪኩም አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ የሚባል ነበርና ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ልጆችን እቀበላለሁ በማለቱ በንዴት ፖሊስ መሆንን ባይፈልጉም ሊመዘገቡ ወደ ቦታው አቀኑ።

ምርጫቸው ህግና ታሪክ ነበር። ስለዚህም በኮሌጁ ገብተው በዚሁ ትምህርት ክፍል ለመማር ወሰኑ። ነገር ግን በዚህ መስክ ይህንን ኮሌጅ መቀላቀል ከባድ እንደሚሆንና ከዘርፉ መልቀቅ እንደማይችሉ ተረዱ። ስለዚህም የትምህርት መስካቸውን በሌላ ለመቀየር አሰቡ። በዚህም ጤና ሳይንስን መርጠው ስድስት ኪሎ በሚገኘው ኮሌጅ ጥያቄ አቀረቡና ተቀበሏቸው። ወደ ጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተዛውረውም በዚያ የህክምና ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።

የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ትምህርትን ከህዝብ ግልጋሎት ጋር በእጅጉ የሚያቆራኙት ባለታሪኩ፤ በዘርፉ በመግባታቸው በጣም ወደውት እንደተማሩት ይናገራሉ። እስካሁንም ከዚህ የትምህርት መስክ ያልወጡበት ምክንያት ይህ እንደሆነ ይገልጻሉ። እናም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ትምህርት አጠናቀቁ። በጤና አጠባበቅ ጣቢያ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ካገለገሉም በኋላ ሌላ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ቀጣዩን ትምህርታቸውን ለመማር ወደ አሜሪካ አቀኑ።

አሜሪካ «ቱሌን» በተባለና በተመረጠ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በዚሁ የጤና ሳይንስ ትምህርት የቀጠሉ ሲሆን፤ በጥሩ ውጤት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው ደግሞ ወደ እንግሊዝ አገር ይወስዳቸዋል። ዩኒቨርሲቲው «ሊድስ» ይባላል። የሦስተኛ ዲግሪያቸውን የተከታተሉበት ሲሆን፤ በኢፕዲሞሎጂ የትምህርት መስክ ነው የተመረቁበት።

የፕሮፌሰርነታቸውንም ማዕረግ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ነው ያገኙት። ከዚህ በኋላ ሥራ መስራት ላይ አተኩረው በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተዘዋወሩ ላገራቸው እያገለገሉ ይገኛሉ። ይሁንና ይህንን ትምህርታቸውን ሊያግዙ የሚችሉ አጫጭር ስልጠናዎችን በተለያዩ አገራት በመዘዋወር ወስደዋል። ክህሎታቸውን ለማዳበርም በዘርፉ የተለያዩ ሥራዎችን መስራታቸውን ይናገራሉ።

ከቤኒሻንጉል እስከ አዲስ አበባ
መጀመሪያ ሥራን «ሀ» ያሉባት ስፍራ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ስትሆን፤ በወቅቱ በወለጋ ውስጥ ተካቶ አንድ አውራጃ እንደነበር ይናገራሉ። በዋናው ከተማ አሶሳ ነበር ሁለት ዓመት የሰሩት። ከዚያ አሶሳ ላይ ሳሉ በተማሪዎች ንቅናቄ ሳቢያ አዲስ አበባ ላይ ያሉ ሰዎችን ሸሽገው ወደ ሱዳን እንዲያሻግሩ ተደርገው ነበርና አገር ክህደት ነው ተብለው ለእስር ተዳረጉ። በዚህም «ማዕከላዊን ያሟሸነው እኛ ነን» ይላሉ። ይህ ሳይበቃቸው ደግሞ ይቀጡ በማለት ወደ ኤርትራ አዲኳላ ከተማ ለሥራ ተልከዋል።

