በትምህርት ዘርፉ ህገ ወጥ አሰራሮችን የሚያጋልጥ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ይፋ ሆነ

14

 አዲስ አበባ:- በትምህርት ዘርፉ የአሰራር ስርዓትን በማዘመን፣ መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍኑ ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፍና ተጠያቂነትን መፍጠር የሚያስችል፣ ህገ ወጥ አሰራሮችንም የሚያጋልጥ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ይፋ ሆነ፡፡

 በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲና በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ትብብር የተዘጋጀ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት›› ትናንት በተመረቀበት ወቅት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም፤ ግልጸኝነት የተላበሰ አሰራርና የዘመነ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መተግበሩ ህገ ወጥ አሰራሮች ተጋልጠው እንዲታረሙ፣ በትምህርት ዘርፉ መተማመንን እንደሚፈጥርና የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

መንግስት በትምህርት ዘርፉ የሚታየውን ህገ ወጥነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ በመግለጽ፤ ተቋማት ባሉበት ሆነው በአጭር ጊዜና በቀላሉ የእውቅና ፍቃዳቸውን የሚያወጡበት፣ የሚያድሱበትና መሰል አገልግሎቶችን ያለ ውጣ ውረድ የሚያገኙበትን ዕድል እንደሚፈጥር ፕሮፌሰር ሂሩት ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ፤ የከፍተኛ ትምህርት ለማስፋት ከቅበላ እስከ ምረቃ ድረስ የሚያስኬድ የበይነ መረብ ትምህርት አቅርቦት መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን፤ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ትምህርትን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ ወቅታዊ፣ የተሟላ ይዘት ያለው፣ ግልጸኝነትን የተላበሰ፣ ከትክክለኛ ምንጭ የተገኘና የተረጋገጠ መረጃ ጥራት ያለው ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያግዝ፣ ተቋማዊ ተልእኮን በውጤታማነት ለመወጣት እንደሚያስችል ፣ ተፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀትና በመተንተን ለሚመለከተው ባለድርሻ አካል ወቅታዊ መረጃና ግብረ መልስ ለማቅረብ የሚያስችል የዘመነ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።

እስካሁን ተቋማት የት እንዳሉ፣ ምን ያህል የማስተማሪያ ጊቢ እንዳላቸው፣ በምን መርሀ ግብር ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙ፣ ምን ያህል ተማሪና መምህራን እንዳላቸው የተሟላ መረጃ እንዳልነበረም ፕሮፌሰር ሂሩት ገልጸው፤ የቀደመው አሰራር በትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ ትልቅ ጫና የፈጠረና ህገወጥነትን የፈቀደ እንደነበር ጠቁመዋል።

የግል ከፍተኛ ተቋማትን የሚመለከቱ አስፈላጊና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ የተጠቃሚ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማጎልበት እንደሚያስችል፣ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልና የአሰራር ስርዓቱ እንዲጎለብቱ ግብዓት ለመስጠት ሚናው የጎላ እንደሚሆንም አክለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶክተር)፤ የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ የከፍተኛ ትምህርትን ለማዘመን እንደሚያግዝ ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑን ፣ ቴክኖሎጂው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጊዜ ቆጣቢና ቀላል አሰራርን የሚተገበርበት እንደሆነና በትምህርት ዘርፉ የሚታየውን ህገወጥነት ለመከላከል እንደሚጠቅም ጠቁመው፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የመረጃ አስተዳደር ስርዓት በመሆኑ አሰራርን ለማዘመን እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶክተር)፤ ተቋሙ ቁጥጥር እንዲያካሂድና የትምህርት ጥራትን እንዲከታተል የተቋቋመ ቢሆንም፤ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ከፍተኛ የህግ ጥሰቶችና ከፍተኛ የጥራት መጓደል መታየቱን ጠቅሰው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በነጻ ሙያ ድጋፍ አበልጽጎ ወደ ትግበራ ማስገባቱን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ፤ ስራው በእጅ በታገዘ ልማዳዊ አሰራር ሲተገበር መቆየቱን ፣ የተማሪዎችንና የመምህራንን ቁጥር ለመለየትም አዳጋች እንደነበር ጠቁመው፤ አዲሱ አሰራር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እውቅና መስጠት፣ እድሳት ማድረግና ክትትል ማካሄድ እንደሚገኝበት፣ የትምህርት ጥራትን እንደሚከታተልና የትምህርት ማስረጃን የማረጋገጥ ስራ እንደሚተገብር ተናግረዋል።

ወደ ዘመናዊ አሰራር መገባቱ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተመራቂዎችን በሙሉ በዳታ ቤዝ መያዝ እንደሚያስችል፣ ቀጣሪ መስሪያ ቤቶች በቀጥታ ማረጋገጥ እንደሚያስችላቸው፣ በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን በቀጥታ በቴክኖሎጂው ለማግኘት፣ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በተያያዘ ዜና ከቅበላ እስከ ምርቃት ድረስ በበይነ መረብ ትምህርት አቅርቦት (on line learning) ለማስተግበር የሚያስችለው እና የተዘጋጀው መመሪያ ወደ ተግባር መግባቱ ለትምህርት ዘርፉ አማራጭ እንደሚሆን የትምህርት ሚኒስርሯ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ላለፉት 18 ወራት ከ20 ባለሙያዎች በላይ የተሳተፉበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012

 ዘላለም ግዛው