ግብጽ የአባይ ውሃ የህልውናዬ ጉዳይ ነው ብትልም ሰፊ የውሃ አማራጮች እንዳሏት ተገለጸ

22

 አዲስ አበባ ፦ ግብጽ የአባይ ውሃ የህልውናችን ጉዳይ ነው ብትልም በተጨባጭ ግን ሰፊ የውሃ አማራጮች እንዳሏት በውሃ ጉዳይ ተመራማሪው ዶክተር ኢንጂነር ጸጋ ጥበቡ አስታወቁ ። ግብጻውያኑን ከዕንቅልፍ መቀስቀስ እና ለአማራጮቻቸው ትኩረት እንዲሰጡ ማነቃቃት እንደሚያስፈልግም አመለከቱ ።

በውሃ ዘርፍ ሰፊ ጥናቶችን በማካሄድ በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ዶክተር ኢንጂነር ጸጋ ጥበቡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፤ ግብጽ ከአባይ ውጪ ሌላ የውሃ አማራጭ እንደሌላት አድርጋ ለዘመናት የሄደችበት መንገድ የተሳሳተና አለምንም ያሳሳተ ነው።

‹‹ግብጽ ከአባይ ውሃ ውጪ በጠጣሩ የኑብያ አሸዋማ ከርሰ ምድር የተከማቸው ውሃ አላት›› ያሉት ተመራማሪው ፤ ከዚህም ውጪ የቀይ ባሕርንና የሜዲትራንያንን ባሕር ከጨው በማላቀቅ አማራጭ የውሃ ምንጭ አድርጋ ልትጠቀም እንደምትችል፤ ለዚህም የሚሆን በቂ እና ርካሽ ቴክኖሎጂ በገበያ ላይ እንዳለ አመልክተዋል ።

 በአፍሪካዊ የመተባበር መንፈስ መንቀሳቀስ ከተቻለ ከላይኛው የዓባይ ተፋሰስ በጆንግላይ ቦይ አማካይነት ወደ ግብጽ በቀላሉ ሊቀለበስ የሚችል ሰፊ የውሃ ሀብት እንዳለ የጠቆሙት ተመራማሪው ፤ ከታላቁ ኮንጎ ወንዝ ወደ ግብጽ ሊቀዳ የሚችል ሰፊ የውሃ ሀብት መኖሩን አስታውቀዋል ። ከሀገሪቱ ከቤት፣ ከኢንዱስትሪ እና ከመስኖ አገልግሎት የሚወጣውን ውሃ እንደገና አጣርቶ ጥቅም ላይ በመዋልም ሰፊ ውሃ ማግኘት እንደምትችል ገልጸዋል።

 የኑብያ ጠጣር አሻዋማ ስነምድር ውስጥ የሚገኝ የከርሰ ምድር ውሃ በመላው ግብጽ፤ ምስራቃዊ ሊቢያ ፤ሰሜን ቻድ እና ሰሜን ሱዳን ውስጥ ተከማችቶ ይገኛል ያሉት ተመራማሪው፤ በቅርቡ በተደረገ ጥናት ወደ 450,000 (አራት መቶ ሀምሳ ሺ) ኪዊቢክ ሜትር ውሃ እንደሚገኝ መረጋገጡን ተናግረዋል ።

የኑብያ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትን ስናስብ ሊቢያን በምሳሌነት ልንጠቅስ እንችላለን ያሉት ዶ/ር ጸጋ፣ ያቺ አገር የከርሰ ምደሩን ውሃ አውጥታ፤ ሰው ሠራሽ የተባለውን ወንዝ ፈጥራ ጥቅም ላይ በማዋል የአረቡን ዓለም በእርሻ ምርት በሥጋና በፍራፍሬ በማጥለቅለቋ ሊቢያውያን ከፍተኛ የኑሮ እርከን ላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል ።

ግብጻውያን ይህንን ፈር በመከተል ከጥቁር ዓባይ ጥገኝነት እራሳቸውን ነጻ ማውጣት እንዳለባቸው፤ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥም ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በጋራ የሚቆሙበትን ስርዓት መፍጠር ተገቢ መሆኑንም አመልክተዋል ። ለዚሁ የሚሆን መርህ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