ከዓመት ቆይታ በኋላም ጎጃም ውስጥ ዳንግላ ጤና ጣቢያ ተቀየሩ። በዚህም እንዲሁ ዓመት ቆይተው በ1968 ዓ.ም ልዩ ሹመት መጣላቸው። የጎንደር ጤና ጥበቃ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ ወደ ጎንደር ተላኩ። ሰባት ዓመታትንም በዚህ ሙያ ላይ አገለገሉ። ይህንን ተከትሎ ነው የለውጥ ጊዜው ብቅ ያለው። ግን ብዙ ችግር ሳይፈራረቅባቸው የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ወደ አሜሪካ አቅንተው ነበርና ሥራው ተቋረጠ።
ከአሜሪካ መልስ ቀጥታ ጅማ ከተማ ተመደቡ። በዚህ ቦታ 22 ዓመታትን አሳልፈዋል። «በትምህርት የተቃኘ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ረሀብን ማጥፋት ይቻላል» የሚለውን ብሂላቸውን ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩትም በዚህ ዩኒቨርሲቲ ነው።

«በእርግጥ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት ነገር አላውቅም። መምህር ሆኜም አልሰራሁም። ይሁንና ጋዋን አልብሶ ከማስመረቅ ባለፈ በእውቀት የተገነባ ወጣት ለማፍራት መትጋት አለብኝ» የሚሉት ፕሮፌሰር፤ ወደ ማስተማሩ ሥራ ለመግባት የወደዱትም ከዚህ አላማቸው እንደመነጨ ይናገራሉ። ችግር ፈቺ ትምህርትን ያነገበውን ሥራ ሲጀምሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን በመሆን ከኩባውያንና ሌሎች አገራት ጋር በመጣመር በአስተርጓሚ ነበር። አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተቀየሩም በኋላ በጤናው ዘርፍ የሥርዓተ ትምህርት መምህር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። የማማከርና የምርምር ሥራም እንዲሁ ይሰራሉ።

በመንግሥት ደረጃ ጡረተኛ ቢባሉም እርሳቸው ግን «መቀመጥ ለምኔ» በሚል እሳቤ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናሉ። ለአገር የትምህርት ለውጥም በመትጋት ላይ ናቸው። «75 ዓመት ላይ ሆኜ መተኛትን አልፈልግም። ፕሮፌሰር መሆን ደግሞ ለአገር ውለታ መክፈል የሚቻልበት ነውና በቃኝ ለእኔ አይሆንም። ስለዚህም በቻልኩት መጠን ለአገሬ ታሪክ ማኖር እፈልጋለሁ» ይላሉ።

በኢፒዲሞሎጂ የተለያዩ ምርምሮችን ያከናወኑት ባለታሪኩ፤ ከ40 በላይ ምርምሮችን ያደረጉ ሲሆን፤ በተለይ በጤናው መስክና በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ አንቱታን ያተረፉላቸውን ሥራዎች ሰርተዋል። በጤናው ላይ የተሰሩት ምርምሮች ውጤታቸው በመንግሥት ተደግፎ ተግባራዊ ሆኗል። ነገር ግን በትምህርቱ መስክ የሚተገበረው ሥርዓተ ትምህርት ውጤታማ ነው ቢባልም በመንግሥት ተደግፎ ወደ ተግባር አለመለወጡ ሁልጊዜ የሚያሳዝናቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በአንድ የትምህርት መስክ የተጀመረው ይህ ሥርዓተ ትምህርት በሌሎችም እየተሞከረ ውጤቱ እየታየ እንደሆነ የሚገልጹት ፕሮፌሰር መኮንን፤ በአገር አቀፍ ሳይቀር ውጤታማ ተብሎ የተነገረለት ሥራ እያለ ከውጪ የሚመጡ ድንገተኛ ጥናቶች ጫና እያሳረፉባቸው መሆኑና ለምን በአገር ምርምር መኩራት እፍረት እንደሆነ እያሳዘናቸው መምጣቱንም አጫውተውናል።

«ለአገሪቱ የትምህርት ጥራት መውደቅ መፍትሄ የሚሰጥና ህብረተሰቡንም ሆነ አገርን የሚለውጥ ምርምር ሰርቻለሁ። ችግር ፈቺ ትምህርት መሆኑንም አረጋግጫለሁ። መንግሥትም አምኖበት ጥሩነቱን መስክሯል። በተግባር የተደገፈ ሥራን በሚገባ የሚያሳይ ነው። ሆኖም አገር መጠቀም ካልፈለገና የተማረውም ከእኔ በላይ ማነው ካለ ምንም ማድረግ አይቻልም። መበለጥ አልፈልግም ሳይሆን በልጬ አገሬን መለወጥ አለብኝ» ማለት ይገባናል ይላሉ።

