የታጁራ ወደብ የድንጋይ ከሰልና የብረት ምርቶች እጥረት ለመቀነስ እንደሚያስችል ተገለጸ

9

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን መጠቀም መጀመሯ የድንጋይ ከሰል እና የብረት ምርቶች እጥረትን በመቀነስ የልማት ፕሮጀክቶችን ሥራ ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ እንደገለጹት፤ ጅቡቲ ካሏት ወደቦች ውስጥ አንዱ የሆነው የታጁራ ወደብ ኢትዮጵያ መጠቀም ጀምራለች። ወደቡ የከሰል ድንጋይ እና ብረት ምርቶች ወደኢትዮጵያ ለማስገባት ታልሞ የተገነባ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ወደቡን መጠቀም መጀመሯ የድንጋይ ከሰል እና የብረት ምርቶችን የሚፈልጉ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።

እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፤ የድንጋይ ከሰል ምርት በተለይ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና ለተለያዩ አምራች ፋብሪካዎች የኃይል አቅርቦት በመስጠት ምርትን ለማሳደግ ይረዳል። የብረት ምርቶችም ለህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ዋነኛው አስፈላጊ ግብዓት ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን ተጠቅማ በዋነኛነት ምርቶቹን ማስገባት መጀመሯ በግብዓት እጥረት ይፈጠር የነበረውን የልማት ሥራዎች መጓተት ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት እየተጠቀመችበት ከሚገኘው ከዋናው የጅቡቲ ወደብ ጋር ሲነጻጸር የታጁራ ወደብ የ13 ኪሎ ሜትር ርቀትን እንደሚቀንስ የገለጹት አቶ አሸብር፤ ወደቡ ለኢትዮጵያ ያለው ቅርበት የተሽከርካሪዎችን ምልልስ በመቀነስ ምርቶች በፍጥነት ለማስገባት እንደሚያስችል ተናግረዋል። ወደወደቡ የሚወስደው እና ከወደቡ ወደኢትዮጵያ የሚያስገባው መንገድም ደረጃን በጠበቀ መልኩ የተገነባ በመሆኑ ለእቃ ጫኝ ተሽከርካሪዎችም አመቺ መሆኑን አስረድተዋል።

በወደቡ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ እና የማሽነሪ አቅርቦት ዘመናዊ በመሆኑ ከመርከብ ላይ አንድ ቀን 5ሺ 670 ቶን እቃ ማራገፍ የሚያስችል አቅም መኖሩን ተናግረዋል። ይህም በፍጥነት ምርቶቹን ወደኢትዮጵያ ለማስገባት እና ለሚፈለገው አገልግሎት ለማዋል ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አቶ አሸብር ገልጸዋል። እንደ አቶ አሸብር ገለፃ፤ ቀደም ባለው ጊዜ የታጁራ ወደብ ግንባታ የተጀመረው የኢትዮጵያን የፖታሽ ምርት ወደውጭ ሀገራት ለመላክ ነበር። ይሁንና በጅቡቲ ወደብ ላይ የድንጋይ ከሰል ምርት ከሌሎች ምርቶች ጋር አብሮ በሚራገፍበት ወቅት በተለይ የምግብ እና የፋርማሲውቲካል ምርቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን ለማወቅ ተችሏል። በወደቡ የድንጋይ ከሰል በሚራገፍበት ወቅትም በዙሪያው የሚገኙ ሌሎች ምርቶች ላይ ጥቁር ብናኝ እየተራገፈ በመሆኑ መንግሥት ምርቱን ለብቻው ማስገባት እንደሚገባ ወስኗል። በመሆኑም የድንጋይ ከሰሉ ሲገባ ተጽእኖ የማያደርስበት ምርት የብረት ምርት በመሆኑ በዋናነት ሁለቱ ምርቶች በታጁራ ወደብ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቀደም ብሎ በ90 ሚሊዮን ዶላር ተገንብቶ ያለሥራ የተቀመጠውን የጅቡቲ ወደብ ኢትዮጵያ መጠቀም ከመጀመሯ ጋር ተያይዞ በርካታ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ተገቢውን የኮሮና ቫይረስ ጥንቃቄ እያደረጉ ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ላይ ናቸው።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም

 በጌትነት ተስፋማርያም