ግብጽ የቀይ ባሕር እና የሜዲትራንያንን ውሃ ተጋሪ ከመሆኗ አንጻር ይህን የውሃ ሀብት ከጨው በማላቀቅ እንደ አንድ አማራጭ የውሃ አቅም አድርጋ ልትወስድ እንደሚገባ ያመለከቱት ተመራማሪው ፤ አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን የባሕርን ውሃ ከጨው የማላቀቁ ሂደት በጣም እየቀለለና በዋጋም እየረከሰ መምጣቱን ጠቁመዋል። ወደፊትም ይበልጥ ዋጋው እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገመታል ብለዋል ።

ግብጻውያን ጨዋማን ውሃ የማጣራት በቂ ልምድ ስላላቸው፤ በዚህ ምንም የሚቸግራቸው ነገር እንደሌላ ጠቁመው ፤ የውቂያኖስ ውሃን በማጣራት ከበቂ በላይ ውሃ ማግኘት እንደሚችሉም አመልክተዋል ።

በተፋሰሱ ሀገሮች መካከል በቂ መተማመን መፍጠር ከተቻለ የላይኛው ዓባይ ላይ ውሃ አጠራቅሞ የዓባይን ፍሰት ማጎልበት ሌላኛው አማራጭ እንደሆነ የጠቆሙት ተመራማሪው፤ ይህ አማራጭ ቀደም ብሎ ግብጽና ሱዳን በታላቋ ብሪታንያ አስተዳደር በነበሩበት ወቅት ተጀምሮ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ተነሰቶ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት መቋረጡን ጠቁመዋል ።

መሠረተ ሃሳቡም ቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ ግደብ ሠርቶ ውሃ በማጠራቀም፤ ውሃው ወደ ነጭ ዓባይ እንዲፈስ በማድረግ ሱድ የተበለውን 8000 (ስምንት ሺ) ኪሎ ሜትር ካሬ የሚሸፍነውን ረግረጋማ መሬት በካናል በማሳለፍ ነጭ ዓባይ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ወደ ሱዳንና እና ግብጽ የጎለበተ ውሃ እንዲወርድ ማድረግ እንደነበረ አስታውቀዋል ።

ከኮንጎ ወንዝ ውሃ በመጨለፍ የነጭ ዓባይን ፍሰት ማጎልበት ተጨማሪ አማራጭ እንደሆነ ያስታወቁት ዶ/ር ጸጋ ፤ የታላቁ የኮንጎ ወንዝ በሴኮንድ 40,000 ( አርባ ሺ) ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ያፈሳል። ዓባይ በ 6750 ኪሎ ሜትር ርዝመት ቢጓዝም ኮንጎ በፍሰት መጠን ዐባይን 7 ጊዜ ይበልጣል ። ይህንን የአፍሪካውያን አኩሪ ኃብት ለጋራ ጥቅም ማልማት ይቻላል ብለዋል ።

ግብጽ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ለቤት ውስጥ አገልግሎት፣ ለኢንዱስትሪ እና ለመስኖ እርሻ እንደምትጠቀም ፤ አገልግሎቱን ጨርሶ የሚባክን ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ መኖሩን ፤ ይህንን ውሃ አጣርቶ በመጠቀም ተጨማሪ የውሃ አቅም መፍጠር እንደምትችል ጠቁመዋል ።

ዶ/ር ጸጋ አህጉራዊ ራዕይ በማዳበር አማራጮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ተመራማሪው፤ አማራጮች ላይ ትኩረት መስጠት የብስለትና የአርቆ አስተዋይነት መገለጫ መሆኑንና ግብጻውያኑን ከዕንቅልፍ መቀስቀስ እና ለአማራጮቻቸው ትኩረት እንዲሰጡ ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በሦስቱ አገሮች መካከል እየተደረገ ባለው ድርድርም አማራጭ የውሃ ግኝት አንደ አንድ የመደራደሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሊነሳ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012

 በጋዜጣው ሪፖርተር