የሥራ ላይ ገጠመኞች
በሥራ ዘመናቸው የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋቸው እንደነበር የሚገልጹት ፕሮፌሰር መኮንን፤ በመጀመሪያ ገጠመኝ የሚሉት የቀይ ኮኮብ ዘመቻ በጎንደር በኩል ሁመራ ላይ በተፈጠረው ጦርነት በሥራቸው ትልቅ ፈተና የሆነባቸው አጋጣሚ ነው። በተለይ ጦሩን ማከም፣ ለእነርሱ የሚሆን የህክምና ጣቢያ መስራትና ሌሎች ኃላፊነቶችን መወጣት ሳይፈለጉ የሚያደርጓቸው ነገሮች መኖራቸው ህይወታቸውን በፈተና ውስጥ እንዲያሳልፉ እንዳደረጋቸው ያወሳሉ።

በዓመቱ እንዲሁ አረንጓዴ ዘመቻ የሚባል ሲጀመር ኃላፊነቱ በእጅጉ ጠንክሮባቸው ስለነበር ሁመራ ላይ የነበረውን የመንግሥት እርሻ 50 ሺ የሆነውን ሠራተኛ ጤና መጠበቅ ደግሞ በእጅጉ ከብዷቸው እንዳለፈ ያነሳሉ። ድርብ ድርብርብ ኃላፊነት መኖሩ ሥራዎችን ቀኑን ሙሉ መስራት ይጠይቃልና እንቅልፍ አልተኛምም ይላሉ። በዚያ ላይ በአካባቢው ማጅራት ገትር የሚባል በሽታ ተከስቶ ነበርና በኢትዮጵያ 32 ሺ ህሙማን ነበሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ በጎንደር ክፍለ አገር 22 ሺ ሰዎች በበሽታው በመያዛቸው ትልቅ ዱብዳ ጥሎባቸው እንደነበርም አይዘነጉትም።

እናም በዚህ ሥራ ውስጥ ሳሉ ህክምና መስጠቱ፣ ጦርነቱ፣ አዳዲስ በሽታዎች መታየታቸውና የፖለቲካ ቀውሱ ተደማምረው በየጊዜው ለሥራቸው እንቅፋት ይሆኑባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ በፖለቲካው ጫና ውስጥ በማለፋቸው እስከህይወት መስጠት የደረሱ ችግሮች ገጥመዋቸው እንደነበርም አውግተውናል። ምክንያቱ ደግሞ እርሳቸው ከተቃዋሚው ወገን የተሰለፉ መሆናቸው ነው። በዚህም በሥራቸው ሦስተኛ ህይወት ቀጥዬ ነው እስከዛሬ የቆየሁት ይላሉ።

የአገር አበርክቶ
የህብረተሰብ ተኮር ትምህርት ሥርዓትን በአገር ደረጃ እንዲጀመር ያደረጉት ፕሮፌሰር መኮንን፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲና በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በችግር ፈቺ ትምህርት ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ያስቻሉ ስለመሆናቸው ይነገርላቸዋል። በ60ዎቹና 70ዎቹ አካባቢ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ህብረተሰቡን አያገለግልም፤ የራሱን ደሴት መስርቶ ነው የሚንቀሳቀሰው ይባል የነበረውን ከሥሩ የነቀሉ እርሳቸው መሆናቸው ይገለጻል። ዩኒቨርሲቲዎች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩና ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው መስመር ያሳዩም ናቸው። ይህ ሁኔታ በተግባር የተደገፈና ዘለቄታዊነት ያለው እንዲሆንም ማዕከል ያቋቋሙ ስለመሆናቸው ይነገራል።

ማዕከሉ ግልገል ጊቤ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ማዕከል የሚባል ሲሆን፤ ለመቋቋሙ መንስኤው ተማሪው የንድፈ ሀሳብ ትምህርቱን በሚገባ ተረድቶ ቢመረቅም ወደትግበራው አይገባምና ከወጣ በኋላ እንዳልተማረው ይሆናል። ከዚያ ባሻገርም በእያንዳንዱ ተማሪ ላይ በተማረው ልክ ያለመፈጸም ችግር ተንሰራፍቷል። በመሆኑም ችግሩ እንዲፈታ ለማድረግ ዓለምአቀፋዊ ንቅናቄ ተጀመረ። ለዚህ ትግበራ ይበጅ ዘንድም በአገር ደረጃ ማዕከሉ ላይ ዓይን በማረፉና የጊቤ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በአፈር እየተሞላ በመምጣቱ እንዲሁም ስጋት ላይ በመውደቁ እርሱንም ለማዳን ሲባል እንዲቋቋም ተደርጓል። ለዚህ ደግሞ መሰረት ጣዩ እርሳቸው እንደነበሩ ብዙዎች ይናገራሉ።

የግልገል ጊቤ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በማዕከል ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተማሪዎችን እንዲያለማምዱ ዕድል ሰጥቷል፤ ትምህርት፣ ምርምርና አገልግሎት መስጠትን አካቶ የሚሰራም ነው። በተለይ ለተመራማሪዎች እየሰጠ ያለው ጥቅም ገደብ የለውም ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

እንግዳችን በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ሌላ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል። የጤና ሳይንስ ምርምር ማዕከልን ያቋቋሙትና በዲፓርትመንት ኃላፊነት ሲመሩ የቆዩትም እርሳቸው ናቸው። በዚህም የጤናውን ዘርፍ በማሳደግ ዙሪያ ሰፊ አስተዋጽኦ ያደረጉ ለመሆናቸው ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ፕሮፌሰር መኮንን፤ «የተማረ ሰው አዲስ ነገር አይቀበልም። ማን ይበልጠኛል የሚል ብቻ ነው። በዚህም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በእጅጉ ይፈልጋል። ይህ መሆን አለበት የሚል መሪ በሁሉም ዘርፍ ሊኖር ይገባል» ይላሉ። ለዚህም ምክንያታቸው ለሁለቱም ማዕከላት ምስረታ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ የላቀ መሆኑን ለማመላከት ነው። የአሁኑም መንግሥት በሚሰሩት ምርምሮች ላይ ጣልቃ በመግባት ወደ ተግባር መቀየር ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ለመጠቆም ነው።

ሽልማት
በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ አገራትም ሆነ ከአገር ውስጥ በርከት ያሉ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል። ይሁንና ውጤታማና የሚያስደስቷቸው ሽልማቶች ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን ይናገራሉ። የመጀመሪያው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በህብረተሰብ ጤና ሳይንስ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪው፣ ማስተር ኦፍ ፕሊክ ሄልዝና ማስተር ኦፍ ሳይንስ በሚባሉ መስኮች እንዲሁም ዶክተር ኦፍ ሄልዝ ሰርቪስስና ፒኤችዲ የሚሉ የትምህርት መስኮችን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ካሪኩለሙን ሰርተው በማቅረባቸው የተሰጣቸው የወርቅ ሜዳልያና የምስክር ወረቀት ነው። በተመሳሳይ በጤናው ዘርፍ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም በመስራታቸው እንዲሁም በቆዩበት የሥራ ዘመን መልካም ስነምግባር በማሳየታቸው የወርቅ ሜዳልያና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ችግር ፈቺ ስርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ውጤታማ የሆነ ተግባር በመከወናቸው የተሰጣቸው የምስክር ወረቀት ነው። በዚሁ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆነው መሰረት የጣሉለት የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበርም የሰጣቸውን አንድ ሜዳልያ በእጅጉ እንደሚወዱት አውግተውናል።

የህይወት ፍልስፍና
«ህይወት ያለውና ህይወት የሌለው በአንድ ጎዳና ተጉዘው እራሳቸውን መለወጥ ካልቻሉ አገር ሊኖር አይችልም» የሚል እምነት አላቸው። አንዱ ለአንዱ መኖር አለበት፤ በአንዱም መኖር ይጠበቅበታል። የትምህርት ሥራውም እንዲሁ ህይወት ላለውም ለሌለውም የሚጠቅም ሲሆን ነው መፍትሄ እያመጣ የሚሄደው። ስለዚህ የአገርን ርሃብ መለወጫ ዋነኛ ቁልፍ በመሆኑ በተግባር የተደገፈና አካባቢውን ሊለውጥ የሚችል ትምህርት በሚገባ መኖር አለበት። የሰው ልጅ የሚገለጽበት ፀባዩ ስስታምነቱ ነው። ከዚህ የተነሳም አንድ ሰው በቤት ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ መኪናዎችን ይይዛል። ከሚገባቸው በላይ ሀብት ያካብታል። ይህ ደግሞ ዓለም መስጠት ከምትችለው በላይ ይጠይቃል። ነገር ግን በሌላ ጫፍ ያሉትን ከድህነት ወለል በታች የሚገኙትን ሰዎች ማየት የማይፈልግ ብዙ ነው። ይህ ደግሞ አንዱ ለአንዱ ፈተና እንዲሆን አስችሏል የሚል እምነት አላቸው።

በምክንያትነት የሚያነሱት የአየር ንብረት ለውጥን ሲሆን፤ ሀብታሞች በማደግ ላይ ያሉ አገራትን እንዲያግዙ የሆነበት ዋና ምክንያት የአየር መበከል ድሃ ሀብታም ስለማይል ነው። እናም የትምህርት ዋጋም ድሃ ሀብታም አይልምና ውጤታማ የትምህርት ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ላይ መሰራት እንዳለበት ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ ፍቱን መድኃኒቱ ቴክኖሎጂን በተገቢው መልኩ መጠቀም ነው ይላሉ። ኤምአይቲ የሚባል የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ምንም ያልተማሩት የገበሬ ልጆች ጋር በመውረድ ታብሌት ይሰጣቸዋል። ይጫወቱበታል ተብሎ ቢገመትም እነርሱ ግን ሲፈላሰፉበት ታይቷል። ይህ ደግሞ ላልተማረው ሳይቀር ቴክኖሎጂ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳልና ለአገር ለውጥ ትምህርትን መጠቀም ቀዳሚ መሆን እንዳለበት እምነታቸው ነው።

ቤተሰብ
ጎንደር በሚማሩበት ወቅት ነበር በቡድን ጥናታቸው ላይ ዓይናቸው አንዲት እንስት ላይ ያረፈው። ከዚያም ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በአንድ ላይ ተመደቡና ፍቅራቸው ጠንክሮ ለትዳር አበቃቸው። ምንም እንኳን ከባለቤታቸው ጋር ከ30 ዓመት በፊት ቢለያዩም አራት ልጆችን ከእርሳቸው ጋር በነበራቸው ቆይታ አፍርተዋል። ልጆቻቸውንም አሳድገው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል። የልጅ ልጅም ለማየት ችለዋል። አንዱን በህይወት ከመነጠቃቸው ውጪ ሁሉም ተምረው በግል ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። እርሳቸው ግን ከእርሷ ውጪ ለምኔ በማለት እስካሁንም አላገቡም።

መልዕክተ መኮንን
«የእኔ አገር ታሪክ በይበልጥ የሚታወቅበት ረሃብ ነው። በየመንግሥታቱም መጠሪያው ይህ ነው። ለዚህ ተጠያቂው ደግሞ ትምህርት ነውና የኢትዮጵያ ትምህርት ይህንን መፍታት አለበት» ይላሉ። መጀመሪያ መንግሥት ከዚያ የተማረው ተባብሮ ትምህርትን ማላቅ ይገባል። ያሉትን ሀብቶች ተጠቅሞ ተግባራዊ ማድረግም ያስፈልጋል።

በአገር ላይ በሚከናወኑ የትምህርት ሥራዎች ከማህበረሰብ የጀመረ ተጠያቂነትና ጠያቂነት ሊፈጠር ይገባል። ባለበት ላይ መደራረብ ሳይሆን ትምህርትን ችግር ፈቺ ማድረግ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም ዋነኛ ድርሻውን መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በአገር ውስጥ የሚሰራውን የምሁራን የሥራ ብርታት ይጨምራል። ሥራዎችም በተግባር የተደገፉ ይሆናሉ።
ዩኒቨርሲቲዎችና የሚመለከታቸው አካላትም በጥምረት ለትምህርቱ ማደግ መስራት አለባቸው። ለአብነት በአሜሪካ አገር እያንዳንዱ ሰው በሙያው ይፈተናል። ይህ ደግሞ እየበቃና ችግር ፈቺ እየሆነ እንዲሄድ ያደርገዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያም ይህንን ተከትላ የተማረውን ኃይል ማብቃቷ በችግር ፈቺነት ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ።

አዲስ ዘመን ጥር 12/2011

ጽጌረዳ ጫንያለው